የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጳውሎስን አገኘሁት /11/

 

ሐዋርያው ጳውሎስ ከዚህ በፊት እንዳደረገው ነገሮችን እስክረዳቸው ድረስ ይጠብቀኝ ነበርና ገረመኝ ። እርሱ ግን፡- “አትገረም እኛ ለጆሮ ስንናገር እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ለልብ ይናገራል ። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያንን ሰው እስኪገልጥለት ድረስ ከተናገርን በኋላ በትዕግሥት መጠበቅ አለብን ። ዓይኑን ጨፍነን ፣ ጆሮውን ደፍነን የምናድነው ሰው የለም ። ከሚያየው ይልቅ የማይታየውን ክርስቶስ ፣ ከሚሰማው ብዙ ነገሮች ይልቅ ወንጌልን ሰምቶ መዳን የሰው ነጻ ፈቃድ ነው” አለኝ ። እኔም መንፈስ ቅዱስ እንዲሠራ ጊዜ ያልሰጠሁበትን ዘመን አሰብሁና ችኮላዬ ሳይሆን ትጋቴ ሰውን እንደሚያተርፍ አስተዋልሁ ። ቅዱስ ጳውሎስም ሁለተኛውን ሐዋርያዊ ጉዞውን ሊነግረኝ ስለፈለገ አሳቤን አቋርጦ ጉዞውን መተረክ ጀመረ ። 

“የመጀመሪያውን ሐዋርያዊ ጉዞ እንዳደረግሁ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም የመጀመሪያውን ጉባዔ አደረጉ ። ይህ ጉባዔ የሲኖዶሶችና የውሳኔያቸው ፊታውራሪ ነው ። ሲኖዶሱም የተሰበሰበው የሰውን መዳን በሚመለከትና የቢጽ ሐሳውያንን መሰናክል አንሥቶ የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናትን ለማጽናት ነው ። በኋላ ዘመን ይደረጉ የነበሩ ሲኖዶሶች በሐዋርያት መንበር ላይ የተሰየሙ አባቶች የሚያደርጉት ቢሆንም ዋዛ ፈዛዛ ነገር የበዛበት ፣ ከጽድቅና ከኰነኔ የማይገቡ ነገሮችን በማንሣት ፣ ጊዜ መግፊያ ፣ ጉንጭ ማልፊያ እንደነበር እናውቃለን ። ሲኖዶስ ግን በጀት አጽድቆ ፣ ወንጀል አውግዞ የሚለያይ ሳይሆን ሰውን ለማጽደቅ ፣ ሽፍታውን ባሕታዊ ለማድረግ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የሚመክር ነው ። እንዴት እናውግዝ ብሎ ውግዘትን የቂምና የበቀል በትር የሚያደርግ ሳይሆን እንዴት የጠፋውን እንመልስ ብሎ የሳቱትን መንገድ የሚያሳይ ነው ። የጭካኔ በትር የሚያሳርፍ ሳይሆን የፍቅር እጅ የሚዘረጋ ነው ። ቤተ ክርስቲያን ልጆችዋ እየተራቡ ገንዘብ በማከማቸት የሚደሰት ሳይሆን ምእመናንን ከረሀብ አትርፎ ገንዘብን አሳንሶ የሚያይ ነው ። በኪራይ ሕንፃዎች የሚኮራ ሳይሆን ሕንፃ ሥላሴ የሆነውን ሰው የሚታደግ ነው ። ከቄሣሮች ጋር ለመስማማት ምን እንበል ? የሚል ፣ ላሸነፈ የሚያድር ሳይሆን ከተጠቁት ጋር የሚቆም ነው ። ለባለጠጎች እውቅና የሚሰጥ ሳይሆን ድሆችን ከችግር የሚያሳርፍ ነው ። ዓለም እየታመሰች የቅንጦት ውይይት ይዞ የእመቤታችን የድንግል ማርያም የዓይኗ ቀለም ጥቁር ነው ወይስ ሰማያዊ ፣ የቅዱስ ቍርባን ጽዋ ውስጥ ዝንብ ቢገባ ዝንቡ ይቀደሳል ወይስ ደሙ ይረክሳል ? እያሉ ይወያዩ የነበሩ የሐዋርያትን ስም የያዙ አባቶች እንደተነሡ በሰማይ ሰምተን ተገርመናል ። እኛ ሰይፍን ተደግፈን የሰበክነውን ወንጌል የወርቅ ዘንግ ይዘው መስበክ ለምን አቃታቸው ? የእነርሱ ዕረፍት የመጣው በእኛ ድካም መሆኑን ለምን ዘነጉት ? ብለን የሰማይ ማኅበረተኞች በሙሉ አዝነናል ።

የመጀመሪያው የሐዋርያት ሲኖዶስ እንደተፈጸመ ሁለተኛውን ሐዋርያዊ ጉዞዬን ቀጠልሁ ። ሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞ በሐዋ. 15፡36 እስከ ምዕራፍ 18፡22 ተመዝግቦ ተቀምጧልና ማየት ትችላለህ ። ማርቆስ እናቱ ናፍቃው ወዲህም መከራው አሰቅቆት ወደ ኋላ ተመልሶ ነበርና እኔም ቆራጥ ፣ ቆፍጣና ፣ ጊዜውን ሳይሆን ነፍሱን አስቀምጦ የሚዘምት ወታደር እፈልጋለሁና አዝኜበት ነበር ። ታዲያ ማርቆስ በመጀመሪያው ጉዞ ተለይቶን በሁለተኛው ጉዞ ልቀላቀላችሁ ብሎ መጣ ። በእርግጥ የሄደበት ጉዳይ የእናት ናፍቆትም ከክርስቶስ ፍቅር በላይ ፣ ሥጋዊ ዕረፍቱም ስለ ወንጌል ከሚቀበሉት ትግል በላይ አስደሳች አይደለምና ተመልሶ መጣ ። ጥሪ ያለው ሰው በፍቅርም በመከራም አሳብቦ ቢመለስም የሚሄድበት ቦታ የመቃብር ስፍራ ፣ ሕይወት የሌለበት መንደር ይሆንበታልና ተመልሶ ይመጣል ። ማርቆስም ተመልሶ መምጣቱ መልካም ቢሆንም ከልፍስፍስ ጋር መሰለፍ አልወድምና እንዳላይህ ብዬ አባረርሁት ። ሰው የሚመዘነው በዕድሜውና ባወቀው መጠን ነው የሚል ሰዋዊ መመዘኛ አልነበረኝም ። የእግዚአብሔር ቃል ሽማግሌውንና ወጣቱን እኩል ያስጠብባልና እገሌ ልጅ ነው እንደፈለገው ይኑር የሚባለውን ሥጋዊ ኀዘኔታ አልቀበልም ። በርናባስ ግን ማርቆስን ጥሎ መሄድ አልሆነለትም ። በዚህ ምክንያት ሊያሳምነኝ በሞከረ ቍጥር እኔ እየጠነከርሁ መጣሁ ። ከምወደው በርናባስ ጋርም እስክንከፋፋ ተጣላን ። በዚህ ጊዜ በርናባስ ማርቆስን ይዞ ወደ ቆጵሮስ ለመስበክ ሄደ ። እኔም ሲላስንና ጢሞቴዎስን ይዤ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቂያ ወጣሁ ። እግዚአብሔር ለበጎ አደረገውና አንድ ቡድን የነበረውን ፣ ሁለት ሐዋርያዊ ጉዞ የሚያከናውን ቡድን አደረገው ። አንድ ቡድን ቢሆን ኖሮ በአንድ ጊዜ ወደ ቆጵሮስም ወደ ሶርያም መሄድ አይሆንልንም ነበር ። እኔም ሲላስን ለመምረጥ ጢሞቴዎስን ለማጥመቅ የበቃሁት በማርቆስ ምክንያት ነው ። ማርቆስ እየበደለን የሚክሰን ሰው ነበር ። 

ሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞዬ ጢሞቴዎስን ያገኘሁበት ነው ። ይህ በዓላማ የሚመስለኝን አማኝ ፣ የሚታዘዝልኝን ልጅ ፣ ዘመኑን የሰጠ ድንግል ቤተ ክርስቲያን ያገኘችው በሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞዬ ነው ። ኋላ ላይም የኤፌሶን ጳጳስ አድርጌ ሾምሁት ። የግሪክ አብያተ ክርስቲያናት የተመሠረቱት በሁለተኛው ጉዞዬ ነው ። በዚህ ጉዞ መነሻ ያደረግነው አንጾኪያን ነበር ። ጉዞው ሶርያ ፣ ኪልቅያ ፣ ደርቤን ፣ ልስጥራን ፣ ፍርግያ ፣ ገላትያ ፣ ጢሮአዳ ፣ ሳሞትራቄ ፣ ናጱሌ ፣ ፊልጵስዩስ ፣ አንፊጶልያ ፣ አጶሎንያስ ፣ ተሰሎንቄ ፣ ቤርያ ፣ አቴና  ፣ ቆሮንቶስ  የተደረገ ነው ። በዚህ ጉዞ 16 ከተሞችን በወንጌል አገልግለናል ። ጉዞው የተጀመረው በ50 ዓ.ም ነው ። በዚህ ጉዞ የፊልጵስዩስ ፣ የተሰሎንቄና የቆሮንቶስ አብያተ ክርስቲያናት ተመሠረቱ ። 

ሦስተኛው ሐዋርያዊ ጉዞዬ በሐዋ. 18፡23 እስከ ምዕራፍ 21፡16 የተመዘገበ ነው ።  በዚህ ጉዞዬም  መነሻዬ አሁንም አንጾኪያ ናት ። ገላትያ ፣ ፍርግያን ፣ አሶን ፣ ሚሊጢን ፣ ኤፌሶን ፣ ቆስ ፣ ሩድ ፣ ጳጥራ ፣ ጢሮስ ፣ አካ ፣ ቂሣርያ በወንጌል ሲከለሉ ፣ በመጨረሻም ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞዬን ቀጠልሁ ። በዚህ ጉዞ 12 አገሮችንና ከተሞችን በወንጌል አገልግያለሁ ። ወደ ኢየሩሳሌም የሄድሁበት ዋነኛ ምክንያትም ከአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ያሰባሰብሁትን የገንዘብ እርዳታ ለማስረከብ ነው ። በዚያም በተነሣ ሁከት ታስሬ በ58 ዓ.ም ወደ ሮም ተወሰድሁ ። በሮምም የቁም እስረኛ ሁኜ ለሁለት ዓመታት ያህል ከቆየሁ በኋላ በቄሣር ችሎት ነጻ ነው ተብዬ ተለቀቅሁ ። ከዚህ ጊዜ በኋላ አራተኛውን ሐዋርያዊ ጉዞ አደረግሁ ። እስጳንያን የጎበኘሁት በዚህ በአራተኛው ጉዞዬ ነው ። በ64 ዓ.ም ኔሮን ቄሣር ሮምን ራሱ አቃጥሎ በክርስቲያኖች ላይ ስላሳበበ በ65 ዓ.ም እንደገና ለእስር ተዳርጌ ከሁለት ዓመት እስር በኋላ በ67 ዓ.ም. ሐምሌ አምስት ቀን በሮም ሰማዕትነትን ተቀበልሁ ። 

በሦስተኛው ጉዞዬ ወቅት እርዳታን ለኢየሩሳሌም ድሆች ለማድረስ መሄዴን እደሰትበታለሁ ።  የገጠመኝ ነገር ታላቅ መከራ ቢሆንም እውነትን በሚገጥመኝ ነገር ሳይሆን በእውነትነትዋ መለካት አለብኝ ብዬ አምን ነበር ። እውነት ከገጠመኝ በላይ ናት ። በዚያ ዘመን ከሰንበት አገልግሎት በኋላ በተወከሉ ሰዎች አማካይነት እርዳታ ለድሆች ይሰባሰብ ነበር ። የመጀመሪያ የእርዳታ ድርጅት የተመሠረተው በመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው ። ድሆችን የረሳች ቤተ ክርስቲያን በምጽአት ቀን በክርስቶስ ፊት ለመቆም ሞገስ የሌላት ቤተ ክርስቲያን ናት ። እናንተም ድሆችን በሚመለከት በጣም ቸልተኛና ጨካኝ እንደሆናችሁ ሰምተናል ። ብድር ለሚመልሱ ሰዎች ደግሞ እያነቃቸው እናጉርስ የምትሉ ፣ እከክልኝ ልከክልህ ማለትን የምትወዱ ሥጋውያን መሆናችሁን ሰምተን ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት አዝናባችኋለች ። ይግባኝ በማይጠየቅበት የፍርድ አደባባይ መልስ እንዳታጡ ድሆችን አስቡ ። ድሆች በክርስቶስ ፊት ጥያቄዎቻችሁም መልሳችሁም ናቸው ። ዳግም ወደ ምድር የመመለስና የመኖር ዕድል ቢገጥመኝ ተግቶ ወንጌልን መስበክንና ድሆችን መርዳትን አከናውን ነበር ። ሰማይ ደርሳችሁ ትልቅ ዋጋ ስትቀበሉ በምድር የሠራችሁት ያንስባችኋል ፣ እኛ ሠርተን ካነሰብን እናንተ ስንፍናን ጌጥ ያደረጋችሁት ፣ ሞልቃቃነት ከእግዚአብሔር እንደሚለይ የዘነጋችሁት ምን ሊሰማችሁ ይችላል ብዬ አስባለሁ” አለኝ ። እኔም በርግጥ ድሀን የምወደው በአፍ ነው ? ወይስ በተግባር ነው ? ብዬ ራሴን ጠየቅሁ ። 

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የካቲት 15 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ