የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጢሞቴዎስ ነኝ (3)

(የወጣት አገልጋይ ፈተና)

የሐዋርያው ጳውሎስ ደጃፍ ላይ ስደርስ በብዙ አሳቦች ልቤ ይንገላታ ነበር ። ወጣት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ስለሆንሁ አብዛኛው ሰው የዕድሜዬን ትንሽነት እንጂ የጸጋውን ትልቅነት አያይም ። እግዚአብሔር በደካሞች የሚጠቀም ትልቅ አምላክ ነው ። ትልልቆች እያሉም ትንንሾችን የሚመርጥ አምላክ ነው ። ቃየን ታላቅ ሳለ አቤልን ፣ እስማኤል ሳለ ይስሐቅን ፣ ዔሣው ሳለ ያዕቆብን ፣ ሮቤል ሳለ ዮሴፍን ፣ ኤልያብ ሳለ ዳዊትን የመረጠ አምላክ አሠራሩ ድንቅ ነው ። ምንም እንኳ የቤተ ክርስቲያን መሪ ጳጳስ ብሆንም ሰዎች በቍጣ የሚፈልጉትን እንድፈጽም ያስገድዱኝ ነበር ። ቍጣ ሰዎችን የራሳቸውን ሐሰት እውነት ለማድረግ የሚጠቀሙበት ፊት መሪ ኃይላቸው ነው ። ለቍጣቸው ቍጣን ስመልስ በእኔ ስህተት ውስጥ ለመደበቅ ይሞክራሉ ። የሰዎችን ቍጣ በሚመለከት ብዙ ዓይነት አሳብ በውስጤ ይመላለሳል ። ሰዎች “ተናግሬ ማሳመን አልችልም” ብለው ሲያስቡ ፣ ሌሎች ከቀረቡአቸው ባዶነታቸውን የሚያዩ ሲመስላቸው ፣ ልዩ አሳብ የሚሰጣቸውን እንደ ጠላት ማየት ሲጀምሩ ፣ የብሶትና እኔ ትንሽ ነኝ የሚል ስሜት ሲያዳብሩ ፣ ወስነው ከሰዎች ጋር ሲወያዩ ፣ ተቃውሞን መቋቋም ሲከብዳቸው ቍጠኛ ይሆናሉ ። አስቀድሞ መቆጣት ሰዎችን አስደንግጦ የፈለጉትን ነገር አምጡ ለማለት ይረዳል ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ ።

አንዳንዶች የሚቆጡት ይችለኛል ብለው የሚያስቡት ሰው ላይ ነው ። ሌላው አናድዶአቸው እኔ ጋ ሲቆጡ እርሱ ይሸከመኛል ብለው እንደ መጡ ይገባኛል ። እሳትን በእሳት ማጥፋት አይቻልምና ለመቋቋም እሞክራለሁ ። በታሪክ ውስጥ ትዕግሥት አጸጸተ ተብሎ ተነግሮ አያውቅም ። ትዕቢትን በትሕትና ፣ ፍቅረ ንዋይን በጸሊዐ ንዋይ ልንዋጋ እንችላለን ። ሁሉን ፈተና ግን በትዕግሥት እናልፋለን ። የትዕግሥታችን መነሻው ፍቅር ከሆነ ፣ በሰዎች መለወጥ ተስፋ እናደርጋለን ፣ የትዕግሥታችን መነሻ ማመቅ ከሆነ ውስጣችነ ተቃጥሎ ያልቃል ። ወጣት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይን አንዳንድ የምግባር ችግር ያለባቸው ሰዎች ቆጣ በማለት አቅሙን ለመነቅነቅና ለመፈተሽ ይሞክራሉ ። ይህ ሲገጥመኝ ጸንቼ በመቆም ፣ ያሉበትን አድራሻ እንዲያውቁት አደርጋለሁ ። ትዕግሥት ፈሪነት ሳይሆን የልብ ስፋት መሆኑን እንዲያውቁት እፈልጋለሁ ። ሽማግሌዎችም የሚቆጡት እኛ ያልነው ብቻ ይሁን በማለት ነው ። ወጣቶች ሽማግሌ እንደሚሆኑ ረስተው ግፍ ያስቀምጣሉ ፣ ሽማግሌዎች ወጣት እንደ ነበሩ ረስተው መፍረድ ያበዛሉ ። በዚህ ሁሉ ውስጥ አገልጋዩ በትዕግሥት መገላገል አለበት ። ቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ ናትና ችግሯ በቤተሰብ ጉባዔ ማለቅ አለበት ። የቤተ ክርስቲያንን ምሥጢር ወደ ዓለም ያወጣ ሰው ክርስቶስን በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ ይሰቅለዋል ። ሊሰድበን አሰፍስፎ ባለው ዓለም ላይ የዘለፋ ርእስ ማበደር ከእኛ የራቀ ይሁን !

የሐዋርያውን ደጃፍ እያንኳኳሁ ሳለሁ የሞት ፍርደኛ መሆኑን አሰብሁ ። ዓለም አንድን ድንግል አንድን መነኩሴ እንዴት ትገድላለች ? ብዬ ማሰብ ጀመርሁ ። መነኮሳት ሞተናል ብለው ከዚህ ዓለም የተለዩ ናቸው ። የሞተን ታዲያ እንዴት እንገድለዋለን ? መነኩሴ ሀብትን ፣ ውርስን ፣ ሥልጣንን አልፈልግም ብሎ ፣ ምሎ በቃል ኪዳን የተለየን ነው ። ከእኛ ምንም የማይፈልገውን ፣ በፈቃዱ ድሀ የሆነውን መነኩሴ በሙሉ ዓይናችን ማየት እንኳ ነውር ነው ። ደግሞም የተከለከለውን ሳይሆን የተፈቀደውን እንኳ ትቶ ራሱን ብሑት ብቸኛ አድርጎ ፣ በጾምና በጸሎት ተወስኖ የሚኖርን መነኮስ ለሞት ማጨት የግፍ ግፍ ነው ። እኛ የማንፈልገውን ጫካ ቤቱ ፣ የማንበላውን ቅጠል ምግቡ አድርጎ የሚኖረውን ፣ በመካነ አራዊት በአጥር ለማየት የምንፈራቸውን አራዊት በዓይኑ እያየ ፣ ግርማ አራዊትን የታገሠውን ፣ ዓለምን በጸሎት የሚጠብቀውን ፣ በፈቃዱ የክርስቶስ እስር የሆነውን መነኮስ መግደል ትልቅ ዕዳ ለዓለም የሚያመጣ ነው።

የአምናን ቀን አማሁት ለአፌ ልጓም የለው ፣
መጣ የዘንድሮ እጅ እግር የሌለው ፤

መነኮሳት ዘማውያንን በምርጫቸው ይገሥጻሉ ። እነርሱን ባየን ጊዜ በአንድ መርጋት አቅቶን ከሆነ ፣ ስለ ክርስቶስ ፍቅር ከሴት ርቆ ፣ ንጽሕ ጠብቆ መኖር ይቻላል ለካ የምንልባቸው ፣ ልካችንን የሚያሳዩን መስተዋት ናቸው ። እነርሱ አባትና እናታቸውን የተዉ በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን ሁሉም ነገራቸው ናት ። ቤተ ክርስቲያን ሰጎን እንቁላልዋን ነቅታ እንደምትጠብቅ መነኮሳትን መጠበቅ አለባት ። ቤተ ክርስቲያን ለመነኮሳት እናት ብቻ ሳትሆን ልጅም ናት ። እነዚህን የክርስቶስ እጮኞች ለአደጋ የጣለች ቤተ ክርስቲያን ነገ የሚረከባት ትውልድ ፣ የሚጠብቃት መንፈሳዊ ወታደር አታገኝም ። ብሉያት በሐዲሳት ፣ ሐዲሳት በሊቃውንት ይተረጎማሉ ። ሊቃውንት ያልተረጎሙትን መነኮሳት በሕይወታቸው ይተረጉሙታል ። እናት ስትሞት ጎጆውም ይሞታል ። መነኮሳት ሲሞቱ ገዳማት ይሞታሉ ። ገዳማት ሲሞቱ ጥበብ መንፈሳዊ አብሮ ይሞታል ። መነኩሴ እንዴት ይገደላል ? የሞተን መግደልስ ምን ይባላል ?

ይቀጥላል

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 3

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ