የትምህርቱ ርዕስ | ገራም

 “እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤…የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ” 1ጢሞ. 3፡2-3
ማር ብቻ አትሁኑ ልሰው እንዳይጨርሷችሁ ፣ እሬትም አትሁኑ እንዳይተፏችሁ ይባላል ። ሚዛናዊ መሆን የምድር ኑሮን ቀላል ያደርጋል ። የሚጨቃጨቅ ሰው የሚኮሰኩስ ነው ። ማቅ ቢሞቅም ይኮሰኩሳልና ምቾት አይሰጥም ። ተጨቃጫቂም ሰው ቢያበላ ቢያጠጣ ያሳቅቃልና ዕረፍት አይሰጥም ። ተጨቃጫቂ ፋታ የማይሰጥ ነው ፣ ገራም ለጊዜና ለእግዚአብሔር እየተወ በሰው መለወጥ የሚያምን ነው ። ተጨቃጫቂ ትላንት ላይ የሚቆም ሲሆን ገራም ነገን የሚያይ ነው ። ተጨቃጫቂ ስህተትን ፈላጊ ሲሆን ገራም ስህተትን የሚሸፍን ፣ እግዜር በምድር ነው ። ተጨቃጫቂ እንደ ምዕራብ የፀሐይ መጥለቂያ ነውና ልብን ያሳዝናል ፣ ገራም እንደ ምሥራቅ የፀሐይ መውጫ ነውና ልብን ያስደስታል ።

መጨቃጨቅ አትኩሮ ማየት ነው ፣ ገራምነት ማለፍ ነው ። መጨቃጨቅ አለማለፍ ነው ፣ ገራምነት ይቅርታ መስጠት ነው ። መጨቃጨቅ ይቅርታ ሲባሉም አለማወቅ ነው ፣ ገራምነት ለሰው ሁሉ ይቅርታ ሰጥቶ መኖር ነው ።መጨቃጨቅ እኔ ብቻ ተጎዳሁ ባይነት ነው ፣ ገራምነት ላስቀይም እችላለሁ ማለት ነው ። ተጨቃጫቂነት ሕመምን አለመርሳት ነው ፣ ገራምነት የበለጠውን እያሰቡ ማመስገን ነው ። ተጨቃጫቂነት ሰው ሁሉ ችግር አለበት ብሎ ማሰብ የሚወልደው ነው ፣ ገራምነት ሰው ከነክፋቱ ጥሩ ነው ብሎ መቀበል ነው ። ተጨቃጫቂነት ነገር መቆርጠም ፣ ቃላት መሰንጠቅ ነው ፣ ገራምነት አርሞ መስማት ነው ። ተጨቃጫቂነት ወዶ መታወክ ነው ፣ ገራምነት የልብ ዕረፍት ነው ። ተጨቃጫቂነት የያዙትን አለመልቀቅ ነው ፣ ገራምነት መንገድ አጋምሶ መቀበል ፣ ሌሎችን ከነአስተሳሰባቸው ማስተናገድ መቻል ነው ። ተጨቃጫቂነት ሆዳምነት ነው ፣ ገራምነት በመጠን መኖር ነው ። ተጨቃጫቂነት በብዛት ማመን ነው ፣ ገራምነት በበረከት ማመን ነው ።
ተጨቃጫቂነት ሁሉን ነገር አጨልሞ ማየት ነው ፣ ገራምነት የተሻለ ቀን መጠበቅ ነው ። ተጨቃጫቂነት ማሩን አምርሮ ፣ ወተቱን አጥቁሮ ማየት ነው ። ገራምነት ነገርን በልኩ የሚያይ ነው ። ተጨቃጫቂነት ወንድሙ አጉረምራሚነት ነው ፣ የገራምነት ወንድሙ የዋህነት ነው ። ተጨቃጫቂነት ድንበሬ ተነካ ማለት ነው ፣ ገራምነት መነካካት ተፈጥሮ ነው ብሎ የሚያምን ነው ። ተጨቃጫቂነት አይረካምና አመንዝራነት አለው ፣ ገራምነት የከተማ መናኝ መሆን ነው ። ተጨቃጫቂነት ወርቅ አለመጥገብ ነው ፣ ገራምነት በመስጠት መደሰት ነው ። ተጨቃጫቂነት ወገናዊ ነው ፣ ገራምነት ግዛቱ ሰፊ ነው ። ተጨቃጫቂነት ነቃፊነትና ቊጣ የሚባሉ ሁለት ክንፎች አሉት ፣ ገራምነት አመስጋኝነትና ትዕግሥት የሚባሉ ሁለት እግሮች አሉት ። ተጨቃጨቂነት ለመብረር ይሻል ፣ ገራምነት ለመራመድ ይፈልጋል ። ተጨቃጫቂነት በራሱ ይናደዳል ፣ ገራምነት በእግዚአብሔር ይደሰታል ።
ተጨቃጫቂነት አምባገነን ነው ፣ ገራምነት ትሕትና ነው ። ተጨቃጫቂነት ራሱ ወድቆ የልጆቹን መቀደስ የሚሻ ነው ፣ ገራምነት ምሳሌ መሆን ነው ። ተጨቃጫቂነት ያለፈውን ስህተት የሚቆጥር ነው ፣ ገራምነት ያለፈውን ጥሩ ጊዜ የሚያስብ ነው ። ተጨቃጫቂነት የሚያስበው ያጣውን ነው ፣ ገራምነት ያገኘውን የሚቆጥር ነው ።
ገራምነት ስሜት አልባ ሁኖ ስድብና ነቀፋን አይሰማኝም ማለት አይደለም ።ገራምነት እንደ ሞኝ ተቆጥሮ ሞፈር ከደጁ ሲቆረጥ ማየት አይደለም ። ገራምነት እግሬ ላይ ቆማችኋል ብሎ ለመናገር እየታመሙ ዝም ማለት አይደለም ። ገራምነት ልብሱን ጨርሰው ቆዳውን ሲገሸልጡት አይበርደኝም የሚል አይደለም ። ገራምነት ሁልጊዜ ይቅርታ ጠይቅ ተብሎ ያለ ጥፋቱ የሚረገጥ አይደለም ። ገራምነት ሌሎች ያሻቸውን ሲያደርጉ ድንበራቸውን የማያሳውቅ አይደለም ። ገራምነት ስለ እርሱ ሌሎች እንዲናገሩለት የሚፈልግ የውክልና ኑሮ ፈላጊ አይደለም ። ገራምነት እርሱ ተበድሎ ይቅርታ የሚጠይቅ አይደለም ። ገራምነት ሰዎችን ካጣሁ ምን እሆናለሁ ብሎ ቢጭኑበት አህያ ፣ ቢለጉሙት ፈረስ መሆን አይደለም ። ገራምነት ውሻውም ዶሮውም ሲነክሰው የሚስቅ አይደለም ።
መጨቃጨቅን ብቻ መተዉ በቂ አይደለም ፣ ገራም መሆን ይገባል ። ገራምነት ቀጥሎ ያለው ነው፡-
1-  ሰውን ዕድሜ እንደሚያስተምረው ፣ እግዚአብሔር እንደሚለውጠው ያምናል ።
2-  ነገ የተሻለ እንደሆነ ይቀበላል ።
3-  ያየውን ለማሳየት ፣ የሰማውን ለማሰማት የማይሻ ነው ።
4-  የጨለመውን ልብ በፈገግታና በመልካም ቃል የሚያበራ ነው ።
5-  በሁለት ዓይን ሰዎችን የማያይ ፣ በሁለት ጆሮ ሰዎችን የማይሰማ ነው።
6-  ሲበድል ማሩኝ ፣ ሲበደል ይቅርታ ለማለት የማይቸገር ነው ።
7-  ይቅርታ ለማድረግ የሚታገል ሳይሆን የይቅርታ ሰው ለመሆን የሚሻ ነው ።
8-  ልበድል እችላለሁ ብሎ የሚያስብ ነው ።
9-  የደረሰብኝ ሌሎች ከደረሰባቸው ትንሽ ነው ብሎ የሚያመሰግን ነው ።
10-         ሰው መልካም ነው የሚያስብ ነው ።
11-         የሰዎችን ግድፈት አትኩሮ አለማየትና አጥብቆ አለመስማት ነው።
12-         እንደ እርሱ የማያምነውንና የማያስበውን ሰው መውደድ ነው ።
13-         ለመብላት የሚያስፈልገው መሰብሰብ ሳይሆን ፈቃደ እግዚአብሔር መሆኑን የሚያምን ነው ።
14-         ሰውን መልአክ አድርጎ የማይስል ነው ።
15-         ምን ጎደለኝ ? ሳይሆን ምን አለኝ ? የሚል ነው ።
ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል ።
1ጢሞቴዎስ 42
ጥር 23 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም