መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ጌታ ይሰማል

የትምህርቱ ርዕስ | ጌታ ይሰማል

“ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ” (ሉቃ .1፥ 13)

መልአኩ ይህን አስደሳች ብሥራት የተናገረው ለካህኑ ለዘካርያስ ነው። ዘካርያስ ማለት የስሙ ትርጓሜ “እግዚአብሔር ያስታወሳል” ማለት ነው ። በርግጥም እንደ ስሙ ትርጓሜ እግዚአብሔር አስታወሰው። ዘካርያስ በማስተስሪያ በዓል ቀን ለእስራኤልና ስለ ዓለም ጸሎትን ሲያሳርግ ሳለ የእርሱን ምኞት የሚሞላ የምሥራች መጣ። ስለ ሌሎች ሲጸልይ የእርሱ ጉድለት ሞላ ። ዓመቱን በሃያ አራት ሰሞን ተከፋፍለው ካህናት ያገለግሉ ነበር። ስለዚህ በዓመት ሁለት ሳምንት ሰሞነኛ ሆነው በእግዚአብሔር ቤት ያገለግላሉና መንፈሳውያን የሆኑ አገልግሎት ወዳዶች እነዚህን ሁለት ሰሞኖች ከልባቸው ይናፍቁ ነበር ። በዚያ ዘመን ከሃያ ሺህ በላይ ካህናት ነበሩ። በእያንዳንዱ ቀንም አንድ ሺህ የሚያህሉ አገልጋዮች ያገለግሉ ነበር። ለአገልግሎትም በዕጣ ይደለደሉ ነበር። ከሁሉ የበለጠው በማስተስሪያ በዓል መሥዋዕትንና ዕጣንን ለእግዚአብሔር ማሳርግ ትልቅ ዕድል ነበረ። በቤተ መቅደስ ተገኝቶ ዕጣን ማጠን የማይገኝ ዕድል ሲሆን ዘካርያስ ዕጣ ወጥቶለት ነበር። በዚህ ታላቅ ደስታ ላይ በሰንበት ላይ ደብረ ዘይት እንዲሉ የምሥራች መጣለት ።

በአይሁድ ባሕል አለመውለድ ትልቅ ውግዘትን ያስከትል ነበር። ያላገቡ፣ አግብተው  ያልወለዱ ሰዎች ትልቅ ነቀፋ ይገጥማቸው ነበር። በዚህ ዘመንም ያሉ ክርስቲያን ፈሪሳውያን ሰው ሲቸገር፣ ሲታመም “ባለማመኑ ነው” ብለው ይደመድማሉ። ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ጉድለት ቢኖርባቸውም እግዚአብሔርን በማምለክ፣ ቃል ኪዳናቸውን በመጠበቅ ጸኑ። ጉድለት የሚመስል ነገር ከእግዚአብሔር ካልለየን ትልቅ ሰዎች ነን።  ቃል ኪዳንም በተራራና በሸለቆ ተያይዞ ለመሄድ የሚደረግ ነውና  ጋብቻ መጽናት አለበት።

መሥዋዕቱ ለኃጢአት የሚቀርብ ዋጋ ነበር። የመሥዋዕቱ ሽታ ጣዕም የለውም። የተቃጠለ ሥጋ ሽታው ይረብሻል።  ኃጢአትም አስከፊና ከሕይወት መዓዛ የሚለይ ነው። መጥፎ ሽታ ራሳችንን፣ አካባቢውን እንድንጠላ የሚያደርገን ነው። ኃጢአት የጥላቻ ስሜት ያመጣል። ስሜታዊ ደስታ እውነተኛ ኀዘን ፣ ጊዜያዊ ፈንጠዝያ ዘላቂ ቁስል የሚገኘው በኃጢአት ነው። ዕጣኑ መሥዋዕቱ በጣዕም እንዲያርግ የሚረዳ ነበር። ጸሎት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ጣፋጭ ሽታ ነው። እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል። ንስሐችን፣ ምልጃችን፣ ምስጋናችን ፣ መሥዋዕታችን የሚያርገው በጸሎት መሰላል ነው። ጸሎት ሰማያዊ ጌታ በቤታችን እንዲገኝ  ፣ ምድራውያን እኛ በሰማይ  እንድንገኝ የሚያደርግ ነው። እግዚአብሔርን መጋበዝና በእግዚአብሔር መጋበዝ እንዴት ደስ ያሰኛል!

ዘካርያስ የጸሎት መልሱ ቢዘገይም ይጸልይ ነበረ። አገልጋይና ጸሎተኛ ከሆንን ዕጣ ወጥቶልን፣ ታላቅ ዕድል ገጥሞን ነው ። እግዚአብሔርን ማገልገል ከሺህ ሰው ለአንድ የሚደርስ ነው ። ዲያቆን ከሆንህ ከቤተ ዘመድ ብቸኛው ሰው አንተ ልትሆን ትችላለህ ? ጳጳስ ከሆንህ ካደግህበት ክፍለ አገር ብቸኛው ሰው ፣ ከሚሊየኖች አንዱ ልትሆን ትችላለህ። ማገልገል ዕጣ ነው። የግል ጸሎት ባይመለስም የጌታ መሆን ከመልስ በላይ ነው። ዘካርያስ አይሰጥህም አልተባለም፣ ጠብቅ የተባለ ሰው ነው። ጀምበር ልትጠልቅ የተቃረበች ቢሆንም መልሱ መጣ። ለእግዚአብሔር መሸ አይባልም። ሰውም ለንስሐ ፣ ለጸሎት፣ ለአገልግሎት መሸ አይባልበትም፡ ከእግዚአብሔር ጋር ሠርኩ ማለዳ ነው። በመሸ ጊዜ የንስሐ ድምፅ ወደ አዳም መጣ። አሁን ካረጀሁ ንስሐ መግባት፣ መላ ሲያጡ መመለስ ደስ አይልም እያለ የራቀ ወገን አለ። እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ የንስሐ ዕድል ቢኖርም ቀኑ ግን ዛሬ ነው። መዳን ቀጠሮ የለውም።

መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይዞት የመጣው የምሥራች ለዘካርያስ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች ደስታ የሚሆን የዮሐንስን መወለድ ነው። በርግጥም ጸሎቱ የጸለየ ቀን ምናልባት የዛሬ ሰባ ዓመት ተሰምቷል ። አፈጻጸሙ ግን ዛሬ ሆኗል። እግዚአብሔርን መጠበቅ አያከስርም፣ ዮሐንስን የመሰለ ልጅ ያሰጣል። እንኳን በሰባ ዓመት በሺህ ዓመት ተጋድሎስ ዮሐንስ ይገኛል ወይ ?

ዮሐንስ የጌታን መንገድ ሊጠርግ የተላከ መልእክተኛ ነው። ዮሐንስ ማለት “እግዚአብሔር ጸጋ ነው” ማለት ነው። ራሱ እግዚአብሔር ጸጋ ነው፣ ቢሳካም ባይሳካም እግዚአብሔር ራሱ ጸጋ ነው። ይህ አለኝ ከማለት እግዚአብሔር አለኝ ማለት ይበልጣል። የሚገርመው ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ይህን ልጅ ለማሳደግ ዕድሜአቸው ገፍቷል። እኔ ባልኖር ልጅ ምን ይሆናል?  የሚል ፍርሃት ሺህ ጊዜ ይገድለናል። ልጅን የሰጠ ጌታ፣ ልጅን ያሳድጋል። ትውፊቶች እንደሚነግሩን ሄሮድስ ሕፃናትን ሊያስገድል በወጣ ጊዜ ኤልሳቤጥ ዮሐንስን ይዛ ወደ ይሁዳ በረሃ ገባች። ዘካርያስን በመቅደስ ያገኙት ወታደሮች ልጅህን አምጣ  ቢሉት አላሳይም በማለቱ ሰማዕት ሆነ። ደሙ በመቅደስ ፈሰሰ ። ኤልሳቤጥም ጥቂት ቆይታ ሞተች፣ ያ ልጅ በበረሃ አደገ። ጌታን የያዘ ምን ይሆናል ይባላል። ነገር ግን  የማይሆነው ነገር የለም። እግዚአብሔር ራሱ ዮሐንስን በበረሃ አሳደገው። ልጁን ለቤተ እግዚአብሔር ወለዱ።

ጸሎት ካልተመለሰ ፍርሃት አለ። ጸሎታችን መልሱ ሊዘገይ ይችላል፣ የጸለይን ቀን ግን ተሰምተናል። ለጸሎት መልስ ከሚረዱ ነገሮች አንዱ ትዕግሥት ነው። ዘካርያስ ጻድቅ ቢሆንም ጉድለት ነበረው፣ ኤልሳቤጥ ቅድስት ብትሆንም ነቀፌታ ነበራት ፣ የቡና መጠጫ ፣ የጠላ ማወራረጃ ነበረች ።

ዘካርያስ የጸሎቱን መልስ በቤተ መቅደስ ሰማ፣ የሰማይ ድምፅ በቤተ ክርስቲያን ይሰማልና መገስገሰ ይገባል። “እቤቴም ይሰማኛል” የሚሉ ሰዎች ዘካርያስ ይህን አያውቅም ነበር ወይ? መገስገስ መሥዋዕት ነው፣ መሥዋዕትም ጸሎትን ሥሙር ያደርጋል። ያለ መሥዋዕት ጸሎት አያርግም። እንቅልፍን፣ ስንፍናን መሠዋት ይጠይቃል።

ጸሎት እንዲሰማ መታዘዝ ይገባል ፣ ያልነውን እንዲፈጽምልን ያለውን መፈጸም ግድ ነው። ሁለተኛው በቤቱ መጽናት ግድ ይላል። ዘካርያስ ዮሐንስ ከተወለደ በኋላ የቆየው ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ነው። ጸሎታችን ለምን እንደ ዘገየ አናውቅም። ወልድ ሆይ በእውቀትህ አድነኝ ብሎ መጸለይ ብልህነት ነው።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ