ሐዋርያውን ብዙ ጥያቄዎች ለመጠየቅ ፈለግሁ ። በሕይወት ዘመኔ ፣ በኑሮ መንገዴ የምማራቸውን ሁሉ በአንድ ቀን ጠቅልዬ የማወቅ ብልጠት አደረብኝ ። እርሱ ቢነግረኝም አንዳንዱ ነገር በጉዞዬ ገዝፎ ካላየሁት እንደማይገባኝ ተረዳሁና ልቤን ተው አልሁት ። ሐዋርያውም ከፊት ከፊቱ ቀደም እያልሁ የምናገረው ትክክል በመሆኑ በፈገግታ ያየኝ ነበር ። ቅዱሳን ትዝብትን ጥለው ሌሎችን መርዳትን ብቻ የሚያስቡ እንደሆኑ አውቃለሁ ። ያስተምራሉ ፣ ትምህርቱ ያልገባውን ደግመው ያስተምሩታል ። በተማረው እንዲኖር ይጸልዩለታል ። በበደል በወደቀ ጊዜም አብረውት ያለቅሳሉ ። በንስሐው አጋር ይሆኑታል ። የቅዱሳን ጠባይ ፣ ክርስቶስን የሚመስሉ ቡሩካን መገለጫ ይህ ነው ። ሐዋርያውም ስለ ሁሉም መልእክታቱ በዝርዝር ለማወቅና ሊቅ ለመሆን መፈለጌን በርኅራኄ አየው ። ቢሆንም መስማት በምችልበት መጠንና በሚያስፈልገኝም መጠን ፣ ለዛሬም በታዘዘልኝ የዕለት እንጀራ ልክ ሊነግረኝ ፈለገ ። እኔም የእግዚአብሔር ቃል ለትላንት ስህተት ስርየትን ፣ ለዛሬ ቁመና ምግብን ፣ ለነገ መድረሻ አቅምን እንደሚሰጥ ተገነዘብሁ ።
ሐዋርያው ቀጠለ፡- “አንደኛ ቆሮንቶስን የተረዳኸው በመልካም ነው ። ሁለተኛ ቆሮንቶስን የላክሁት ለማጽናናትና መደሰቴን ለመግለጥ ነው ። የሚጽናኑበትም ምክንያት አንደኛ ቆሮንቶስ በተባለውና ከዚያ በፊት በነበረው መልእክቴ መክሬና ተግሣጽ አስተላለፌ ስለነበረ ነው ። አሁን ግን የበደለው ንስሐ በመግባቱ ፣ የተቀጣው ሰው በመጸጸቱ ፣ ሥልጣንን ተጋፍቶ አገልጋዮቹን የናቀው በመመለሱ ደስታ ተሰማኝ ። ደግሞም ለኢየሩሳሌም ድሆች ልባቸው ራርቶ ስለሰጡም ላመሰግናቸው ፈለግሁ ። በዚህ ምክንያት ሁለተኛውን የቆሮንቶስ ጦማር ጻፍሁ ። ገላትያ ዛሬ በቱርክ ግዛት ውስጥ ብትገኝም እኔ በሥጋ በነበርሁበት ዘመን የሮማ ግዛት ነበረች ። የገላትያ ቤተ ክርስቲያን በአክራሪ አይሁዳውያን ታውካ ነበር ። እነዚህ አይሁዳውያን ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን የገላትያ ክርስቲያኖች አውከው ነበር ። ሁከቱ የመጣውም በእኔና በትምህርቴ ነው ። ጳውሎስ ሐዋርያ አይደለም ፣ ደግሞም ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም ። ወንጌል ያለ ኦሪት ፣ ጥምቀት ያለ ግዝረት ፣ ክርስቶስ ያለ ሙሴ የማዳን አቅም የላቸውም ብለው በማስተማራቸው ብዙዎች ታውከውና ልባቸው ተከፍሎ ነበር ። በሮማ ግዛት የአይሁድ ሃይማኖት ትልቅ ክብር አግኝቶ ስለነበር ተሰሚነታቸው እውነቱን ሐሰት ለማሰኘት እየጣረላቸው ነበር ። እኔም ጸጋውን በእምነት እንደተቀበሉ እንዲጸኑ መዳናቸውን እንዳይጠራጠሩ ለመንገር ይህን መልእክት በቀዳሚነት ጽፌአለሁ ።
የኤፌሶን መልእክትም አስደናቂ መልእክት ነው ። ዛሬ ቱርክ ብላችሁ በምትጠሩአት አገር ምዕራባዊ ዳርቻን ይዛ የተመሠረተች ውብ ከተማ እንዲሁም የጣዖታት መገኛ ነበረች ። በዚህች አገርም የተለያዩ ትርኢቶች ይከናወኑ ነበር ። ዛሬ በአሸዋ ተውጣ የቀረችው ያች ምድር በዚያ ዘመን ለእስያ አውራጃ እንደ መዲና ነበረች ። በግሪክ ቆሮንቶስ በእስያ ኤፌሶን መጠራታቸው የዘመኑ ልማድ ነበር ። ይህችን ቤተ ክርስቲያን በቀጥታ ባይሆንም መሪዋን ጢሞቴዎስን ለመምከርም አንደኛና ሁለተኛ ጢሞቴዎስን ጽፌአለሁ ። ዮሐንስም በራእዩ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መልእክት ሲያስተላልፍ ኤፌሶን ቀዳሚ ነበረች ። በእስር ላይ ሁኜ ከጻፍኩአቸው መልእክታት የኤፌሶን መልእክት ተጠቃሽ ነው ። የኤፌሶን መልእክት ለወቀሳ ለተግሣጽ አልተጻፈም ። የተጻፈው በሰማያዊ ስፍራ ያላቸውን ሀብትና ክብር እንዲያውቁት ለማሳሰብ ነው ። ሰው ዋጋውን ካወቀ በኃጢአትና በጣዖት አይወድቅምና ።
የፊልጵስዩስ መልእክት በእስር ላይ ሳለሁ የጻፍሁት ነው ። ፊልጵስዩስ የሰሜናዊ ግሪክ የመቄዶንያ አውራጃ ደማቅ ከተማ ናት ። በዚህች ከተማ የሚኖሩ አነስተኛ ኑሮ የነበራቸው ምእመናን ነበሩ ። ይህች ከተማ የወታደር ከተማ እንደ መሆንዋ ኑሮዋ ዝቅተኛ ነው ። ታዲያ ከዚህ ኑሮአቸው በአፍሮዲጡ እጅ ለእስራቴ እጅ መንሻ ልከውልኝ ነበር ። እውነተኛ ስጦታ ከትርፍ ሳይሆን ከጉድለት የሚደረግ ነው ። ስጦታዬ እስካልተሰማኝና እኔን እስካልጎዳኝ ገና አልሰጠሁም ማለት ነው ። እኔም “ተቀብሎ የማያመሰግን ቀማኛ ነውና” ላመሰግናቸው ይህን መልእክት ጻፍሁ ። ደግሞም ቢጽ ሐሳውያን ገብተውባቸው የክርስቶስን ልዕልና እንዳይቀበሉ ይገፋፉአቸው ነበር ። የመናፍቃን አንዱ ተግባር ድፍረትን ማለማመድ ነው ። በዚህ ምክንያት ትዕቢትን አስለምደዋቸው ነበር ። ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ ሳለ የባርያውን መልክ ይዞ መጥቷልና ትሑታን መሆን እንደሚገባቸው ከስህተት አስተማሪዎችም እንዲጠበቁና ሁልጊዜ በክርስቶስ ደስ እንዲላቸው ይህን መልእክት ጻፍሁ ።
የቈላስይስ ቤተ ክርስቲያን እኔ ራሴ ያልመሠረትኋት በኤጳፍራና በአክርጶስ ስብከት ያመነች ናት ። በዚህች ቤተ ክርስቲያን የስህተት ትምህርት ባየለ ጊዜ በሁሉ ዘንድ ተሰሚነት ያለው ጳውሎስ መልእክት ቢጽፍ የሚል አሳብ ከእነ ኤጳፍራ ስለመጣ ይህችን ቤተ ክርስቲያን በመልእክቱ ጎበኘኋት ። ስለ ትክክለኛው ትምህርት መጀመሪያ ገለጥሁ ። ትክክለኛውን ማወቅ ትክክል ያልሆነውን ለማወቅ ይረዳልና ስለ ሐሰት ከማጥናት ስለ እውነት ማጥናት መልካም ነው ። በሁለተኛው ክፍል ደግሞ ስለ ስህተት ትምህርቶች መልስ ሰጠሁ ። ቈላስይስ ለኤፌሶን ጎረቤት የሆነች ዛሬ በቱርክ ግዛት በእኔ ዘመን ደግሞ በሮም ግዛት የነበረች ከተማ ናት ። እነዚህ ቢጽ ሐሳውያን ስለ ግዝረት ፣ ስለሚበሉና ስለማይበሉ ምግቦች በማንሣት ከክርስትና እምነት ወደ ኋላ እንዲሉ አድርገዋል ። በአንድ እግዚአብሔርና በክርስቶስ ያመኑ አይሁዳውያን ወንድሞች ሲባሉ ከጥምቀት ጋር ግዝረት ፣ ከክርስቶስ ጋር ሙሴ ከሌሉ ሙሉነት የለም ብለዋልና ሐሳውያን ተብለዋል። በዚህ ምክንያት ቢጽ ሐሳውያን ወይም ሐሰተኛ ወንድሞች እንላቸዋለን ።
ዴማስ በውበትዋ ተስቦ ከጠፋባት ከተሰሎንቄ ከተማ የሚኖሩ ምእመናን ነበሩ ። በሩቅ ቢያያት ውብ መሰለችው ፣ በውስጥዋ ያሉ ተሰሎንቄአውያን ግን በክርስቶስ አምነው ነበረ ። እነርሱ በአካል በተሰሎንቄ ቢኖሩም ልባቸው ግን በሰማይ ነበረ ። ከተሰሎንቄ ውጭ የነበረው ዴማስ ግን አካሉ በሌላ አገር ሁኖ ልቡ በተሰሎንቄ ነበረ ። ልባችን ባለበት እንኖራለንና ጠፋ ። የተሰሎንቄ አማንያን ግን ክርስቶስ ይመጣል ብለው በተራራ ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው ወጥተው ይጠባበቁ ነበርና አንደኛና ሁለተኛ መልእክቴን ጻፍሁ ። ተሰሎንቄ ሰሜናዊ የግሪክ ግዛት የሆነው የመቄዶንያ አውራጃ ዋና ከተማ ናት ። ብዙ ጠላቶችም የእኔን ስም እያጠፉ ነበር ። ስሜ ጠፋ ብሎ መልእክት መጻፍ ነውር ቢሆንም አዳዲስ ምእመናን ግን እንዳይጎዱ በማሰብ ለማረጋጋት ይህን መልእክት ጽፌአለሁ ። ደግሞም በክርስቶስ ምክንያት መከራ እንደ ጸናባቸው ስላየሁ ከመልእክቶቼ ሁለተኛ አድርጌ የተሰሎንቄን መልእክት ጻፍሁ ። ከገላትያ መልእክት ቀጥሎ የጻፍሁት ነው ። ወገኖቻቸው በሞት ስለተለዩአቸው ኀዘን በማብዛታቸው ፣ የክርስቶስ ምጽአትም የራሱ የሆኑ ሂደቶች እንዳሉት ለመግለጥ እነዚህን መልእክታት ጽፌአለሁ ።
አንደኛና ሁለተኛ ጢሞቴዎስን የጻፍሁት ለመንፈስ ልጄ ፣ ለኤፌሶን ጳጳስ ፣ ለሥራ ባልደረባዬ ለወጣቱ ለጢሞቴዎስ ነው ። መንፈስ ቅዱስ ልቡን ከሰበረው ወጣትም ጳጳስ ሊደረግ ይችላል ። የደቡባዊ ቱርክ የልስጥራን ተወላጅ ለነበረው በእናቱ አይሁዳዊ በአባቱ ግሪካዊ የሆነው ባልደረባዬ ጢሞቴዎስ ስለ አገልግሎትና ስለ አገልጋዮች ፣ ስለፈተናውና ስለመስፈርቱ ስጽፍ እርጅና እየተጫጫነኝ ሞትም እየተቃረበ ነበርና ሁለተኛውን መልእክትም ለስንብት ጽፌአለሁ ። የቲቶ መልእክትም ተመሳሳይ ነው ። ቲቶ የቀርጤስ ጳጳስ የዛሬዋ ዩጎዝላቪያ የድሮዋ ድልማጥያ መምህር የነበረ እንደ ጢሞቴዎስ ወጣትና ባልደረባዬ የነበረ ቅን ሰው ነው ። ትውልዱ እንደ ሉቃስ ከአሕዛብ ከግሪክ ነው ። ስለ አገልግሎትና ስለ አገልጋዮች መስፈርት ጽፌለታለሁ ።
የፊልሞና መልእክትም የራሱ ዓላማ ነበረው ። ፊልሞና በቆላስይስ ከተማ ይኖር የነበረ ክርስቲያን ተማሪዬ ነው ። ባርያው አናሲሞስ ብዙ ንብረት ሰርቆ ወደ ሮም በሄደ ጊዜ እኔን አገኘኝ ። እኔም በእስራት ላይ ሆኜ ሳለሁ አስተምሬ እንዲያምን አደረግሁት ። ወደ ጌታው መመለስም ግድ ሆነብኝ ። የአናሲሞስም አእምሮ ማረፍ አለበት ፣ እኔም የወዳጄን ባሪያ ይዤ መቅረት ተገቢ አይደለም ። የተጨነቅሁት ግን ሁላችን በክርስቶስ ነጻ ወጥተናልና እንደ ወንድማማች እንድንተያይ ደግሞም በዚያ ዘመን ጌታው ባሪያውን ቢገድለው እንኳ ንብረቱ ስለሆነ ሕጉ ይፈቅድለታልና ፊልሞና እንዳይጨክን ወደ ሕግ ሳይሆን ወዳዳነው ጸጋ እንዲመለከት ለማሳሰብ ነው ። የዕብራውያን መልእክቴም ለአይሁድ የተጻፈ ነው ። በይሁዳ አይሁድ ፣ በያዕቆብ እስራኤል እንደ ተባሉ በዔቦርም ዕብራውያን ተብለዋል ። እነዚህ ክርስቲያን አይሁድ ከወገኖቻቸው በደረሰባቸው መከራ ወደ ኦሪት ሊመለሱ ተቃርበው ነበርና ባሉበት እንዲጸኑ የጻፍሁት ነው ። ሁሉን ብተነትንልህ ደስ ይለኝ ነበር ። ያንተ ጊዜ ግን አጭር ስለሆነ ይበቃሃል ። በል ዝቅ በልና በረከት ልስጥህ ።
እግዚአብሔር በሰማያዊና በምድራዊ በረከት ይባርክህ ! ባርኮ ለበረከት ያድርግህ ! የሰጠህን መልካም ነገር ያጽናልህ ! አምነህ ለመኖርና ለመሞት ያብቃህ !”
እኔም፡- አሜን ፣ አሜን ፣ አሜን አልኩኝ ።
ወደ ነበርሁበት ምድር ስመለስም “ጳውሎሰን አገኘሁት” ብዬ በልዑል ድምፅ ተናገርሁ ። በርግጥም ጳውሎስን አገኘሁት ።
ተፈጸመ ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም.