የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጳውሎስን አገኘሁት /12/

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ መልእክታቱ ይተነትንልኛል ብዬ አስቀድሜ ብጠይቅም የረሳው መስሎኝ ነበርና ለማስታወስ ስሞክር አንድ ምሥጢር ብልጭ አለልኝ ። በዓለመ ነፍስ መርሳት እንደሌለ ፣ የፈጠረውንና ዕቅዱን የማይረሳውን እግዚአብሔር የሚያገለግሉ ወገኖች እንደማይረሱ ገባኝ ። በምድር ላይ የሚኖሩ ኑሮና ሕይወትን ፣ ምድርና ሰማይን ፣ ዓለምና ቤተ ክርስቲያንን ፣ እግዚአብሔርንና ሰውን ለመያዝ ስለሚሞክሩ ለመርሳት ይዳረጋሉ ። በሰማይ ግን ኑሮ ፣ ምድር ፣ ዓለም ፣ እንዲሁም ከንቱ የሆነው የሰው ይሁንታ/ሙገሳ የለም ። ኑሮ ባለመኖሩ መባከን ፣ ምድር ባለመኖሯ መርከስ ፣ ዓለም ባለመኖርዋ ከንቱነት ፣ ሰዋዊ ሙገሳ ባለመኖሩ ጉልበት መጨረስ የለም ። በሰማይ ለአንድ ጌታ ማደር ስላለ አሳብ ሁሉ ያርፋል ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልእክታቱን እንዴት እንደ ጻፈ ለመናገር ሲዘጋጅ እኔም ከሮሜ መልእክቱ ቢጀምር ብዬ አሰብሁ ። እርሱም ቀና ነውና ደስተኛ ሆነ ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን በአንደበት ሳይሆን በልባችን እናወጋና እንግባባ ነበር ። ወደ ምድር ስመለስ ተናግሬ የማልግባባቸውን ሰዎች አሰብሁና አዘንሁ ። እንደገናም ይህ ዓለም ስላለኝ ፣ ጉዞዬን ስፈጽም ተመልሼ ስለምመጣ ደስ አለኝ ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሮሜ መልእክቱ መናገር ጀመረ፡- “በርግጥ እኔ እንኳን ከመጀመሪያው መልእክቴ ከገላትያ መልእክት ልጀምርልህ አስቤ ነበር ። እየመረጥን ያለነው ከመልካምና ከመልካም ነውና ከየትኛውም ብንጀምር ደስተኛ ነኝ ። የመልእክታቴን ቅደም ተከትል ለማወቅ ከፈለግህ  የመጀመሪያው የገላትያ መልእክት ፣ ሁለተኛው አንደኛ ተሰሎንቄ ፣ ሦስተኛው ሁለተኛ ተሰሎንቄ ፣ አራተኛው አንደኛ ቆሮንቶስ ፣ አምስተኛ ሁለተኛ ቆሮንቶስ ፣ ስድስተኛው የሮሜ መልእክት ፣ ሰባተኛው ወደ ቆላስይስ ሰዎች የተላከ ፣ ስምንተኛው የፊልጵስዩስ መልእክት ፣ ዘጠነኛ የፊልሞና መልእክት ፣ አሥረኛው ወደ ጢሞቴዎስ የተላከ አንደኛው መልእክት ፣ አሥራ አንደኛ የኤፌሶን መልእክት ፣ አሥራ ሁለተኛ የቲቶ መልእክት ፣ አሥራ ሦስተኛ ሁለተኛ ጢሞቴዎስ ፣ አሥራ አራተኛ ወደ ዕብራውያን ሰዎች ናቸው ። መልእክታቱንም የጻፍኩበት ዘመን ከ48-66 ዓ.ም ገደማ ነው ። መልእክታቱም በአንደኛ የወንጌል ጉዞ የገላትያን መልእክት ፣ በሁለተኛ የወንጌል ጉዞዬ አንደኛና ሁለተኛ ተሰሎንቄ እንዲሁም አንደኛና ሁለተኛ ቆሮንቶስ ፣ በሦስተኛ የወንጌል ጉዞዬ ዋዜማ ላይ የሮሜን መልእክት ጽፌአለሁ ። ሌሎቹን መልእክቶች በሮም በእስራትና በቁም እስረኛነት ሁኜ ጽፌአለሁ ። የእሥራት መልእክቶቼ የኤፌሶን ፣ የቈላስይስ ፣ የፊልጵስዩስ ፣ የፊልሞና መልእክታት ናቸው ። ከእስር ከተፈታሁ በኋላ ደግሞ አንደኛ ጢሞቴዎስን ቲቶን ስጽፍ በሁለተኛው እስራቴ ደግሞ ሁለተኛ ጢሞቴዎስን ፣ በመጨረሻም አሳሳቢ የነበረውን ሁኔታ ለመግፈፍ የዕብራውያን መልእክቴን ጽፌአለሁ ።

መልእክታቱን የጻፍሁት ለአብያተ ክርስቲያናት ፣ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ለግለሰቦች ነው ። ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች የጻፍሁት ለጢሞቴዎስና ለቲቶ ነው ። ለግለሰብ የጻፍሁት ለፊልሞና ነው ። ለመሠረትኋቸው አብያተ ክርስቲያናት ስጽፍ ላልመሠረትኋቸው አብያተ ክርስቲያናትም ጽፌአለሁ ። እነርሱም ሮሜና ቈላስይስ ናቸው ። መልእክታቱን የጻፍሁት ለማበረታታት ፣ ስህተትን ለማረም ፣ ወደ ኋላ እየተመለሱ ያሉትን ለመገደብ ፣ የተጣሉትን ለማስታረቅና አገልጋዮችን አይዟችሁ ለማለት ነው ።

እኔ ከሞትሁ በኋላ ቤተ ክርስቲያንን የተረከቡ አባቶች የሮሜ መልእክቴን የመጀመሪያ አድርገው በማስቀመጣቸው ደስ ብሎኛል ። ሌሎቹ መልእክታት ወቀሳና ተግሣጽ ፣ ወቅታዊ ጉዳይ አለባቸው ።፣ የሮሜ መልእክቴ ግን ወቀሳ የለበትም ። ሙሉና ወጥ የሆነ የጽድቅ መልእክት ነው ። ይህን ከፊት ማድረጋቸው በወቀሳ መጀመር ተገቢ አይደለም ብለው ነውና ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ ። ሮሜ ወይም ሮም የኢጣልያ ዋና ከተማ ናት ። የተመሠረተችውም ከክርስቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው ምእተ ዓመት ገደማ ነው ። ብዙዎችን ያማከለ ሥልጣንን ለመከተል ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ጉዞ የጀመረችው ሮም ይህ የአስተዳደር ዘይቤዋ በሦስተኛው ምእተ ዓመት ፈራረሰ ። በዚህ ምክንያት አገሪቱ በእርስ በርስ እልቂትና በመሳፍንት አገዛዝ ስትታመስ ከቆየች በኋላ አገሪቱን አንድ አድርጎ የሚገዛ አንድ ጠንካራ መሪ ሲፈለግ ጁሊየስ ቄሣር ተገኘ ። አገሪቱም በእርሱ አስተዳደር ብትረጋጋም ቆይቶ ግን በተቃዋሚዎች ተገደለ ። ከእርሱ ቀጥሎ አውግስጦስ ቄሣር ነገሠ ፣ አውግስጦስ ቄሣር ዓለም ሁሉ እንዲጻፍ ትእዛዝ ያወጣ ሲሆን ጌታችን የተወለደውም በእርሱ የሥልጣን ዘመን ነው ። ይህ አውግስጦስ ቄሣር እስከ 14 ዓ.ም. አስተዳድሮ የሥልጣን ዘመኑ አበቃ ። ከእርሱ በኋላም ጢባርዮስ ቄሣር እስከ 37 ዓ.ም. ድረስ አስተዳደረ ። ልብ አድርግ ጌታችን የሞተው በጢባርዮስ ቄሣር የሥልጣን ዘመን ነው ። ከጢባርዮስ ቀጥሎ ቀላውዴዎስ ቄሣር ከ41-54 ዓ.ም ነገሠ ። ከ54 ዓ.ም. እስከ 68 ዓ.ም ደግሞ እኔን የገደለኝ ኔሮን ቄሣር ነገሠ ።

የሮም መንግሥት ሰላምን በማስፈኑ ፣ ፍርድን በመስጠቱ ፣ ለጊዜው ባሕልና ሃይማኖትን ባለመንካቱ ተወዳጅ ነበር ። ክርስትና የተመሠረተውም የተሰበከው በዚህ ሮም ከእንግሊዝ እስከ መካከለኛ ምሥራቅ እስከ ሰሜን አፍሪካ በምትገዛበት ዘመን ነው ። በአምስተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻም እዚህ ግባ የማይባል የሽፍቶች ቡድን የሮምን መንግሥት ጣለው ። በዚህ ምክንያት የሮም አወዳደቅ እያላችሁ ትተርካላችሁ ።

በዚህች በሮም ደማቅ ከተማ ለሚኖሩ ምእመናን የጻፍኩት የሮሜ መልእክት ተብሎ ይጠራል ። እኔ እነርሱን እያሰብሁ ብጽፍም መንፈስ ቅዱስ ደግሞ እናንተን እያየ ያጽፈኝ ነበር ።”

እኔም ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ ታሪኮችን ስለነገረኝ ፣ ታሪክ የመገንዘብ አቅሜን ተጠራጠርሁትና ትንሽ ለማሰላሰል ከዚያም ወደ ሮሜ መልእክት ጭብጥ አሳብ ለመግባት ጠየቅሁት ። እርሱም ደስ እያለው እሺ አለኝ ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ