የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጢሞቴዎስ ነኝ (1)

(የወጣት አገልጋይ ፈተና)

ደጁን ስጸፋ ፈጥኖ “አቤት” ያለው ቅዱስ ጳውሎስ ነበር ። ቅዱስ ጳውሎስ፡- “የእኔን በር የሚጸፉ የጌታን ደጅ እንደሚመቱ ነው ። እርሱ በሩን በጸሎት ሲያንኳኩ ደስ ይለዋል ፣ ፈጥኖም ይከፍታል ። ደግሞም ወደ ቤቴ በእንግድነት የሚመጣው በሚታየው ሰው ውስጥ የማይታየው ክርስቶስ ነው” ብሎ ያምናል ። ስለዚህ በሩን ስመታ ፈጥኖ “አቤት” አለ ። “አቤት” ለማለትና ተነሥቶ ለመክፈት እነ ማርቆስ ፣ እነ ቲቶ ነበሩ ። ጳውሎስ ግን ክብርን በክርስቶስ ስላገኘ የፕሮቶኮልና የዲፕሎማሲ ክብርን ተጸይፎት ነበር ። ምክንያቱም ውሸት ነውና ። የፕሮቶኮል ክብር አንዱን ሰው ፣ በቀን ውስጥ ሁለት ዓይነት ሰው አድርጎ ያውለዋል ። በቀይ ምንጣፍ ላይ የሚሄዱት እቤት ሲገቡ ዳዴ እያሉ ከልጃቸው ጋር ይጫወታሉ ። የአገር በጀት አጽድቀው በቤት ወጪ ከሚስታቸው ጋር ሲጨቃጨቁ ያመሻሉ ። ብዙ ሰዓት ያነበቡ የመሰሉ ወይዛዝርት ፀጉራቸውን ሲሠሩ አንግተዋል ። በሌሎች ጭንቅላት ያስባሉ ፣ በሌሎች እጅ ይጽፋሉ ። ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያን የሆነው ይህ ሰልችቶት እንጂ ፣ ይህን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማምጣት አልነበረም ። እውነተኛ ክብርን የሚሰጥ ነበር ። የእውነተኛ ክብር መገኛው ፍቅር ነው ። የማንወደውን ሰው አናከብረውም ፣ የምናከብረውንም እንወደዋለን ።

ሰው ሁሉ ለራሱ ክብር አለው ። ባልንጀራውን እንደ ራሱ ሲወድድ ያከብረዋል ማለት ነው ። ዘመናዊነት ክብርን ያሳጣ ፣ ክብርንም በማታለያ የለወጠ ፣ በጥርስ እየሳቀ በልብ የሚያንቅ ነው ። ዘመናዊነት ሰውን በሕፃን ባሕል የለወጠ ፣ የተጣበቀ ልብስ ፣ ጣፋጭ የበዛበት ምግብ ፣ ተራ ንግግርን ያበዛ ነው ። ሰው በምድር የተቀመጠ ልዑል ነው ። የንጉሥ ልጅ ነውና ። ልዑል የሚናገረው የቤተ መንግሥት ቋንቋ ፣ የክብር ልሳን ነው ። ዝንቦች በቆሻሻ ቦታ እንዳሉ ፣ ውርደት ባለበትም አጋንንት አሉ ። በድን ወዳለበት አሞራ እንዲሰበሰብ ቅሌት ባለበትም ሕፃናተ አእምሮ ይከማቻሉ ። ክርስቲያን ለክብር ባይኖርም ክብሩን ጥሎ ግን አይኖርም ። ዱርዬ የሚባለው ክብር ሲሰጡት የሚቆረቁረው ፣ ሌላውንም ለማክበር የሚቸገር ነው ። ከመንግሥተ ሰማያት እንጦሮጦስን ፣ ከአኃዜ መንጦላዕት/መጋረጃ ያዥነት ስደትን የመረጠው ሰይጣን ይባላል ።

ቅዱስ ጳውሎስ ከአንጾኪያ እስከ ሮም ድረስ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት መሥራችና አባት ነው ። በሌላ አነጋገር የዓለም አብያተ ክርስቲያናት አባት ነው ። አጭር ፣ በበሽታ ያደቀቀው ፣ ልብሱ የነተበ መሆኑን ያየ ጳውሎስ ነው ብሎ አይገምትም ነበር ። በሲላስ ጥንካሬ ፣ በማርቆስ መለሎነት በእኔ በጢሞቴዎስ ለጋነት መሐል ፤ አንድ እንደ ማታ ጀምበር ውበቱ የሚናፍቅ ሰው አለ ። ጳውሎስ ሐዋርያ በወርቅ በተሠራ አዳራሽ ፣ በዝሆን ጥርስ በተጌጠ ቤተ መንግሥት የሚኖር አልነበረም ። አንድም ቀን በጌጠኛ መቅደስ አልቀደሰም ። በዋሻና በድሆች ክርስቲያን ቤቶች ቀድሶ አቍርቧል ። ጳውሎስ መንግሥተ ሰማያት የሌለች ያህል በምድር ላይ ገነትን በሕንፃ ልሥራ ብሎ የታገለ አልነበረም ። ብርና ወርቅ የለኝም ብሎ ፈውስ ግን ያለው ሐዋርያ ነበር ። በድህነቱ ኮርቶ የሚኖር መናኝ ነበር ። ብርና ወርቅ ያላቸው ግን ፈውስ የላቸውም ። የሚሰማቸውን አያረጋጉም ። ዓለምን ለመናቅ የሄደው ሕዝብ ፍቅረ ንዋይ አድሮበት ይመለሳል ። በንብረት የሚወዳደር አገልጋይ ሌቦችን ያፈራል ። ጳውሎስ ድንግል ፣ መናኝ እንጂ መሳፍንት አልነበረም ። እንደ ወይዛዝርት በወርቀ ዘቦ የሚኵነሰነስ ፣ እዩኝ ብሎ አደባባዩን የሚሞላ አልነበረም ። የማንንም ሆድ አባብቶ የመዝረፍ ዕቅድ አልነበረውም ። ደቀ መዛሙርቱንም የልመና ስልት አላስጠናም ። ሰውን መውደድ አስተማረ እንጂ ።

ጳውሎስ የተጠጋውን እንደ እሾህ የሚያደማ ፣ እንደ ቆንጥር የሰውን ልብስ ይዞ የሚያበላሽ አልነበረም ። ደመወዝ ነሥቶ ክሰሱኝ ብሎ የሚናገር ሰውም አይደለም ። ሰው እየራበው ይሞታል እንጂ እንዴት ይከስሳል ? አጥሩ የእሳት ፣ በሩ የናስ አልነበረም ። የበሩ መወርወሪያም ከተበላሸ ቆይቷል ። አጥሩም በሩም አንድ ስለ ነበር ሲንኳኳ ቶሎ ይሰማል ። በቀላሉ የሚገኝ ፣ ልጆቹን ከማግኘት የበለጠ ተግባር ያልነበረው አባት ነበር ። እግሮቼ ወደ ጳውሎስ ቤት ይፋጠናሉ ። ያየሁትን የሮምን መውደም ፣ የሰውን በኀዘን መዋጥ ፣ በክርስትናው ላይ የተጋረጠውን አደጋ የምረሳው ጳውሎስ ሲናገር ስሰማ ብቻ ነው ። የአገልጋይ ድምፅ የሞት ሁከትን ጸጥ ያደርጋል ። ሳቁም ያጽናናል ፣ ተግሣጹም ያበረታል ፤ ዓይኑም እጁም ይናገራል ። ጳውሎስ ተቀምጦ ሲያስተምረኝ ብቻ ሳይሆን በሩን ሳንኳኳ እርሱ “አቤት” ቢለኝ ይዤው የመጣሁት ሸክም ይቀለኛል ። ችግሮች ወደ ወዳጅ ስንሄድ ከገለባ ይልቅ ይቀላሉ ። ሰነፍ ነንና ይህን አናደርግም ። ሰነፍ አይጽናናም ።

ይቀጥላል

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 1

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ