የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጳውሎስን አገኘሁት /14/

 

ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደ መሠረተ ማሰብ ጀመርሁ ። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተው ሁለተኛውን ሐዋርያዊ ጉዞ እያገባደደ ባለበት ወቅት ነው ። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያንን ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ያህል ተቀምጦ አገልግሏል ። ግሪክ ሰሜናዊና ደቡባዊ የሆኑ ሁለት ታላላቅ ግዛቶች አሉአት ። ሰሜኑ መቄዶንያ ሲባል በዚህ ግዛት ውስጥም የቤርያ ፣ የተሰሎንቄ ፣ የፊልጵስዩስ አብያተ ክርስቲያናት ሲገኙ በደቡብ ትልቅ ግዛት በአካይያ ደግሞ የቆሮንቶስ የክንክራኦስ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ ። የአካይያ ዋና ከተማም ቆሮንቶስ ነበረች ። ቆሮንቶስ እንደ ኤፌሶን የወደብ ከተማ ስትሆን የኤፌሶን አቻ የምትሆን ውብ ከተማ ነበረች ። ኤፌሶን በዛሬዋ ቱርክ ግዛት ስትገኝ ቆሮንቶስ ደግሞ በግሪክ ግዛት ውስጥ ትገኛለች ። ኤፌሶንና ቆሮንቶስ በቅርብ ርቀት በመርከብ ይገናኛሉ ። በዚያ ዘመንም ከኤፌሶን ወደ ቆሮንቶስ እየተዘዋወሩ መኖር የተለመደ ነበር ። ኤፌሶንም ቆሮንቶስም በዚያ ዘመን ሁለቱም የሮም ግዛቶች ነበሩ ። ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ሲመሠርት በብዙ ችግር ፣ በአይሁዳውያን ተቃውሞ ነበር ። ፊቱንም ወደ አሕዛብ ሲመልስ ከአረማዊነት ወደ ክርስትና የመጡት መሠረት ስላልነበራቸው አስቸግረውት ነበር ። 

ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ መልእክቱን የጻፈው በኤፌሶን ተቀምጦ ሳለ ነው ። የጻፈውም በሁለት ምክንያቶች ሲሆን የመጀመሪያው በቤተ ክርስቲያኒቱ የነበረውን የሥነ ምግባር ችግር መስማቱ ነው ። ሁለተኛው ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት የተነሡትን ጥያቄዎች በደብዳቤ ጽፈው መልእክተኞች ይዘው በመምጣታቸው ለዚያ መልስ ለመስጠት አንደኛ ቆሮንቶስን ጽፏል ። አንደኛ ቆሮንቶስን አንደኛ ብለን የጠራነው የመጀመሪያው መልእክት ስለጠፋ ነው ። በመጀመሪያው መልእክቱ ሐዋርያው ስለ ሴሰኝነት ብርቱ መልእክት አስተላልፎ ነበር ። ይህም “ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጻፍሁላችሁ” ባለው ይታወቃል ። /1ቆሮ. 5፡9 ።/ ይህ መልእክት ጠንካራ ከመሆኑ የተነሣ የቆሮንቶስ ምእመናን አጥፍተውት ሊሆን ይችላል ። ቆሮንቶስ ከምዕራብና ከምሥራቅ ለሚመጡ ዋነኛ ወደብ ነበረች ። ከምሥራቅ ከእስያ ፣ ከሶርያ ፣ ከእስራኤል ለሚመጡ ፣ ከምዕራብ ከኢጣልያ ፣ ከእስፔን ለሚመጡ መገናኛ ወደብ ነበረች ። በሮማ ግዛትም ዋነኛ መተላለፊያ ምዕራብና ምሥራቅን የምታገናኝ የባሕር መስመር ነበረች ። በዚህች ከተማም በጳውሎስ ዘመን ከ600 ሺህ በላይ ሕዝብ ይኖር የነበረ ሲሆን ከከተማዋ ታላቅነት የተነሣም የሮማው ንጉሥ ምክትል ቆንሲል መቀመጫ ነበረች ። ይህች ከተማ ነጻ ቀጠና ስለነበረች ከተለያየ ዓለም የሚመጣው መንገደኛ ያርፍባታልና ብዙ ባሕልን በየቀኑ ታስተናግድ ነበር ። ከፍተኛ የንግድ መተላለፊያ በመሆንዋም ብዙ ባለጠጎች ነበሩባት ። የመላው ዓለም ወሬም በዚህች ከተማ ይሰማ ነበር ። በዚህች ከተማ የአፍሮዲቴ የተባለ ጣዖት ይመለክ ስለነበር ለአምልኮቱ አስፈጻሚ ካህናት በፈቃዳቸው ራሳቸውን ለዝሙት የሰጡ አንድ ሺህ ሴተኛ አዳሪዎች ነበሩባት ። 

የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በዚህች ታላቅ ከተማ ጥቂት የነበሩ ፣ በወቅቱ ተቀባይነትና ክብር አግኝተው በነበሩ አይሁዳውያን የተጠሉ ፣ ብዙ ድሆች የነበሩባት ቤተ ክርስቲያን ናት ። በዚህች ቤተ ክርስቲያን ባለጠጎች የነበሩ እንዲሁም የከተማዋ መጋቢ ወይም ከንቲባ አባላት እንደ ነበሩ አይረሳም ። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ችግሮች ውስጥ ስታልፍ አንድ ሰውም እኔ አለቃ ነኝ በማለት የሐዋርያው የጳውሎስን ሥልጣን መጋፋትና ምእመናኑን ማሳደም ጀምሮ ነበር ። በዚህች ቤተ ክርስቲያንም የአባቱን ሚስት የእንጀራ እናቱን ያገባ ሰው ነበር ። ይህች ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተች ገና አምስት ዓመት በቅጡ ያልሞላት ስትሆን ሐዋርያው ጳውሎስ ቀሎዔ የተባለች እመቤት ባሮች የሆኑ ሰዎች ስለቤተ ክርስቲያኒቱ የመከፋፈል ሁኔታ ለጳውሎስ ነግረውት ነበር ። መልእክቱንም የጻፈበት ዓላማ የመጀመሪያው ከቀሎዔ ቤተሰብ ያሉትን ጥፋቶች መስማቱ ሲሆን ሁለተኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ጥያቄአቸውን በጽሑፍ አድርገው ለጳውሎስ መላካቸውነው ። የጥያቄውንም ደብዳቤ ይዘው የመጡት እስጢፋኖስና ፈርዶናጥስ አካይቆስም የተባሉ ወኪሎች ናቸው ። 1ቆሮ. 7፡1 ፤ 16፡17 ። 

ሐዋርያው ይህን መልእክት በኤፌሶን ሁለት ዓመት ተቀምጦ በነበረበት ጊዜ ጽፎታል ። መልእክቱም በ55 ዓ.ም ገደማ ተጽፎአል ። መልእክቱም ተግሣጽ ፣ የጥያቄዎች መልስና ለኢየሩሳሌም ድሆች ስለሚዋጣው እርዳታ የሚመለከት ነው ። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያውና ትልቁ ችግራቸው መለያየት ነው ። ይህም የዓለም ጥበብ በውስጣቸው እንደ ተስፋፋ ያመለክትና ከንቱ መሆኑንም ይገልጥላቸዋል ። የዓለም ጥበብ ከፋፍለህ ግዛ ነው ። የእግዚአብሔር ጥበብ ግን አንድነትን የሚወድ ነው ። በዚህች ቤተ ክርስቲያን አራት ዓይነት ቡድኖች ተነሥተው ነበር ። የጳውሎስ ነኝ ፣ የአጵሎስ ነኝ ፣ የኬፋ ነኝ ፣ የክርስቶስ ነኝ የሚሉ ቡድኖች ነበሩ ። የጳውሎስ ነኝ የሚሉት መሥራቹ እርሱ ነው በሚል ስሜት ነው ። የአጵሎስ ነኝ የሚሉት አጵሎስ ሊቅና ከጳውሎስ ቀጥሎ ቤተ ክርስቲያኒቱን የመራ በመሆኑ ነው ። የኬፋ ነኝ የሚሉት የአይሁድ መምህር ኬፋ የተባለው ጴጥሮስ ነውና ወደ ኦሪት ያዘነበሉት ናቸው ። የክርስቶስ ነኝ የሚሉት ደግሞ ከሁሉም የበላይ ክርስቶስ ነውና እኛ የክርስቶስ ነን ብለዋል ። የክርስቶስ ነኝ የሚሉትም በቡድን ስሜት ነውና የተመደቡት ከክፉ ነው ። 

ከምዕራፍ አንድ እስከ አራት ስለመከፋፈላቸው ፣ ከምዕራፍ አምስት እስከ ስድስት በመካከላቸው ስለተገኘው ዝሙት ፣ በዓለም ፍርድ ቤት ስለመካሰሳቸውና ስለ ዝሙት ጠንቅ ይናገራል ። ከምዕራፍ ሰባት እስከ አሥራ አምስት ለጥያቄዎች መልስ ሲሆን ስለ ጋብቻና ድንግልናዊ ሕይወት ፣ ለጣዖት የተሠዋ ምግብን ስለመብላት ፣ ስለ ቅዱስ ቍርባን ፣ ስለጸጋ ስጦታዎች አጠቃቀም ፣ ስለሴቶች ድርሻ ፣ ስለ ትንሣኤ ሙታን ይናገራል ። በመጨረሻው ምዕራፍ በምዕራፍ 16 ደግሞ ስለ ኢየሩሳሌም ድሆች የእርዳታ መዋጮ ፣ ስለወደፊት እቅዱና ስንብት ሰላምታ ተጽፎአል ። 

ቀለሜንጦስ የሮም ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሆኖ በ88 ዓ.ም ገደማ የተሾመ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የታወቀ አባት ነው ። ይህም ቀለሜንጦስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የጻፈው ደብዳቤ ቀዳሚ ነው ። ይህን መልእክት ለመጻፍ ያነሣሣው ሐዋርያው ጳውሎስ ሲታገልለት የነበረው የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እርስ በርስ አንድ አለመሆን በቀለሜንጦስ ዘመን አገርሽቶ ነበርና ምእመናን መሪዎቻቸውን እስከማውረድና ማባረር ደርሰው ነበር ። “ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይቀርም” እንዲሉ ። ቀለሜንጦስ ከሮም ሁኖ የጻፈው ደብዳቤ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ወደ አንድነትና ሥልጣንን ወደ ማክበር እንድትመለስ የሚያስተምር ነው ። በዚህ መልእክት ውስጥም ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ማስተማሩን ፣ ቅዱስ ጳውሎስም ወደ ስፔን ሄዶ ወንጌልን መስበኩን ይናገራል ። ይህ መልእክትም በየሰንበቱ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ይነበብ ነበር ። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ጳውሎስ እስከ ቀለሜንጦስ ብዙ አገልጋዮችን ያደከመች ነበረች ።

አንደኛ ቆሮንቶስ በውስጡ የአንድነትን መልእክት የያዘ መለያየትም ከእግዚአብሔር ጥበብ የወጣ መሆኑን ይናገራል ። እንዲሁም የተለያዩ ስህተቶችን ይገሥጻል ። ጋብቻን በሚመለከት እርስ በርሳቸው በአንድነት እንዲኖሩና አንዱ ላንዱ መቀደስ ምክንያት እንደሚሆን በመናገር ያላመኑ ባሎች የነበሩአቸውን ያጽናናል ። እንዲሁም የድንግልናዊ ሕይወት የተሻለና ዘመንን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ ብዙ ሩጫ ለጌታ ለመሮጥ አስፈላጊ መሆኑን ያትታል ። ሁለቱም ግን ፈቃድ እንጂ ግዴታ እንዳይደሉ ያሳውቃል ። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የዘመኑን ሥልጣኔ በመጠቀም ሴቶች በጉባዔ ወንዶችን መናገርና መዝለፍ ያበዙ ነበርና ይህንንም ገሥጾአል ። ቆሮንቶስ ብዙ ጣዖታትና አረማውያን የነበሩባት ከተማ ናት ። እያንዳንዱ ሰው መሥዋዕት ያቀርብ ነበር ። በልደትም በሰርግም የሚቀርበው መሥዋዕት ብጣሽ ሥጋ ያሳርጉና ተረፈ መሥዋዕቱ ለካህናት ይሰጥ ነበር ። ካህናቱም ሥጋውን ገበያ አውጥተው ይሸጡ ነበር ። በዚህ ምክንያት በከተማው ላይ ይሸጥ የነበረው ሥጋ የሚበዛው ለጣዖት ከተሠዋው የተረፈ ነበርና ክርስቲያኖች ለመብላት ተቸግረው ነበር ። ሐዋርያውም ለዚህ መልስ ይሰጣቸዋል ። ቅዱስ ቍርባንና አጋፔ በተባለው የፍቅር ግብዣም ድሆችን ማግለል ተከስቶ ነበርና ለዚህም ሐዋርያዊ ምክር ይሰጣል ። በጸጋ ስጦታ አጠቃቀማቸውም ዘላን ነበሩ ። ጸጋን ማገልገያ ሳይሆን መወዳደሪያ አድርገውት ነበር ። ከሁሉ የሚበልጠው ጸጋም ፍሬም ፍቅር መሆኑን ሐዋርያው ይነገራል ። ትንሣኤ ሙታንን የሚክዱ ተነሥተው ነበርና ለዚህም በቂ ምላሽ በ15ኛው ምዕራፍ ላይ ይሰጣል ። በመጨረሻው ሰላምታና በየሰንበቱ ይደረግ የነበረውን የድሆች መዋጮ እንዲያጠነክሩት ያሳስባል ።

ከመምህራን የሰማሁትን ትምህርት እንዲህ ሳሰላስል ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ መልእክት የሁልጊዜ መለኪያ መሆኑን ገለጠልኝ ። እኔም “እንዴት?” ብዬ ተናገርሁ ። “አሁን ያላችሁት ክርስቲያኖች አንድነት የላችሁም ። አንዱ ሲሞት አንዳችሁ ትስቃላችሁ ። ዳር እየተጎዳ ከመጣ ወደ እናንተ እንደሚደርስ ዘንግታችኋል ። ስትለያዩ ኃይላችሁ ይከፋፈላልና ጠላት ይንቃችኋል ። ደግሞም ጥያቄ መጠየቅ አትፈልጉም ። መምህራኖቻችሁም ጥያቄ ይፈራሉ ። ለምን ጥያቄ ጠየቃችሁ እያላችሁ ሰውን ትገፋላችሁ ። መልስ ያለው ጥያቄን አይፈራም” አለኝ ። እኔም “እውነት ነው” ብዬ እጅ ነሣሁ ።

ይቀጥላል 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ