የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ግን ለምን ?

“ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።” (መዝ. 45፡2 ።)

ቀጥሎ ያለውን መጠይቅ ስናነብ ከራሳችን ጋር ሙግት ውስጥ ሳንገባ አንቀርም፡-

“የሚፈልጉንን ችላ እንላለን ፣ ችላ የሚሉንን እንፈልጋለን ፤
የሚጎዱንን እናፈቅራለን ፣ የሚያፈቅሩንን እንጎዳለን ፤ ግን ለምን ?”

“የወላጅና የልጅ ፍቅር እንደ ጅረት ውኃ ከላይ ወደ ታች እንጂ ፣ ከታች ወደ ላይ አይፈስም” ይባላል ። ለሚወዱን ምላሽ የለንም ። በሚጠሉን እንበሳጫለን ፣ የሚወዱንን ግን እንደ ስጦታችን ማየት አንችልም ። ስልክ አላነሣ ያሉንን እንደውልላቸዋለን ፣ ስልክ የሚደውሉልንን ወዳጆች ግን ዝም እንላለን ። እነዚያ ሰዎች ስንወዳቸው የጣሉን ፣ እኛም የሚወዱንን ስለጣልን ነው ። መዝራትና ማጨድ በምድር ነው ። “ጠላትህን ውደድ” ከሚል ትእዛዝ ጋር ብዙ ጊዜ እንታገላለን ። ጠላትን መውደድ የሚቻለው ግን ወዳጅን ሲወድዱ መሆኑን እንረሳለን ። ጠላትህን ውደድ የተባለው አፍቅረው ማለት ብቻ አይደለም ። ጠላትህ ባይኖር ዝርክርክ ሆነህ ትቀር ነበር ። ሁሉም ዘመድ አለመሆኑን ያስታወቀህ ጠላትህ ነው ። ወዳጆችህ ሊነግሩህ የፈሩትን ቆሻሻ ያለ ይሉኝታ የነገረህ መስተዋትህ ጠላትህ ነውና ውደደው ። እርሱ እንዳያገኝህ ስትሸሽ ከመጠጥ ቤት ርቀሃል ፣ ጠላትህ “ተቀደስ” እያለ የሚጮህ ንስሐ አባትህ ነው ። ራስን ችሎ መቆም ፣ አንሶ አለመገኘት ፣ ጥገኛ አለመሆን ፣ ጸንቶ መታገል … እነዚህን ሁሉ ያስተማረህ ጠላትህ ነው ። ወዳጆችህ እየተንቀጠቀጡ መርፌውን አልወጉህም ፣ ዓለምን የምታውቅበትን መድኃኒት ጨክኖ የወጋህ ግን ጠላትህ ነው ። ሰው ማለት ማን መሆኑን ያወቅህበት ትምህርት ቤትህ ነውና ጠላትህን ውደደው ።

“ምቀኛ ጎረቤት ዕቃ ያስገዛል” እንዲሉ ጠላትህ ባይኖር ኖሮ ቤት አትሠራም ነበር ። ጸሎተ ሃይማኖትን በጣም ትወደዋለህ ፣ ያ ጸሎት ግን የተረቀቀው ቤተ ክርስቲያን ጠላት ተነሥቶባት ነው ። የተደላደለ የነገረ መለኮት ትምህርት የመጣው አጽራረ ቤተ ክርስቲያን በመነሣታቸው ነው ። ስለዚህ ጠላት ከሚያሳጣህ የሚሰጥህ ይበዛልና ውደደው ።

ምድር ብትነዋወጥ ፣ ወዳጆች ግልብጥብጣቸው ቢወጣ አትፍራ ። የእኔ የምትለው ሰው ይቅርና የእኔ የምትለው አካል የለህምና በከዱህ ሰዎች አትዘን ። እጅና እግርህ እንኳ ያንተ ካልሆነ ሰዎች ለምን የእኔ አልሆኑም ብለህ ትጨነቃለህ ? ሰው የገዛ ልቡ የሚከዳው ፣ ለራሱ እንኳ ዘመድ የማይሆን ነው ። አንዲት ሕይወት ሺህ ፈተና አለባት ። አንዲት ቅጽበት ብዙ ወዳጆችን ታሳጣለች ። ስላጠፋህ የሚሸሹህ ቀድሞም ወዳጆችህ አይደሉም ፣ እውነተኛ ወዳጅ ለሚወድደው የእንደገና ዕድል የሚሰጥ ነው ። ራሳቸውን ይቅር እያሉ አንተን ይቅር ካላሉህ እንደ ራሳቸው አልወደዱህም ማለት ነው ። ድንገተኛው መከራ ለዘመናት የማታውቃቸውን የሰዎችን ማንነት ይገልጥልሃል ። ማዕበሉ ባሕሩን የሚያናውጠው ባሕር ከረጋ ስለሚሸት ነው ። መከራም ከመሞት የሚያድንህ ነው ። እግዚአብሔር ሞትን በሕመም ይለውጣል ። ሁሉን መቀየም ሞኝነት ፣ ሁሉን መለማመጥ ደካማነት ፣ ሁሉን ነገር አክብሮ ማየት ጅልነት ነው ። ንቆ በመተው ብቻ የሚድን ብዙ ሕመም አለ ። የስሜት ስብራት ንቆ በመተው ይድናል ። በቀል ሽንፈት ነው ፤ ይቅርታ ራስን ማዳን ነው ፤ ከዳተኞችን ችላ ማለት ግን አስተዋይነት ነው ።

የኢየሩሳሌም ነፋስ አሥራ ሁለት እንዲሉ ፣ የሰው ልጆች ተለዋዋጭነት እየበዛ ነው ። በሳንቲም የሚሠሩ ማሽኖች ካልከተቱባቸው የያዙትን በጎ ነገር እንደማይሰጡ ፣ ካልበሉ የማይስቁ ጥቅመኞችን ይህ ዘመን ተሸክሟል ። እስከ ዛሬ የነበረው የመደነቅ መግለጫ “ፐ” የሚል ነው ። ዘንድሮ “ፑ” ደርሷል ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ። እኛ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር እንማራለን ፣ እርሱ ግን ፍቅርን አልተማረም ። በባሕርዩ ፍቅር ነው ። እኛ ሰዎችን ስለማንጠላ እንወዳቸዋለን ብለን እናስባለን ፣ እግዚአብሔር ግን መጥላት ስለማይችል የወደደን ሳይሆን ፍቅር ስለሆነ የወደደን ነው ። አዎ ምድር ብትነዋወጥ ከአጠገባችን የነበረው ርቆ ቢተኩስ ፣ አለሁ ያለን ቢሰወር እግዚአብሔር ግን ከእኛ ጋር ነው ። በርግጥም ጣኦት የሆነብን ነገር ተሰብሯልና በመከዳታችን ማዘን አይገባንም ። እግዚአብሔር መሥራት ሲጀምር በእኛ መሠረት ላይ አያንጽም ፣ እግዚአብሔር መሥራት ሲጀምር በማፍረስ ይጀምራል ። አጠገባችን የሚፈርሱትን ነገሮች ስናይ እግዚአብሔር እየሠራ ነውና ደስ ይበለን ! ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን !

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ