“ቀንዴን ከፍ ለማድረግ ባሰበ ጊዜ በጠላት መካከል ከበበኝ ።” ቅዱስ አግናጥዮስ
“እንቅፋት የሚጥለው ወደፊት ነው” ይላል የአገራችን ሰው ። እንቅፋቱ የሚያም ቢሆንም መንገዱን ግን ያጋምሳል ። ጋሬጣ በተቀመጠ ቍጥር ከነሕመማችን ወደፊት እየሄድን ነው ። የእንቅፋቱ ዓላማ አቍስሎ ወደ ኋላ ሊመልሰን ፣ የተመታንበት ቦታ በምሬት እያለቀስን እንድንኖር ሊያደርገን ነው ። እንቅፋት ከመታን ተራምደናል ማለት ነው ። እንቅፋት አለ ተብሎ ጉዞ አይቀርም ። እንቅፋቱን ግን እንደ ዕድል ከተጠቀምነው ከነሕመሙም ቢሆን እልፍ ያደርገናል ። እግዚአብሔር እየፈዘዘ ያለውን ማንነታችንን የሚያነቃው በእንቅፋቶች ነው ። ከእንቅፋት ጋር ተከባብሮ መኖር ይቻላል ። ካልሄዱበት አይመጣም ። ከተራመድን ግን እንቅፋት ይገጥመናል ። ሰነፎች እንቅፋት የለባቸውም ። ምክንያቱም ከመቀመጫቸው አይነሡምና ። ሀኬተኞች እንቅፋት አይገጥማቸውም ፤ ምክንያቱም ከመኝታቸው አይወርዱምና ። የማይሠሩ ሰዎች አይሳሳቱም ። የሚሳሳት ሥራ የጀመረ ነውና ። አለመሳሳት ፍጹምነት አይደለም ። አለመሞከር ነው ። እንደ ተፈጠርን መጥተን እንዲሁ መሄድ ይቻላል ። ፍሬ የማያፈሩ ሰዎች ግን ምድርን ያጎሳቁላሉ ። የተሰጣቸውን ዕድል ለተጨማሪ ስንፍና ስለሚጠቀሙበት ይቆረጣሉ ። እንቅፋትን በሚመለከት ሦስት ዓይነት ሰዎች አሉ፡- ዘለው የሚያልፉ ጎበዞች ፣ ቆስለው የሚሻገሩበት ጽኑዓን ፣ ዘላቂውን ራእይ ሳይሆን ጊዜያዊውን ሕመም አስበው ወደ ኋላ የሚመለሱ ደካሞች ።
ሰውዬው ድሀ ነው ። የድህነቱ ምንጭ ግን ፍርጃ ሳይሆን ስንፍና ነበር ። ዝናቡ ሲመጣበት በገዛ ቤቱ ይንቆራጠጣል ። ወደማያፈሰው በኩል እየሄደ ይቀመጣል ። አንድ ጊዜ ጠግኖ በሰላም መኖር ሲችል ክረምት በገዛ ቤቱ እያባረረው ይኖራል ። ታዲያ ደኅና ጣራ የነበረው ወደ መስኮቱ አጠገብ ነበርና በቤቱ ከዝናብ ተጠልሎ ማዶ ማዶ ያያል ። አንድ ባለጠጋም በዝናብ እየተደበደበ ከብቶችን ሲነዳ አየውና፡- “እንኳን ባለጠጋ አልሆንሁ ዝናብ ይመታኝ ነበር” አለ ይባላል ። እጆቻችን በሥራ ከቆሸሹ ቤታችን ንጹሕ ይሆናል ። እጆቻችን ሥራን ተጸይፈው ንጹሕ ከሆኑ ኑሮአችን ጎስቋላ ይሆናል ። ዝናብን የሚፈራ ከቤቱ አይወጣም ። ከቤቱ የማይወጣም እንጀራ አይበላም ። ይልማ ዴሬሳ የተባሉ ባለሥልጣን በክረምት የበታች ሠራተኛቸው አርፍዶ ሲገባ ቀድመው ይጠብቁታል ። “ለምን አረፈድህ ?” ቢሉት “ዝናቡ ይዞኝ ነው” አላቸው ። እርሳቸውም፡- “አንደኛህን ክረምት ሲወጣ ለምን አትመጣም?” አሉት ይባላል ።
ጠላት በተለያየ መንገድ ይነሣል ። ሰይጣን የመንገዳችን እንቅፋት ፣ የግባችን ባላጋራ ነውና ብዙ ድምፆችን በማሰማት ከመንገዳችን እንድንቀር ይታገለናል ። አንዳንድ ጠላት ውጫዊ ነው ። አንዳንድ ጠላት ግን ውስጣዊ የገዛ ሥጋችንን የተተገነ ምኞት ሊሆን ይችላል ። ዐረቦች፡- “ቤት ውስጥ ካለ አንድ ጠላት ውጭ ያለ መቶ ጠላት ይሻላል” ይላሉ ። ሰይጣን የሰዎችን ፈቃድ ተጠቅሞ ልባቸውን መቆጣጠር ይፈልጋል ። ልባቸው የክፉ ምኞቱ መድረክ ከሆነ እርሱን በግብር የሚመስሉት ልጆቹ ይሆናሉ ። ሰይጣን አመክንዮን ፣ ክፋትና ምቀኝነትን ስለሚያስታጥቃቸው የሚጠሉን ሰዎች ራሳቸውን በጨለማው አምሳል ይቀርጻሉ ። በታሪክ ሁሉ እንደ ታየው ግን ጠላት ያሳድጋል እንጂ አያሳንስም ። በሕይወታችን ከመፍዘዝ የምንወጣው እንቅፋት ሲገጥመን ነው ። ያን ጊዜ መንገዳችንን በትክክል ማየት እንጀምራለን ። ዋጋ ከፍለን ስለምንጓዝም በቀላሉ ውጥናችንን አንተውም ። መውደቅ ቢገጥመንም የተስፋ ችቦ የሚለኮሰው ሰውዬው በፈቀደ መጠን እንጂ ለአንድ ጊዜ ብቻ አይደለም ። የጠፋውን እምነት በተስፋ መፈለግ ፣ የራቀንን ፍቅር በተስፋ ገንዘብ ማድረግ ይቻላል ። ሰው ተስፋ ሲቆርጥ ራሱን ይጠላል ፣ ራሱንም ሲጠላ ሰዎችን እየጠላ ይመጣል ። የቆሰለ ሰው ከሕመሙ ጋር እልህና ቀናዒነት በውስጡ ይመጣል ። ጠላትንም የሚያሸንፈው በሥራ ብቻ መሆኑ ሲገባው ያለ ሰዓት ገደብ መሮጥ ይጀምራል ። ድንገተኛ ኃይል ሰውን ከተፈጥሮ በላይ እንዲራመድ ያደርገዋል ። በአደጋ ሰዓት ወፍራሙ ሰው በቀጭን ቀዳዳ ሾልኮ ይወጣል ። እግሮቼ መራመድ አይችሉም የሚለው ሰው ችግር ሲገጥመው በሩጫ ያመልጣል ። ጣር የያዘው ሰው የአደጋ ድምፅ ሲሰማ በሽታው ሄዶለት ፣ ከአልጋ ላይ ወርዶ ደጅ ላይ ይገኛል ። አስቸጋሪ ሁኔታዎች የሚያመጡልን ዕድል አለ ። የምንጠቀምበት ኮምፒዩተር እንኳ በመሳሳት ሌላ አዲስ እውቀት እንድናገኝ ያደርገናል ። ተሳስተናል ፣ ግን አዲስ ነገር ብልጭ ብሎልናል ።
ጠላት አልባ ስንሆን ፍዝ እንሆናለን ። ጠላት አልባ ስንሆን ምቾት ሥራ ፈት ያደርገናል ። ጠላት አልባ ስንሆን አእምሮአችን መፍትሔ ማፈላለግ ያቆማል ። ጠላት አልባ ስንሆን ሥጋችን እየዛለ ፣ እውቀታችን እየተነነ ፣ መንፈሳችን እየተዳከመ ይመጣል ። ጠላት አልባ ከሆንን የማንጠቅም የማንጎዳ ተደርገን ተቆጥረናል ማለት ነው ። ጠላት አንፈጥርም ፣ የተፈጠሩትን ጠላቶችም መፍራት አይገባንም ።
እግዚአብሔር ቀንድን ከፍ ከፍ ያደርጋል ። ቀንድ መለያ ነው ። ቀንድ ኃይል ነው ። ቀንድ የጽናት መገለጫ ነው ። ቀንድ የዜማ ዕቃ ነው ። ቀንድ መከላከያ ነው ። ቀንድ ክብር ነው ። እግዚአብሔር ይህን ቀንድ ለማሳደግ የሚጠቀመው አንድ ነገር አለ ። በጠላት ይከበናል ። ለካ ይህም አለ የሚል አዲስ እውቀት የምናገኘው ጠላት ሲነሣብን ነው ። ያለንን ነገር መጠቀም የምንጀምረው ጠላትን ድል ለመንሣት ስንነሣ ነው ። ቀንድ አልባ ከሆንን በቀላሉ እንበላለን ። ጠላት ባይኖር ቀንድ አያስፈልግም ነበር ።
ቅዱስ አግናጥዮስ፡- “ቀንዴን ከፍ ለማድረግ ባሰበ ጊዜ በጠላት መካከል ከበበኝ” አለ ። አንድ ሰውም፡- “ጠላቶችህ አንተ ራስህን ከምታየው በላይ በጠራ መልኩ ያዩሃል ። ጠላቶችህ ኃይለኛ ሃያሲዎችህ ናቸው” ብሏል ። ጠላቶች ስላሉ የጠራ ሥራ እንሠራለን ማለት ነው ። ሳንከፍላቸው የሚያርሙን ፣ እንከናችንን ያለ ይሉኝታ የሚነግሩን ጠላቶቻችን ናቸው ። ለበጎ ከተጠቀምንበት ጠላቶቻችን የጠራ ተግባር እንዲኖረን እኛን የሚጠብቁ ዘቦች ናቸው ። ይህን ተረድቶ ደስ የሚለው ግን ብልህና ግቡን የሚያውቅ ነው ። አንድ የላቲኖች አባባል፡- “የመድረሻ ወደቡን የማያውቅ መርከብ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚነፍስ ነፋስ አይረዳውም” ይላል ። የሚያጠፋው ነፋስ ወደ ግብ የሚገፋ ይሆናል ። ነገር ግን መድረሻን ማወቅ ይፈልጋል ።
ከክፉ ነገሮች በጎ ነገርን የሚያወጣ እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይድረሰው !
የብርሃን ጠብታ 25
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 20 ቀን 2014 ዓ.ም.