“መስተዋት ይገዛል ሞኙ የሰው ልጅ ፣
ሁሉን የሚያሳየው መሰንበት ነው እንጅ ፤”
“የተራበ አይዘልም ፣ የጠገበ አያርፍም” ይባላል ። ሰውን የሚያጨምተው ማጣት ነው ። ማግኘት የምስጋና ርእስ ፣ ተካፍሎ የመብላት ምክንያት ሊሆን ሲገባ የመዝለልና የመፎከር ሰበብ መሆኑ ያሳዝናል ። ሁሉን ሰጪው እግዚአብሔር የቱን እንደሚሰጠን የተጨነቀ ይመስላል ። ካልጠገቡ አይዘሉም ፣ ካልዘለሉ አይሰበሩም ይባላል ። የሰው ልጅ ሕመም እንኳ የሚባባሰው በጾም ወራት ሳይሆን በፍስክ ወራት ነው ። ከመጠን ያለፈ ሥጋዊ ደስታ ኀዘን ይከተለዋል ። እንኳን ምድራዊ ጭፈራ ማኅሌት ሲደምቅም ሊቃውንቱ ያስቆማሉ ። እውነትም ከልካይ ከሌለ እስክስታ ይጀመራል ። በስብሐተ እግዚአብሔር ላይ ሥጋዊ ደስታ እንዳይቀላቀል ፣ መሥዋዕቱ እንክርዳድ እንዳይበተንበት ይከላከላሉ ። ለእግዚአብሔር ክብር የሚቆጭ ፣ የሚደመጥ አዋቂ ዛሬ ይኖር ይሆን!?
“የዘፈን ቤት ሳይፈርስ አይቀርም” እንዲሉ ብዙ የተጨፈረበት ቤት ሳይለቀስበት አይቀርም ። የተማረ ባለቤት ቤት ደስታን በልክ ማድረግ አለ ። ብዙ እዩኝ ማለት ለመጥፋት ፣ ብዙ ጥጋብ ለውርደት ይሆናል ። የሚጠላን የበለጠ የሚጠላን ጭፈራ ስናበዛ ነው ። የብልህ ልኩ ጨርሶ አለመሳቁ ነው ። ለምን እንዲህ ይሆናል ? ደስታን ኀዘን ለምን ይከተለዋል ? እግዚአብሔር ሊከብር ሲገባው ሰይጣን ክብሩን በመውሰዱ ፣ ሁለተኛ በዚያ ድግስ ምክንያት ሰዎች በኃጢአት ስለሚወድቁ ፣ ሦስተኛ በሚጨፈርበት ቤት አጠገብ በረሀብ የሚያለቅሱ ሰዎች መኖራቸው ፣ አራተኛ የዛሬው ጨፋሪ የትላንት አልቃሽ እንደ ነበር መርሳቱ ነው ። ሰብአ ትካትም ሰብአ ሰዶምም ሲጨፍሩ ጠፍተዋል ። ብዙ ሰርገኞች ከመጠን በላይ ጭፈራ አብዝተው ደክሟቸው እንደ ተኙ በእሳት ሲያልቁ ሰምተናል ። ሥጋዊ ደስታን ኀዘን ይከተለዋል ። መንፈሳዊ ደስታ ግን በውስጥ ሰውነት ሕያው መሆን ፣ በተመስጦ ጽርሐ አርያም መውጣት ፣ በክርስቶስ ፍቅር ማንባት ፣ ሰውን ሁሉ በክርስቶስ ለማወቅ መጣር ያለበት በመሆኑ ማንንም አያውክም ። መንፈሳዊ ደስታ በአንዳች ምድራዊ ነገር ላይ አይመሠረተም ። የቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት የዘመናትን እውነት የሚገልጥ ፣ የእግዚአብሔርን አሠራር የሚያስረዳ ነው ። “የተራቡትን በበጎ አጥግቦአል ፤ ባለጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል ።” (ሉቃ. 1 ፡ 53) ።
እግዚአብሔር ያረፈደውን ደስታ ካላዋለው ምሽቱ አስጨናቂ ነው ። ጊዜ የሚያሳየን የተራበው ሲጠግብ ፣ የጠገበው ሲራብ ነው ። ጎዳና የነበረው ባለ ሕንፃ ሲሆን ባለብዙ ቤቱ ጎዳና ሲወድቅ ነው ። መስተዋት የሚያሳየው ጥቂት ነገር ነው ። መስተዋት የአሁኑን ፊት ብቻ ያሳያል ። የትላንቱን መልክ ፣ የነገውን ውበት አያሳይም ። መስተዋት የአሁን ምስክር ነው ። ዞር ሲሉ ምስክርነቱ ሊበላሽ ይችላል ። መስተዋት ምንም ቅርብ ቢሆን ጀርባን አያሳይም ። ሁሉን የሚያሳይ ግን ጊዜ ይባላል ። በጊዜ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍርድ ይከናወናል ። የወጣው ሲወርድ ፣ የወረደው ይወጣል ። ላይና ታች መሆኑ ጽዋ እንጂ ቋሚ ርስት አይደለም ። ገጣሚው እንዲህ አለ፡-
“እንደምን ነህ ጊዜ ፣ ጊዜ መስተዋቱ ?
ገልጠህ የምታሳይ ሁሉን እንደ መልኩ ፣
ሁሉን እንደ ልኩ ።
እንደምነህ ጊዜ ?
ወደ ጽርሐ አርያም የከፍታው መውጫ ፣
ወይም ወደ ጥልቁ ቁልቁል መፈጥፈጫ ።
እንደምን ነህ ጊዜ ?
የሕይወት ምሕዋር ዑደት ማስቀጠያ ፣
የመከፋት ድባብ የደስታው ገበያ ።
ጊዜ ሁሉን ዳሳሽ ጊዜ ሁሉን አወቅ ።
እውነተኛው ዳኛ ፍትሕ የማትሰርቅ ።
ዐይተን ነበር ያኔ ፣
ጌቶች ሎሌ ሆነው ሎሌዎች ሲነግሡ፣
ጋጣ ሙሉ አጋንንት ቅድስቱን ሲሞሉ ፣
በጻድቃን ምኩራብ ውስጥ ለድርያ ሲያደሉ ።
ዐይተን ነበር ያኔ ፣
በጥንግ ድርቡ አጋንንት ሲያጌጡ ፣
የኤልዛቤል ካህናት ጸጋን ሲሻሻጡ ።
ዐይተን ነበር ያኔ ፣
ዲታዎች ሲጠግቡ ቁንጣን ሲይዛቸው ፣
ብስናት ሲወራቸው ፣
ዕብሪት ሲያንራቸው ፣
ምስኪኖች ሲያነቡ ተስፋ እየራቃቸው ።
ይኼውና ዛሬ ፣
ብያኔህ ሲቀና ፣
ጽዋቸው ሲሞላ ፣ ባንተ እየተሾሙ ባንተ እየተሻሩ ፣
ሁሉም ሲሄዱ አየን ቦታ እየቀየሩ ።”
ጊዜ መስተዋቱ !
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም.