የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጥምቀትና ንስሐ

የዮሐንስ መጥምቅ ስብከት ፣ የጌታችንም የመጀመሪያ አዋጅ “ንስሐ ግቡ” የሚል ነው ። ንስሐ ከሰማይ ወደ ምድር የተላከች የሕይወት ሳሙና ናት ። ንስሐ በጥምቀት ትመሰላለች ። ንስሐ የእንባ ፈሳሽ አላትና ። ንስሐ የሰውን መጸጸት እግዚአብሔር በምሕረቱ ሲያከብረው ማለት ነው ። ሰይጣን ፣ ሰይጣን ሆኖ የቀረው ንስሐን በመጥላቱ ነው ። ሰውንም ሰው የሚያሰኘው ይቅርታ ሲጠይቅ ነው ። ንስሐ ጀርባችንን ለሰጠነው ጽድቅ ፊትን መስጠት ነው ። ንስሐ መመለስ ነውና የኃጢአትን ጉዞ አለመጨረስ ነው ። ንስሐ መዶሻ ነውና ሰማይ ጠቀስ የሆነውን ጥቅመ ሰናዖር/የኃጢአት ግንብ ማፍረስ ነው ። ንስሐ ስለት ነውና እኛንና ደጉን አባት የከለለውን ጥቁር መጋረጃ መቅደድ ነው ። በሕይወት ውስጥ ፣ በመንፈሳዊ ዓለምም ንስሐ ቀዳሚ ነው ። ጸጋን ከመለመን ንስሐ መግባት ፣ የበደልነውን ሰው ጥቅሙን ከመፈለግ ይቅርታ መጠየቅ ቀዳሚ ነው ። ንስሐ ቀዳሚ ጸጋ ነው ። ይቅር ከመባል የበለጠ ጸጋ የለም ። በምድር ላይ ሰዎች ይቅር እንዲሉን እንፈልጋለን ፣ ያንን ማግኘት ግን ከባድ ነው ፤ ሰዎች ይቅር እንዲባሉ እንጂ ይቅር እንዲሉ አይፈልጉም ። እግዚአብሔር ግን የምሕረት እጁን ዘርግቶ ይቅር እላችኋለሁ ኑ ሲለን እንዘገያለን ። ጌታችንም ፣ ዮሐንስ መጥምቅም ንስሐን የመጀመሪያ ስብከታቸው ማድረጋቸው እውነት ነው ።

ጌታችን ወደ ዮሐንስ መሄዱ የዮሐንስን አገልግሎት ለማጽደቅም ነው ። ይህን የመሰለ ዕድልና አንደበት ይዞ በበረሃ መቀመጡ ብዙዎችን አስገርሞ ይሆናል ። ጌታችን ግን የሚሻል ነገር እንደ መረጠ ለመመስከር ወደ ዮሐንስ ሄደ ። ዮሐንስ የወንጌል መድረክን ያነጠፈ ፣ ንጉሡ ሲመጣ የተሰወረ ሎሌ ፣ ሙሽራውን እንዳይጋርድ ቁመቱን የደበቀ ሚዜ ነው ። ንስሐ ግቡ የሚለው ትምህርት ከሮማ ባርነት ነጻ ለመውጣት ፣ ለዕድላችን መኮላሸት ምክንያቱ ቄሣር ነው ለሚለው ሰበበኛ የሚጥም አይደለም ። ጫካ ለገባው ቀነናዊ ቡድን ፣ ወኔን ለሚቀሰቅሱ ፈሪሳውያን የማይጥም መልእክት ነው ። ትልቁ ባርነት ግን ከቄሣር ይልቅ የዲያብሎስ ነው ። ትልቁ ነጻነትም ከሥጋ የነፍስ አርነት ነው ። ኃጢአት ጨለማ ነውና ዓይንን ያውራል ። ኃጢአት ባርነት ነውና በፍላጎት ብቻ ቀንበሩ አይሰበርም ። ያማ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ከኃጢአት ሊያድነን ባልመጣ ነበር ። ኃጢአት ግዛት ነውና ከዚያ ለመውጣት ነፍሱን አሲዞ የሚታደግ ነጻ አውጪ ይፈልጋል ። ኃጢአት በሽታ ነውና በዙሪያ ያሉትን ሁሉ ይበክላል ። አዎ ተላላፊ በሽታ ነው ። ንስሐ የሚባል ክትባት ይፈልጋል ። ኃጢአት ውስጥ ያለውን ሰው የሚያማክሩ አባቶች ሳይቀር በጸሎትና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ መሸፈን አለባቸው ። “ጨው ውኃ ልትቀዳ ወደ ወንዝ ወረደች ፣ እንኳን ልትቀዳ ውኃ ሆና ቀረች” እንዲሉ ።

እኛ እኮ የአብርሃም ልጆች ነን እያሉ የሚኩራሩ ከንስሐ ይዘገያሉ ። እምነት ራስን በመስጠት እንጂ በታሪክ ብልጽግና የሚድኑበት አይደለም ። ታሪክ መልካም ነው ። በውስጡ ብዙ ዋጋዎችን ያሳያል ። ታሪክ ግን ካልደገሙት ሕመም ነው ። ክርስትና ሕያው ነው ። ታሪክን እንደ ጣኦት የሚያመልኩ አይሁድ ክርስቶስን ለመቀበል ተቸግረዋል ። ንስሐ እምነት ነው ። ሰው በገዛ አፉ በደሉን የሚያምንበት ነው ። ፍርድ ቤት ትልቁ ክርክር ሰው ጥፋቱን እንዲያምን ወጥመድ መዘርጋት ነው ። በንስሐ ግን ሰው ያለ ከሳሽ ራሱን ይከስሳል ፣ ያለ ዳኛ በራሱ ይፈርዳል ። ውጤቱም በራሱ የፈረደ አይፈረድበትም ። እኛ የአብርሃም ልጆች ነን እያሉ የአብርሃምን አምላክ መስቀል የሚገርም ነው ። ትምክሕት ማንም ባልወደቀበት በደል እንድንወድቅ ያደርጋል ። ትምክሕት ምሽግ ነውና ሰባኪ ይህን ምሽግ ሲያፈርስ የተጠላ ይሆናል ። በአገራዊ ቋንቋ ባንዳ ፣ በመንፈሳዊ ቋንቋ መናፍቅ ይሰኛል ።

ጌታችን በተነሣሕያን መካከል መገኘቱ ንስሐን የሚወድድ አምላክ መሆኑን ያሳያል ። ሊቀ ካህኑ በተነሣሕያን መካከል ተገኘ ። ካህን ፣ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአትን ይቅር የሚል አበሳን የሚደመስስ ነው ። ይቅር ሲል እንደ ትላንትናው ቀን ፣ ተመልሶ እንደማይመጣው ያሳልፈዋል ። ሲደመስስ ጽሕፈቱ ዳግም ላይታይ ይፍቀዋል ። አዎ በበደልን ቍጥር ራሳችን ላይ ሞትን እየመዘገብን ነው ፤ ጽሕፈቱ ፣ የእኩይ ፍልስጣ ብዕሩ በንስሐ ይደመሰሳል ። /እኩይ ፍልስጣ የሚባል ሰይጣን እየተከታተለ የሰውን በደል የሚመዘግብ ነው ይባላል/

ዮሐንስ ተነሣሕያኑን በውኃ የሚያጠምቀው ይቅር መባላቸው እንዲሰማቸው ነው ። ንስሐ የራስን ኃጢአት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ምሕረት ማመን ነውና ። መታጠቡ ኃጢአት የሚያቆሽሽ ጭቃ ስለሆነ ነው ። ጭቃን ለልብሳችን እንሰቀቀዋለን እንኳን ለነፍሳችን ። ጭቃ ቶሎ የመታጠብ ፍላጎትን ያሳድራል ። በንስሐ ከታጠባችሁ ስንት ዓመት ሆናችሁ ?

ልባችንን ለንስሐ ያነቃቃልን !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ