ምድራዊ ጥበብ ተፈጥሮን ቸር ይላል፣ ሰማያዊ ጥበብ ፈጣሪ ሰጪ ነው ይላል። ምድራዊ ጥበብ የተሠራውን ያደንቃል፣ ሰማያዊ ጥበብ ሠሪውን ያወድሳል። ምድራዊ ጥበብ ከሰውም ከአጋንንትም ነው፣ ሰማያዊ ጥበብ ከመንፈስ ቅዱስ ነው። ምድራዊ ጥበብ ብልጥ ያደርጋል፡ ሰማያዊ ጥበብ የዋህ ያደርጋል።
ምድራዊ ጥበብ አድርጉ ይላል፣ ሰማያዊ ጥበብ ሁኑ ይላል። ምድራዊ ጥበብ ስስትን ኢኮኖሚ ይላል፣ ሰማያዊ ጥበብ ኃጢአትን በስሙ ይጠራዋል። ምድራዊ ጥበብ ነውሩን አይደብቅም ፣ ሰማያዊ ጥበብ ማሰናከያን አያደርግም። ምድራዊ ጥበብ የወንድሙን ገመና ይነግድበታል፣ ሰማያዊ ጥበብ ወንድሙን ጋርዶ ያጸዳዋል። ምድራዊ ጥበብ እግዚአብሔርን በመድፈር ይጀምራል፣ ሰማያዊ ጥበብ ፈሪሀ እግዚአብሔርን አልፋ ያደርጋል።
ምድራዊ ጥበብ ማግበስበስን ያስተምራል፣ ሰማያዊ ጥበብ ያለኝ ይበቃኛልን ያስተምራል። ምድራዊ ጥበብ በምድር ጀምሮ በምድር ያበቃል፣ ሰማያዊ ጥበብ ከላይ መጥቶ ሰማያዊ ያደርጋል። ምድራዊ ጥበብ ዓይኑ በሰው ላይ ነው፣ ሰማያዊ ጥበብ ራስን ያሳያል። ምድራዊ ጥበብ አፈኛ ቃላተኛ ያደርጋል፣ ሰማያዊ ጥበብ ዝምታንና ጽሞናን ያስተምራል ። ምድራዊ ጥበብ ፍለጋው አያልቅም፣ ክለሳው ብዙ ነው፤ ሰማያዊ ጥበብ አንድ ጊዜ የተሰጠ ዘላለማዊ ነው።
ምድራዊ ጥበብ ነገ ከነገ ወዲያ የሚል ነው፣ ሰማያዊ ጥበብ እምነትና አሁን መዳን ነው። ምድራዊ ጥበብ ራስን ማጽደቅ ነው፣ ሰማያዊ ጥበብ የንስሐ ሕይወት ነው። ምድራዊ ጥበብ አገልጋዮችንና ቅዱሳንን የሚጠላ ነው፣ ሰማያዊ ጥበብ ላይን ሳይሆን ጸጋን የሚያከብር ነው። ምድራዊ ጥበብ ከሌለህ የለህም ባይ ነው፣ ሰማያዊ ጥበብ ራስን መካድ ነው። ምድራዊ ጥበብ ታጥቦ ቀረብ፣ የሌላውን ልፋት ቀምቶ የእኔ የሚል ነው፣ ሰማያዊ ጥበብ ያለውን የራሱን የሚተዉ ነው። ምድራዊ ጥበብ ስለመብት የሚያወራ ነው ፣ ሰማያዊ ጥበብ ስለፍቅር የሚያወራ ነው። ምድራዊ ጥበብ ለምሳ ያሰበህን ለቁርስ አድርገህ ቅደመው ባይ ተበቃይ ነው፣ ሰማያዊ ጥበብ ታራቂ ነው። ምድራዊ ጥበብ ለሕዝብ ርእስ ሰጥቶ የሚያስጨንቅ ነው፣ ሰማያዊ ጥበብ ዕረፍትን የሚያድል ነው ።
ምድራዊ ጥበብ ችግሩን ገልጦ መፍትሔ የለኝም የሚል ነው፣ ሰማያዊ ጥበብ መድኃኒቱን የሚያውጅ ነው። ምድራዊ ጥበብ በጦር መሳሪያ የሚኰራ ነው፣ ሰማያዊ ጥበብ መስቀልን ዓርማው የሚያደርግ ነው ። ምድራዊ ጥበብ ተፈሪ ሁን ይላል፣ ሰማያዊ ጥበብ ተወዳጅ ሁን ይላል። ምድራዊ ጥበብ ሲወዱህ ኩራ ይላል፣ ሰማያዊ ጥበብ ጠላትህን ውደድ ይላል። ምድራዊ ጥበብ ችግርህን ለመርሳት ደንዝዝ ይላል፣ ሰማያዊ ጥበብ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው ይላል። ምድራዊ ጥበብ ስለ ግል ጥቅም ያስባል፣ ሰማያዊ ጥበብ ስለ ዓለም ሰላም ይጸልያል። ምድራዊ ጥበብ ንጉሥን ተጠጋ ይላል፣ ሰማያዊ ጥበብ የማይናወጠውን መንግሥት ተቀበል ይላል።
ምድራዊ ጥበብ ዓለምን በጦር ስላስገበሩ ሰዎች ይናገራል፣ ሰማያዊ ጥበብ ዓለምን በፍቅር ስላስገበረው ጌታ ይናገራል። ምድራዊ ጥበብ ሺህ የገደሉትን ጀግና ይላል፣ ሰማያዊ ጥበብ ለሺህ የሞተውን ኃይል ይላል። ምድራዊ ጥበብ ሰው የሚወደውን ያደርጋል፣ ሰማያዊ ጥበብ ለእውነት ይገዛል።
አቤቱ ጥበብ የሆንከው የማርያም ልጅ ፣ ጊዜ የማያልፍባት ያንተ ጥበብ ከእኛ ጋራ ትሁን። አሜን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 30 ቀን 2017 ዓ.ም.