የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 10

ድንበር ጠብቆ መኖር

የወጣት አገልጋይ ፈተና

ነገሥታት የቤተ ክርስቲያን ጠላት በነበሩበት ጊዜ ሰማዕታትን አበዙላት ። የቤተ ክርስቲያን ወዳጅ በሆኑ ጊዜ መናፍቃንን አበዙባት ። ቤተ ክርስቲያን ንጉሠ ነገሥት ክርስቶስ የሚያዝዛት በምድርና በሰማይ ያለች ናት ። እርሱ እንደ ራስ ሆኖ በፍቅርና በክብር ያዝዛታል ። ቤተ ክርስቲያንም ራስዋን አክብራ ፣ የአካልነት ግዳጅዋን ትወጣለች ። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ የሥልጣኑ ጠባቂ ሳትሆን የቤተ ክርስቲያን የሥልጣን መሠረት እርሱ ነው ። ሠራዊቱን የሚጠብቅ ድንቅ ንጉሥ ነው ፤ የተሸከሙትን ኪሩቤል የተሸከመ ታላቁ ባለ አልጋ ነው ። እሾም አይል ንጉሥ ፣ አገኝ አይል ባለጠጋ ነው ። ምድራውያን ነገሥታት ግን ለሥልጣናቸው ዘብ ሊያደርጓት ቤተ ክርስቲያንን ይፈልጉታል ። ከትልቁ ንጉሥ አፋትተው የራሳቸው የቤት አሽከር ሊያደርጓት ይመኛሉ ። ከቤተ ክርስቲያን እየበሉ ወደ ነገሥታት የሚውጡ ምንደኞች ረጅም እጅ ሆነው ያስደፍሯታል ። የቤተ ክርስቲያን መሪም ከውስጥ የነገሥታት ወኪልና ወሬ አቀባዮች ፣ ከደጅ ሰይፍና ጎመድ የያዙ ጭፍሮች ያስጨንቁታል ። የቤተ ክርስቲያን ኃይል የምእመናን ቍጥር አይደለም ፣ ተረትቶ የማይገባው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። መሪው ይህን ዓለም የሚያሸንፈው በእምነት ብቻ ነው ። የከበቡትን ሳይሆን የከበቡትን የከበበውን አቅም ያያል ። ቢታሰር ይፈታል ፣ ቢሞት ይቀበራል ፣ አንድ ቀንም ይነሣል ።

ቤተ ክርስቲያንን የሚደፍር ውስጥ አዋቂ ነው ። የሚያውቅ የሚመስለው ግን የማያውቀው ሰው እርሱ ቤተ ክርስቲያንን ደፍሮ ያስደፍራታል ። ምድራዊ ገዥዎችን ክንድ አድርገው ቤተ ክርስቲያንን የሚታገሉ የሳጥናኤል የውስጥ ካድሬዎች ፣ ለመጣ ለሄደ ሲዘፍኑ የሚኖሩ ፣ ይሉኝታ የሌላቸው ፣ የተዛመዳቸው ሲያፍርላቸው እነርሱ ግን ምንም እፍረት የሌላቸው የጉድ ሙዳይ ናቸው ። ንጉሥ ዕጣን ዕጣን ከሸተተ ፣ ካህን ፖለቲካ ፖለቲካ ከሸተተ ነገር ተበላሸ ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚነሡ የሥልጣንና የሀብት ጥያቄዎች ቤተ ክርስቲያንን በዓለማውያን እንድትዳኝ ያደርጓታል ። ቤተ ክርስቲያን የሕግና የፍትሕ መገኛ የሆነው የክርስቶስ አካል ናትና ፍትሕ መንፈሳዊን ማስፈን ፣ ወደ ምድራውያን ፍርድ ቤቶች ጉዳዮች እንዳይሄዱ መከልከል አለባት ። እውነተኛ አባትም ቤተ ክርስቲያን በዓለም ችሎት ፊት ከምትቆም እኔ ሁሉን ጥቅሜን እተዋለሁ ማለት አለበት ። ዛሬም ክርስቶስን በአደባባይ የምናራቁተው በምድራውያን ፍርድ ቤቶች ስንካሰስ ነው ። ይህ ምስክርነታችንን ያበላሻል ። ተአማኒነታችንን ያሳጣል ። ለመካድ በቋፍ የሆነው ሰውም የሩጫ ተኩስ ይሆንለታል ።

ነገሥታትንና ከሃይማኖቱ ውጭ ያሉትን ወገኖች በሚመለከት መሪው መያዝ የሚገባውን አቋም ሐዋርያው እንዲህ ጽፎልኝ ነበር ። “እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ።” (1ጢሞ. 2፡1)። ስለ ሰው ሁሉ ፣ ስለ ነገሥታት በአምልኮ መጽናት ይገባል ። አሊያ ወገን ይዘን ፣ የበለው ጡሩምባ ከነፋን ጸጥና ዝግ ብለን መኖር እንቸገራለን ። የምናገለግላቸው ምእመናንን አደጋ ላይ እንጥላለን ። ስለ ሰው ሁሉ ስንጸልይ ሰዎች ይወዱናል ። መማለድ ትልቅ የፍቅር መግለጫ ነውና ። ነገሥታትም ስማቸውን ጠርተን በቅዳሴው ፣ በመሥዋዕቱ ፣ በአስተብቍዖቱ ስናስባቸው የሚትጸልይላቸውን ቤተ ክርስቲያን ለመጉዳት ይቸገራሉ ። ቢሆንም የቤተ ክርስቲያን መንገድ የመስቀል መንገድ ነውና ሁልጊዜ የመከራ አጀብ አለው ። ዓለም ከምታሳጣን ክርስቶስ የሰጠን ይበልጣል ።

ይህ ሁሉ አሳብ በውስጤ እየተመላለሰ የባሕሩን የየብሱን መንገድ ፈጸምሁ ። አሁን ከጳውሎስ ደጃፍ ላይ “ጢሞቴዎስ ነኝ” ስል ራሴን አገኘሁት ።

ይቀጥላል

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 10

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ