የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ግን…

እግዚአብሔር እንደሚያደርግልን እንጂ እንዴት እንደሚያደርግልን አናውቅም፡፡ እንዴት የሚለውን መጠይቅ ያልተሻገረ እምነት አይደለም ፡፡ አምናለሁ ግን… የሚል አስመሳይ ከሃዲ ነው ፡፡
እግዚአብሔር ፍቅር ነው “ግን” አይባልም ፡፡ አፍራሽ የሌለው “ግን” የማይከተለው እግዚአብሔር ፍቅር ነው ፡፡ በርግጥ እንደ ወደድነው ባናውቅም በርግጥ እንደ ወደደን እናውቃለን ፡፡ ራሳችንን እንደ ሰጠነው እርግጠኛ ባንሆንም ራሱን ግን ሰጥቶናል ፡፡ እንዳገለገልነው በሙሉ አፍ ባንናገርም ፣ እንዳገለገለን ግን እንመሰክራለን ፡፡ እርሱ ከፍ ባለው ዙፋን ፣ ዝቅ ባለው በረት ፤ ከፍ ባለው ንግሥና ፣ ዝቅ ባለው እግር ማጠብ ፤ በደሙ በመግዛት በይሁዳ በመሸጥ ሁሉ በሁሉ ሁኖ ይታያል ፡፡ የሰው ፍቅር ሂደት ነው ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር የተፈጸመ ነው ፡፡ የምንወደውን ባንሆንም የሆነውን መውደድ የተፈጥሮ ግዴታችን ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ግን ግራ በገባን ነገር ላይ መልስ ነው፡፡
ክርስቲያን ነኝ ግን… አይባልም ፡፡ ግን ከተጨመረበት ክርስትና የለም ፡፡ እግዚአብሔርን ማመን ፣ ትእዛዙን መፈጸም ፣ ምሥጢራትን ማክበር ፣ ከሌሎች ጋር በፍቅር መኖር ፣ የተጨነቁትን ማረጋጋት ፣ ሥጋዊ ደስታን መጠየፍ የክርስትናው ግዴታ ነው ፡፡ በመሥዋዕት እዚህ የደረሰ ክርስትና ያለ መሥዋዕትነት አይቀጥልም ፡፡ በዛሬው ዘመን ትልቁ ሰማዕትነት ዓለምን እንቢ ማለት ነው ፡፡ ዓለምንና እግዚአብሔርን ለማስታረቅ መሞከር እግዚአብሔርን ያለ ማወቅ ውጤት ነው ፡፡ ክርስቲያን ዘመናዊ ሳይሆን ዘላለማዊ ነው ፡፡ አንድ ጊዜ ተመሥርቶ ዘመኑን በሙሉ ግን የሚታነጽ ነው፡፡ እርሱን የሚመስሉትን አማንያን የሚወድ ነው ፡፡ ላላመኑ የፍቅርና የአዘኔታ ልብ ያለው ነው ፡፡ በድሀ የማይጨክን ፣ ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ የሚሆን ነው ፡፡
ኦርቶዶክስን እወዳታለሁ ግን … አይባልም ፡፡ ቤተ ክርስቲያን እናት ናትና ያለ “ግን” ልትወደድ ይገባታል ፡፡ እናቱን የሚሰድብ እንደሌለ ካለም የተረገመ እንደሆነ ሃይማኖቱንም የሚያቃልል የቀለለ ነው ፡፡ በዓለም ላይ ፍጹም ቤተ ክርስቲያን የለችም ፡፡ ፍጹሙ እግዚአብሔር ያላት ቤተ ክርስቲያን ግን አለችን ፡፡ ፍጹም ነገር መፈለግ አንደኛ ስቃይ ነው ፤ ምክንያቱም አይገኝምና ፡፡ ሁለተኛ፡- ቢገኝም እኛ መግባት አንችልም ፤ ምክንያም ፍጹም አይደለንምና  ፡፡ ሦስተኛ፡- ፈቅደው ቢያስገቡን እንኳ እኛ የገባን ቀን ፍጹምነቱ ያበቃል ፡፡ አዎ በአስተዳደሩ ሃይማኖትን ፣ በአገልጋዮቹ እግዚአብሔርን መጥላት ተገቢ አይደለም፡፡
ክርስቲያኖችን እወዳለሁ ግን… የሚል ቀድሞም አይወድም ፡፡ ፍቅር ፍጹም ነገርን ከፈለገ ፍቅር አይደለም ፡፡ ፍቅር ጎዶሎውን ፍጹም አድርጎ ሲመለከት ያን ጊዜ ፍቅር ነው ፡፡ ገና ዘላለም አብረነው የምንኖረውን አማኒ ዛሬ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አብረነው መኖር ካቃተን በራሳችን ላይ መንግሥተ ሰማያትን እየዘጋን ነው ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ተስማምቶ ከሰዎች ጋር በጠብ የሚኖር ገና ከእግዚአብሔር ጋር አልተስማማም ፡፡ ምክንያቱም በፍቅር ኑሩ ያለውን የእግዚአብሔርን ቃል አላከበረምና ፡፡
ትዳሬን እወዳለሁ ግን… የሚል ሐሰተኛ ነው ፡፡ ትዳር ማለት ሠርግ ማለት አይደለም ፣ ስለዚህ ሁልጊዜ ደስታ አይጠበቅም ፡፡ የትዳር ጓደኛ ማለትም ተማሪ አይደለም ፣ ስለዚህ በሁለት ዓይን አያዩትም ፡፡ ትዳር ልዩነት የታረቀበት እንጂ የተጨፈለቀበት አይደለም ፡፡ የትዳር ውበቱ የተለያየ ጾታ ፣ መልክና ፍላጎት መሆኑ ነው  ፡፡  ትዳርን ለዜና ፍጆታ አሳልፎ መስጠት ተገቢ አይደለም ፡፡ “ሰው አባቱና እናቱን ይተዋል ፣ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል” ማለት የትዳሩን ምሥጢር ከቤተሰቡም ጋርም አይማከርም ማለት ነው ፡፡ ለቤተሰብ የማይነገረው የትዳር ምሥጢር ዛሬ የሕዝብ ማጫወቻ መሆኑ ያሳዝናል ፡፡ እግዚአብሔርም ይቀጣል ፣ ዝም አይልም ፡፡
መንፈሳዊ አባቴን እወዳቸዋለሁ ግን… ማለት ስህተት ነው ፡፡ ከአገልጋዮች ጋር ያለን ግንኙነት ከግል ሕይወታቸው ጋር ሳይሆን ከተሰጣቸው ቃሉና ጸጋው ጋር ነው ፡፡ በተገቢው ርቀት ከኖርን መልካም ግንኙነት ይኖረናል ፡፡ እፍ ካልን ግን ልንጠፋ ፣ ልናጠፋ ፣ ልንጠፋፋ እንችላለን ፡፡ እፍ ያጠፋልና፡፡ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሊመረቁ ይገባል እንጂ ሊረገሙ አይገባም ፡፡ በጸሎት ማገዝ እንጂ ቁመት መለካካት ተገቢ አይደለም ፡፡ እግዚአብሔር አፈኛውን አሮንን ሳይሆን አፈ ትቡን ሙሴን መርጧል ፡፡ እግዚአብሔር አገልጋዩን ማንም አይመርጥለትም ፡፡
አገሬን እወዳታለሁ ግን… ማለት ቀድሞም አለመውደድ ነው ፡፡ አገር የእግዚአብሔር ስጦታ ናት ፡፡ እኛን ከዚህ ወገንና አገር ሲፈጥረን እግዚአብሔር አልተሳሳተም ፡፡ አገርን በፓርቲ ፣ ሕዝብን በመሪዎች ማየት ስህተት ነው ፡፡ አገዛዝ ይወድቃል ፤ አገርና ሕዝብ ግን ቋሚ ሁኖ ይኖራል፡፡ ደግሞም “ጋን ቢለቀለቅ ጭልፋ ይሞላል” ይባላልና አነሰ በዛ ሳይሉ አገርን መርዳት ፣ ድሆቿን ከራብ ማሳረፍ ይገባል ፡፡
ያለ “ግን” መውደድ ይሁንልን ፡፡
የደስታ ቋጠሮ /9/
ተጻፈ አአ
ሐምሌ 3/2010 ዓ.ም
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ