ሥጋ እንደ ልብስ ፣ ነፍስ እንደ አካል ፤ ሥጋ እንደ ታቦት ፣ ነፍስ እንደ ጽላት ፤ ሥጋ እንደ ሰገባ ፣ ነፍስ እንደ ሰይፍ ፤ ሥጋ እንደ ገበታ ፣ ነፍስ እንደ እንጀራ ፤ ሥጋ እንደ አደባባይ ፣ ነፍስ እንደ ቃል መሆኗን ያወቅሁት ዘግይቶ ነው ። ሥጋ የነፍስ መጎናጸፊያ ናት ፣ ምድር የሥጋ አገር ናትና በአገርዋ ነፍስን የምታላምድ ናት ። ሥጋ እንደ ምላስ ስትሆን ነፍስ ደግሞ በምላስ ውስጥ እንዳለ ቃል ናት ። ሥጋ እንደ አረጀ ልብስና እንደ ቆሸሸ ሰገባ ናት ። ነፍስ ግን ሰይፍ ናት ። በቀላሉ የምትወለወል ፣ የክፉውን አሳብ ለመጣል የምትታገል ናት ። ሁልጊዜ ነፍስ ወደ ላይ ፣ ሥጋ ወደ ታች ይሳሳባሉ ። የመሳሳቡ ሜዳ “መኖር” ሲባል ሲላቀቁ ሥጋ “አፈር” ፣ ነፍስም “መንፈስ” ይሆናሉ ። ሥጋ እንደ ልባሽ ጨርቅ ፣ እንደ አረጀ ሰገባ ፣ እንደ ድሮ ዕቃ ፣ እንደ ቆሸሸ ገበታ ፣ እንደ ፈረሰ አደባባይ መሆኗን ያ ቀን ነገረኝ ። ሽቅብ ወደ ላይ ስጓዝ በተጓዝሁ ቍጥር ሥጋዬ ትርቀኝ ነበር ። ወደ ነፍስ መጓዝ ከሥጋ ፣ ወደ ሰማይ መጓዝ ከምድር መራቅ ነው ። ልቀቀኝ እያሉ መታገል ነፍስን ከሥጋ ፣ መንፈስን ከምድር አይለይም ። ወደ አንደኛው መጓዝ ከሌላኛው መራቅ ነው ። በመጓዝ እንጂ ቆሞ በመደራደር መላቀቅ የለም ።
ከሥጋ ወጥቼ በነፍስ አካልና አቋም በነፍስ የኑሮ ሥርዓት ውስጥ ስገባ ፍርሃት ፣ ጭንቀት ፣ መርገብገብ ፣ መንታ ማንነት ፣ የተለዋወጠ ስሜት ጥሎኝ ሲሄድ ታወቀኝ ። ፍርሃትም ልክ አለው ። የፍርሃት ልኩ እስከ ሰማይ ነው ። በሥጋዬ ሁለት ጌታ ተሸክሜ እኖር ነበር ። የነፍስ ጉዞ ስጀምር ግን ለአንድ ጌታ አደርሁ ። ለአንድ ጌታ ማደር ክብር ነው ። ለሁለት ጌታ ያደረ ሁለቱም አያምኑትም ። እርሱም ሚዛኑን ላስተካክል ሲል በጭንቀት ያብዳል ። ለማረፍ የጀመረው ጉዞ ጭንቀት ይሆንበታል ። ወደ እግዚአብሔር ገነት እየተቃረብሁ ስመጣ ገነት የአትክልት ስፍራ ናት የሚለው ግምቴ ከንቱ ሆነብኝ ። አትክልት የሚያስፈልገው ደረቅ ነገር ስላለ ነው ። በገነት ግን የእግዚአብሔር ልጅ የዘላለም ልምላሜ ነውና አትክልት አያስፈልግም ። ገነት ሲባል አበባ ያለባት ውብ ስፍራ ትመስለኝ ነበር ። መልአኩ ግን ነጠቅ አድርጎ ፣ የልቤን አውቆ “የቅዱሳን መዓዛ ክርስቶስ ነው” ብሎ የአባቶቼን ምስጋና አስታወሰኝ ። ዛፍ የሚያስፈልገው ቃጠሎ ላለበት ነው ፣ ገነት ግን ከፀሐይ በላይ ናትና ዛፍ አያስፈልጋትም ። ገነትን የሚያጠጡ ወንዞች በሰማይም እየጠበቅሁ ነበር ። ክርስቶስ እርካታ በሆነበት ስፍራ ምንጭ አስፈላጊ አልነበረም ።
ቅዱሱ መልአክ፡- “መጥተህ ርስትህን እንደ ቸርነቱ እስክታገኝ ድረስ ለዛሬ የተፈቀደልህ ሐዋርያውን ቅዱስ ጳውሎስን እንድታገኝ ነው” አለኝ ። በመቀጠልም፡- “ይህ የብቃትህ ውጤት ሳይሆን አገልግሎትን ሳይጀምሩ የጨረሱ የሚመስላቸው በዝተዋልና በጳውሎስ አንደበት ገና መሆኑን እንዲሰሙ ነው ። ለዚህም አንተ ድምፅ ማጉያ ነህ ። አንድ ቀን ወደዚህ መምጣትህ አይቀርምና ሰማይ ደርሼ መጣሁ እያልሀ አታውራ ። የክርስቲያን ጠባቂው ትሕትናና ምሥጢር የመያዝ አቅም ነው” አለኝ ። እኔም በቅዱሱ መልአክ ፊት ጆሮ እንጂ አፍ አልነበረኝም ። ሰማይ አስደሳች ግርማ ያለበት ነው ። በምድር ላይ የነበረኝ ድፍረትና ቀደም ቀደም ማለት አልተከተለኝም ። የሥጋ ትልቅነትም በሰማይ ስፍራ የለውም ። በሰማይ ማወቅ ጥቅም የለውም ። በሁሉ ጌታ መታወቅ ብቻ የዘላለም ሕይወት ተብሎ ይጠራል ። በሰማይ የሃይማኖት ትምህርት የለም ፣ የሃይማኖት ዋጋ የሆነው እግዚአብሔር ግን አለ ። ብዙ ምርምር ለሰማይ አይጠቅምም ፣ የመጨረሻ እውቀት በዚያኛው ዓለም ገና አዲስና ዝቅተኛ እውቀት ነው ።
ዓይኖቼ ቅዱሱን መልአክ ሰርቀው ያያሉ ። ባሻገር ደግሞ አንዳንድ ሰዎችን ያያሉ ። የማልጠብቀው አንድ ኃጢአተኛ ታየኝ ። ዓይኔን ማመን አቃተኝ ። “እንዴት እርሱ እዚህ ተገኘ?” የሚል መደነቅ ያዘኝ ። እኔ ስለምወዳቸው የሚጸድቁ የመሰሉኝን የእኔን ጀግናዎች ብፈልግ ብቅ አይሉም ። በልቤ፡- “እነ እገሌ እንዴት እዚህ ተገኙ ? እነ እገሌስ እንዴት ከዚህ ጠፉ ?” ልል ስል ቅዱሱ መልአክ ለካ የልቤን አሳብ ያውቀው ነበርና፡- “አንተ በዚህ ስለመገኘትህ ብቻ አመስግን ሌላው ያንተ ድርሻ አይደለም” አለኝ ። እኔ የመጣሁበት ዓለምና አገር ሰው የራሱን አስቀምጦ የሰውን የሚጫወትበት ፣ የሚመለከተውን ለይቶ የማያውቅበት ነው ። ቅዱሱ መልአክም በግሣጼም መለሰኝ ። በሰማይ ማዳለል የለም ። መልሼ ውስጤ ትሑት የሆነ መሰለኝና፡- “እኔ እዚህ በመገኘቴ እንዳላረክሳቸው” አልኩኝ ። ትሕትናዬም ትዕቢት ነበርና ቅዱሱ መልአኩ ገሠጸኝ ። “በአንተ ኃጢአት የሚረክስ መቅደስ ከሆነ ቀድሞም ቅዱስ አልነበረም ማለት ነው ። ከንቱ ትሕትና ከክርስትናና ከአገልግሎት ያወጣሃልና ተጠንቀቅ” አለኝ ። ቅዱሱ መልአክ ትዕቢቴንም ትሕትናዬንም ገሠጸው ። ትሕትና የሚመስሉ ሰይጣናዊ ማስበርገጊያዎች አሉ ። ከተመኘሁ አይቀር ባመነዝር ፣ በልቤ ከጠላሁ አይቀር ብገድልስ ፣ በእግዚአብሔር ቤት ሆኜ ከምበድል በዓለም ሆኜ የፈለግሁትን ብሠራ ይሻለኛል ። ያልኖርኩትን ከመናገር ስኖር ብሰብክ መልካም ነው ። እኔ ታምሜ ስለ ሌላው ድካም እጨነቃለሁ ። ለራሴ መግቢያ የለኝ ብዙ ስደተኛ አስከትላለሁ የሚሉ የትሕትና ማር የተላበሱ ሰይጣናዊ እሬቶች ናቸው ። በሰማይ እውነት ብቻ ስፍራ አለው ። ውሸቴ ታረመ ። ትሕትናዬም የትዕቢት ታናሽ ወንድም ነበረ ።
ሐዋርያውን ቅዱስ ጳውሎስን ለማግኘት ብመጣም በዚሁ ጌታዬን ባየሁት ብዬ ማሰብ ጀመርሁ ። ቅዱሱ መልአኩ ግን፡- “ጳውሎስን ስታይ ክርስቶስን ታያለህ” አለኝ ። እኔም ሐዋርያው ያለውን አስታወስሁ ። “እኔ ክርስቶስን እንደምመሰል እኔን ምሰሉ” ያለውን አስታወስሁ ። ቅዱሱ መልአክም፡- “እኛም ክርስቶስን የምናየው በዓይን ሳይሆን በማመን ነው ። ዓይን የሚያየው የመጠኑን ያህል ነው ። ክርስቶስ በምድርም በሰማይም ብትሆን የሚታየው በእምነት ነው” አለኝ ። እኔም አንድ ጊዜ በምድር ሳለሁ “እምነት እግዚአብሔርን የምናይበት መነጽር ነው” የሚል ትምህርት እንደ ሰማሁ አስታወስሁ ። ከመልአኩ ጋር እያወራሁ ወደ ምድር መመለስ እያስፈራኝ መጣ ። “ደስታውን ሳታጣጥም ስለመመለስ ለምን ታዝናለህ?” በማለት መልአኩ አረጋጋኝ ። እኔም ለመልአኩ፡- “ሐዋርያው ጳውሎስ እስከ ሦስተኛ ሰማይ ድረስ መጥቶ እንደ ገና ተመልሶ ማገልገል መፈለጉ ይገርመኛል” አልኩት ። “አዎ ሰማይ ስትደርስ ትልቅ የመሰለህ አገልግሎትህ ያንስብሃል ። ተመልሰህ ማገልገልና የሃይማኖት ገድል መፈጸም ትፈልጋለህ” አለኝ ።
ከመልአኩ ጋር እያወጋሁ ሳለሁ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲመጣ ከሩቅ አየሁት ። እኔም መንገድ አጋምሼ ብቀበለው ብዬ ሳስብ መልአኩ ከለከለኝ ። “ገና ወደ ሥጋ ማደሪያ የሚመለሱ ከዚህ ማለፍ አይችሉም ፣ ሙሉውን ክብር የምታየው ቆርጠህ ስትመጣ ነው ። የምታየው በመጣህበት የቆራጥነት መጠን ነው” አለኝ ። ከደስታ የተነሣ ልቤ መዝለል ጀመረ ። ደስታ እያንጠራራኝ ፣ የሟሸሸውን ሰውነቴን እየወጠረው መጣ ። ነፍሴ በሐሤት ተሞላች ። መልአኩ የሚመልስልኝን መልስ መምህሬ የኔታም ይሰጡኝ ከነበረው ፍቺ ጋር ተቀራረበብኝ ። በሰማይና በምድር አንድ ድምፅ አለ ። እርሱም እውነት ነው አልኩኝ ። ጥያቄ አንድ እስከሆነ ድረስ በሰማይም በምድርም የምሰማው መልስ ተመሳሳይ ነው ። ተመሳሳይ መልሶች የተመሳሳይ ጥያቄ ውጤት ናቸው ። ኦ እግዚአብሔር ይመስገን ጳውሎስን አየሁት ፣ ጳውሎስን አገኘሁት ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታሕሣሥ 18 ቀን 2013 ዓ.ም.