ጌታችን በቤተ ልሔም ሲወለድ ክስተቶች ታይተዋል ። በ12 ዓመቱም ወደ ቤተ መቅደስ ሲመጣ አንዳንድ ወሬዎች ወጥተዋል ። እስከ ሠላሳ ዓመቱ ግን በጫካ ሳይሆን ችምችም ባለው በናዝሬት የድሆች መንደር ኖሯል ። በናዝሬት የኑሮ ጫና አለ ፣ ሕዝቦችዋ ግን ጠንካሮች ናቸው ። በሽተኛቸውን ሐኪም ዘንድ ለመውሰድ ይቸገሩ ይሆናል ። ዙሪያውን ከብቦ ለማስታመም ፣ ሳይጸየፉ ለማገላበጥ ግን ይቀላቸው ነበር ። የንጽሕና ዕቃዎች ላይኖሩ ይችላሉ ፤ በናዝሬት ግን ሳይጸየፉ ወገንን መርዳት ይታያል ። ድሆች የገንዘብ እንጂ የፍቅር ችግረኞች አይደሉም ። የሚሰጡት ንብረት ላይኖራቸው ይችላል ። ራሳቸውን ሰጥተው የሚያፈቅሩ ናቸው ። ራሱን ሊሰጥ የመጣው መሢሕ ራሳቸውን ለመስጠት በማይሳሱት በድሆች መንደር አደገ ። በድሆች ሰፈር በትንሹ በረከት መደሰት ይዘወተራል ። በትንሽ ችግር ግን አይበገሩም ። ሁልጊዜ ጫጫታ ስላለ እንደ ባለጠጎች ሰፈር ጭው ያለ ፣ ፍርሃት ያጠላበት አይደለም ። ለሰርጋቸው ባንድ አይቀጥሩም ፣ ከሰርጉ ቀን በፊት ለሦስት ወራት ከበሮ ተከራይተው ይጨፍራሉ ። የአንዱ ሰርግና ልቅሶ የሁሉም ነው ። ሚዜ አይከራዩም ፣ የሬሳ ተሸካሚ አይቀጥሩም ።
የድሀ ልጆች ተጠጋግተው ይተኛሉ ፣ እስከ ሞት ድረስም ይዋደዳሉ ። የባለጠጋ ልጆች ግን በየክፍላቸው ቆልፈው ከስልካቸው በቀር ዘመድ የላቸውም ። በድሆች ሰፈር በር አይቆለፍም ። የአንዱ እንግዳ የሁሉ ነውና ዘው ብሎ ገብቶ እንጀራ አጥፎ መውሰድ የተለመደ ነው ። የባለጠጎች ሰፈር የአካባቢ ጥበቃ ፣ የቤት ዘበኛ ፣ የኤሌክትሪክ ሽቦ ፣ አደገኛ አጥር ፣ ካሜራ ፣ ጽኑ በር ፣ የጦር መሣሪያ አለው ። ቅዠቱ ግን ተመን የለውም ። መዋኛ ያለው ቤት ቢሠሩም ዋኝተው አያውቁም ። እስከ ዛሬ ድረስ ገብተው የማያውቁበት ክፍል አላቸው ። ቅቤና ማሩ ለቤቱ ክብር ቢገባም አይበሉትም ። “ታየዋለህ እንጂ አትበላውም” የተባለው ተፈጽሟል ። አብዛኛው ባለጠጋ የንብረቱ ዘበኛ ነው ። የጥንት ሰው ምርቃት የሚመስል እርግማን ነበረው፡- “ቤትህ አይቆሽሽ” ይላል ። ሰው የማይመጣበት ቤት አይቆሽሽም ፣ ግን ቆንጆ መቃብር ነው ። ሰው የሚመጣበት ግን ይቆሽሻል ፣ ሕይወት ያለበት ነው ። “ሰው ከነክፋቱ መልካም ነው” ይባላል ። ከሰው ርቆ ፣ ከቢጤ ጋር ተቧድኖ ቢኖሩት የሚያገፋፋ እንጂ የሚያቀራርብ ነገር የለም ።
ማግኔት የሚስበው ተቃራኒውን ነው ። ሰውም ከእርሱ ከሚያንሰው ጋር ቢኖር መደጋገፍ ይኖራል ። እግዚአብሔር ላንዱ ጤናን ፣ ላንዱ ገንዘብን ፤ ለአንዱ ሙያን ለሌላው አቅምን ሰጥቷል ። ድሆችና ባለጠጎች ተፈላላጊ ናቸውና ተደባልቀው ቢኖሩ ሕይወት ጣዕም ይኖረዋል ። “ድሀ ፒያሳ ምን ይሠራል ? ባሕር ዳር ሄዶ አይኖርም ወይ ?” ብለዋል ያለፉት መሪ ። ከተማይቱን እንደ ቅኝ ገዥዎች የባለጠጋና የሕጋዊ ዘራፊ ለማድረግ ፣ ድሀውን ጎርፍ እንደ ተፋው ደለል ዳር ለማውጣት ብዙ ተሞክሯል ። የሚገርመው የድሀ ልጆች የሆኑት ድሀን መጥላታቸው ነው ። ድሆችና ባለጠጎች ተመጋጋቢ ናቸው ። ባለጠጎች የድሆችን የሆድ ክፍተት ይሞላሉ ፣ ድሆች የባለጠጎችን የደስታ ክፍተት ይሞላሉ ። ጌታችን ከድሀ ተወለደ ። ከድሆች ከተማ ከቤተ ልሔም ልደቱን አደረገ ። ከድሆች መንደር ከናዝሬት አደገ ። ከብርጭቆ ይልቅ በጠራው ውኃ በአባናና በፋርፋ ሳይሆን በድፍርሱ በዮርዳኖስ ተጠመቀ ። ንዕማን በናቀው ወንዝ ጌታችን ተጠመቀ (2ነገሥ. 5 ፡ 12) ።
እርሱ ድፍርሶችን ይወዳል ። ቶሎ የሚደሰቱ ፣ ቶሎ የሚከፉትን ስንጥቅ ልባቸውን ገጥሞ ይዟል ። ጨርሶም በደስታ እንዳይጠፉ ፣ ጨርሶም በኀዘን እንዳይሞቱ ሚዛኑን ይቆጣጠራል ። እርሱ ስሜቱ ቶሎ የሚነካውን ፣ ሆደ ባሻውን ፣ ጀውጃዋውን ጴጥሮስን መርጧል ። ድፍርሶች ሁልጊዜ በተጠንቀቅ የሚኖሩ ናቸው ። መከራን ሦስት ጊዜ ይቀበሉታል ። መጀመሪያ፡- በስጋት ፣ ሁለተኛ፡- በቀጥታ ፣ ሦስተኛ፡- በትዝታ ይጎዱበታል ። ድፍርሶች ስሜታቸው ቶሎ የሚታወቅ ፣ አድብተው መግደል የማያውቁ ፣ አፋቸውና ልባቸው አንድ የሆነ ፣ ቶሎ የሚያለቅሱ ፣ ለወደቀ የሚንሰፈሰፉ ፣ ያላቸውን ሲበትኑ ለነገ የማይሉ ፣ የተጎዳ እየፈለጉ አብረው የሚውሉ ፣ ዙፋን ሲዘረጉላቸው መሬት የሚመርጡ ፣ ዓለም ከንቱ ሥጋም ፈራሽ መሆኑ የገባቸው እንደሆኑ ጌታ ያውቃል ።
ዮርዳኖስ ድፍርሱ እስከ ዛሬ ድረስ ይፈስሳል ። ሆደ ባሾች ዛሬም አሉ ። ሆደ ባሾች ፣ ቶሎ የሚከፉ ፣ ሰው የለኝም የሚሉ ፣ የራሳቸውን ብዙ ስጦታ አሳንሰው የሌላውን ጥቂት ስጦታ አተልቀው የሚያዩ ፣ ከሰው የሰውነትን ግብር ፈልገው ባጡ ቀን የሚያለቅሱ ናቸው ። ክፉዎች ፣ ሁሉ ሰው እንደ እነርሱ ስለሚመስላቸው ፣ ከሰው ቀርቶ ከመልአክም መልካም ነገር አይጠብቁም ። ሰውን ለመጠቀሚያነት ብቻ ይፈልጉታል ። የጠራ ውኃ ናቸው ። ፊታቸው ብርሃን ፣ ጥርሳቸው በረዶ ነው ። ልባቸው ግን የአረም እርሻ ነው ። እግዚአብሔር ጉዳዩ ከስሜተ ስስ ሰዎች ጋር ነው ። ቃል ኪዳኑም የድንጋዩን ልብ ፣ ቶሎ የማይነካውን ከውስጣችሁ አውጥቼ ፣ በጣት ሲነኩት ስርጉድ የሚለውን ፣ በቀላሉ የሚነካውን የሥጋ ልብ እሰጣችኋለሁ የሚል ነው (ሕዝ. 36 ፡ 26) ። ይህ ቃል ኪዳን ነውና በእግዚአብሔር ቤት ገና በስሌት ፣ በሽምቅነት ፣ በሽንገላ ፣ ሌላውን በማደንዘዝ የምንኖር “ጌታ ሆይ ደንዳናውን ልቤን ፣ ስሜት አልባውን በድንነቴን ከእኔ አውጣልኝ” ብለን መጸለይ ይገባናል ። ድፍርስነት ቋሚ ጠባያችን እንዲሆን የማይፈቅደው ፣ ስሜታችንን ተረድቶ ሊያግዘን ከእኛ ጋር ነው !
ጌታችን ከድሀ ሰፈር አደገ ፣ ከድሆች ወንዝ ከድፍርሱ ዮርዳኖስ ተጠመቀ ። በማር በቅቤ ሳይሆን በርካሹ ውኃ ተጠመቁ አለ ። ባለጠጎችና ድሆች በጥምቀት አንድ ይሆናሉ ። በውኃና በዕራቁትነት።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 30 ቀን 2016 ዓ. ም.