የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ ታኅሳስ ፳፫/ ፳፻፮ ዓ.ም.
እግዚአብሔር አምላክ ሰውን መፍጠር ያስፈለገው ብቸኝነት ተሰምቶት እንዲያጅበው፣ ድካም ኖሮበት እንዲያግዘው፣ ማለፍ ኖሮበት እንዲተካው አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው ድካም፣ በመንግሥቱ ሽረት፣ በህልውናው ህልፈት የለበትም፡፡ ሰውን እንዲፈጥር ያስገደደው ፍቅር የሆነው ባሕርዩ ነው፡፡ በፍቅር ምክንያት ፈጠረው፣ በፍቅር ምክንያት አዳነው፡፡ እግዚአብሔር በሰው ላይ ያለው ዓላማው ፍቅር ነው፡፡ የሰው ልጅ የመፈጠሩም ሆነ የመዳኑ ዋስትና ይህ መግለጫ የሌለው ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ገነትን አዘጋጅቶ እንዲፈጥረው ያደረገው፣ በመስቀል ላይ ሞቶ እንዲያድነው ያስገደደው፣ ኋላም በዘላለም መንግሥቱ የሚያሳርፈው የገዛ ፍቅሩ ነው፡፡ ሰው ሲወድቅ ትንሣኤው፣ ሲሞት ሕይወቱ ይህ ፍቅር ነው፡፡ እኛ ባልታመንን ሰዓት እንኳ እግዚአብሔር ስለ ታማኝነቱ ብዙ ዘመን መልካም አድርጎልናል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ ከሙሉ ነጻነት ጋር ፈጥሮታል፡፡ ሰው ነጻ ፈቃዱን ማንም የማይጋፋው ፍጡር ነው፡፡ ይህን ነጻነት ለሰው የሰጡት ነገሥታት አይደሉም፣ ይህ ነጻነትም ሥልጣኔ የወለደው ሳይሆን ሰው በአፈጣጠሩ ነጻ ፍጡር ነው፡፡ ምናልባት ነገሥታትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይህን ነጻነት ያስመልሱ ይሆናል እንጂ ለሰው አይሰጡትም፡፡ እግዚአብሔር የነጻነታችን አባት ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በነጻነት መፍጠሩ ለሰው ያለውን ክብርና ፍቅር ያመለክታል፡፡ ፍቅር ለሚወደው ነጻነትን ይሰጣልና፡፡ እግዚአብሔር ከነጻነት ጋር ባይፈጥረን ኖሮ ፍቅር ነው ብለን ለመናገር ባልቻልን ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን የወደድነውን የመምረጥ ነጻነት ያለን አድርጎ ፈጠረን፡፡ የተሻለውንም እንድንመርጥ ዕውቀትን ሰጠን፡፡ እግዚአብሔርን አማራጭ አጥተን ሳይሆን መርጠን እንድናመልከው ተፈጥረናል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ እርሱን ይመስለው ዘንድ ሰውን በመልኩ ፈጥሮታል፡፡ እግዚአብሔር ቢወደን እንደ ልጆቹ ቢቆጥረን እርሱን እንድንመስል ፈቀደ፡፡ እኛን እንዲመስሉ የምንፈልገው ልጆቻችንን ነው፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረን በባሪያ ደረጃ ሳይሆን በልጅ ወግ በመሆኑ ደስ ሊለን ይገባል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የፈጠረን ከሚታይ ሥጋና ከማትታይ ነፍስ ነው፡፡ ስለዚህ በአፈጣጠራችን የሁለት ዓለም ዜጎች፣ የሁለት ዓለም ወራሾች ሆነን ተፈጥረናል፡፡ እግዚአብሔር በድርብ ክብር የፈጠረን ፍቅር ስለሆነ ነው፡፡ ከሁሉ በፊት እግዚአብሔር ሰው አድርጎ ስለፈጠረን ልናመሰግነው ይገባል፡፡ ሰው መሆናችን የእኛ ሳይሆን የእግዚአብሔር ምርጫ ነውና፡፡ ሰው ሆነን በመፈጠራችን መምረጥ የምንችል፣ መውደድና ፍቅራችንን መግለጥ የሚቻለን ሆነን ተፈጥረናል፡፡ አሳባችንን የምንገልጠው፣ በዕውቀትም የምናድገው ሰው ሆነን በመፈጠራችን ነው፡፡ የክርስቶስ ቤዛነት የደረሰን የአምላክን ንጹሕ ፍቅር ያየነው፣ ሰማይንም የምንወርሰው ሰው ሆነን ስለተፈጠርን ነው፡፡
ነቢዩ፡- “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች፡፡ እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ፥ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም፡፡ ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖች ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ” ብሏል (መዝ. 138፥14-16)፡፡
የሰው ልጅ ግሩምና ድንቅ ሆኖ ተፈጥሮአል፡፡ ግሩም ማለት ተፈሪ ማለት ነው፡፡ ሰው በፍጥረት ፊት ግሩም ነው፡፡ ፍጥረታት ሁሉ ለእርሱ ይገዛሉ፡፡ ሰው ደክሞት ወደ ቤቱ ሲገባ ፀሐይ ልሰወር ልዑሉ ተኝቷል፣ የራስጌ መብራት ጨረቃ ትውጣለት ትላለች፡፡ አራዊቱም ያ ተፈሪ ገብቷልና ከማደሪያቸው ይወጣሉ፡፡ ፍጥረት ሁሉ ልዑሉ እንዳይረበሽ ፀጥ ይላሉ፡፡ ልዑሉ ከእንቅልፉ ሊነቃ ሲል ወፎች ዝማሬ ይጀምራሉ፣ ጨለማም ይሸሻል፣ አራዊትም በዱር ይገባሉ፡፡ አዎ ሰው በፍጥረት ፊት ባለ ግርማ ነው፡፡
ሰው በፍጥረት ፊት ባለ ግርማ ብቻ ሳይሆን ሰው በራሱ ፊትም ድንቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ያለ ሕያው ሕንጻ ከአፈር ማነጹ ይገርማል፡፡ ከብረት፣ ከወርቅ፣ ከአልማዝ ሳይሆን ከአፈር ቤትን ሠራ፡፡ በአፈር ቤት እንዲህ ያለውን ውድ ንብረት አስቀመጠ፡፡ ከራስ ፀጉራችን እስከ እግር ጥፍራችን ያለውን እያንዳንዱን ተፈጥሮ ጠበብቶች ተከፋፍለው ቢያጠኑትም ገና አልደረሱበትም፡፡ እግዚአብሔር ድንቅ አድርጎ ይህችን አጭር ቁመትና ጠባብ ደረት ትልቅ ፋብሪካ ሊሠራ የማይችለውን ሥራ እንድትሠራ አድርጎ መፍጠሩ ይደንቃል፡፡ እግዚአብሔርን ለማድነቅ ተሸክመን የምንዞረው ሰውነታችን በራሱ በቂ ነው፡፡
ነቢዩ፡- “ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ” አለ (መዝ. 138፥16)፡፡ ሳይሠራ የሚያይ የሥነ ሕንጻ ባለ ሙያ ነው፡፡ ትልቁ መሐንዲስ እግዚአብሔር አስቀድሞ አየን፣ ወላጆቻችን ሳያዩን፣ ወዳጆቻችን ሳያዩን፣ ራሳችንን ሳናየው አየን፡፡ ቤቱ እንድንሆን አነፀን፡፡ እግዚአብሔር የምናልፍበት የሕይወት ጎዳና ሁሉ አየ፡፡ የሚደርሱብን ነገሮች ሁሉ በእርሱ ታይተዋል፡፡ ሕይወት ፍልስፍና፣ ሕይወት ያልታወቀች አይደለችም፡፡ ሕይወት መለኮታዊ ድርሰት ናት፡፡ የመጨረሻዋ ምዕራፍ ሳይቀር በደራሲው ተጽፏል፡፡ የመጨረሻ ምዕራፉም መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡
እኛስ ግሩምና ድንቅ ሆነን ስለ መፈጠራችን እናመሰግን ይሆን? እግዚአብሔር ለራሱ ፈጥሮናል፡፡ በዘላለም ቤቱም ይሰበስበናል፡፡ ግን በእርሱ አምነናል? እንደ ፈቃዱስ ኖረናል?