የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 13

መስፈርት የሌለበት ዘመን

(የወጣት አገልጋይ ፈተና)

ወዳጁን ለማግኘት የሚጓዝ እግር በደመና ላይ እንደሚንሳፈፍ ያህል ይሰማዋል ። ሩቅ መንገድ በፍቅር ምክንያት ቅርብ ነው ። ተራራውን ሜዳ ፣ ሸለቆውን ሙሉ የማድረግ አቅም ወትሮም የፍቅር ነው ። ብዙ ዓይነት ፍቅር ባለበት ዓለም ላይ ብዙ ዓይነት ወዳጆችም አሉ ። ወላጆች ፣ አብሮ አደጎች ፣ የሙያ አጋሮች ፣ የትዳር ጓዶች ፣ ልጆች … ወዳጆች ተብለው ይጠራሉ ። የመምህርና የተማሪ ፍቅር ግን ከዚህ ሁሉ ይለያል ፤ ይበልጣልም ። የፍቅሩ መሠረት በሥጋ መወለድ ሳይሆን ከእግዚአብሔር መወለድ ነው ። ግቡም ምድራዊ ርስት ማውረስ ሳይሆን ሰማይ ማድረስ ነው ። ሩቅ መንገድ የሚጓዝ ፍቅር መንፈሳዊ ብቻ ነው ። ምድራዊው ፍቅር ከፊት ወረት ፣ ከኋላ ሞት ይገድበዋል ። ቅዱስ ጳውሎስ በጸሎት ምጥ ፣ በአገልግሎት ጭንቅ የወለደኝ መንፈሳዊ አባት ነው ። እኔ ለኤፌሶን ምእመናን አባት ብሆንም የእኔ አባት ግን እርሱ ነው ። እርሱን ለማግኘት ያውም በመጨረሻው የዕድሜ ዘመኑ ጥሪውን ተቀብዬ ስመጣ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል ። በአንድ ዓይኔ አለቅሳለሁ ፣ መሄጃው ጊዜ ደርሷልና ። ምድር መካሪዋን ስታጣ ትጨነቃለች ። በሁለተኛው ዓይኔ እስቃለሁ ። መምህሬን ላገኝ ነውና ።

ተማሪ መምህሩን በጣም ከመውደዱ የተነሣ የአባቱን ስም በመምህሩ ይቀይራል ። ያማረ ምግብ ሲያገኝ ወጣትነቱና የመብላት ፍላጎቱ ሳያሸንፈው “ይህን ለመምህሬ” ይላል ። የመምህሩን እግር እያጠበ ዘወትር ይመረቃል ። መምህሩንም ሲጠራ “የኔታ” ይላል ፣ የኔ ጌታ ማለት ነው ። ፍቅሩ ታላቅ አክብሮት ያለበት ነው ። ተመርቆ የወጣ እንደሆነ በዓመት አንድና ሁለት ጊዜ የቀድሞ ተማሪዎችን አስተባብሮ ፣ ካገኘው ላይ በረከት ይዞ መምህሩን ይጠይቃል ። መምህሩም ምድራዊ ወገንና ዘመዶቹን ክዶ ተማሪዎቹን ዘመድ አድርጓልና ደስ ይለዋል ። ወጉ ይህ ነው ፤ የመምህርና የተማሪ ወግ የሌለው ዘመን ዘመነ አዳፋ ነው ። ከአባቴ በፊት ነበርሁ የሚል ልጅ በትዕቢት አእምሮውን ያጣ ነው ። በሥጋ መውለድ ልዩ ችሎታ አይደለም ፣ በእውቀት መውለድ ግን ልዩ ተሰጥኦና ትልቅ አባትነትም ነው ። ልደት ያላገኙ አእምሮዎች የገዳይነት ዋሻ ናቸው ። መምህሩ የነፍስ አባት ነውና ነፍስን በእውቀት ይወልዳል ። ሰው ገንዘብ ቢሰጠን ከኪሱ ነው ፣ እውቀት ግን የነፍስ ስጦታ ነውና ከሁሉ ይበልጣል ። መምህራን ክብር ይገባቸዋል ። እንኳን የሰማይን መንገድ ይቅርና “የሮም መንገድ በዚህ በኩል ነው” ያለ ሰው ውለታው አይረሳም ። መምህሩ ሲዋረድ ተማሪ እያነሰ ይመጣል ። ተማሪ ሲጠፋ ትውልድ የጨለማ እስረኛ ይሆናል ። ተማሪ መምህሩን ሲያዋርድ ሰይጣን ታናሽ ወንድም ይሆናል ። መንፈሳውያን መምህራን ክብራቸው ሊመለስ ይገባል። ቀዳሽ ቢቀድስ ፣ ሰባኪ ቢሰብክ ፣ ማኅሌታይ ቢዘምር ምንጩ መምህራን ናቸው ። “ማን ላይ ቆመሽ ፣ ማንን ታሚያለሽ?” እንዲሉ ።

በጉዞዬ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ አገልጋዮች መስፈርት የነገረኝን እያስታወስሁ ነበር ። አገልግሎት መስፈርት የለውም ። አገልጋዮች ግን መስፈርት አላቸው ። መስፈሪያው የእግዚአብሔር ቃል ነው ። በምድራዊ መስፈሪያ ተለክተው ሲታጩ የሚፈጥሩት መደናገር ብዙ ነው ። ቤተ መንግሥቱንና ቤተ ክህነቱን ለማገናኘት ባለ ሁለት መታወቂያ ናቸው ተብለው ሲታጩ የማያቋርጥ ማዕበል በቤተ ክርስቲያን ላይ ያመጣሉ ። አዝማደ መንግሥት ናቸው ተብለው ሲሾሙ ከእግዚአብሔር ይልቅ ጎሣቸውን ያገለግላሉ ። በሰው ታምነው ደረጃውን የወጡ የታመኑበት ሲታመም ፣ እነርሱም ትኩሳት ይጀምራቸዋል ። በወኔና በማስፈራራት ስፍራ ሲሰጣቸው ደጋጎችን ስፍራ ይነሣሉ ። በጉቦና በመማለጃ አባት ልሁን ሲሉ አባትነት ስጦታ እንጂ ግዥ አይደለምና ለብዙዎች መጥፋት ምክንያት ይሆናሉ ። “ነውር ካለባቸው ይታዘዛሉ” ተብለው በማሸማቀቂያ ካርድ ሲሾሙ “ከዚህ በኋላ ማን ይነቀንቀኛል ? ለራሱ ሲል ሁሉም ይጠብቀኛል” ብለው ክፋታቸውን ሕጋዊ ያደርጉታል ። መስፈርት የሌለው ግለሰብ የቆሻሻ መጣያ ነው ። መስፈርት የሌለው አገር ሲመክን የሚኖር ነው ። መስፈርት የሌላት ቤተ ክርስቲያን እንደ ድመት ወልዳ የምትበላ ናት ። መስፈርት ያስፈልጋል ። በእውነት መስፈርት ቢኖር የተገፋው ባለወንበሩ ፣ የተነቀፈው ባለ ሙያው መሆኑ ይታወቅ ነበር ። ቤተ ክርስቲያን ዘመድ ማፍሪያ ፣ የወንዝ ለወንዝ ጨዋታ መናኸሪያ ስትሆን ከነገድ ከቋንቋ የዋጃት ክርስቶስ ያዝናል ። መጥቀምና መጠቃቀም ለቤተ ክርስቲያን የጉዳት ዘመንን ያመጣባታል ። በቤተ ክርስቲያን ለተቸገሩት እርዳታ እንጂ ሥልጣን አይሰጥም ። ላልተማረና መንፈሳዊነት ለሌለው ሥልጣን መስጠት ለእብድ ሰይፍ መስጠት ነው ።

ይህን እያሰብሁ ከሮም ሕንፃዎች ጋር አወራ ነበር ። አዎ መስፈርት ያስፈልጋል ። መስፈርቶቹም ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ ። መስፈርት ሲጠፋ ወጣቱ አገልጋይ መስፈርት በሌላቸው ሰዎች እየታወከ ይመጣል ።

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 13

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ