“በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አይገኝለትም” ይባላል። ብዙ ሰዎች ችግራቸውን ደብቀው መጨረሻ ላይ ሊረዱ በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ሆነው ይገኛሉ። ራሳቸውን እንደ ገደሉ ያህል ይቆጠራል፣ አብሯቸው ያለውም ሰው መርዳት ባለ መቻሉ ያዝናል። የማኅበራዊነትና የቤተሰብ ጥቅሙ መመካከር መቻሉ ነው። መመካከር ከሌለው ከተማው በረሃ ነው። የሰው ቅርጽ ማየት ሳይሆን የሰውነትን በጎነት መለዋወጥ የመኖር ትርጉም ነው።
ለመንፈሳዊ አገልጋይ ያለበትን ውድቀት የደበቀ ምእመን ለሰይጣን ምርኮኛ መሆኑ የታወቀ ነው። ከሰይጣን ታላላቅ ፈተናዎች አንዱ ድብቅነት ነው። ልጆች ድብቅ በሆኑ ቁጥር ውሎአቸውንና ስሜታቸውን በሰወሩ መጠን እየተጎዱ ይመጣሉ። ብዙ ልጆች በቤት ውስጥ ቢኖሩም ወላጆቻቸውም አያውቋቸውም። የዚህ ችግር ልጆችን በሁሉ ነገር መቆጣት ፣ ማቅረብ አለመቻል ነው። ምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ እንደምንቀበላቸው ካወቁ፣ የልባችንን ስፋት ካስተዋሉ ሊነግሩን ይችላሉ። ለልጆች ወላጅ ብቻ ሳይሆን ጓደኛም መሆን መልካም ነው። ሁሉን ለማወቅ ጥረት ካደረግን ልጆች ድብቅ ይሆናሉ። ማንም ለመርማሪ ፖሊስ ግልጽ መሆን አይፈልግምና ።
መፍትሔ የሚገኝበት ቦታ ላይ ድብቅ መሆን አደጋው ከፍ ያለ ነው። ለወላጆች፣ ለጓደኛ፣ ለሐኪም ፣ ለሥነ ልቡና አማካሪ ፣ በአበ ነፍስ፣ ለአገልጋይ ግልጽ መሆን በጣም ጠቃሚ ነው።
ድብቅነት ብለን ያነሣነው ካለማወቅና በእውቀት ድብቅ የሆኑ ሰዎችን ለማረም ነው። ድብቅነት ሽሽግነት ፣ ሽማቂነት፣ ስውርነት ፣ ለሰዎች ቅኔ መሆን፣ በልብና በአካል ከወዳጆች መሸሸ፣ ምንነቱ የማይታወቅ ሰው መሆን ፣ ግራ በማጋባት መደሰት ነው። ድብቅነት በተለያዩ ምክንያቶች ይመጣል። አሳብን መግለጽ በማይቻልበት ቤተሰብ በማደግ ሊመጣ ይችላል። የጨዋነት መለኪያ ዝምታ አይደለም። በአንዳንድ ቤተሰብ ልጆች እንዳይናገሩ በገደብ ያድጋሉ። ግልጽ በመሆናቸው ምክንያት ቁጣና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ድብቅ ይሆናሉ። ሌሎች ደግሞ በጉራ ኑሮ ተሸፋፍነው ስለሚኖሩ ሰዎች ከቀረቡአቸው ባዶነቱ ገሀድ እንዳይወጣ ድብቅ ይሆናሉ።
ያልሆነውን እንደሆንን አድርጎ ማቅረብ የሆነውን እንድንደብቅ ያደርጋል። በዚህ ዓለም ላይ ጥቅሙም ጉዳቱም የባለቤቱ የሆነበት ምርጫ ብዙ ነው። ባለጠጋ፣ አዋቂ፣ ጌጠኛ ብንሆን ለራሳች ን ነው። ይህ ሁሉ ባይኖረንም የመኖር መብት አለን። የድብብቆሽ ኑሮ እንዳንኖር የሆነውን መቀበል ያስፈልጋል። ራሳችንን ስንቀበል ሰዎች ይቀበሉናል። በሽታችንን፣ መልካችንን፣ ኑሮአችንን መቀበል ስልጣኔ ነው። መቀበል ለዓለም ችግር ትልቅ መፍትሔ ነው:: ችግሮች ሰባ ፐርሰንት የሚቀንሱት በመቀበል ነው። ትክክለኛ ማንነታችን ሁልጊዜ ሊገኝ ይችላልና አናፍርም፣ ስለዚህ የሆነውን ይዞ መቅረብ ይገባናል። ያን ጊዜ ከሰዎች ፍቅርና ክብር እናገኛለን። ድብቅነት ሰዎች ራሳቸውን አስረው የሚያሰቃዩበት የዓለማችን ትልቁ እስር ቤት ነው። ድብቅ በሆንሁ መጠን ክብር አገኛለሁ ብሎ ማሰብ ሥቃይ ውስጥ ይከታል።
ድብቅነት የአእምሮ ፈተና፣ የሰይጣን ውጊያ ሊሆን ይችላል። ሁሉ ሰው ስለ እነርሱ ጥናት እያደረገ የሚመስላቸው፣ ሰዎች ይከታተሉኛል ብለው በማሰብ በብዙ አጥር ውስጥ ራሳቸውን የሚከቱ ሰዎች አሉ። የዚህ ችግር ለከፍተኛ ጭንቀት እየዳረጋቸው ይመጣል። ነገሮችን በቀላሉ ከማየት እያከበዱት ይመጣሉ። እያንዳንዱን የሰላምታ ልውውጥ እየፈሩት ይመጣሉ። እፈልጋለሁ አልፈልግም ብለው ቁርጡን ከመናገር ዙሪያ ገባውን የሚዞሩ ይሆናሉ። ማንኛውም ሰው ሊያጠቃኝ ይቻላል ብለው ስለሚያስቡ የቅርብ ሰዎቻቸውንም አያምኑም። በሚፈለጉበት ሰዓት ከመገኘት በአሳቻ ሰዓት ራሳቸው ሌሎችን መፈለግ ይመርጣሉ። የማላውቀውን ስልክ አላነሣም ፣ ብዙ ሰዓት ሰዎችን ማግኘት አልፈልግም ፣ ጨዋታ ይረብሸኛል ወደ ማለት ይሄዳሉ:: ስላሉበት ሁኔታ ማንም ሰው አለማወቁ የድል ስሜት እየመሰላቸው ይመጣል።
የድብቅነት ችግሩ ጉልበት ይጨርሳል። ጦርነት በሌለበት እየፈጠረ ይዋጋል። ነገሮችን አጋኖ ይመለከታል፣ ስልክ ለመደወል ላስብበት ይላል። ችግር ላለመስማት ሽሽት ውስጥ ይገባል። የማይታወቅ ፍርሃት ይንጠዋል። የቀን ሰላም፣ የሌሊት እንቅልፍ ይከዳዋል።
ለሁሉ ሰው መገለጽ ተገቢ አይደለም። በቦታው ግልጽ አለመሆን በሽታ ነው። ድብቅነት ከሰዎች ጋር ያለንን ኅብረት ያፈርሳል። አንዳንድ ሰዎች ከስለላ ስልጠና የተነሣ ድብቅ ይሆናሉ፣ ሌሎች ደግሞ ተንኮለኛ በመሆን ድብቅ ይሆናሉ። ስለ እኔ ማንም አያውቅም የሚል ጨዋታ መጫወት ድል ይመስላቸዋል። የእነዚህ ድብቆች የኋላ ዕድሜ በጣም ከባድ ይሆናል። ትዳራቸውም ፣ ወዳጅነታቸውም ላይጸና ይችላል። ድብቅነት ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ ይዘወተራል። ግልጽ መሆን ሕይወትን ቀላል ያደርጋል። ሰዎች ከእኛ ጋር መሆን የሚፈልጉት ቀለል ያለ ሕይወት መምራት ስንችል ነው።
ድብቅነት እንደ ክፉ ሰው እንድንታይ ያደርጋል። ሰዎች እየፈሩን ይሸሹናል። የሰዎችን እርዳታ በፈለግን ሰዓት እንኳ እንዳናገኝ ያደርገናል። ድብቅነት ለሞት ይደርጋል፣ አሰቃይቶ በመግደልም የታወቀ ነው። ሐኪም ቤት ስንሄድ የመጀመሪያው ምርመራ “ተንፍስ” የሚል ነው። መተንፈስ የተቃጠለውን አየር ያወጣል፣ ያለንበትን ሁኔታ ይገልጣል፣ መፍትሔ ያመጣል።
ትልቅ መንፈሳዊ ውድቀት የሚመጣው በድብቅነት ነው:: ካህኑ ሲናዝዝ፦ “መንፈስ ቅዱስ ያወቀውን፣ ሰይጣን የሸመቀውን ኃጢአታቸን ይቅር ይበለን” ይላል። ሽምቅነት የሰይጣን ጠባይ ነው:: ሽምቅነት ችግሩ አለ፣ መፍትሔ እንዳያገኝ መደበቅ ነው ።
ከድብቅነት እንውጣ! በየጊዜው መተንፈስን እንለማመድ ፣ ከቅርብ ሰዎቻችን ጋር እንመካከር፣ አብሮ የመኖር ዋጋው ደስታና ችግርን በጋራ መካፈል ነው::
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 7 ቀን 2018 ዓ.ም.