የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጊዜና ማጣት

“ሰው ከጊዜና ከማጣት ብዙ ይማራል ።”

እግዚአብሔር አስተማሪ ነው ። እግዚአብሔር የሚያስተምረውም በተለያየ መንገድ ነው ። ተማሪው በመረጠው መንገድ ሳይሆን አስተማሪው በመረጠው መንገድ ያስተምራል ። “እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማን ነው ? በሚመርጠው መንገድ ያስተምረዋል” ይላል ። መዝ. 24 ፡12 ። ለእኛ የመረጠልን ምን ይሆን ? ብለን መጠየቅ መልካም ነው ። ለአንዳንድ ሰው የተመረጠለት ሕመም ሊሆን ይችላል ። አንዳንድ ሰውም የተመረጠለት ስደት ነው ። ለሌላውም የተመረጠለት እስር ቤት ይሆናል ። እግዚአብሔር በመረጠው መንገድ ያስተምራል ። ተግባራዊ የሕይወት ትምህርት የሚገኘው ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው ። እግዚአብሔር በሕይወት እያሳለፈ የማስተማር ሥልጣን አለው ። እግዚአብሔር የሚያስተምርበት ዓላማ እርሱን እንድናውቀውና ከትዕቢት እስራት እንድንፈታ ነው ። የሰው ልጅ የሌለውን ነገር እንዳለው አድርጎ ማሰቡ ትዕቢት ሲሆን በእርግጥ አለኝ እንዲለው የተፈቀደለትን እግዚአብሔርን አለኝ አለማለቱ ደግሞ አለማመኑ ነው ። እግዚአብሔር የሚያስተምረው ለምስክር ወረቀት ሳይሆን ለሕይወት ለውጥ ነው ። በመስቀል ላይ የተሰቀሉት ሁለት ወንበዴዎችን ስናይ መከራ አንደኛውን እንዲያምን ሲያደርገው ሌላኛውን ደግሞ እንዲክድ አደረገው ። መከራ በራሱ አይለውጥም ። ትሑት ልብ ላላቸው ግን መከራ ሰማይን የሚያዩበት ሽንቁር/ቀዳዳ ነው ።

ራሳችንን የምናውቀው ይመስለናል ፣ ግን አናውቀውም ። ሰዎችን የምናውቃቸው ይመስለናል ፣ ግን አናውቃቸውም ። ዓለሙን የምናውቀው ይመስለናል ፣ ግን አናውቀውም ። እየኖርንበት ያለውን ይህን ቀን የምናውቀው ይመስለናል ፣ ግን አናውቀውም ። ራሳችንን ከፍ አለ ስንል ሲዘቅጥብን እናገኘዋለን ። ሰዎች ገቡ ስንል ሲወጡ እንመለከታለን ። ዓለሙ ተሻሻለ ስንል ወደ ድንጋይ ዘመን ሲጓዝ እናስተውላለን ። ቀኑን በሰላም ጨረስኩት ስንል ምሽት ላይ ጣጣ ይዞ ይመጣብናል ። የዛሬው ስሜታችንም ፣ የሰዎች ተለዋዋጭነትም ፣ የዓለሙ መውረድም ፣ የቀኑ ክፋትም ሁሉም ያልፋሉ ። የማያልፍ አንድ ነገር ቢኖር እግዚአብሔር በዚህ ሁሉ ውስጥ የሚያስቀርልን ትምህርት ነው ። እርዳታ የሚያደርጉልን ሰዎች ስለመስጠታቸው እንጂ ስለ ትምህርታችን አይጨነቁም ። የሚያክሙን ሐኪሞች ስለሕክምናቸው እንጂ ስለ ትምህርታችን አይጨነቁም ። የሚዳኙን ዳኞች ስለ ሕጉ እንጂ ስለትምህርታችን አይጨነቁም ይሆናል ። እግዚአብሔር ግን በደረሰብን ነገር ሁሉ ትምህርቱ እንዳያመልጠን ስለ እኛ ያስባል ። እግዚአብሔር የማይረሳ ትምህርት ፣ በዓለት ላይ የተጻፈ ፊደል የሚቀርጽልን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንድናልፍ በመፍቀድም ነው ። አብርሃም ሁሉን አጥቶ ሁሉን አገኘ ። ሁሉን ለማግኘት ሁሉን ማጣት ያስፈልጋል ። አንድ የአገር መሪ ሲነግሥ የመኖሪያ ቤቱን ፣ ማኅበራዊ እሴቱን … ሁሉን ነገሩን ያጣና ሁሉም የእርሱ ይሆናል ። ሙሴ ከቤተ መንግሥት እየበላ ወደ ድሆች ይውጥ ነበር ። ከባዕድ ሰብስቦ ከዘመድ ጋር ለመብላት ይጨነቅ ነበር ። እግዚአብሔር ግን በልዑልነቱ ሳይሆን በእረኛነቱ ለታላቅ ራእይ አበቃው ። ነቢዩ ዳዊት በብዙ መንከራተት ውስጥ ፣ ነቢዩ ዳንኤል በስደት አገር ፣ ሠለስቱ ደቂቅ በነደ እሳት ፣ ሶስና በረበናት ክስ እግዚአብሔርን ይበልጥ አዩት ።

ከዚህ በፊት የማናውቀውን የእግዚአብሔር ጣት የምናየው ጠመዝማዛ መንገድ ውስጥ በማለፍ ነው ። ራሳችን ብርቱ መስሎ ይሰማን ነበር ። ችግር ሲመጣ ግን ደካማ መሆናችንን አሳወቀን ። እግዚአብሔርን ያሳወቀን ችግር ፣ ቀጥሎ ራሳችንን አሳወቀን ። በሰላም ቀን ካንተ በፊት ያድርገኝ ይሉ የነበሩ ሰዎች ችግር ሲመጣ አላውቀውም ብለው እንደ ጴጥሮስ ሲክዱን ሰዎችን አወቅን ። ስንመነዝረው የማያልቅ የመሰለን ነገር ሲሟጠጥ ገንዘብ ሥር እንደሌለው ተረዳን ። አናታችን ላይ መንበራችሁን ሥሩ ሲሉን የነበሩት ሲያዋርዱን ዓለም ወረተኛ የወረት ቤት መሆኗ ተረዳን ።

ጊዜ ብዙ ያስተምራል ። ጊዜ የተባለውም እግዚአብሔር የሚሰጠው ዘመንና ዕድል ነው ። በጊዜ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍርድ ይታያል ። በጊዜ ውስጥ እታች ያለው ሲወጣ ፣ እላይ ያለው ሲወርድ መሐል ላይ ይገናኛል ። በጊዜ ውስጥ ቀዩ ሲጠቁር ፣ ጥቁሩ ሲቀላ ፣ ማሩ ሲመርር ፣ ወተቱ ሲጠቁት ይስተዋላል ። ጊዜ የእግዚአብሔር ባሪያ ነውና ጣል ሲለው ይጥላል ፣ አንሣ ሲለው ያነሣል ። ሰው ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ ከመማር ወሬ ያሯሩጣል ። በእነ እገሌ የመሸ ዓለም በእርሱ የሚመሽ አይመስለውም ፣ ወዳጁንና ልጁን ቀብሮ እየተመለሰ እርሱ የሚሞት አይመስለውም ። ዛሬ በሌላው ይስቃል ፣ ነገ በእርሱ እንደሚሳቅበት አይረዳም ። በጊዜ ውስጥ ብርቱ ጉልበታችን ሲደክም ፣ የሰጠ እጃችን ሲነጥፍ ፣ ያማረ መልካችን ሲረግፍ ፣ የከበቡን ሠራዊቶች ሲበተኑ ፣ ያቀፉን እጆች ሲገፈትሩን እናያለን ። ባንኖር ይህን ሁሉ አንማርም ነበርና መኖር ደግ ነው ።

ማጣት የማይለመድ የሰው ልጆች የእሳት ጅራፍ ነው ። ማጣት ቀና ያለውን አንገቱን ይሰብረዋል ። ማጣት የከበረውን ያዋርደዋል ። ማጣት ትላንት በሰጣቸው ሰዎች እንዲሰደብ ያደርገዋል ። ያጣ ሰው ጥበብ ቢናገር አበደ ይባላል ። እውቀት ቢናገር ምነው ዝም ባለ ይባላል ። ሰው የእውነት ሳይሆን የገንዘብ አገልጋይ በሆነበት ዓለም ፣ ያጡት ላይ ድንጋይ መጫን ይቀናዋል ። የመሸው ቀን ይነጋል ፣ የጠፋውም ሀብት ይመጣል ። ወዳጄ ሆይ በሚያልፍ ቀን ውስጥ የማያልፈውን እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ ። “ጊዜ የማይሽረው ቍስል የለም ።

በችግር በመከራ ውስጥ የመትረፉ ነገር ያስፈራው ጸሎተኛ እንዲህ አለ፡-

“አብም ያንተ ስም ነው ፣
ወልድም ያንተ ስም ነው ፣
መንፈስ ቅዱስም ያንተ ስም ነው ፤
ብጠራህ ብጠራህ አቤት አላልህም ምነው ።”

እግዚአብሔር ሦስት ስም ፣ አንድ አምላክነት እንዳለው አወጀ ። ዳግመኛም ዘገየህብኝ ብሎ ጮኸ ። አቤት የሚል ታናሽ ነውና አቤት አላልህም ፣ አንተ ጌታ ነህ ብሎ መሰከረ ።

አዎ በጊዜና በማጣት ውስጥ ያስተማረን እግዚአብሔር ስሙ የተቀደሰ ይሁን ! ያጣ ወዳጃችሁን እስቲ ዛሬ አስቡት ፣ አለሁ በሉት ።

የብርሃን ጠብታ 27

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ