መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ጀምበር ሳይጠልቅ

የትምህርቱ ርዕስ | ጀምበር ሳይጠልቅ

ጊዜ በዘላለማዊነት ሲለወጥ፣ እግዚአብሔር ወደ እኛ ሕይወት ሲመጣ ሥራችንን ፈጽመን ያገኘን ይሆን? በዕድሜ የገፉ አንድ ሽማግሌ ታላቅ ሥራ ጀምረው አገኘኋቸው ። እኚህ አባት ዘጠና ዓመት አልፏቸዋል። “እኔ እንኳ ከሰማይ ጥሪ መጥቶልኛል፣ በዚያ ሊሾመኝ ና እያለኝ ነው፤ ለቀሪዎቹ ላስተካክል ብዬ ነው” አሉኝ። በዕድሜ የገፉ ረጅም ቀጠሮ አይዙም ፣ አስቸኳይ ጥሪ ሊመጣ ይችላል ብለው በየዕለቱ ሥራቸውን ይፈጽማሉ። ጀምበር ሲያዘቀዝቅ ያልሠራነው ተግባር ፊታችን ላይ ድቅን ብሎ እንዳያስተክዘን ቶሎ ቶሎ ሥራችንን መፈጸም አለብን። ዕድሜአችን ቀኑን ይመስላል፣ ቀኑ ይመሻል የእኛም ዘመን ያበቃል። ቆመን ውለን ማታ እንተኛለን ፣ ኖረን አንድ ቀን እንሞታለን።

ሥራችንን በመፈጸማችን እግዚአብሔርን እናከብረዋለን። አንድ ልጅ ትልቅ ደረጃ ሲደርስ ዘመድ አዝማድ ወላጆቹን እንኳን ደስ አላችሁ፣ የእናንተ የልፋት ውጤት ነው ብሎ ያመሰግናቸዋል ፣ ደግሞም ያከብራቸዋል። እግዚአብሔርም በጸጋ የወለደን ፣ በፍቅር ያሳደገን አባታችን ነውና በእኛ ሥራ ምስጋናና ክብርን ይቀበላል። በሕይወታችን ደስታን የምናገኘው እግዚአብሔር በእኛ ምርጫና ተግባር በተመሰገነውና በከበረው መጠን ነው። እግዚአብሔርን በእኛ ምድር እናከብረዋለን ፤ በእርሱ ዓለም በሰማይ ያከብረናል።

ሥራውን ያልፈጸመ ሰው በሕሊናው ዕረፍት፣ በመንፈሱ ሐሴት የለውም። ሥራውን የፈጸመ ለመሞትም ዝግጁ ነው። ጀምበሩ ሲያዘቀዝቅ፣ ቀኑ ሲፈጸም ከቍጭት የሚድን ተግባሩን የፈጸመ ሰው ብቻ ነው።  መሥራት እየፈለግን ያልሠራናቸው ብዙ ተግባራት አሉ። ቆይ እያልን የገፋናቸው ሥራዎች ፊት ለፊታችን ድቅን እያሉ ያውኩናል። የእኛ ቀን ዛሬ ነውና ልንጀምራቸው ይገባል። ጀምረን ባይሳካ እንኳ አለመሳካት ያናድዳል እንጂ አያጸጽትም። ስላለፈው ትላንት መቆጨት ጥቅም የለውም። ዛሬ በእጃችን ላይ ያለች መክሊት ናት። የዛሬው መነሣት ትላንትን የሚክስ ፍሬ ሊኖረው ይችላል።

ጀምበር ሳያዘቀዝቅ ቀኑ ሳይፈጸም ፣ የሕሊና ወቀሳ ሳይጀምር፣ ሁሉም ነገር ከሄደ በኋላ መሰማራት ሳይመጣ ፍቅራችንን ለወዳጆች እንግለጥ። ባለ ውለታዎቻችንን ሳናመሰግን ሞት እንዳይወስዳቸው ንቁ እንሁን። ስልክ እንኳ ለመደወል እያሰብን እጃችንን የያዘን ምንድነው? ከማያረኩን ጋር ጊዜን እየፈጸምን እነዚያን የልብ ሰዎች ባሰብን ቁጥር መቆጨት ውስጥ መግባት ሊያበቃ ይገባዋል።

የበደልናቸውን ይቅርታ ሳንጠይቅ ሞት እንዳይመጣብን ፣ የበደል ቋጥኝ ተሸክመን ወደ ሰማይ እንዳንሄድ ዛሬ ልናውቅበት ይገባል። የበደልናቸው የሞቱ ቀን መቃብራቸው ላይ ዋይ ዋይ ከማለት፣ ይቅር በሉኝ እያሉ ከንቱ ጩኸት ከመጮህ ዛሬ ይህች ጀምበር ሳትጠልቅ ሰላም ማውረድ ይገባል።

ከሁሉ በላይ እንደ ዓይን ብሌን የሚጠነቀቅልንን፣ አበሳችንን የሸፈነልንን፣ ብቻውን የረዳንን ጌታ ሳናገለግል፤ ለወንጌሉ ሥራ ሳንቆም ዘመናችን እንዳይፈጸም ዛሬ መነሣት ይገባል። በበደላችን ሁሉ ይቅር እንዲለን በንስሐ ወደፊቱ መቅረብ ያስፈልገናል።

መኖር ደስ የሚለው የመሥራት፣ የመካስ ፣ ይቅርታ የመጠየቅ፣ የማመስገን ዕድል ስለሆነ ነው።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 24 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ