የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጢሞቴዎስ ነኝ (2)

(የወጣት አገልጋይ ፈተና)

የሮም መንገዶች ጭርታ ነግሦባቸዋል ። ኔሮን ቄሣር ቤተ መንግሥቱን ለመሥራት ብሎ የሮምን ከተማ ከግማሽ በላይ በእሳት አጋይቶት ነበር ። የዘመናት ጥበብ ፣ አስደናቂ ኪነ ሕንፃዎች ፣ አብያተ ጣዖታት ፣ አብያተ መንግሥታት ወደሙ ። “የኔሮን እሳት” ተብሎ የሚጠራው ይህን ውድመት ንጉሡ ተራራ ላይ ሁኖ በደስታ ይመለከት ነበር ። ኋላ ላይ የመጣው ሰውን እያቃጠሉ መደሰት በዚህ የጀመረ ነበር ። ያቺ ውብ ከተማ ፣ እንደ ቆንጆ አሮጊት ውበትዋ በሩቅ የሚፈለግ መናገሻ ዛሬ በቁሟ ተለብልባ ነበር ። በዓለማችን ላይ ያለች ሰፊ ኩሽና ሆነች ፣ በጭስ ጠቆረች ። እሳት በልቶ በቃኝ ማለት ይቸገራልና ሺህ ዓመታት ከሰልና አመድ ሁነው ፣ ታሪክ እያለ እንደሌለ ሁና ነበር ። ፍላጎት ድንበር ፣ ቅምጥልነትም ልክ ሲያጣ ከተማ ምድጃ ፣ አእላፋትም ማገዶ ይሆናሉ ። ኔሮን የግል ችግሩ ዓለምን አስቸግሮ ነበር ። ከኢየሩሳሌም እስከ ቍስጥንጥንያ ፤ ከአንጾኪያ እስከ ሮም መንግሥቱ እየተናወጠ ነበር ። ሞቶም ያዝዝ ፣ አብዶም ይገዛ ነበር ። እልፍኝ ለመሥራት ከተማን አቃጠለ ፣ እርሱ ለመኖር ብዙዎችን አሳዘነ ። የጭምትነቱ ዘመን ለዐሥር ዓመታት ነበረ ። የማይረካው ፍላጎቱ መወራጨትን ፣ ወሰን አልባነቱም ጨካኝነትን አመጣበት ።

በሮም መቃጠል ምክንያት ሕዝቡ ሊበላው ተነሣ ። የሕዝቡን ቍጣ ለማብረድ የነበረው አንድ መንገድ ክርስቲያኖችን ጭዳ ማድረግ ነበር ። የሮምን ከተማ ያቃጠሉት ክርስቲያኖች ናቸው ብሎ ለሕዝቡ ጠላት ፈጠረላቸው ። አምባገነን ነውና ጠላት ካልፈጠረ የሚኖር አይመስለውም ነበር ። ሕዝቡም እብደቱን ቢያውቀውም ስማው ተብሎ የተፈረደበት ያህል ምክንያቱን ተቀበለው ። ሕዝቡ ጋ ሲደርስም ሁለት ዓይነት መልክ ፈጠረ ። አንደኛው ቡድን ክርስቲያኖች አቃጠሉት ሲል ፤ ሁለተኛው ደግሞ ክርስቲያኖች ባሕላችንንና አማልክቶቻችንን በማሳዘናቸው ከተማዋ በአማልክት ቍጣ ፈረሰች ማለት ጀመረ ። አርእስተ ዜናውን ከሰጡት ብዙኃኑ ወገን ዝርዝር ዜናውን ያስተነትነዋል ። እርካታ ያጣ አባወራ ልጆቹን እያስራበ ሁለት ትዳር ይመሠርታል ። እርካታ ያጣ ካህን በሐሰተኛ ትንቢትና ፈውስ ሕዝብን አስከፍሎ ያሳብደዋል ። እርካታ ያጣ መኰንንም ሁሉም አልቆ እኔ ልኑር ያሰኘዋል ።

አንዳንዴ ሕዝብ እንደ መስኖ ውኃ ወደ ቀየሱት ይፈስሳል ። ስለዚህ ከኔሮን ጋር በመግደል ተባባሪ ሆነ ። ሮም ስደርስ ይህ ሁሉ ጥላ አጥልቶባት ነበር ። ጳውሎስ ያዘዘኝን የብራና መጻሕፍት በጀርባዬ ተሸክሜ በጎዳና ላይ ብቻዬን እሄዳለሁ (2ጢሞ. 4 ፡ 13) ። ቀጥሎ የሚሰማኝ የራሴው የእግር ኮቴ ብቻ ነው ። ጸጥታው ምቾት የወለደው ሳይሆን ፍርሃት ያመጣው ነበር ። ሁለት ዓይነት ጸጥታ አለ ። የልብ ጽሞና ያለበት የአካባቢ ጸጥታ የመጀመሪያው ሲሆን ፤ የሰው ረሀብ የወለደው ፣ ወገን ወገኑን ፈርቶ እቤቱ የሚቀመጥበት ፣ የተሸበረ ልብ የሚወልደው የአካባቢ ጸጥታ ሁለተኛው ነው ። ሰላማዊ የሆነ ጸጥታ ለጸሎት ይረዳል ። ጎዳናውን ሁሉ ከጌታ ጋር እያወሩ ለመሄድ ከጸሎት እልፍኝ በላይ ይረዳል ። ክርስቲያን በመልካሙ ጊዜ ከመጸለይ ፣ በክፉውም ጊዜ ተግቶ ከመጸለይ ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም ። የመግደል ድፍረት ባይኖረውም ፣ የመሞት አቅም ግን አለው ። ሮም ውበትዋ አሮጌነትዋ ነበር ። አሮጌነት ሁሉ ማስጠላት ፣ አዲስነት ሁሉ ማማርም አይደለም ። ኔሮን ግን የእሳት እራት አደረጋት ። እሳት ቢበላም ሆድ ስለሌለው በቃኝ አይልም ።

ዋርካ ምን ያፈራል ? ብለው ሳይጠይቁ ፣
ዋንዛ ምን ያፈራል ? ብለው ሳይጠይቁ ፣
ሾላ ምን ያፈራል ? ብለው ሳይጠይቁ ፤
ቆርጠው ፣ ቆርጠው ጣሉት እነ ጣዕም አያውቁ ።

የሮም ሕዝብም ንጉሡን ቢጠላውም ክርስቲያኖችን በማሳደድ ግን ተባበረው ። የሰማው ምክንያት ባያሳምንም እመን ተብሎ የተፈረደበት ያህል ወንጌላውያንን ለማጥፋት ዘመተ ። እኔ ሮም ስደርስ ሁሉም የፈራበት ጊዜ ነበር ። ንጉሡ በሠራዊት መሐል ሁኖ ፈርቷል ። ሕዝቡ ባለ አገር ቢሆንም አገር ያመለጠው ያህል ፈርቷል ። ክርስቲያኖችም ወደ ካታኮምፕ ዋሻ ገብተዋል ። ጳውሎስ ግን ለክርስቶስ የሚሞትበትን ቀን እንደሚሞሸርበት ቀን ይናፍቀው ነበር ። ያለ ጌታ ከመኖር በጌታ መሞት ደስተኛ ያደርጋልና ።

ይህን ሁሉ እያሰብሁ ሐዋርያው ጳውሎስ የተከራየው ቤት ደጃፍ ላይ ደረስሁ ። “ማነው ?” ሲለኝ እኔም “ጢሞቴዎስ ነኝ” አልኩት ። በልቤ ያለውን ሁሉ ለማውራት ጓጉቻለሁ ። ከመጣሁበት መንገድ ፣ በሩ እስኪከፈት ያለው ደቂቃ ራቀብኝ ። ይሁና ! ሰው ሲገኝ እናወራዋለና !

ይቀጥላል

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 2

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 14 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ