የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 15

የጳጳስ ክብሩ

(የወጣት አገልጋይ ፈተና)

ጳጳሳትና ዲያቆናት ሲሾሙ የራሱ የሆነ መስፈርት አለው ። ዲቁና የሁሉ መነሻ ነውና መስፈርቱ ጠበቅ ማለት አለበት ። አሊያ ድንቁርና አድጎ ባለ ግዛት ይሆናል ። ጵጵስና ስሙ ሹመት ይሁን እንጂ በደሙ ፈሳሽነት ላዳነን ጌታ የሚደረግ የፍቅር አገልግሎት ነው ። ጳጳሳት መንጋውን ለሰማዕትነት የሚያዘጋጁ ፣ እኔ ጋ እስኪደርስ ብዙ ሕዝብ ያልቃል ብለው የሚተምኑ ፣ ጦር እያዘመቱ በሌላው ነፍስ የሚኖሩ አይደሉም ። ጳጳሳት መግለጫ የሚሰጡ ፣ ምእመን ሲሞት ሬሳ የሚቆጥሩ አይደሉም ። እረኛው ከመንጋው ፊት ሁኖ መሥዋዕትነት ይከፍላል ። በደግ ዘመን እረኛው ለመንጋው ይሞታል ፤ በክፉ ዘመን መንጋው ለእረኛው ይሞታል ። እረኛ ነፍሱን አስይዞ ካልገባ እረኛ መሆን አይችልም ። ጳጳስ የሚሆን ሕይወቱ በሚያገለግለው ሕዝብ ምስክርነት ያገኘ መሆን አለበት ። አሊያ በምእመናን መካከል መለያየትና ሐሜት ይነግሣል ። በቃል ኪዳን የጸና ወዳጅነቱ ቋሚ ፣ ወረትን ድል የነሣ መሆን አለበት ። ስሜታዊነትን ያሸነፈ ፣ ተናግሮ የሚያስብ ሳይሆን አስቦ የሚናገር መሆን አለበት ። ፍላጎቱን ያሸነፈ ፣ ለኑሮው ለከት ያለው መሆን ያሻዋል ። እንደ መናኝ እንጂ እንደ መሳፍንት የሚኖር ሊሆን አይገባውም ። መዋያውም የድሆች ሰፈር እንጂ የነገሥታት ማዕድ አይደለም ። ድሀውን ድሀ ቄስ እንዲያገለግል ፣ ባለጠጋውን ጳጳስ እንዲባርክ የቤተ ክርስቲያን ወግ አይደለም ። “ተወልዶ ብልጫ” እንደሌለ ሁሉ ውሉደ እግዚአብሔር የሆኑ ምእመናን ሁሉም እኩል ናቸው ።

ጳጳስ የሚሆን ፍርድ የሚያውቅ ፣ የድሀ እንባ ሲፈስስ የክርስቶስ ደም እንደ ፈሰሰ ያህል የሚሰማው መሆን አለበት ። የሰውን ደመወዝ እያገደ ክሰሱኝ የሚል መሆን የለበትም ። ሰው የሚከሰው እየበላ እንጂ እየሞተ አይደለምና ደመወዝ አግዶ ክሰሰኝ አይባልም ። ከሩቅ ለሚመጡት የአባትነቱን ፍትሕ ለሚፈልጉት አብሮ ማዕድ መቅረብ ፣ በእንግድነት መቀበል ይገባዋል ። ፍትሕን ሊያውቅ ድሀ ተበደለ ብሎ ሊጮኽ ፣ ነገሥታትን ሊያቀና ፣ መኰንኖችን ተዉ ሊል ያስፈልገዋል ። በገንዘብ ፣ በጥላቻ ፣ በጎሠኝነት ፣ በፖለቲካ ወጥመድ ተይዞ ደርሶ አውጋዥ መሆን የለበትም ። ከንቱ ግዝት ራስን እንጂ ማንንም አያስርም ። ማስተማር እንጂ መራገም የቤተ ክርስቲያን ሥራ አይደለም ። ቤተ ክርስቲያን በር ከፍታ የምታስገባ እንጂ በር ከፍታ የምታስወጣ አይደለችም ። ጳጳስ የሚሆን ይህን ሁሉ ማወቅ አለበት ። እንደ ቆላ ቄስ ለጤና አዳሙም ፣ ለእንስላሉም ገዝቻለሁ እያለ ግዝትንና ውግዘትን የሚያረክስ መሆን የለበትም ። መናፍቃንን ለማስተማር ፣ ለመጠየቅ ብዙ ያነበበ መሆን አለበት ። አሊያ “እኛ አንልም” በሚል ፈሊጥ ብቻ ስሑታንን መመለስና መገሠጽ አይችልም ።

ጳጳስ አዲስ ዘመንና አዲስ ትውልድን የሚያውቅና የሚቀበል መሆን አለበት ። አዲስ ትውልድ ነገረ መለኮትን ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ፣ ትውፊተ አበውን ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክን ፣ አገር መውደድን እንዲማር ማቀድ ፣ የክህነት ወገንን ማብዛት አለበት ። የአበውን ሃይማኖት በትውልድ ቋንቋ መግለጥ አለበት ። ይልቁንም ቀጣዩ ዘመን ምን ሊሆን ይችላል ? በማለት ቀድሞ መዘጋጀት ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከፈተና መጋረድ ያስፈልገዋል እንጂ እየተቃጠሉ አይሸተኝም የሚል መሆን በፍጹም አይገባውም ። እረኛ አሻግሮ ያያልና ። ጳጳስ ዋነኛ ሥራው ገንዘብ መቆጣጠር ፣ ነገር ሲዳኙ መዋል ሳይሆን ማስተማርና የክህነትን ግዛት ማስፋት ነው ። የሚያስተምር ነውና አቅም እንዳያንሰው ራሱን መጠበቅ ፣ ምግብ መመገብ አለበት ። ከሁሉ ሁሉ ማስተማር ይጎዳል ። ስለዚህ ጳጳሱ ጠገን ያስፈልገዋል ። የሚያሰክር መጠጥ ክብርን ይነካል ። ጠጅ የነገሥታት መጠጥ ነው ። ጠጅ እግር ይይዛል ። ንጉሥ በስካር ተይዞ ፣ በዘፈን ተማርኮ ተነሥቼ ልጨፍር እንዳይል ጠጁ እግሩን አስሮ ያስቀምጠዋል ። እድምተኛው ሲወጣ ደግፈው ያስገቡታል ። ጳጳስ ፈጽሞ መጠጣት የለበትም ። መነኮስ የሆነ ከዓለም ተለየ የሚባለው ከሚያሰክር መጠጥ ሲለይ ነው ። መጠጥ ማንን አስከብሮ ያውቃልና ጳጳስ መጠጥን ይወድዳል !

ጳጳስ ገራም ፣ ልበ ሰፊ ፣ ነገር አላፊ መሆን አለበት ። እንደ ነሐሴ ዝናብ እኝኝ የሚል መሆን የለበትም ። ትልቅ ኃላፊነት አለበትና በትንንሽ ጉዳይ አእምሮውና ጊዜው መያዝ የለበትም ። መመሪያ መስጠት እንጂ መነዛነዝ አያስፈልገውም ። ክብረ ነክ ነውና ። ያዘዘው መፈጸሙን ማየት አለበት ። ትእዛዝ ተቀባይ ከሌለው ፈጥኖ እርምጃ መውሰድ ያስፈልገዋል ። ፍቅረ ንዋይን ማሸነፍ ያሻዋል ። ስለተጎዱት ማሰብ ይገባዋል ።

እኔ ጢሞቴዎስ ወደ ጳውሎስ ሐዋርያ ስሄድ መስፈርት የሌለው የጳጳሳት ሹመት ፣ ቤተ ክርስቲያንን በራስዋ ልጆች እንድትፈርስ ያደርጋታል የሚል አሳብ ይዞኝ ነበር ። አበ ብዙኃን የሚሆነው ፣ አባትነትን በጸጋ የሚቀበለው ጳጳስ ጠባብ መሆን አይገባውም ። መንበሩ የመከራ እንጂ የምቾት አይደለምና መከራ ከሌለ ምን ችግር ገጥሞኛል ? ማለት አለበት ።

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 15

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ