በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ሕፃናት ተወልደዋል ፣ ወላጆችም በሕፃኑ ላይ ተስፋ ጥለው ሊሆን ይችላል ። እንደ ሕፃንነታቸው ወጣትነታቸው አላስደስት እያለ መልሰው ኀዘን ሆነዋል ። ተስፋን ሊፈጽም አንድ ሕፃን በቤተ ልሔም ተወለደ ። ተስፋ ላጣው ዓለም ተስፋ ሊሆን ፣ የብቸኞችንና የግፉዓንን መከራ ሊካፈል አንድ ሕፃን በበረት ተወለደ ። በምድር ላይ የተወለዱ ሕፃናት ሁሉ እናታቸውን የመምረጥ ዕድል አላገኙም ። ይህ ሕፃን ግን እናት የምትሆነውን መረጠ ። “ከደኅና ተወለድ አሊያም ከደኅና ተጠጋ” በሚባልበት ዓለም ከድሀ መወለዱ የሚቆጨው ብዙ ወገን አለ ። በቅድስና መስፈርት እናቱን የመረጠው የቤተ ልሔሙ ሕፃን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። በማይቆጠር ዘመን ከአባቱ ቅድመ ዓለም የተወለደው ፣ በታወቀ ፣ በተረዳና እውነትም በሆነ ዘመን ከድንግል ተወለደ ። ልክ በሌለው ክብር ሲኖር ሳለ ልክ የሌለውን ዝቅታ መረጠ ። ሰውነታችንን ሰው ሁኖ አዳነው ። የእኛን ድሀ ሥጋ ተዋሕዶ የእርሱን አምላክነት ለሥጋ ሰጠ ። ከመወለዱ በፊት የነበረ እርሱ ብቻ ነው ። እናቱን የመረጠ እርሱ ብቻ ነው ። በምድር አባት ፣ በሰማይ እናት የሌለው እርሱ ብቻ ነው ። አባቱ ያልቀደመው ፣ ከአባቱ ጋር የዘመንና የክብር እኩያነት ያለው እርሱ ነው ። ባለመለየት ከአብ የተወለደ እርሱ ነው ። ልዩ በሆነ ልደትም ከድንግል የተወለደው እርሱ ነው ።
አብን አባት ያሰኘ ይህ ልጅ ነው ። ልጅ በሌለበት አባት መባል የለምና ዘላለማዊ አብን ካመንን ዘላለማዊ ልጁን እናምናለን ። ያላቸውን የሚሰጡ ቸር ተብለዋል ፣ ራሱን የሰጠን የእግዚአብሔር ልጅ የደጎች ደግ ነው ። ቤተ ልሔም ሰማይን መሰለች ። ቅዱሳን መላእክት የዘመናትን ጨለማ የሚገፍፍ ዝማሬ አሰምተውባታልና ። ድንግል ማርያምም ኪሩቤልን መሰለች ፣ አምላክን ተሸክማለችና ። ከተዋሕዶ በኋላ ክርስቶስን አምላክ ብቻ ደግሞም ሰው ብቻ ብሎ መጥራት አይቻልም ። በማፈራረቅም አምላክና ሰው አይባልም ። ፍጹም ሰው ፣ ፍጹም አምላክ ነው ። ተዋሕዶው ዘላለማዊና መለየት የሌለበት ነው ። በአንድ አካል በአንድ ባሕርይ አንድ ክርስቶስ ተብሎ የሚጠራ ነው ። ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሊጠመቅ የሄደ ፣ አብም ልጄ ብሎ የመሰከረለት አንዱ ክርስቶስ ነው ። በምራቁ ዕውር ያበራው እርሱ ነው ። ምራቁ የሰው ብቻ ቢሆን አያድንም ፣ የመለኮት ብቻ ነው እንዳንል መለኮት ምራቅ የለውም ። ምራቁም ፣ ዓይን ማብራቱም የአንዱ ክርስቶስ ግብር ነው ።
በገነት የወደቀውን በገነት የፈለገው ዛሬም በቤቱ ውስጥ የወደቁትን አገልጋዮች የሚፈልግ እርሱ የተወለደው ክርስቶስ ነው ። ገነትም ያለ ክርስቶስ አያረካምና እርሱ ገነታችን ሆኖ መጣ ። ከገነት ጫካዎች እስከ ቀራንዮ ፈለገው ። እንጨት በልቶ ፣ በእንጨት መካከል ተደብቆ የነበረውን አዳምን በእንጨት ላይ ተሰቅሎ አዳነው ። በብልጠት የፈለገውን አምላክነት በፍቅር አካፈለው ። ክፉና ደጉን የማወቅ ጥበብ አድጎ ሰማይን በክርስቶስ አየነው ። ሰማይን ለማየት ሰማይ መሄድ ግድ ይል ነበር ። አሁን ዝቅ ብሎ መመልከት በቂ ሆነ ። ቤተ ልሔም ታላቅ ትሕትና የተገለጠባት ስፍራ ናት ። ክርስቶስም የሚገኝበት መስመር ትሕትና ብቻ መሆኑን የተማርንባት ትምህርት ቤት ቤተ ልሔም ናት ። ብዙዎች ብዙ ነገሮችን በማግኘታቸው ደስ ይላቸዋል ። እሰይ ተወለደ ፣ የዓለምን መድኃኒት አገኘነው ፣ ሃሌ ሉያ ። ልጅ ቢወለድ ለቤተሰብ ደስታ ነው ፣ ለዓለም ደስታ የሆነ ልጅ በቤተ ልሔም ዛሬ ተወለደ ። በቤተ ልሔም በሥጋ ተገለጠ እንጂ ህልውናው አልጀመረም ። እርሱ ዘላለማዊ ነው ። ልደቱ የድኅነት ተግባር ጅማሬ ነው ። ፍጻሜውም በሞቱና በትንሣኤው ነው ። ልደቱና ሞቱ ተናባቢ ናቸው ። ያልተወለደ አይሞትምና ። ሞት ሳይነገርም ትንሣኤ የለም ። ከክርስቶስ ጋር ለመነሣት ከእርሱ ጋር መሞት ግድ ይላል ። ዓለም ተደራጅታ ልትጠብቀው የሚገባውን መሢሕ ዮሴፍና ድንግል ማርያም ብቻ ተቀበሉት ። ዓለም ተዝረክርካ ተቀበለችው ፣ ሳይታዘብ ሊያስተካክላት ይችል ነበር ፣ ላንተ የሚሆን ስፍራ የለኝም ብላ መለሰችው ።
ዛሬም የክርስቶስ ልደት አሁናዊ የአምልኮ ርእሳችን ነው ። ዓለም ግን ተራ ልደት ፣ ስጦታ መቀባበያ ፣ የገና ዛፍ መትከያ ፣ ትእይንት ፣ የፎቶ መርሐ ግብር አድርጋ ትቀበለዋለች ። ይህ እርሱን ደስ አያሰኘውም ። ልደቱ የመስከሪያና የጭፈራ ምክንያትም አይደለም ። ለዳግም ልደት ሊያበቃን ሁለተኛ ተወለደ ። በልደቱ ልንወለድ እንጂ በኃጢአት ልንሞት አይገባንም ። ሊወልደን የተወለደ ሕፃን ፣ ዓለምን እየመገበ ከእናቱ ጡት የለመነ ልጅ ማንም የለም ። እርሱም የነፍሴ ጌታ ክርስቶስ ነው !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 27 ቀን 2018 ዓ.ም.