“ምግብን እንደ መድኃኒት ውሰዱ ፣ አሊያ መድኃኒትን እንደ ምግብ ትወስዳላችሁ ።” /ሲቲቭ ጆብስ/
ሲቲቭ ጆብስ የአፕል ኩባንያ መሥራች ነው ። ሀብቱ እጅግ በርካታና የዓለምን የሥልጣኔ ሂደት ያፋጠነ አዋቂ ሰው ነው ። ይህ ሰው ብዙ ሀብቱ ከሞት አላዳነውም ። ለበሽታውም የሚታመምለት ቤዛ መቅጠር አልቻለም ። በሽታና ሞትን የሚጋራ ሠራተኛ መቅጠር አይቻልም ። በተወለደ በ56 ዓመቱ በጣፊያ ካንሰር ሞተ ። መስከረም 24 ቀን 2004 ዓ.ም ይህ ሰው መሞቱ ለዓለም ትልቅ ዜና ነበር ። ሊሞት በተቃረበበት ሰዓት ያሰማው ኑዛዜ የዓለምን ከንቱነት የሚያጋልጥ ነበር ። ታዲያ ስቲቭ ጆብስ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ምግብን እንደ መድኃኒት ውሰዱ ፣ አሊያ መድኃኒትን እንደ ምግብ ትወስዳላችሁ ።”
የሰው ልጅ በምጥ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በሕመም ይህን ዓለም ይሰናበታል ። ሕይወት ግን የእግዚአብሔር ዕቅድ ናትና አስደሳች ናት ። ሰው ለመሆን ለእግዚአብሔር አሳብ አቅርበን ወደዚህ ዓለም አልመጣንም ። ይህን ዓለም ለቀን ስንሄድም ለራሳችን ደወል ደውለን ሳይሆን ና ተብለን ተጠርተን ነው ። ሞትን ስናስብ እግዚአብሔር ያስቀመጠውን የማይረሳ አምላክ መሆኑን ያስታውሰናል ። “ያዕቆብም ለፈርዖን አለው፡- የእንግድነቴ ዘመን መቶ ሠላሳ ዓመት ነው የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ሆኑብኝ፥ አባቶቼ በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያህሉም።” ዘፍ. 74፡9። ታላቁ አባት ያዕቆብ 130 ዓመት ትንሽ ነው ማለቱ አይደለም ። በርግጥ ከአባቶቹ አንጻር አነስተኛ ነው ። ያዕቆብ ግን ዘመኑን የፈጸመው በስጋትና በፍርሃት ነበር ። ሃያ ዓመት በግ በመጠበቅ ያጠፋ ሰው ነው ። ለታላቅ ዓላማ ተጠርቶ በግ በመጠበቅ ሃያ ዓመትን አጠፋ ። እየበላ ይርበው የነበረ ፣ የሚወደውን ለማግኘት የማይወደውን የሚዛመድ ፣ የገዛ ልጆቹ ጥያቄ የሆኑበት ፣ ተስሎ ያገኘው ነገር እርካታውን ያጠፋበት ፣ የእግዚአብሔር የሆነውን በረከት ሳይሆን ራሱን እግዚአብሔር በመጨረሻ የተመኘ ሰው ነው ። አሁን ደግሞ በረሀብ ምክንያት ወደ ግብጽ ወርዶ ፣ ሞተ የተባለው ልጁ ሕያው ሆኖ አገኘው ። ያዕቆብ በሐሰተኛ መርዶ እውነተኛ ልቅሶ ሲያለቅስ ለአሥራ ሦስት ዓመታት አሳለፈ ። ልቅሶውን የፈበረኩት ልጆቹ ነበር ። በአባታቸው ልቅሶ የሚደሰቱ ልጆች የወለደ ፣ የልጅ ባላጋራ የገጠመው ምስኪን ሰው ነበር ። በርግጥም ያዕቆብ ገና በእናቱ ቤት እያለ ሳሎኑን በፍርሃት አይቶት የማያውቅ በጓዳ የኖረ ወጣት ነበረ ። እግዚአብሔርን ለመቅደም ብሎ በቀየሰውና በተቀየሰለት መንገድ ስደት ትርፉ የሆነ ፣ በይሉኝታ ብቻውን የተጎዳ ሰዎች መከራውን ያልተካፈሉት ፣ ዘመኑን በሙሉ ወንድሜ ይገድለኛል እያለ ተሳቅቆ የኖረ ገራገር ሰው ነው ። የአባቱን ርግማን የፈራ ፣ የእናቱ ናፍቆት ያስጨነቀው ፣ የሸሸበት አጎቱ አሽከር ያደረገው ፣ የአማች ብልጠት ዘመኑን የጨረሰበት ፣ በሚስቱ ራሔል ሞት የተሰበረ ፣ ቢንያምን እያየው ቢሞትስ እያለ የተጨነቀ ፣ ልጆቹ ተጣልተው ሲመጡ አገሬው ቢወረኝስ ? በማለት የተንቀጠቀጠ ሰው ነው ። ያዕቆብ በትክክል የኖረበትን ዘመን አሰላና ዘመኔ አነስተኛ ነው አለ ። 130 ዓመት የተቀመጠበት ነው ፣ የኖረበት ግን አነስተኛ ነው ።
ይህን ዓለም የእንግድነት ቤት አለው ። ለእንግድነት ቤትም እንደ አባቶቹ በድንኳን ኑሮውን መግፋት ጀመረ ። አሥራ ሦስት ልጆች ፣ አራት ሚስቶች ፣ ብዙ ከብቶች የእርካታ ጥያቄውን አልመለሱለትም ። ጥሩ ኑሮ ቢያጣ ጥሩ ቀብር ተመኘና አገሬ ቅበሩኝ ብሎ ተናዘዘ ። በርግጥም ከኑሮው ቀብሩ ያምር ነበረ ። የትኛውም ወዳጅ የማስደሰት አቅም ላይኖረው ይችላል ። ቀብርን ማሳመር ግን ይችላል ። ጌታችን በድህነት ኖሮ በባለጠጋ መቃብር ተቀበረ ። ያዕቆብም በጭንቅ ኖሮ ቀብሩ ግን ንጉሣዊ ነበር ። ያዕቆብ ይህ ዓለም የእንግድነት ቤቱ ስለነበረ የራሱን ይተዋል እንጂ የማንንም ንብረት አልቀማም ። በቁስ እንደማይኖር ገብቶት በረከትን ለመነ ። የእንጀራ ጥያቄው አያል ነበረ ። እንጀራው ሲገኝ ግን ሰላሙ ጠፋበት ። “አልጋው ሲገኝ ባሉ አይገኝ” አለች አሉ ሴቲቱ ።
የአፕል ኩባንያ መሥራቹ “ምግብን እንደ መድኃኒት ውሰዱ” አለ ። መድኃኒት በሰዓቱ ነው የሚወሰደው ፤ ምግብንም በሰዓቱ መውሰድ ይገባል ። ሥጋ የሚቆመው ፣ አእምሮው ማሰብ የሚችለው ምግብ ሲኖር ነው ። መድኃኒት በመጠን የሚወሰድ ነው ። ምግብንም እንደ መድኃኒት በመጠን መውሰድ ይገባል ። የልዑላንና የልዕልቶች ዕድሜ ከሃምሳ ዓመት ማለፍ እያቃተው ሲሞቱ ታሪክ ይነግረናል ። ምቾት ዕድሜን ይቀንሳል ። ድህነት ክፉ ፣ ምን ልብላ ? ማለት ከባድ ጥያቄ ቢሆንም ምቾትም የጤና ድሀ ያደርጋል ። ምግብ ለመኖር የሚያስፈልገውን ያህል ፣ መጠን ከሌለው መኖርን የሚጋፋ ነው ። የመንፈስ እርካታን ባለማወቅ አገር ለማየት ፣ ወንዞችንና መልክአ ምድሮችን ለመጎብኘት ፣ ከለመዱት ስፍራ ወጣ ብሎ በተፈጥሮው ውስጥ ያለውን አስደናቂ ነገር ለማጣጣም ያልቻሉ ሰዎች በየቀኑ ከብት እያረዱ በመብላት ኑሮአቸውን ወስነዋል ። ምግብ መጠን ኬለው እንደ በላነው ይበላናል ። እግዚአብሔር ለሁሉም ነገር ልክ አስቀምጧል ። አብዛኛዎቻችን አዲስ ምግብ ቤት እንጂ አዲስ መጻሕፍት ቤት አንጎበኝም ። ለእንጀራ ብቻ እንጂ ለቃሉ አልኖርንም ።
ይህ ባለጠጋ ሰው ትልቅ ትምህርት ቤታችን ነው ። ገንዘብ ሞትን ማስቀረት ቀርቶ ማዘግየት አይችልም ። ይህችን ዓለም ተሰናብተን ስንሄድ አዲስ ከፈን/ጨርቅ ጣል አድርገን ነው ። “ምግብን እንደ መድኃኒት ውሰዱ ፤ አሊያ መድኃኒትን እንደ ምግብ ትወስዳላችሁ” አለ ። ያዩት ሲነግሩን የተሻለ ነው ። በጥንቃቄ ያልኖረ ሰው መጨረሻ ላይ መድኃኒትን እንደ ምግብ መቃም ይጀምራል ። ያም ሆኖ ወደ ቀድሞ ጤና መመለስ አይቻልም ። ፍቅርን ፣ ጓደኝነትን ፣ ቤተሰብን ፣ ሃይማኖትን ፣ ኅብረትን ችላ ብለው የሮጡ ሰዎች በመጨረሻ ላይ የሮጡለት ነገር ሳይሆን ትንሽ የኖሩለት ፍቅር ትዝታ ሁኖ ይመግባቸዋል ። ንጽሕናን መጠበቅ ፣ በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ፣ ክብደትን መቀነስ ፣ ጤናን መጠበቅ ፣ ሱስን ማራቅ ፣ ለበሽታ የሚዳርጉ ጠባዮችን ማስወገድ ፣ አመጋገብን ልከኛ ማድረግ ይገባል ። ልብ አድርጉ በሽታ ላይገድል ይችላል ፣ አጉል ነዋሪ ግን ያደርጋል ።
እባካችሁ ጤናችሁን መጠበቅ አትርሱ ። ጤናን መጠበቅም የወንጌልን ቃል ማክበር ነው ። ጤናን መጠበቅ ለአምልኮ ፣ ለወንጌል ተልእኮ ፣ ሌሎችን ለመርዳት አስፈላጊ ነው ። የመጣብንን በሽታ በትዕግሥት መቀበል ፣ ያልመጣብንን በሽታ በጥንቃቄ ማራቅ ይገባል ።
አቤቱ ጌታ ሆይ ፣ በጤና በረከት ባርከን።
የብርሃን ጠብታ 7
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 3 ቀን 2014 ዓ.ም.