“እብድ ቢጨምት እስከ ቀትር ነው” ይባላል። ሌሊቱን በሙሉ ሲጨፍር አድሯልና ጠዋት ሲያገኙት እብድ ጭምት ነው። የሚያቀዘቅዝ ነገር የሚፈልግ ታማሚና ተለማማጭ ነው። ተኝቶ የማይጠግብ ፣ ከአልጋ ለመነሣት ጉልበት የሚያጣ ፣ ቢሰድቡት መልሶ የማይሳደብ ፣ ረሀብና እንቅልፍ በአንድ ጊዜ የመጡበት ፣ መኝታው ላይ ምግብ የሚያላምጥ ምስኪን ነው ። ወዲህ ሚስቱ አሊያም እናቱ ብቻ ሳይሆን ጎረቤትም ያዝንለታል ። በተኛው እንቅልፍ ፣ በበላው ምግብ ኃይሉን ሲያሰባስብ እብድ ቀትር ላይ መነቃቃት ፣ መንጎማለል ፣ ሐፍረቱን መጣል ይጀምራል። እየተገላመጠና እየተሳደበ ከሱቅ ውኃ ገዝቶ ይመለሳል። ቡናውን ሲጠጣ ይነቃቃል፣ እብደቱን በይፋ ይቀላቀላል። ቢያጠፋም የሚቀየመው አጥቶ ሁሉም ሰው የአገር ዕዳ አድርጎ ይቀበለዋል። እብድ ቢጨምት እስከ ቀትር ነው።
ብዙ ጨዋ ሰዎች ፣ ሰላምታቸውን ለመስማት ጆሮአችንን ዝቅ ማድረግ የሚያስፈልገን ፣ መሬት ሲረግጡ መሬት እንዳትቆረስ የሚጨነቁ የሚመስሉ ቀትር ላይ ጠራራ ይሆናሉ። “ጅብ እስኪነክስ ያነክስ” እንዲሉ ። እነዚህ አድፋጮች በወዳጃቸው ቀትር ላይ ይጠርራሉ/ጠራራ ይሆናሉ/። የሰው ስም ሲነሣ ሐሜትን ይፀየፉ የነበሩ፣ በተውኔት ቅድስና የብዙዎችን ቀልብ የሳቡ የተጠቃን ለማጥቃት ምላሳቸውን ያረዝማሉ፣ ማንም ያልተሳደበውን ስድብ ከባንካቸው አውጥተው ይሳደባሉ። “የእንጦጦ መምህር ቢናገር ባመት ያውም እሬት” እንዲሉ። እንዴት ተገፍተው ዳር ወጥተው የነበሩ ዛሬ መሐል ላይ ነን ብለው ሌላውን ይገፋሉ? ተሰደው ሳለ ለማሳደድ፣ ሰማቸው ጠፍቶ እንዳልነበር ስም ለማጥፋት እንዴት ይቻኮላሉ? ያዘመመ ሁሉ የሚወድቅ መስሎአቸው፣ ዳሩን ሳይለኩ እንዴት ይራገማሉ? የሚያቀሉ ቀኖች አሉ። ጊዜ የሚገልጣቸው ሰዎች አሉ። ለወዳጃቸው ወዳጅ መሆን የሚያቅታቸው እየበዙ ነው። አንገታቸው ወደ ኋላ ዞሮ የማያይ ፣ ግራና ቀኛቸውን ማያነቡ ብዙ እየሆኑ ነው። በወደቀ ላይ ድንጋይ የሚጭኑ ፣ ባልሞተ ላይ የመቃብር አፈር የሚበትኑ፣ ከብዙኃኑ ጋር ማበድ ደስ የሚላቸው፣ ብዙኃኑ አይከሰስምና እነርሱ ግን ትዝብት ላይ ይወድቃሉ።
በሌሎች ውድቀት ላይ ደረጃህን አትሥራ። የፀና ድንጋይ እንጂ ያልፀና አፈር ደረጃ መሆን አይችልም። የወደቀ ብታገኝ በመርገጥ ሳይሆን በማንሣት ትልቅ ትሆናለህ። ። የወደቀ ትልቅ ሰንጋ እየፈለግህ ቢላህን ይዘህ ቆዳ አትግፈፍ ፣ ብልት አታወራርድ ። ትልቅነት በትልቅ አስተሳሰብ እንጂ ትልቅን በመሳደብ አይገኝም፡ ወልደው ሳይጨርሱ በሰው ልጅ አይስቁ ይባላል። ኖረው ሳይጨርሱ በሰው ውድቀት አይስቁ ብለህ አንብበው። የእውቅና ጥማት ያለው ሰው ፈተናው ከፍተኛ ነው ። በሥራ መታወቅ ቢያቅተው በሴራ፣ በቅንነት መጉላት ቢሳነው ቅንቅን በመሆን ለመግነን ይሞክራል። ብዙ ጭምቶች በሰው ቀትር ላይ ሲያብዱ ይታያሉ። ይህ ዘመን የሚያስተዛዝብ ዘመን ነው።
ጊዜ መስተዋቱ
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም.