የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጳውሎስን አገኘሁት /13/

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሮሜ መልእክት ሊነግረኝ ሲዘጋጅ አእምሮዬ ቅዱስ አውግስጢኖስን አስታወሰ ። ቅዱስ አውግስጢኖስ፡- “በአንተ ማረፍ ማን ይሰጠኛል ? ልቡናዬ ይጥለቀለቅ ዘንድ ፥ ክፋቴን እረሳ ዘንድ ፥ አንተን ብቸኛው ሀብቴን አቅፍ ዘንድ ! ወደ እኔ መግባትህን ማን ይሰጠኛል ? አንተ ለእኔ ምንድነህ ? እንድናገር በርኅራኄህ አንደበቴን ዳስሰው ፥ እንዳፈቅርህ ግድ የምትለኝ ፥ ምላሽ ባልሰጥ ቍጣህ የሚነደውና ከለላ የሚያሳጣኝ ፥ እኔ ለአንተ ምንድነኝ ? አንተን አለማፍቀር ራሱ ጉስቍልና አይደለምን ? ኦ ! አቤቱ ጌታዬ አምላኬ ፥ በርኅሩኅነትህ መልስልኝ ፥ አንተ ለእኔ ማን ነህ ? እሰማህ ዘንድ ተናገረኝ ፥ እነሆ በፊትህ የልቡናዬ ጆሮዎች ተከፍተዋልና ፥ አቤቱ ጌታዬ ክፈትና ‘ለነፍሴ እኔ ነኝ መድኃኒትሽ’ በላት ።  ይህን ድምፅ በሩጫ ተከትዬ በመጨረሻም አንተን ልይዝህ እፈልጋለሁ ፤ ሰምቼህ ወደ አንተ ልሩጥ ፥ በአንተም ላይ ራሴን ልጣል ፥ እባክህ ፊትህን ከእኔ አትሰውር ፤ ላለ መሞት ልሙት ብቻ ፊትህን ልይ” ያለው በውስጤ ይመላለስ ነበር ። ቅዱስ አውግስጢኖስ በዓለም ፍልስፍና ተይዞ ከክርስትና ተቃራኒ ሁኖ ሲኖር እናቱ ቅድስት ሞኒካ ስለ እርሱ ብርቱ እንባ እያፈሰሰች ትጸልይ ነበር ። ልጅዋ ወደ ሕይወት መንገድ እንዲመጣም የሮሙን ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አምብሮስን በእንባ ትጠይቀው ፣ ያስተምረው ዘንድም ትማጸነው ነበር ። ቅዱስ አምብሮስም “ይህን ያህል እንባ የፈሰሰለት ልጅ ጠፍቶ አይቀርም” በማለት ተስፋ ሰጣት ። ቅዱስ አውግስጢኖስ አንድ ቀን የሮሜን መልእክት ምዕራፍ 13፡11፡- “ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና ። ሌሊቱ አልፎአል ፥ ቀኑም ቀርቦአል ። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ” የሚለውን ሲያነብ ልቡ ተነካ ወደ ክርስትናም ተመለሰ ። ዛሬ ሰሜን አፍሪካ አልጀሪያ ብለን የምንጠራት በዚያን ጊዜ አጠራርዋ ሂፖ ተብላ የምትጠራው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነ ። 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመልእክቱ ፍሬ የሆነውን ቅዱስ አውግስጢኖስን ምነው ባወቀው ብዬ ሳስብ ሐዋርያው፡- “ሰዎች አይሰሙም ብለህ መናገር አታቁም ፣ መስማት በፈለጉ ቀን እንዲጠቅማቸው ዛሬ በውስጣቸው መልእክት አስቀምጥ” ሲለኝ ደነገጥሁ ። ለካ ለመስማትም ፣ የሰሙትን ለማስተዋልም ጊዜ አለ ብዬ ማሰብ ጀመርሁ ። ሐዋርያው ወደ ሮሜ ሰዎች መልእክቱን የጻፈው በ56 ዓ.ም ገደማ ነው ። ቅዱስ አውግስጢኖስ የነበረው በ4ኛው ክፍለ ዘመን ነው ። ዘመናት በረዘሙ ቍጥር እውነትን ከማዳፈን እንዲጠራ ያደርጉታል ። ዘመናት አመድ ቢለብሱም እውነትን ግን መቅበር አይችሉም ብዬ ማሰብ ጀመርሁ ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለ ሮሜ መልእክት ሊተነትንልኝ ተነሣ፡- 

“በሮም የነበረችው ቤተ ክርስቲያን በበዓለ ሃምሳ በጴጥሮስ ስብከት ባመኑ የሮሜ ሰዎች ማለትም በሮም በሚኖሩ አይሁዳውያን የተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን ናት ። ጥንታዊነቷም ክርስትና መላውን እስራኤል ሳይከልል በሮሜ ቤተ ክርስቲያን ተቋቁማ ነበር ። በሮሜ ቤተ ክርስቲያን አይሁዳውያንና አሕዛብ በክርስቶስ አንድ ሆነው በአንድነት ያመልኩ ነበር ። እምነታቸውም በዓለም ሁሉ ተሰምቶ ማመንማ እንደ ሮሜ ሰዎች ነው እየተባለ ሲነገር ወሬ ሰማሁ ። በዚያን ጊዜ በግሪክ ደቡባዊ ግዛት በአካይያ በቆሮንቶስ ከተማ በጋይዮስ ቤት እንግድነት ተቀምጬ ሳለሁ ወሬ ሰማሁ ። ቆሮንቶስ የወደብ ከተማ ነበረችና በወደብ ከተማ የዓለም ወሬ ሁሉ ይሰማል  ። በዚያን ጊዜም የሮሜ ሰዎች እምነታቸው በዓለም ሁሉ ተሰምቶ ነበር ። እኔም ወጥ የጽድቅ መልእክት ልጽፍላቸው ፈለግሁ ። በመካከላቸውም አይሁድነትና አሕዛብነት የመፈራረጃ ርእስ እንዳይሆን ላሳስባቸው ፈለግሁ ። የሮሜ መልእክት በውስጡ ያለው ጭብጥ አሳብ ወንጌል በዓለም ላይ ካሉት ኃይላት የበለጠ መሆኑን መናገር ነው ። በወንጌል ደግሞ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጧል ። በዓለም ላይ የአገራት ፣ የባሕላት ፣ የጎሣዎች የራሳቸው የሆነ ጽድቅ አለ ። አንዳንዱ እንግዳ ተቀባይ ነው ፣ ነውረኛ ተግባርን ግን የሚያጸድቅ ነው ። ሌላውም ማኅበረሰብ ቁጥብ ነው ፣ ፍቅር ግን የሌለው ነው ። የእግዚአብሔር ጽድቅ ግን ምሉዕ ነው ። በዚህ ጽድቅ ውስጥም የእግዚአብሔር ልጅ ሰው መሆኑ ፣ ጽድቅን ሁሉ መፈጸሙ ፣ ኃጢአተኞችን ማጽደቁና የቅድስና አቅም መሆኑን ተገልጧል ።  

የሮሜ መልእክትም መላው ዓለም ኃጢአተኛ መሆኑን ይናገራል ። አሕዛብ የሕሊናን ሕግን ሽረው ፣ አይሁድ የጽሑፉን ሕግ ሽረው በኃጢአት መውደቃቸውን ፣ እኔ መልካም ነኝ የሚል እስከማይኖር ድረስ ሰው ሁሉ በኃጢአት መያዙን ያመለክታል ። ዓለሙ ሁሉ በአንድ ዓይነት በሽታ ከተያዘ መድኃኒቱም አንድ መሆን አለበት ። ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ቤዛ ሁኖ መጣ ። ኵነኔውን ያመጣው የሙሴ ሕግ ቢሆን ኑሮ አይሁድ ተኰንነው አሕዛብ ይድኑ ነበር ። ጽድቅም በሕግ በኩል ቢሆን ኖሮ አይሁድ ድነው አሕዛብ ይኰነኑ ነበር ። ኵነኔው የመጣው በአዳም በደል ነውና ከአዳም የተወለዱ ሁሉ በዚህ ኵነኔ ተይዘዋል ። ከዚህም ሊያድን የሚችል አልተገኘምና የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ ። እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ሊያሰኘን እርሱ የሰው ልጅ ወደ መባል ዝቅታ መውረድ ነበረበት ። ከፍ ሊያደርገን ዝቅ አለ ። ሰማያዊ ሊያደርገንም ምድራዊ ሆነ ። 

የሮሜ መልእክት አሁንም የሚናገረው ዓለሙን ሁሉ ሊያድን ስለተገለጠው ስለ ክርስቶስ ነው ። በአንድ አዳም እንደ ተኰነንን ካመንን በአንድ በክርስቶስ ጽድቅ እንደምናገኝ ማመን አለብን ። አእምሮአችን ኵነኔን እየተቀበለ ጽድቅን መቀበል ሊያቅተው አይገባም ። ከአዳም በደል የክርስቶስ ጸጋ ይበልጣል ። ቀዳማዊ አዳም ያጠፋውን ይክስ ዘንድ ክርስቶስ ዳግማዊ አዳም ሆኖ መጣ ። ጠብታ ቆሻሻ በጠብታ ውኃ አትጠራም ። የእኛም ኃጢአት በበዛው በክርስቶስ ጸጋ ታጠበ ። መዳናችን በፍጡር ያልሆነው ፣ ሰው በሆነው አምላክ በክርስቶስ የሆነው ኦሪት “በፍጡር የሚያምን ርጉም ይሁን” ብላለችና ከርግማን ለመዳንም ነው ። ደግሞም ማዳን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ግብር ነው ። ከእርሱ በቀርም የሚያድን የለም ። በዚህ ምክንያት ሰውን ለማዳን የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሆነ ። 

5500 ዘመን ሲጠበቅ የነበረው ፣ በአበው ተስፋ ፣ በነቢያት ትንቢት ፣ በአሮን አገልግሎት ፣ በእንስሳት መሥዋት ፣ ሲመሰል ሲነገር ፣ ሲናፈቅ የነበረው መዳን የራሱ ዓላማ አለው ። ዓላማውም ቅድስና ነው ። ቅድስና ለሚመለከቱን ሰዎች ፣ ለማኅበራዊ ከበሬታ ሳይሆን ቅድስና ለእግዚአብሔር ነው ። ቅድስናን መለማመድ የሚገባው አገልጋዮች ስለሚያዩንም አይደለም ። አገልጋይ የቅድስና ሰባኪ እንጂ ነጥብ ያዥ አይደለም ። ቅድስና ለእግዚአብሔር መሆኑን ኦሪትም አውጃለች ። እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና ልጆቹ እርሱን እንዲመስሉት ይፈልጋል ። እግዚአብሔርን የምንመስለውም በቅድስና ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአት አውጥቶን ኃጢአት ውስጥ ፣ ካልሠራነው ከአዳም ኃጢአት አድኖን ከምንሠራው ከዛሬው ኃጢአት ውስጥ አይተወንም ። ቅድስናም መንፈስ ቅዱስ በአማንያን ሰውነት ውስጥ የሚያከናውነው ተግባር ነው ። 

የሮሜ መልእክት ሌላው አሳቡ የግልግል መድረክ ነው ። አይሁድ አሕዛብን ሕግ የለሽ ቢሉ ሕጉ በእነርሱም ፈራጅ ሆኖ እንደ ቆመ አላወቁም ነበር ። አሕዛብም ሕግን ማወቅ ምን ይጠቅማል እንዳይሉ የእግዚአብሔር ቃል የተሰጣቸው አይሁድ ከቃሉ የተነሣ ክቡራን ናቸው ። ደግሞም አሕዛብ ወደ ክርስትና ሲገቡ አይሁድ ቢከፉም እግዚአብሔር ማዳኑ ለሁሉ ነው ። አይሁድ ክደው አሕዛብ ቢያምኑም ለጊዜው ያኮረፉ እንጂ ክደው የሚቀሩ አይደሉም ። አይሁድ ታላቅ ልጅ ናቸውና ለታናሽ ልጆች ለአሕዛብ ማዘን ፣ አሕዛብም እንደ ታናሽ ልጅ ጨካኝ ከመሆን መራራት ይገባቸዋል ። እግዚአብሔር ግን በማይመረመር ጥበቡ አይሁድን ያድናል ። አይሁድ ማለትም ሕዝበ እግዚአብሔር ማለት ነውና አይሁድ ብሎ መሳደብ ኃጢአት ነው ። ደግሞም የአብርሃም ልጆችና የቃል ኪዳኑ ወራሾች ናቸውና እነርሱን መርገም ርግማን ያመጣል ። የሚባርኩህን እባርካለሁ ብሎ ለአብርሃም ቃል ኪዳን ገብቷልና አይሁድን ስንባርክ እንባረካለን ። 

በመጨረሻም ክርስቲያን በሕሊናው ፊት በቅንነት ፣ በአገር ውስጥ በዜግነት ግዴታ ፣ በቤተ ክርስቲያን የሌሎችን ክብር በመጠበቅ መኖር እንደሚገባው ከምዕራፍ 12 እስከ 14 ገልጫለሁ ። ይህን የሮሜን መልእክት የጻፍኩበት ዓላማ ቅድም እንዳልኩህ ወጥ የጽድቅ ትምህርት እንዲያገኙ ፣ አይሁድና አሕዛብ በስምምነት እንዲኖሩ ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ይዤ የምሄደው እርዳታ ድሆች የሆኑት ወገኖች በቀና ልብ እንዲቀበሉት የሮሜ ሰዎች በጸሎት እንዲያግዙኝ ፣ ኋላም የምድር ጥግ የምትሆነውን እስጳንያን ወይም ስፔንን ለመጎብኘት አቅጃለሁና በአራተኛው ሐዋርያዊ ጉዞዬ የገንዘብ እርዳታ እንዲያደርጉልኝ ለመጠየቅ ነው ። እንዳሰብኩትም በሐዋርያነት ሳይሆን በእስረኝነት ወደ ሮም ገባሁ ። የታሰርኩትም ስለ ወንጌል ነውና ሰንሰለቱም ሰባኪ ነበር ። ሰባት ዓመታት የሚሆነውን ጊዚ በሮም አሳልፌ በሰማዕትነት ተጋድሎዬን ፈጸምሁ ። 

ልጄ የሮሜን መልእክት እንዲህ በአጭር ሰዓት ተንትኜ የምፈጽመው አይደለምና መምህራንን እየጠየቅህ ትርጓሜውን ተረዳ ።

እኔም ዝቅ ብዬ እጅ ነሣሁ ። በረከት እንዲሰጠኝ ሐዋርያውን ለመንኩት ። እርሱም፡- “የእግዚአብሔር አብ ጸጋ ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኅብረት ካንተ ጋር ይሁን” ብሎ ባረከኝ ። እኔም “አሜን” አልሁ ። 

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም.

የዲያቆን አሸናፊ መኰንንን ትምህርቶችና ስብከቶች ለመከታተል ከስር የተቀመጡትን ማስፈንጠሪያዎች ይመልከቱ፡—

https://t.me/Nolawii

https://t.me/nolawisebketoch

https://www.facebook.com/ashenafi.mekonnen.357

YouTube player

http://ashenafimekonen.blogspot.com/

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ