መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ድሉ የክርስቶስ ነው

የትምህርቱ ርዕስ | ድሉ የክርስቶስ ነው

ሕይወት ሩጫ ናት ። ሩጫ ልምምድና አሰልጣኝ ይፈልጋል ። ሕይወት በተጓዝን ቍጥር እየለመድናት ትመጣለች ። ትዕግሥት የለኝም የሚለው አይሠራም ፣ ስንጠረብ ስንሞረድ ትዕግሥትን እየተለማመድን እንመጣለን ። ትዕግሥት የኋላ እሸት ነው ። ሕይወት አሰልጣኝ ትፈልጋለች ። አሰልጣኙ ሯጩን እንደ ልጁ ፣ እንደ ተማሪው የሚያይ ፣ የእርሱ ከፍታ የእኔም ክብር ነው ብሎ የሚያስብ ነው ። ስልጠናው እንዳያንስም እንዳይበዛም ፣ በተጠና መንገድ አሰልጣኙ ይቆጣጠራል ። በልምምድ ላይ የተጎዳ ከውድድር ሳይደርስ ይቀራል ። በልምምድ ላይ የቀሩ ሯጮች አሉ ። በሚቀኑባቸው ተጎድተው ፣ ሌባና ሽፍታ ገጥሟቸው ፣ የመኪና አደጋ ደርሶባቸው ልባቸው ሩቅ አገርና ትልቅ ደረጃ እያሰበ የቀሩ አሉ ። አሰልጣኙ እነዚህን መሰናክሎች ሁሉ ይከታተላል ፣ ተማሪውን ይጠብቀዋል ። ለዚህ ውድድር ትመጥናለህ ብሎ ይለፍ የሚሰጠውም ያ አሰልጣኝ ነው ። በሕይወት ውስጥ የማይታየው መሪ እግዚአብሔር ነው ። እርሱ ግን የሚታዩ ወኪሎችን መምህራንንና ካህናትን አስቀምጧል ። መምህራን ከመጠን በላይ በልምምዱ እንዳይጎዳ ለምእመንና ለአዲስ አገልጋይ ስልቱን ያሳያሉ ። “አዲስ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል” እንደሚባለው በአፍላነቱ እንደ ጥጃ ዘሎ እንዳይሰበር ይቆጣጠሩታል ። ሕፃን ልጅና አዲስ ክርስቲያን ያደክማሉ ። ግለቱ ፣ ስሜቱ ፣ ትኩሳቱ ጥሩ ነው ። አንዳንዴም የሰው ልጆች ጠላት የሆነውን ዲያብሎስ ለምን ዝም አላችሁት ( እኔ በረሃ ወርጄ ፣ በኣቴን ዘግቼ አሸንፈዋለሁ ብሎ ከሰይጣን ጋር ነጻ ትግል ይገጥማል ። ብዙዎቹ የአእምሮ በሽተኛ ይሆናሉ ። ክርስቲያን የሆንነው ለውጊያ ሳይሆን ለመዳን ነው ። መዳናችንን አላስነካም ብለን ግን እንዋጋለን ። ኢትዮጵያዊ የሆነው ከጎረቤት አገር ጋር ለመዋጋት አይደለምና ።

መምህራንና ካህናት አዲሱን ምእመን መጠበቅ አለባቸው ። ዘሎ የኖረውን ነገር ካላየሁ ፣ የቤተ ክርስቲያንን ገቢ ኦዲት ካላደረግሁ ሲል ብዙ ቀሳፊ መልአኮች እጅ ይወድቃል ። በማመኑ እንዲጸጸት አድርገው ይሸኙታል ። የህልውና ውጊያ የሚያደርጉ ፣ በአገልግሎቴ የመጣውን በሕይወቱ እመጣበታለሁ የሚሉ ብዙ ጨካኞች በቤተ እግዚአብሔር ጥግ ጥግ ይዘው ተቀምጠዋል ። አዲሱን አማኝ ከእነዚህ ቀሳፊዎች ፣ ከልጅነት ችኮላው መጠበቅ ይገባል ። “ከፖፑ በላይ ካቶሊክ” እንዲሉ ከፓትርያርኩ በላይ ኦርቶዶክስ ነኝ ሊል ይችላል ። ልጅ አይከሰስምና መግራት የአባቶች ድርሻ ነው ። “ወደ ቤተ ክርስቲያን በቀረብህ ቍጥር ከእግዚአብሔር ትርቃለህ” ይላሉ ፈረንሳዮች ። የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ ውስጥ መግባት ዓላማን ያስታል ። ልብ አድርጉ ከአገልጋዮች ጋር ያለን ግንኙነት ከአገልግሎታቸው ጋር እንጂ ከሕይወታቸው ጋር አይደለም ። ከሕይወታቸው ጋር ግንኙነት ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ባሳለፍኩት ዘመን እንዳየሁት ከካህን ጋር ታግሎ ያሸነፈ ምእመን የለም ። እንኳን አንተ ጭቁኑ እነ ዐፄ ቴዎድሮስም ሞክረው ተከታይም ቀባሪም ያጡበት ጉዳይ ነው ። አዳዲስ ምእመናን መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ማገዝ ፣ ርቀታቸውን ጠብቀው ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን እንዲቀበሉ ማስተማር ይገባናል ።

በሩጫው ላይ ከጅምሩ የሚፈጥኑ አይፈጽሙም ። አቅማቸውን ቶሎ ስለሚጨርሱ የመጨረሻውን ድል አያቀዳጁም ። ሁሉም ነገር የዕድገት ሕጉን ካልጠበቀ ዕድሜ የለውም ። አትክልት እንኳ ከቀኑ በፊት እየደረሰ በመሆኑ ለተለያየ በሽታ እየዳረገ ነው ። የወተት ፣ የእንጀራ ፣ የአጥንት ዘመን አለ ። ስሜታዊነት ያስጀምራል እንጂ አያስፈጽምም ። በሕይወት ላይ ችኩልነትን በትጋት መለወጥ ይገባል ። በሩጫ ላይ አቋርጠው የሚወጡ አሉ ። የአየሩ ክብደት ፣ ድንጋጤ ከሩጫው ማቋረጥን ያስከትላል ። ዛሬ በአገራችን ብዙ ወጣቶች ሩጫውን እያቋረጡ ራሳቸው ላይ ሲወስኑ ይታያሉ ። አንድ ሯጭ ሩጫውን ሲያቋርጥ ልፋቱን ሁሉ ወደ ኋላ ጥሎ ነው ። ዛሬ ሞትን ስንመኝ ያሳለፍነውን ትግል ከንቱ ማድረጋችን ነው ። የትላንቱ እንዳለፈ የዛሬም ትግል ያልፋል ። ላያልፍ የመጣ ምንም ነገር የለም ። ሩጫውን በድል የሚፈጽም አለ ። ተረጋግቶ ፣ መስመሩን ጠብቆ ፣ ፍርሃትን አሸንፎ ፣ የት ቦታ ላይ ፍጥነት መጨመር እንዳለበት ተምኖ የሚሮጥ እርሱ ለድል ይበቃል ። በሕይወት ውስጥም እኛን የሚጠብቁ ፣ ድላችን ድላቸው የሆኑ ሰዎች አሉ ። ስለ ራሳችን ከሩጫው ለመውጣት ብንፈልግ እንኳ ስለ እነርሱ ስንል መበርታት አለብን ። ሰው የሚኖረው የሚኖርለት ነገር ካለ ነው ። ሁላችንም በዕይታ ውስጥ ነን ። የምናስፈልጋቸው ፣ አርአያ የምንሆናቸው ወገኖች አሉ ። ስለ እነርሱ ስንል ፣ ለትውልድ ክፉ አርአያ አልሆነም ብለን መታገሥ አለብን ።

ከአጠገባችን ያሉትን መጎሰሞች አለመታገሥ ከድል የሚያስቀር ነው ። ቀና ስንል ወንጭፍ የሚለማመድብን ብዙ ነው ። ባልንጀሮቻችን ሳይቀር ጠላት ይሆኑናል ። ስም ማጥፋት ፣ የቅጥር ተሳዳቢዎች ርእስ መሆን ይመጣል ። እንደ ጅምሩ ፍጻሜው እንዲያምር በዝግታ ጀምሮ በፍጥነት መጨረስ ይገባል ። የማናደርገውን ነገር አለመናገር ጥሩ ነው ። ስንናገረው አንጎላችን እንደ ተፈጸመ ያስባልና ለመቀጠል አቅም አይኖረንም ። ሯጭ በድብቅ ይለማመዳል ፣ ዓለም እያየው ይሮጣል ። ለድል የሚያበቃን በድብቅ መጸለይ ነው ።

በርቱ ድሉ የክርስቶስ ነው ። ደካማ ነኝ አትበሉ ፣ በጣም ጎበዝ ናችሁ ፣ የተሸከማችሁት ሸክም ከባድ ቢሆንም እስካሁን አላችሁ ። እንደ እናንተ ጎበዝ የለም ። ልዑል ሆይ እነዚህን ባሪያዎችህን ስለ ስምህ ስትል አበርታ ። እኔንም በይቅርታህ አስበኝ ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ