ማለዳው የሚጨግበት ጊዜ ብዙ ነው። ትላንት የዋልንበት ክፉ ውሎ ፣ ማለዳ ላይ የከፈትነው ስልክ ግማሹን ቀን ይበላዋል። ወጪ ስንጠየቅ የለኝም ከማለት አንቺ እኮ ድሮም የሚለው መጥፎ ንግግር ለቀጣይ አንድ ዓመት ጦርነትን ይከፍታል። በይቅርታ ያልፈታነው ፣ ያለ ንግግር የተኛንበት ጉዳይ እንቅልፋችንን የማቃሰት፣ ማለዳውን የማኩረፍ ያደርገዋል። ውጤታማ ሰዎች በጊዜ ተኝተው ማልደው የሚነቁ ናቸው። አጉል ማምሸት ከነገ መበደር ነው። ግማሹን ቀን በመኝታ ላይ ማሳለፍ የቁም ሞት ያመጣል። ጸሎቱም ከቀን መኝታ ያድነን የሚል ነው።
ትልቁ አቅም ያለበት ፣ ብዙ የሚሠራበት የቀኑ ወለላ ሰዓት ባደረው ችግር ይባክናል። ለነገ የምንሠራው ዛሬ ነው። ትላንት ዛሬን እንዲያዝ እንፈቅድለታለን ። ትላንትና ላይ ዛሬን ተበድረን በልተናታል። ግማሹ ቀን ትላንት በዋልንበት ውሎ ፣ ባመሸንበት ኃጢአት ጸጸት የሞላበት ይሆናል። በራሳችን በጣም እንናደድና እግዚአብሔርስ ቢሆን ለምን እዚህ ላይ ተወኝ? በማለት የበዳይ አኩራፊ እንሆናለን። ግማሹ ቀን ንስሐ በሌለው ጸጸት ያልቃል።
ዓይናችንን ለመግለጥ ፣ ከእንቅልፍ በደንብ ለመንቃት የከፈትነው ስልካችን ብዙ ቁርጥራጭ ወሬዎችን በማምጣት ረጅም ነገር እንዳናዳምጥ ትዕግሥት አልባ ያደርገናል። የአንድ ደቂቃ ተማሪዎችና አድማጮች መሆንም የቁም ሞት ነው። በአንድ ደቂቃ መረጃ እንጂ እውቀት ሊገኝ አይችልም። ግማሹ ቀን በማይመለከተን፣ ሄደን በማንረዳቸው ወሬዎች ያልቃል። ማለዳ ላይ የሚያጠምዱን ሰዎች ለመብል ሳይጠሩን ለመጠጥ ይፈልጉናል። እንቢ ብንላቸው እሺ እስክንል ድረስ ይወተውቱናል። በጠዋቱ በሞት መክሊት ይገዙናል። ገንዘባችንን በሚሰርቁ ሌቦች እየተናደድን ሕይወታችንን የሚሰርቁትን እንከተላለን። በሬ ካራጁ ይውላል እንዲሉ ። ግማሹ ቀን ጠዋት ላይ በሰማነው መርዶ ይወሰዳል። ልቅሶ አልሄድንም ግን ብቻችንን በውስጣችን እናለቅሳለን ። ግማሹ ቀን ጠዋት ላይ በሰማነው ክፉ ወሬ፣ ስለ እገሌ በሰማነው የሰብቅ ወሬ አእምሮአችን ተይዞ ይባክናል። ሰይጣን ማልዶ የሚወጣ ለክፋት የሚተጋ ነው። ጠዋቱ ከተያዘ ከሰዓቱም የእርሱ ነው። ማልዶ ይወጣል። ሕፃንነታችንን ሊበላ፣ ማለዳችንን ሊሰርቅ፣ ጅምራችንን ሊቀጭ ይፈልጋል።
ግማሹ ቀን በሚያሰክር አሳብ ካለቀ በኋላ ከሰዓቱን ራሳችንን ካለንበት ስሜት ለማውጣት ተራ ነገር ላይ እንድንውል ያደርገናል። ማግኘት የማንፈልጋቸውን ሰዎች በማግኘት ያናደዱንን ሰዎች መርሳትና መበቀል እንፈልጋለን። ውስጣችን ደስታ ስለራቀው የሚያስቅ ነገር እንፈልጋለን። ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር ማውካካት ያምረናል። የአንድ ቀን ወዳጅነት ያሻናል። የወደድነውን ብናጣ የጠላነውን እንቀላውጣለን። ፍርሃታችንን ለማስታገሥ፣ የእኔ የምንላቸው ሰዎች የወሰዱብንን ድፍረት ለመመለስ ከሰዓት በኋላ መደበቂያ ቦታ እንፈልጋለን። በዚያ የምናገኛቸውን ሰዎች አብረናቸው ብንበድል ደግመን ስለማናገኛቸው ደስ ይለናል። ሰውን ተጠቅመን ለመጣል፣ ከእውነት ለስሜት ለመኖር ይዳዳናል።
በሰላም ከገባን የጠዋቱ ኩርፊያና ጭቅጭቅ ይቆየናል። ሰክረን ከገባን እንክብካቤ ተደርጎልን እንተኛለን። ስለዚህም ሞኝ አንግሥ የሆነውን መጠጥ እንመርጣለን። ያልሆንነውን ማንነት እንይዛለን። በሐሰተኛ ደስታ እንያዛለን። ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ በሚል ስሌት እንወድቃለን። አውቀን መሳሳታችን ቢቆጨን አለማወቅ ያምረናል። በማያውቁ በደለኞች መቅናት እንጀምራለን። ግማሹ ቀን በአዲስ ጦርነት ሲባክን ከሰዓት በኋላው እሳቱን ለማጥፋት ይውላል። ቀኑ ወደ ዓመት ይዘልቃል ፣ ተታለን ዘመናችን ያልቃል።
ስለዚህ ማለዳ ሰውን ሳናገኝ ከጌታችን ጋር እንገናኝ። ቃሉን እናንብብ። የዕለቱን ሥራ በትጋት እንሥራ። በቂ የአካል እንቅስቃሴ፣ በቂ ንጽሕና በማለዳው ያስፈልገናል። ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ከሰዓት በኋላ መጠቀምን መልመድ ፣ እርሱንም በገደብ ማድረግ አለብን። ማለዳው ብርቱ የምንሆንበት ሰዓት ነውና ለሥራና ለዓላማችን እናውለው።
ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም.