ጊዜው ራቅ ይላል ። ምናልባት16 ዓመት ሊያልፈው ይችላል ። ትዝ የሚለኝ እንደ ሕልም ነው ። ድምፁ ግን እንደ ነጎድጓድ ዛሬም ይሰማኛል ። ዕድሜው አርባዎቹን እያጋመሰ ያለ ነው ። ከአሜሪካ አገር ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በሀብቱና በእውቀቱ አገሬን አገለግላለሁ ብሎ መውተርተር ጀምሯል ። ደኅና ቤት ተከራይቶ ፣ ከአሜሪካ አገር ይዞት የመጣውን ምቹና ግዙፍ መኪና ይዞ ይንቀሳቀሳል ። ነገር ግን እንዳሰበው አልሆነለትም ። ያለው ሀብት የሚነሣለት እንጂ የሚጨመርበት አልሆነምና ገንዘቡን ጨረሰ ። እንጥፍጣፊ ላይ ደርሶአል ። ቁመናው ፣ ቁፍጥናው ፣ ጉብዝናው በፊቴ ላይ አለ ። አንድ ቀን ማለዳ ላይ ስልክ ደወለና ልመጣ ነው አለኝ ። እኔም ሳመነታና ሌላ ቀን ስለው እርሱ ግን “እሺ መጣሁ” ብሎ የሚያስበውን ሰምቶ ስልኩን ዘጋው ። እኔም ቁጭ ብዬ እየጠበቅሁት ነው ። በተወሰኑ ደቂቃዎች ውስጥ ደረሰ ። እንደ መጣ ሲያየኝ አለቀሰ ። “እህል ከቀመስኩ ሦስት ቀኔ ነው ፣ መኪናውን የምነዳው ነዳጁ እስኪያልቅ ድረስ ነው ፤ ከዚህ አገር መጣሁ ብዬ ይህን መኪና ይዤ ማንን ልለምን” ሲለኝ ተያይዘን ተላቀስን ። ያን ቀን አብረን ዋልን ። ከዚያ ቀን በኋላ አላየሁትም ፣ ላገኘውም አልቻልኩም ። ከዚያ ቀን ጀምሮ ግን ጥሩ የለበሰም ፣ ከፈረንጅ አገር የመጣም ፣ መኪና የያዘም ሊርበው ይችላል ወደሚል አስተሳሰብ ውስጥ ገባሁ ። ጌታችን ምስጋና ይድረሰውና “እንግዳ ተቀበሉ” ያለው ለዚህ ነው ። እኛ የምናነበውን ወንጌል የሚተረጉሙት እናቶቻችን ናቸው ።
እንግዳን በር ከፍቶ ፣ ጥርስ አሳይቶ መቀበል ብቻውን በቂ አይደለም ። “ከፍትፍቱ ፊቱ” ማለት ፊት ይቀድማል ፣ ፍትፍት ይከተላል ማለት እንጂ ይቀራል ማለት አይደለም ። ሰው እንግዳን የማይቀበለው ገንዘብ ስለሌለው አይደለም ። ባለጠጎች ትልቁ ፈተናቸው ይህ ነው ። ብዙ ባለጠጎች ሰሐኑ እንጂ እንጀራው የላቸውም ። ቤታቸውን ያስጎበኛሉ እንጂ ቁራሽ አያቀርቡም ። ለወትሮም ቢሆን በበረከት የበለጸገና በስስት የበለጸገ ልዩነት አለው ። ለእንግዳ ምግብና መጠጥ አለማቅረብ እግዚአብሔር አልሰጠኝም ብሎ መካድ ነው ። እኛ ጋ እስኪደርስ የበላውን ምግብና የነበረውን አቅም ጨርሷል ። በባዶ ማጫወት በባዶ መሸኘት ሊሰቅቀን ይገባል ። እያለን ካልሰጠን እየሌለን እንሰጣለን ወይ ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። ካለን ነገር ላይ ካልሰጠን ከሌለን ነገር ላይ መስጠት አንችልም ። ብዙ ትዳር የሚታወከው ለእንግዳ የሚሆን ልብ ስለሌለው ነው ። በአንዳንድ ቤት እንግዳ ሲመጣ ሚስት ታኮርፋለች ፣ ወይም ባል ቤት ለቅቆ ይወጣል ። ከሰው ጋር ያልበሉት በሽታ እንደሚሆን አልገባንም ። ብዙ ባሎች ደጅ የሚያመሹት ትዳራቸው እንግዳን መቀበል ስለማይችል ፣ ቤት እንደሌለው ሰው እየተሰማቸው ጓደኞቻቸውን በደጅ እየሸኙ ነው ። ብዙ ሚስቶች በኑሮአቸው ኀዘነተኛ የሚሆኑት ከሰው ተፈጥረው ብቻቸውን ተዘግቶባቸው ሲኖሩ ነው ።
ሌላም ወጣት ትዝ አለኝ ። ነገርን ነገር ያነሣዋልና ። ይህ ወጣት ደኅና የለበሰ ፣ ዘመናዊነት የሚታይበት ነው ። ወደ እኔ የመጣው ድንገት ነው ። እኔ ጋ ሲደርስ ሳይቀመጥ አንድ ነገር አለኝ፡- “ወደ አንተ ስመጣ እየጸለይኩ ነበር ። እርቦኛልና ምግብ ብላ ባለኝ ፣ ሻይ ጠጣ ባለኝ እያልኩ ነበር” ብሎ ስላልቻለ አለቀሰ ። ነጭ ለብሰው የተራቡ እንዳሉ እኔ ምስክር ነኝ ። ሆድን በልብስ አትለኩት ። ልብሱ የዛሬ ሦስት ዓመት የተገዛ ነው ። ሆድ ግን የአሁን ነው ። አንድ ችግረኛ ምግብ ከበላ በኋላ እንዲህ አለኝ፡- “ይህን ሆዴን ምን ላድርገው ? አሁን በልቼ ጠግቤአለሁ ምሳ ሰዓት ደግሞ ይክደኛል” ሲል አሳዘነኝ ። አዎ ሆድ ከሀዲ ነው ። መለመን ያፈሩ ፣ ከረሀባቸው ጋር የሚውሉና የሚያድሩ ስንቶች እንደ ሆኑ የፈጠረው ይወቀው ። ጌታችን “እንግዳ ተቀበሉ” ሲለን እንግዳ ስድስቱን ቃላተ ወንጌል ስለሚያሟላ ነው ። እንግዳ ረሀብተኛ ፣ ጥማተኛ ፣ ልብሱ የቆሸሸበት እርዝተኛ ፣ መንቀሳቀስ የማይችል እስረኛ ፣ የአሳብ ሕመምተኛ ነው ። ከዚህ ቀን ጀምራችሁ ቃል ግቡ ። እቤቴ የመጣውን ማንኛውንም እንግዳ እህል ውኃ ሳይቀመስ አይወጣም በሉ ። ትእዛዙን የሰጠ እግዚአብሔር በጀቱንም ይልካል ።
እርቦት መጥቶ የፖለቲካ ወሬ ጋብዘነው የሄደው ሰው መንገድ ላይ ወድቆ ሊሆን ይችላል ። ቤታችን ቤቱ እስኪመስለው ድረስ ፍቅር አልሰጠነውምና አልነገረንም ። አንድ ቀን ሰማይ የሚባል ሩቅ ሀገር በእንግድነት እንሄዳለንና እንግዳን መቀበል አንርሳ ። መድኃኔ ዓለምን በቤታችን ከተቀበልነው በቤቱ ይቀበለናል ። ለድሮ ከባልንጀሮቻችን ጋር ልንለያይ ስንል መሣፈሪያ አለህ ወይ ብለን እንጠያየቅ ነበር ። አፍሮ ካልጠየቀ አሁን አምጡ ይላል ። በእግሩ ሲሄድ መሽቶበት በወንበዴ እጅ ሊወድቅ ይችላል ። የስሌት ኑሮ ውስጥ ስለገባን ይህን ለመቀበል ይተናነቀናል ። በሃይማኖት የቆመውን አገር በአስኳላ ትምህርት ማፍረሳችን የሚገርም ነው ። የፈረሱ ከተሞችን በማየት የምንሳሳለት ቤትና ገንዘባችን ከንቱ መሆኑን እንማር ። እንኳን ስለ ቤታችን ስለ ከተማችንም ዋስትና በሌለን ዘመን ላይ ደርሰናል ። ትዳር የእንግዶች መቀበያ መሆኑን አትዘንጉ ። እንግዳን የምንጠላው የመጀመሪያው እምነት ስለሌለን ፤ ሁለተኛው ሙያ ስለሌለን ነው ። ሁለቱንም ግን ዛሬ መማር ይቻላል ። ስንፍናም እንግዳን ትጠላለች ።
ጌታ እግዚአብሔር፡- “ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ” ይላል ። ኢሳ. 65፡1 ። እንግዶች ሳይጠይቁን በበረከት ልንገለጥላቸው ይገባል ። አምጡ ሳንባል የቤት ወጪን መስጠት መልመድ ያሻል ። ለቤታችን ማሰብ እንጂ መጠየቅ የለብንምና ። ለለመኑን ብቻ ሳይሆን ላለመኑን መስጠትም መለማመድ ያስፈልጋል ። ወንጌልን ያህል ሀብት ያገኘነው ፈልገነው ሳይሆን እግዚአብሔር ላልጠየቁት በሚገለጥበት ቸርነቱ ነው ። ጴጥሮስ ዓሣ እየፈለገ ፣ ጳውሎስ ወንጌልን ሊያጠፋ እየተፋጠነ ብርሃን በራላቸው ። የምሥራች ላልጠየቁ የሚገለጥ ነው ። የሞላ ነገር ይፈስሳልና የምሥራች ከእኛ ተርፎ የሚፈስስ ነው ። ለዓለሙ የሚሆንን ነገር ለግላችን ብንይዘው ትርፉ መጨነቅ ብቻ ነው ። ወንጌልም ለሰው ልጆች ሁሉ ነው ። ሰዎች ባይጠይቁንም ልንሰጣቸው ይገባል ። “ወንጌል እንግዳ ብሆን ተቀብላችኁኛል” ትላለች ። ማቴ. 25 ፡ 35 ።
“ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ ፣ ላልፈለጉኝ ተገኘሁ” ያለው ለአሕዛብ ስለደረሰው የወንጌል በረከት ነው ።
እግዚአብሔር ሆይ እንደ ዘመኑ ሳይሆን እንደ ቃልህ እንድኖር እርዳኝ ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም.