የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ግንቡ ፈረሰ

“እርሱ ሰላማችን ነውና ፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው ።” ኤፌ. 2 ፡14-17 ።

ወደ ጥሬ ትርጉሙ መግባት አለብን ። ክርስቶስ ሰላምን የሰጠን ራሱ ሰላም ሁኖ ነው ። ነቢያት ፣ ካህናት ፣ ነገሥታት በመካከለኛነት ሊያገናኙት ያልቻሉትን ክርስቶስ ሰላማችን ሁኖ አንድ አድርጎናል ። እርሱ ሰላማችን የሆነው አስፈልጋችኋለሁ ብሎን ነው ። የሚበጀንን የማናውቅ ከንቱዎች ነንና ። ነገን ያዩልን ሰዎች የሕይወታችን ትልቅ ርእስ ናቸው ። ዘላለምን ያየልን ሰላማችን ክርስቶስ የአምልኮአችን ርእስ ነው ። ሰዎች ሰላምን ለማግኘት የሚከፍሉት ዋጋ ገንዘብ አይደለም ። ራሳቸውንና የሰዎችን ሕይወት ነው ። እነ እገሌ ቢሞቱ እናርፍ ነበር ሲባል እንሰማ ይሆናል ። ሞቶ ያሳረፈን ግን ክርስቶስ ብቻ ነው ። እነ እገሌ ሲሞቱ አሳባቸው ሕያው እየሆነ ይመጣል ። ቆመው ከበደሉን ሞተው የበደሉን ሊበዛ ይችላል ። ጌታችን ግን በሞቱ ብዙ አተረፈልን ። እርሱ ሰላማችን በመሆኑ ሁለቱን እንዳዋሐደ ሐዋርያው ይናገራል ። ሁለቱ የተባሉት ሕዝብና አሕዛብ ናቸው ። ሕዝብ የተባሉት እስራኤል ናቸው ። በአንድ አምላክ የሚያምኑ ፣ የእምነት ምልክት የሆነውን ግዝረትን የተቀበሉ ናቸው ። አሕዛብ በብዙ ጣኦታት የሚያምኑ ፣ በዕድልና በጥንቆላ ፣ በንግርት የሚመሩ ናቸው ። ትዳራቸው ብዙ የሆነ ፣ በዝሙት ኪዳናቸውን የሚያረክሱ ናቸው ። በአሕዛብ ልማድ ዝሙት ሸቀጥና የአደባባይ ጨዋታ ነው ። በጣኦት ቤቶቻቸው መሥዋዕት ሁኖ ይቀርብ የነበረው ዝሙት ነበረ ። ራሳቸውን ለሰይጣን አሳልፈው የሰጡ በሺህ የሚቆጠሩ የዝሙት ተዳዳሪዎች ነበሩአቸው ። ሥጋን ባለመግዛት ፣ የሰውነትን ክብር ዝቅ አድርገው ይኖሩ ነበር ። በዚህም የትውልድ ውድቀት ሲመጣ ከሁሉ በላይ እግዚአብሔር ያዝን ነበረ ። ሰው የሠራውን አምላኩን ትቶ ራሱ ያበጀውን ጣኦት ማምለክ ከባድ ነው ። እስራኤልም የአምላክ ልጆች ናቸውና ከእነዚህ ጣኦታውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖራቸው በሕግም ፣ በነቢያትም ፣ በሞራልም ተከልክለው ነበር ። እንደውም እስራኤል ሲበድሉ በእነዚህ አረማውያን ይቀጡ ነበር ።

ብሉይ ኪዳን በጠባዩ አንድን ሕዝብ አድራሻ ያደረገ ፣ የአዲሱ ኪዳን መዳረሻ ነበር ። ሁሉን ለማቀፍ የአዲስ ኪዳንን ኃይል የሚጠብቅ ኪዳን ነበር ። ተስፋውም ምድራዊ ሲሆን እርስዋም ምድረ በረከት የሆነችው ከነዓን ናት ። በብሉይ ኪዳን አሕዛብ ታቅፈው ቢሆን ኖሮ መላው ዓለም እስራኤልን ለመውረስ ይጋደል ነበር ። የአዲስ ኪዳን በረከት ግን ሰማያዊ በመሆኑ ሁሉን ያቅፋል ፣ ለሁሉ ይበቃል ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ምንም የሕጉ ባለቤት ሁኖ ሕዝብና አሕዛብ እንዲለያዩ ቢፈቅድም በአዲሱ ልደት ግን አንድ ይሆኑ ዘንድ ፈቀደ ። የአብርሃም የሥጋ አባትነት ሁሉን አንድ ማድረግ አልቻለም ፣ የክርስቶስ ጌትነት ፣ የአብርሃም እምነት ግን ሁሉን አንድ አደረገ ። ሕዝብና አሕዛብ የተለያዩበትን ግንብ ቢያንስ ሦስቱን መጥቀስ ይቻላል ።

የመጀመሪያው ግንብ ግዝረት ነው ። ግዝረት ወንድ ልጅን የሚመለከት ሲሆን በወንድ ልጅ ውስጥ ሴት ልጅ አለች ተብሎ ይታሰባል ። ምክንያቱም የሴት መገኛዋ ወንድ ነውና ። በሌላ አገላለጽ የመጀመሪያዋ እናት መሬት ፣ ሁለተኛው እናት አዳም ፣ ሦስተኛዋ እናት ሔዋን ናቸው ። አዳም ከመሬት ፣ ሔዋን ከአዳም ጎን ፣ አቤል ከአዳምና ከሔዋን ተገኙ ። የሴት ልጅ ግዝረትም ያልታዘዘ ነው ። ወንድ ልጅ ግን የአብርሃምን አምላክ የማምለክ ምልክትና የቃል ኪዳን ማኅተም የሆነውን ግዝረት በተወለደ በስምንተኛው ቀን ይፈጽም ነበር ። ይህ ግዝረትም የተጀመረው በአብርሃም ዘመን ሲሆን ከክርስቶስ ልደት ሁለት ሺህ ዓመት ቀደም ብሎ ነው ። ግዝረትም እስራኤል ከአሕዛብ የሚለዩበት ነው ። ግዝረት የማይጠፋ ምልክት ፣ እስከ ሞት ድረስ የሚኖር ትእምርት ነው ። ይህ ግዝረትም ለጥምቀት ምሳሌው ሁኖ አገልግሏል ። ግዝረትና ጥምቀት ተናባቢ ናቸው ። ጥምቀት መሞት ነው ብለናል ። ግዝረትም የአካል ክፍል ተቆርጦ የሚጣልበት ነውና የሞት ሥርዓት አለው ። ጥምቀት ለሕፃናት የሚፈቀደው ግዝረት ለስምንት ቀን ልጅ ስለ ታዘዘ ነው ። እንዴት ሳያምን አይባልም ። ምልክቱ ይቀድማል ፣ እምነቱ ይቀጥላል ። ምሳሌው ሕፃናትን ካልከለከለ እውነቱ የሆነው ጥምቀትም ሕፃናትን አይከለክልም ። በራሳቸው እምነት ልጆቻቸውን ሐኪም ቤት የሚወስዱ ወላጆች በራሳቸው እምነት ልጆቻቸውን ወደ ጥምቀት አለመውሰዳቸው ይገርማል ።

ሁለተኛው ግንብ የመብል ሕግ ነው ። አሕዛብ ሁሉን የሚበሉ ሲሆኑ እስራኤል ግን መርጠው የሚበሉ ናቸው ። እስራኤል የሚኖሩት አካባቢ ሞቃታማ ነው ። የአሣማ ሥጋ ቢበሉ በንዳድ ያልቁ ነበር ። የተከለከሉት ምግብም በተፈጥሮው ርኵስ አይደለም ። ምክንያቱም እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም እንደሆነ ተጽፎአል ። ሕግ ግን አረከሰው ። አንዳንድ ምግቦችም የሰውነት ጠረንን የሚቀይሩ ናቸውና ተከልክለዋል ። ይህ ግንብም “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ” ተብሎ ከተዘመረ በኋላ ሥራውን ፈጽሟል ። የመብል ሕግ የባሕላችን እንጂ የነፍሳችን ጉዳይ አይደለም ። አሕዛብ የነበሩት ግብጻውያንም ፣ ግሪካውያንም ከነመብል ሕጋቸው ክርስቲያን ሁነዋል ። እኛ ግን ብሉይ ኪዳንን ስለተቀበልን የመብል ሕግን እንጠነቅቃለን ። ግዝረትንም ለሃይማኖት ሳይሆን ለውበትና ለጤንነት እናደርገዋለን ። ከጥምቀት ወደ ግዝረት ዘወር ለማለት ጸጋችን አይፈቅድልንም ።

ሦስተኛው ግንብ አሕዛብ የእስራኤልን አምላክ ፈልገው ቢመጡ እንኳ በቤተ መቅደሱ የማይገቡበት ክልል ነበር ። ይህ ክልልም በግንብ የታጠረ ነበር ። በአንድ መቅደስ ውስጥ በግንብ ተለያይተው ሲያመልኩ አንድ የምንሆነው መቼ ነው እያሉ ነበር ። ሰላማችን የሆነው ክርስቶስ ግን ግንቡን አፍርሶ ሕዝብና አሕዛብን በደሙ አንድ አደረጋቸው ። ቤተ አይሁድም በቤተ ክርስቲያን ተተካ ። የሁሉ ሰብሳቢ ቤተ ክርስቲያንም በሰማይና በምድር ግዛቷን አሰፋች ። በሰማይም አባላት ስላሉአት ስለ ሞቱን ትጸልያለች ። የሞቱትም ስለ ቆሙት ይጸልያሉ ። አንድ አካል ነንና ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ