የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጳውሎስን አገኘሁት /10/

 

እኔም በተመጠነልኝ ዘመን የምኖር ፣ በተመጠነልኝ በረከት ኑሮዬን የምገፋ ስለሆንሁ ላውቀው እስከተፈቀደልኝ ድረስ ለማወቅ ከዚያ ያለፈውን ግን “እግዚአብሔር ሁሉን ያውቃል” ብዬ ልደሰት ወሰንሁ ። በልቤ ግን ሐዋርያው ስለ ሐዋርያዊ ጉዞዎቹ ቢነግረኝ ብዬ አሰብሁ ። የእግዚአብሔር መንፈስ ባለበት ሰዎች ሳይነጋገሩ ይግባባሉ ፣ መንፈሱ ሲርቅ ደግሞ ሰዎች ተነጋግረውም መግባባት አይችሉም ። ሐዋርያውም የልቤን መሻት አወቀ ። ከአንዱ መንፈስ እየጠጣን ነውና የምናስበው አንድ ዓይነት አሳብ ነበረ ። ሐዋርያው ሦስት ታላላቅ ሐዋርያዊ ጉዞዎችን እንዳደረገ አራተኛው ሐዋርያዊ ጉዞውን አድርጎም በእስራትና በሞት ተጋድሎውን እንደፈጸመ ነገረኝ ። ሐዋርያው በጉባዔ ብዙ ሕዝብ እንደሚያስተምር ለእኔ ለአንድ ሰው ተግቶ ይናገር ነበር ። የእግዚአብሔር ቃል ስለሰሚው ማንነት ሳይሆን ቃሉ ስለተገኘበት አምላክ በክብር መነገር አለበት ። ሐዋርያው ቀጠለ፡-

“ወደ ክርስትና እምነት ከመጣሁ በኋላ የበደልኩትን ክርስቶስ የምክስበት ፣ የእኔ ያልሆነ ዘመን ላይ እንዳለሁ አስብ ነበር ። በማመን የቀደሙኝን ሐዋርያትን በታላቅ ክብር አከብራቸው ነበር ። ሁላችን በጸጋ የተቀበልን ነንና የምንመካበት ምንም ነገር አልነበረንም ። በመካከላችንም ትሕትና መከባበር ፣ መደማመጥና መፈላለግ ሰጥቶን ነበር ። እኔም ጽሞና ፣ ከአባቶች ምክርና ጸሎት አስፈላጊዬ እንደነበር ተረድቻለሁ ። ትላንት በስሜት አማኝ በነበርሁ ጊዜ ነፍሰ ገዳይ ሆንሁ ። አሁን ስሜትን በእምነት ስተካ ሦስት ነገሮች ያስፈልጉኝ ነበር ። እነርሱም ራሴንና የመጣሁበትን መንገድ ለማየት ጽሞና ፣ መገዛትን ለመልመድና ሥልጣንን ለማክበር የአባቶች ምክር ፣ የቀጣዩን ምሪት ለመቀበል ጸሎት አስፈላጊዬ ነበሩ ። ሐዋርያዊ ጉዞ ያደረግሁት ከ48 ዓ.ም. እስከ 58 ዓ.ም ለአሥር ዓመታት ያህል ነው ። በር ከፍቼ ፣ ልጅ ጥዬ ብመጣ ኑሮ ለዐሥር ዓመታት ዓለምን መዞር አልችልም ነበር ። ድንግልናዊ ሕይወቴ ግን ትጥቄን አጠር እንዳደርግና በአንድ ልብ ለክርስቶስ እንዳድር አግዞኛል ። ለዘላለምም በሰማይ የሚቀጥለው ከክርስቶስ ጋር መኖር ነበርና በምድር ስለጀመርሁት ደስ ይለኛል ። ያገቡት ቅዱሳን በሰማይ ትዳራቸው አልቀጠለምና እኔም የድንግልናዊ ሕይወቴን ወድጄዋለሁ ። ሐዋርያዊ ጉዞዬ ከመጀመሪያው የሐዋርያት ሲኖዶስ ከኢየሩሳሌሙ ጉባዔ ማለትም ከ50 ዓ.ም. በፊትና በኋላ የተካሄደ ነው ። አንደኛውን ሐዋርያዊ ጉዞዬን ከበርናባስና ከማርቆስ ጋር ከኢየሩሳሌሙ ጉባዔ በፊት አደረግን ። በ50 ዓ.ም ግን ጉባዔው ላይ መገኘት ስለነበረብን ወደ ኢየሩሳሌም መጣን ። የሐዋርያዊ ጉዞው ዓላማ ሦስት ነው ። 

የመጀመሪያው፡- አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን ለመትከል ነው ። ያልተከሉትን አይጸድቅምና ፤

ሁለተኛው፡- የተተከሉትን አብያተ ክርስቲያናት ለማጽናት ነው ። የተከለ ገበሬ ለማረም ለመንከባከብ ይመለሳልና ፤ 

ሦስተኛው ለኢየሩሳሌም ድሆች እርዳታ ለማሰባሰብ ነው ። ግማሽ አካል ተርቦ ግማሹ ቢጠግብ ደስታው ሙሉ አይደለምና ። ደግሞም በችግር ቀን መረዳዳት የማይረሳ ፍቅርን ትቶ ይሄዳል ። 

የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉዞዬ በ48 ዓ.ም. ገደማ የተካሄደ ሲሆን ይህን ጉዞ በሐዋርያት ሥራ በምዕራፍ 13 እና 14 ላይ ተመዝግቦ ታገኘዋለህ ። በዚህ ጉዞ መነሻ ያደረግነው ለአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት እናት ከነበረችው ከአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ነው ። በዚህ ጉዞዬን አብረውኝ በርናባስና ማርቆስ ነበሩ ። በጉዞም አይሁድ ባስነሡት ስደት ማርቆስ ተረብሾ ጥሎን ወደ ኢየሩሳሌም በመሄዱ ልቤ አዘነበት ፣ ውስጤም ተቀየመው ። ማርቆስ ልጅነትም ስለነበረው ከመከራው ጋር እናቱ ናፍቃው ተመልሶ ይሆናል ። ኋላ ሁለተኛውን ሐዋርያዊ ጉዞ ልንጀመር ስንል ከእኛ ጋር ተቀላቀለ ። እኔ ግን አብሮን ይሄድ ዘንድ ፈቃደኛ አልነበርሁምና በዚህ ምክንያት ልበ ሰፊ ከነበረው ከበርናባስ ጋር እስክንከፋፋ ድረስ ተጣላን ። በታሰርሁበት ጊዜ ግን የማርቆስን ትጋት ሰምቼ ልቤ ይቅርታ አድርጎለት ከመሞቴ በፊት እንዲያየኝና እንድልከው ፈልጌ ለጢሞቴዎስ ጽፌለት ነበር ። ይህ ማለት ከ14 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው ። አይጠቅመንም ብዬ ያባረርሁት ሰው ኋላ ላይ ይጠቅመኛል ብዬ ፈለግሁት ። ለካ እግዚአብሔር የሚታገሠው የማይጠቅመው ሰው ለጥቅም እስኪሠራ ነው ። ዛሬ ያሳዘኑን ነገ እንደሚጠቅሙን የእኔ ሕይወት ምስክር ነው ። እግዚአብሔር በእኔ መጨከንና በበርናባስ ርኅራኄ መካከል ማርቆስን ይሠራው ነበር ። የማርቆስ ወንጌልንም የጻፈው ከዚህ በኋላ ነው ። ስደትን መፍራቱ ፣ እናቴ ናፈቀችኝ ማለቱ ወደ ዓላማና ወደ መስመሩ እስኪገባ ድረስ ያልረጋው ስሜቱ የወለደው ነው ። 

በመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉዞዬ ሴሌውቅያ ፣ ቆጵሮስ ፣ ስልማና ፣ ጳፉ ፣ ጵንፍልያ ፣ ጴርጌን ፣ ጲስድያ ፣ ኢቆንዮን ፣ ልስጥራን ፣ ደርቤን ፣ ጵንፍልያ ፣ ጴርጌን ፣ አጣልያን አዳረስን ። በዚህ ጉዞአችን አሥራ ሦስት ከተሞችን የነካን ሲሆን ሁለት ሺህ ኪሎ ሜትሮች ያህል በእግራችን ተጉዘናል ። አንተ የአፍሪካ ሰው ስለሆንህ እነዚህን አገሮች መረዳት ትቸገር ይሆናል ። መነሻ ያደረግነው ከሶርያ አንጾኪያ ነው ። ከአንጾኪያ ወደ ደቡብ ሴሌውቅያ እንደገና ወደ ምዕራብ ደቡብ በመሄድ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ደሴት ፣ ከቆጵሮስ ደሴት የደሴቱ ምሥራቃዊ ክፍል ስልማና ፣ ከዚያም ወደ ደሴቲቱ ደቡብ ምዕራብ ወደ ጳፉ ፣ ከዚያ በመርከብ ባሕር አቋርጠን ወደ ሰሜን ጵንፍልያ ፣ አጠገብ ወዳለችው ከተማ ወደ ጴርጌን ፣ ከዚያም ወደ ኢቆንዮን ፣ ልስጥራን ፣ ደርቤን ፣  … እያልን አገለገልን ። 

አይሁድም ሞተ ብለው እስኪተውኝ ድረስ በድንጋይ ወገሩኝ ። እኛም ወደ እግዚአብሐር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል እያልን ወደ ልስጥራንና ኢቆንዮን ወደ አንጾኪያ ተመለስን ። ወደ ተነሣንበት መመለስ አቅም ለማግኘት ነው ። ወደ ተነሣንበት ስንመለስ ቀጣዩን ጉዞ ለማየት ምክክር እናደርጋለን ። የገላትያ መልእክትንም የጻፍኩት ከኢየሩሳሌም ጉባዔ በፊት በመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉዞዬ ወቅት ነው ። እነዚህ የገላትያ ምእመናን ወደ ኋላ እየተመለሱ ነበርና ፈጥኜ መልእክቱን ሰደድኩላቸው ። የመጀመሪያው መልእክቴም የገላትያ መልእክት ነው ። የኋላ አባቶች የሮሜ መልእክትን የመጀመሪያ ያደረጉት መልእክቴን ከጽድቅና ከምስጋና ለመጀመር አስበው ነው ፤ የገላትያ መልእክት ማስጠንቀቂያና ተግሣጽ ነውና ። በመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉዞዬ እንደ አማልክት እንሠዋላችሁ ያሉን ሰዎች ነበሩ ፣ እንደ እባብ በድንጋይ ቀጥቅጠውም ሞቱ ብለውን ጥለውን የሄዱ ነበሩ ። 

ወጣትና ጀማሪ ልጆች ገና የእናት እንክብካቤ የሚናፍቃቸው እንደሆኑ መረዳት ይገባል ፣ በመከራም ሲደነብሩ ለሐዋርያዊ ጉዞ ከባድ ነው ። ሐዋርያ ብሆንም በማርቆስ አዝኛለሁ ። ምክንያቱም እንደ እርሱ ወጣት የነበረ እስጢፋኖስ ገና በለጋ ዕድሜው ሰማዕት ሁኗልና ፤ ጸጋው የሚያግዘን በልባችን ቆራጥነት መጠን እንጂ ጸጋው አእምሮአችንን አስቶ ወደፈለገው የሚወስደን አይደለም ። እናንተም ገና ዓለምን ያልጠገቡ ፣ ሁሉም ነገር አዲስ የሚመስላቸው ፣ እንደ ጀግና ጀምረው እንደ ፈሪ የሚጨርሱ ፣ ምግብ አልመች ሲላቸው ወይኔ እናቴ የሚሉ ደቀ መዛሙርት ሲገጥሙአችሁ ተስፋ እንዳትቆርጡ አደራ እላለሁ ። መገሠጽ ፣ ወደ ኋላ እንዳይጎትቱ መሸኘት ቢኖርም የሚያዝንላቸው የበርናባስ ልብ ደግሞ ያስፈልጋል ። ሲያስተውሉና ዓለም አዲስ ነገር የሌለው መሆኑን ሲረዱ ተመልሰው ይመጣሉ ። ቢሆንም እኔ ማርቆስን ሳጣ እግዚአብሔር ጢሞቴዎስን ሰጥቶኛል ። አንድ ሰው ሲሄድ አንድ ሰው ይመጣል ። እግዚአብሔር ብዙ ሰው አለውና ማዘንና መቆም አይገባችሁም ። ማርቆስ በመሄዱ ሲላስንና ጢሞቴዎስን እንድመርጥ አድርጎኛል ። አንድ ሰው ሲሄድ ሁለት ሰዎች የሚሰጥ እግዚአብሔር አለና ሰዎችን ለእግዚአብሔር ሥራ የምታዘጋጁ ከሆነ ሲለግሙ እዘኑ ግን ተስፋ አትቍረጡ” አለኝ ።

ወደ ታላቅ ተመሥጦ ስለገባሁ ሐዋርያው ሁለተኛውን ጉዞ ለመተረክ መቆየትን መረጠ ። እኔ ወደ ዓለም ሁሉ መሄድ ሳይሆን ዓለም ሁሉ ወደ እኔ ቢመጣ ለማገልገል እወጣለሁ ወይ ? ብዬ አሰብሁ ። ዛሬ በጳውሎስ እግር የተተኩ አባቶች ሐዋርያዊ ጉዞአቸው የመሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥ ፣ ሕንፃ ለመመረቅ ነው ወይስ ያልተጠመቁትን ወደ ጥምቀት ፣ የራቁትን ወደ አሚነ ሥላሴ ለመመለስ ነው ብዬ ማሰብ ጀመርሁ ። ሐዋርያዊ ጉዞ ዛሬም ያስፈልጋል ።

ይቀጥላል 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ