ገና በለጋ ዕድሜሽ የዘላለም ምሪትን እንዴት አገኘሽ ? ከሁሉ በላይ የሆነውን ስትቀበዪ አሁንም በትሕትና እንዴት ጸናሽ ? ሰው አምላኩን በሕልሙ አይቶ ይታበያል ፣ አምላክን ወልደሽ አሁንም ትሑት መሆንሽ ይገርማል ። ድንግል ሆይ ! ተከታዮችሽን ደናግል አበዛሽ ። ደናግል መሐን አይደሉም ፣ ታላላቆችን እንደሚወልዱ ባንቺ ተምረዋል ። ድንግልም እንደምትወልድ ያንቺ ሕይወት ያስተምራል ። ልጅሽም በገዳመ ቆሮንቶስ ቆይቶ የደናግል መኖሪያን ባረከ ፣ በቃና ዘገሊላም ሰርገኞችን ቀደሰ ። ድንግል ሆይ ! አምላክን ማገልገል የከበረ ዋጋ አለው ፣ አምላክን መውለድ ግን ከዚህ ሁሉ በላይ ነው ። ጽኑ ፍላጎትሽ ታናናሾችሽን ማገልገል ነው ፣ ታላቁን አምላክ በማኅፀንሽ ማስተናገድ ፣ በክንዶችሽ መታቀፍ ግን ላንቺ ሁኗል ። ማንም ቢመኝ የማያገኘውን ፣ በመመረጥ ብቻ አንቺ አግኝተሽዋል ። በዚህም ከሴቶች ሁሉ ይልቅ ቡርክት ነሽ ። አይሁድ ለሕጋቸው ቀንተው እንዳይጎዱሽ ጥበቃ ሆነልሽ ፣ ሕግን የሰጠው ግን በማኅፀንሽ ነበረ ። ሄሮድስ እስከ ግብጽ አሳደደሽ ። ልጅሽ የሚጠላ ሁሉ አንቺንም ይጠላሻል ።
ድንግል ሆይ ! የልጅሽ ስደት ያንቺ ስደት ነው ። የምእመናን ስደትም የልጅሽ ስደት ነው ። ከአነስተኛዋ ከተማ ከናዝሬት የአርያሙን ንጉሥ ስተቀበዪ ፣ ገዳዮች ባሉባት መንደር ጠባቂውን መልአክ ገብርኤልን ስታዪ ፣ በረከሱት አገር የተቀደሰውን ልጅሽን ስታስተናግጂ ከቶ ምን አልሽ ይሆን ? አብርሃም በድንኳኑ ሥላሴን አስተናገደ ፤ አንቺ ግን በማኅፀንሽ አስተናገድሽ ! አንቺን የወደደ እግዚአብሔር አብ ቡሩክ ነው ። የዘላለም አባት ሳለ አንቺን እናቴ ብሎ የጠራ እግዚአብሔር ወልድ ቡሩክ ነው ። የተዋሕዶው አጋፋሪ የሆነው አንቺን ያከበረ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱም ቡሩክ ነው ። ጭልጥ ብለው የጠፉ ፣ ደረስን እያሉ ይበልጥ ከመፍትሔው የሚርቁ የዚህ ዘመን ሰዎች አንቺን ሊማሩሽ ይገባቸዋል ። ትሑት በመሆን ታላቅ መሆንን ካንቺ እንማራለን ።
ድንግል ሆይ ! ጉልበት የለሽ ማንንም አትጎጂም ፣ በዘመንሽ ግን ብዙ ጠላትነትን አተረፍሽ ። ሁሉ በሩን ዘግቶብሽ ልጅሽን በበረት ወለድሽ ። ጌታን ወልጄ እንዴት እሰደዳለሁ ባለማለትሽ ዓለሙ ሁሉ እናቴ አለሽ ። በነፍስሽ ሰይፍ በማለፉ የሰማዕታት እናት ሆንሽ ፣ የሕማም ሰው ክርስቶስን በመውለድሽ አዛኝቷ ተባልሽ ። በእውነት ላንቺ ሰላምታ ይገባል ። ቅጥሩ የፈረሰበት ፣ እውቀት እብደት የሆነበት ፣ ሃይማኖት የሕይወት ለውጥ መሆኑን የዘነጋው ፣ መንፈሰ እግዚአብሔርን ትቶ መንፈሰ ትውዝፍትን/የምንዝር ጌጥ ወዳድነትን/ የተከተለ ፣ ቃለ እግዚአብሔርን አግኝቶ ሳለ መልሶ የጣለው ፣ ሁሉን በሚያሳድረው በልጅሽ ብርሃን ምነው በተሰወረ !!!
ማርያም ሆይ ስለዚህ እንወድሻለን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 4 ቀን 2014 ዓ.ም.