የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 5

ኑፋቄን እንዴት እንዋጋ ?

ልዩ ትምህርት በአበው ፣ በነቢያት ፣ በሐዋርያት ፣ በመጻሕፍት የማይታወቅ ነው ። ልዩ ትምህርት ኑፋቄ ነው ። እንክርዳድ የተቀላቀለ ስንዴ ነው ። ሰው በዝሙት ፣ በስርቆት መፈተንን ከባድ አድርጎ ያየዋል ። የኑፋቄ ፈተና ግን ከዚህ የባሰ ነው ። ኑፋቄ የእግዚአብሔርን ትክክለኛ መልክ ይወስድብናል ። የእረኞቻችንን መልካምነት ያጠለሽብናል ። ጸሎታችንን እምነት አልባ ያደርገዋል ። የግላችንን የሥነ መግባር መርሖ እንድናወጣ ፣ ጆሮ ነሥቶ አፍ ብቻ ያደርገናል ። ከዚህ ለመውጣት የጠራውን ምንጭ ፣ ነገረ እግዚአብሔርን ከዓይናማ መምህራን መማር ፣ በጸሎት መማጸን ፣ እምነታችንን ሊያጠናክሩ ከሚችሉ ሰዎች ጋር መዋል ፣ የተቀደሱ መጻሕፍትን ማንበብ ፣ የበረቱ አባቶችን የጸሎት እርዳታ መጠየቅ ይገባል ።

ኑፋቄ የሚያምሳት ቤተ ክርስቲያን ወዳጅና ጠላትዋን መለየት ያቅታታል ። እረኛውም ልቡ በኀዘን ፣ አእምሮው በጥርጣሬ ይመታል ። ከፍተኛ ቅራኔ በምእመናን መካከል ይፈጠራል ። መከፋፋትና መጠፋፋት ይመጣል ። በዚህ ውስጥ እረኛው ወይም ወጣቱ አገልጋይ ትዕግሥትን ገንዘብ ማድረግ አለበት ። ማስተማር እንጂ ማሳመን የእርሱ ድርሻ አለመሆኑን አምኖ መረጋጋት ፣ ዛሬ የተገፋው እውነት አንድ ቀን እንደሚረታ መገንዘብ አለበት ። ሰድበውት የሄዱት አልቅሰው እንደሚመጡ እርግጠኛ መሆን አለበት ። ውሸት ሁልጊዜ ጥላ አይሆንምና ።

ልዩ ትምህርት የሚመጣበት ምክንያት የመጀመሪያው ሰርገው በሚገቡ የኑፋቄ አራማጆች ነው ። ሰይጣን ከቤተ ክርስቲያን ማስወጣት ብቻ ሳይሆን ወደ ቤተ ክርስቲያንም አስርጎ ያስገባል ። የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመጉዳት የጥርጣሬ ሠራዊቱን ያዘምታል ። ሁለተኛው መምህር በሌለበት የሚደረጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለኑፋቄ መነሻ ይሆናሉ ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት መልካም ቢሆንም ስንስት የሚመልሱን መምህራን ቢኖሩ የተሻለ ነው (የሐዋ. 8፡30-31)። እግዚአብሔር መጽሐፉን በመንፈሱ እንዳጻፈ ፣ በመንፈሱም ይተረጕምልናል ። ለማጻፍ ሰዎችን እንደ ተጠቀመ ለመተርጎምም መምህራንን ይጠቀማል ። የዓይናማ መምህራን የትርጓሜ መጻሕፍትም ጥናታችንን ሊያግዙ ይችላሉ ። ሦስተኛው የስህተት ትምህርት መግቢያው የሰይጣን ፈተና ነው ። ሰይጣን በስንዴው ላይ እንክርዳድ ፣ በእምነት ላይ ጥርጣሬ መንዛት ልማዱ ነው ። በርኵስ መንፈስ ውጊያ ውስጥ የሚያልፉ የኑፋቄ ፈተና ይገጥማቸዋል ። የሥላሴን ምሥጢር ፣ የክርስቶስን ጌትነት ፣ የምሥጢራትን ክብረት ለመረዳት ይቸገራሉ ። አራተኛው የስህተት ትምህርት መገኛ ሥልጣንና ገንዘብ ፈላጊነት ነው ። በስህተት ትምህርት መንጋውን ነጥቆ ፣ እረኛውን በማባረር ስፍራውን መቆጣጠር የሚፈልጉ ፣ አሊያም በጎችን ሰርቀው የራሳቸውን ማኅበር ሊመሠርቱ የሚሹ መሣሪያ የሚያደርጉት ልዩ ትምህርትን ነው ። ልዩ መባሉም በነቢያት ፣ በሐዋርያት ፣ በሊቃውንትና በቤተ ክርስቲያን ጉዞ የማይታወቁ ስለሆኑ ነው ።

ልዩ ትምህርትን ያመጡ ሰዎች ሲገኙ ወጣቱ አገልጋይ ማስተዋል ያለበት ነገር አለ ። ልዩ ትምህርት የመሰለው እርሱ ስላልተማረ ወይም ስላላወቀው ነው ወይስ በእርግጥም ልዩ ትምህርት ነው ወይ ? ብሎ መጠየቅ አለበት ። ብዙዎች ሰምተው የማያውቁተን እውነት ሲሰሙ ውሸት ይመስላቸዋል ። በሁለተኛ ደረጃ የልዩ ትምህርት አምጪዎቹን በግል ጠርቶ ማነጋገር ያስፈልጋል ። ከባለቤቱ ሳይሰሙ ፍርድ መስጠት እንኳን በመንፈሳዊ በዓለምም ችሎት የለም ። አንዳንድ ጊዜ በቅናት ፣ በምቀኝነት ለሰው ስም መስጠት አለና ። የሚፈሩትን ሰው መናፍቅ ማለት የተለመደ ነው ። በጉቦ ማውገዝም የሰው ጠባይ ነው ። አዎ ውግዘት በፖስታ አይላክም ። ደርሶ ማውገዝ የሚወዱ በመጨረሻ እርስ በርስ ይወጋገዛሉ ። ውግዘት ለቤተ ክርስቲያን የጭንቅ መፍትሔዋ እንጂ ደስ እያላት የምታደርገው አይደለም ።

ያ ልዩ ትምህርት የያዘው ሰውም እንደ ጠላት ሳይሆን በእምነት እንደ ደከመ ሰው ታይቶ እርዳታ ሊደረግለት ይገባዋል ። የያዘውን ትምህርት እንዲገነዘበው ጊዜ መስጠት ፣ እንዲመለስም መማጸን ይገባል ። አንዱ ሰው አንድ አይደለምና ብዙዎችን ይዞ ይሄዳል ። ከስህተቱ አልመለስ ብሎ ፣ ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን የማሰላሰያ ጊዜ ንቆ በክፋቱ የበረታ እንደሆነ ሊለዩት ይገባል ። ይህ መለየትም እስኪመለስ እንጂ ጨርሶ እንዲጠፋ አይደለም ። አካለ ክርስቶስ የሆነች ቤተ ክርስቲያን በሌሎች መጥፋት አትደሰትምና ። የውግዘት ዓላማው በቀል ፣ በርን መዝጋት ሳይሆን በፍቅር መቅጣት ነው ።

የሚሆነው ሲሆን የነበረ ነውና ልዩ ትምህርት ሲነሣ መደናገር አይገባም ። የደነገጠ መሪ ወዳጆቹንም ያጠፋል ። መሪ ሲደነግጥ ፣ አውሬ ሲቆስል እርምጃው ልክ የለውም ። ከዚሁ ጋር የቤተ ክርስቲያን አንድነት ዶግማ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ። አንድነትን የሚጎዳ ነገር ሲመጣ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ። ነቢዩ ኢሳይያስ 700 ዓመት አሻግሮ ትንቢት ተናገረ። ቤተ ክርስቲያን ሰባት መቶ ዓመት አሻግራ የምታይና የምትዘጋጅ ናት ። የምታየው በዓይነ መለኮት ነውና ።

አገልጋይ ሆይ ! በውስጥ ከስህተት አስተማሪዎች ፣ በውጭ ከአረማውያን ጋር ትግል አለብህና እግዚአብሔር ያጽናህ !

ይቀጥላል

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 5

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ