የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ድባቴ – ድብርት – መደንዘዝ

የሰው ልጆች ከታላላቅ ችግሮችና ውጣ ውረዶች በኋላ ከሚገጥሟቸው የሥነ ልቡና ጉዳቶች አንዱ ድባቴ ወይም ድንዛዜ ነው ። ድባቴ ችግር ስለመጣ የሚሰማን ስሜት ሳይሆን የነበሩት ችግሮች ጥለውብን የሚያልፉት የድንዛዜ ስሜት ነው ። ድባቴ ከኀዘንና ከልቅሶ ዘመን በኋላ የሚመጣ ስሜት በመሆኑ ማንም ሰው በቀላሉ ሊገነዘበው አይችልም ። መከራው ድምፅ ያለው ሲሆን ድባቴ ግን ድምፅ የለሽ ነው ። መከራው ብዙ ወዳጆችን ሊሰበስብና ሊበትንብን ሲችል ድባቴ ግን ብቻችንን የምናልፍበት የሕይወት ቀጠና ነው ። ሰዎች ብቻ ሳይሆን እኛ ራሳችንም ሳይቀር ይህን ስሜት ላንለየው እንችላለን ። ቀድሞ የምናደርገውን ነገር ዛሬ ማድረግ አለመቻላችን ፣ ፊት ያስደስቱን የነበሩ ነገሮች አሁን የማያስደስቱን መሆናቸው ፣ ፍቅርና ደግነትም ሕይወት ሳይሆን ሥራ እየሆኑብን ሲመጡ ምን ሆኛለሁ ብለን በስሱ ልንጠይቅ እንችላለን ። ይህ ግን ድባቴ ሊሆን ይችላል ። ድባቴ በተለያየ መንገድ ሊመጣ ይችላል ። ድባቴ ከጎርፍ በኋላ ያለ ትንሽ ፈሳሽ ፣ ከዶፍ በኋላ ያለ ካፊያ ልንለው እንችላለን ። ድባቴ ከቊስል በኋላ ያለ ጠባሳ ሲሆን ጠባሳው ግን የሚወጥር ስሜት አለው ።
ድባቴ የተለያዩ መነሻዎች ሊኖሩት ይችላሉ ። ትዳራቸውን እስከ ሞት ድረስ አስበውት እስከ መፋታት የሆነባቸው ሰዎች ድንገት ድባቴ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ። የፍርድ ቤት ክርክር ላይ ንዴት እንጂ ድባቴ የለም ። ሁሉም ነገር አብቅቶ ቁጭ ስንል ድባቴ ሊጀምር ይችላል ። በጣም የሚወዱት ልጅ በአደጋ ሕይወቱ ማለፉ ወደ ድባቴ ሊከት ይችላል ። ኋላ የመጣ ልጅ ቀድሞ መሄዱ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡ ይህን አደጋ እንዴት ያለ ትርጉም ይሰጠዋል ብለን ማሰብ ስንጀምር ድባቴ ሊቆጣጠረን ይችላል ። በመውለድ ሰዓት የሚመጣ ድባቴ ሊኖር ይችላል ። ይበልጥ ብቸኝነት በሚያጠቃው በፈረንጅ አገር ይህ ስሜት ሊጫጫን ይችላል ። በአገራችን ወላድን ከበብ ፣ ከበብ ማድረግ በረጅም ጉዞ ውስጥ የደረሱበት ትልቅ እውቀት ነው ። መውለድ ደስታ ቢሆንም ሊያስከትለው የሚችለው ድባቴም ይኖራል ። ከእስር የተፈቱ ሰዎች ይህ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል ። ከዓለሙ ጋር እኩል መጓዝ ሲያቅታቸውና መገለሉ የማያባራ ፈተና እየሆነ ሲመጣባቸው ራሳቸውን በዚህ ስሜት ውስጥ ሊያገኙት ይችላሉ ። ወዳጆቻቸው በተለያየ ምክንያት ከአጠገባቸው የራቁአቸው ሰዎችም አስበው ፣ አስበው ሲደክማቸው ድባቴ ውስጥ ይገባሉ ። የኑሮን እውነት አለመቀበል ለድባቴ ያጋልጣል ። የውስጣቸውን ገልጠው ለመናገር የማይፈልጉና መሸነፍ የሚመስላቸው ሰዎችም ድባቴ ያጠቃቸዋል ። ትልቅ ሕክምናና የዕድሜ ማራዘሚያ ውስጥን መግለጥ መሆኑን የሚያውቁ ጥቂቶች ናቸው ። አስቸጋሪ ጉዞ ያለውን ትዳራቸውን ተሸክመው የሚኖሩ ሰዎች ከዚህ በኋላ ዝም ማለት ነው ያለብኝ ብለው መቻል የሚመስል መቃጠል ውስጥ ሲገቡ ወደ ድባቴ ይገባሉ ። ከረሀብ ዘመን በኋላ የሚመጣው የማግኘት ዘመንም የራሱ ድባቴ አለው ። ሁሉንም ነገር ያደርግና “ታዲያ ምንድነው ትርጉሙ ? ” ብሎ ሲያስብ ድባቴ ውስጥ ይገባል ። ሱስ የለመዱ ሰዎች ሱሱ የቀረ ሲመስላቸው የሚሰማቸው የመደበት ስሜት አለ ።
ትኩስ መከራዎች ንዴትን ፍርሃትን ፣ መፍትሔ ፍለጋን ሲወስዱ ድባቴ ግን ትዕግሥት የሚመስል መደንዘዝና አጉል ድፍረትን ወይም ፍርሃን የተሸከመ ነው ። መከረኞች የመውጫውን መንገድ ሲፈልጉ በድባቴ ውስጥ ያሉ ሰዎች ነገሮች እንዲተረማመሱ ይፈልጋሉ ። ሁከትና መደበላለቅን የሚፈልጉ ሰዎች የዚህ ስሜት ተጠቂዎች ናቸው ። ሰዎች በዚህ ስሜት ውስጥ እንዳሉ ለማወቅ ከፍተኛ የድካም ስሜት ውስጥ ይገባሉ ። ስለ ሞቱ ሰዎች ከማዘን ተገላገሉ ብለው ያስባሉ ። በአደባባይ የሚታዩ ከሆነ መታየትን እየጠሉ ይመጣሉ ። ቀላል የነበሩ ተግባሮችን አሁን ለመከወን አቅም ያጣሉ ። በይሉኝታ ፍቅርንና አክብሮትን ቢሰጡም ይህ ግን ለእነርሱ ትልቅና የግድ የሆነ ሥራ ነው ። ደስተኝነት ማጣት ፣ ሁሉንም ነገር ሰዎች ያድርጉልኝ ብሎ በውክልና መኖር ፣ ገለልተኝነት ማብዛት አንዱ ምልክት ሊሆን ይችላል ።
በድባቴ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሊያስቡት የሚገባ ነገር አለ ። ያለፉት ቀኖች ላይስተካከሉ ይችላሉ ፣ የተሻለ ተግባር ግን ከትላንት ይልቅ ነገ ላይ አለ ። ያለፈውን በአስተማሪነቱ እንጂ በሕያውነቱ መጠቀም አንችልም ። በጸሎት ሁሉን ለእግዚአብሔር መግለጥ ትልቅ መንፈሳዊ ፈውስ ያመጣል ። ወደ አማካሪዎች ሂዶ በፍጹም ግልጥነት ማውራት ይጠቅማል ። በይበልጥ የሃይማኖት አባቶች በጸሎትና በመንፈሳዊ ምክር ስለሚያግዙ ይጠቅማሉ ። ቆየት ያሉና ነጻነት የሚሰጡን ወዳጆችን ማግኘትም የተሻለ መፍትሔ ያመጣል ። ማንበብና የሰውነት እንቅስቃሴ ወይም ስፖርት መሥራት አንዱና አስፈላጊ ነገር ነው ። ያለፉትን ዘመናት በይቅርታ መዝጋትና ነገን በአዲስነት መጠበቅ ትልቅ መፍትሔ ነው ። የድባቴ ስሜት ከእምነት ማነስ የመጣ ስሜት ነው በሚል ራስን መውቀስ ከንቱ ነገር ነው ። በተወሰነ ሰው ላይ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው የሰው ልጅ የሚያልፍበት መስመር መሆኑንም መረዳት መልካም ነው ። ብዙ ሰዎች እንዲህ ያለውን ስሜት ተቀብሎ ወደ አማካሪ ዘንድ መሄድ የውድቀት ያህል ያዩታል ። የጨጓራቸውን መታመም እየተቀበሉ ከጨጓራቸው ይልቅ ትልቅ ሥራ ያለበትን አእምሮአቸውን ሊረዱት አለመቻላቸው ይገርማል ።
የድባቴ ዘመን ሲያበቃ ድንገት ብርሃን ይበራል ። ምንድነው የያዘኝ ? በማለት ፈጥኖ ወደ ሥራው ይቀላቀላል ። ድባቴ የዘላለም ዕጣ ወይም የአምላክ ቅጣት አይደለም ። ወዳጆች ሆይ ይህም ያልፋል ።
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በዚህ ውስጥ ለሚያልፉ ወገኖች ሁሉ የድል ብርሃንን ያብራ ። አሜን ።
ዲአመ
ነሐሴ 24 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ