የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጳውሎስን አገኘሁት/ 2

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ እኔ እየተጠጋ ሲመጣ በታላቅ ደስታ ውስጥ ሆኜ በሲቃ ድምፅ መናገር ጀመርሁ ። እርሱ ግን ከዚህ በፊት እንደሚያውቀኝ በታላቅ መረጋጋትና ፍቅር እየቀረበኝ መጣ ። እውነት የራስዋ ግለት አላት ፣ ስሜትም የራስዋ ግለት አላት ። የእውነት ግለት እንደ ፍም በመሆኑ ይቆያል ፣ የስሜት ግለት ደግሞ እንደ ቅጠል እሳት በመሆኑ ቶሎ ያበቃል ። ፍም አመድ አለውና ቀሪ ነገር አለው ፣ የቅጠል እሳት ግን አመድ የለውም ። ከሚግለበለበው የቅጠል እሳት ዝም ያለው የፍም እሳት የተሻለ ነው ። አንዳንድ ሰዎች ብክነታቸውን ትጋት ፣ ቍጣቸውን መንፈሳዊ ቅንዓት ይሉታል ። ሁሉን ልያዝ ሁሉን ልጨብጥ በማለት ዓለም ቤቴ ናት ይላሉ ። የእነርሱን ትንሽ እውቀት ውኃ ጨምረውበት ለሰው ዘር ሁሉ ለማዳረስ ይፈልጋሉ ። እንቅልፍ በማጣታቸውና በመናገራቸው ትውልድን እየወለዱ መስሎ ይሰማቸዋል ። መንፈሳውያን ሰዎች ትኩስ ናቸው ። ትኩሳቱ ግን እንደ ፍም እሳት የሚቆይ ነው ። ምድራውያን ሰዎች ግን ቶሎ የሚያበቃ ትኩስነት አለባቸው ። ሐዋርያው እስከ ነገ በሚተርፍ ነገ ከተባለው ከጊዜ ቀጠሮም የሚዘልል መንፈሳዊ ግለት አየሁበት ። እኔ ከምድር የመጣሁ በመሆኑ ያየሁትንና የሰማሁትን ሳላጣጥም ፣ እገሌን አየሁት ብዬ የመረጃ ሽያጭ ለማድረግ እፈልጋለሁ ። ሰበር ዜና ብዬ የወሬ እሽቅድድም ውስጥ እገባለሁ ። ሁሉ አይወራም የሚለው ጨዋነት ጠፍቶ ሁሉን የማውራት የሕፃን ባሕል ውስጥ ገብተናል ። 

ሐዋርያው ጳውሎስ መልኩ ምን እንደሚመስል ያዩት  ሰዎች ገጣጥመው አስቀምጠውልናል ። ጭንቅላቱ ትልቅና ራሰ በራ ፣ የሁለቱ ቅንድቦቹ ጠጉር የተጋጠሙ ፣ ዓይኖቹ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ሲሆኑ ዘወትር ብርሃን ነበሩ ። አፍንጫው ትልቅና ቀጥ ብሎ የወረደ ጽሕሙና ሪዙም ረጃጅም ሲሆኑ ከአንገቱ አጠር ያለ ሁኖ ትከሻው ክብና ጎባባ እግሮች ደግሞም ከጉልበቱ ላይ የተቃረቡ ናቸው ። ቁመቱ አጠር ያለ ከድንክ የረዘመ ደንደን ያለ ሰው እንደነበር ይነገርለታል ። የሰማሁትን ያንን መልኩን ስፈልግ የነፍስ መልኳ ሁለት ዓይነት መሆኑን ተገነዘብኩ ። ነፍስ ወይ ክርስቶስን ወይ ሰይጣንን ትመስላለች ። ነፍስ የምትመስለው ምርጫዋን ነው ። ነፍስ ዘር የላትም ፣ ግዙፍና ቀሪ አይደለችምና ። ነፍስ ጎሣ የላትም በክርስቶስ ከመዛመድ ውጭ ልክ የሚሆናት አታገኝምና ። ሐዋርያው አጠገቤ ሲቆም ሰላም ተሰማኝ ። እኔ የማውቃቸው መንፈሳውያን ነን ብለው የሚያስቡ አጠገባቸው ሰው ሲደርስ እንዲወድቅ የሚፈልጉ ግርማዊ ምኞት ያላቸው ናቸው ። እውነተኛ መንፈሳዊነት ግን እንደ ማግኔት ተቃራኒውን ይስባል ። የተቀደሱ ሰዎች ለረከሱ ሰዎች ዕረፍት ይሰጣሉ ። የእግዚአብሔር ንጽሕና አያስበረግግም ። 

ሐዋርያውን “እንዴት ነህ ?” ብዬ ምድራዊ ሰላምታ ላቀርብለት ፈለግሁ ። ሰው የሚሰጠው ያለውን ነውና ። “በክርስቶስ ያደረ ግን እንዴት ነህ ?” አይባልም ። ሁለት ልብና ዓለም ያለው ብቻ እንዴት ነህ  ? ይባላል ። ስለ እኛ ዓለም ልተርክለት ፈለግሁ ክፋት የማይዳነቅበት ዓለም መሆኑን በዓይኑ ገርመም አድርጎ አሳወቀኝ ። ደግሞም “እነዚህ የሚወራው ስለ እግዚአብሔር ቅድስና እንጂ ስለ ፍጡር ክፋት አይደለም” አለኝ ። ቅዱሱ መልአክም አልተለየኝም ። መላእክትን ልዩ የሚያደርጋቸው የእግዚአብሔር ልጆችና የቅዱሳን ጠባቂዎች መሆናቸው ነው ። ልጁን ጠባቂ የሚያደርግ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። መላእክት ለጥበቃቸው የሚያገኙት ደመወዝ የእግዚአብሔር ፍቅር ይበዛላቸዋል ። 

ሐዋርያው ጳውሎስ ብርቱ በሆነ ራስ ምታት የሚሰቃይ ሰው ነው ። ከራስ ምታቱ የተነሣ ዓይኑን እንኳ መግለጥ ይቸገር ነበር ። በዚህ ምክንያት አንዳንድ መልእክቶቹን ዓይኑን ጨፍኖ ለፀሐፊ ሲነግር ጻፊው ብራናና ብርዕን አስማምቶ ይጽፍለት ነበር ። በጨርቁ ቅዳጅና በጥላው ድውይ የሚፈውስ ሰው እንዴት የራሱን ራስ ምታት ማስወገድ ያቅተዋል ? ለሚል ወታደር በተሰጠው መሣሪያ አገሩንና ሕዝቡን እንጂ ራሱን አያገለግልም ብለን እንመልስለታለን ። ጸጋ መሣሪያ ነው ፣ መሣሪያነቱም ሌሎችን ለመጠበቅ ነው ። ሐዋርያውን ሳየው ያ ሕመሙ ትዝ አለኝ ። እርሱ አሁን በሕመም ውስጥ ባይሆንም ሕመሙ ግን በበሽታ የሚሰቃዩ አገልጋዮችን ያጽናናል ። የተጻፈው ሁሉ ለሦስት ነገሮች ተጽፎአል ። ለትምህርት ፣ ለተግሣጽና ለማጽናናት ።

ሐዋርያው እንደ ተገናኘን ከየት መጣህ ? ከየትኛው አህጉር ነበርህ ? አላለኝም ። ሰዎችን በክርስቶስ እንጂ በአገርና በቋንቋቸው ለማወቅ የማይፈልግ ነበረ ። ሰማይ ያለ እንደ ምድራውያን ከቀይና ከነጭ አፈር ፣ ከጥቁርና ከቢጫ አፈር እያለ ጭቃ አያማርጥም ። አፈርም አፈር ነው ፣ ደምም ቀይ ነው ። ሐዋርያው የዘመን እላቂ እንደደረሰብን ነገረኝ ። “ያን ጊዜም ዘመኑ ደርሶአል ይባል ነበረ ። ዛሬም ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላ ዘመኑ ደርሶአል ይባላል” አልኩት ። እርሱም፡- “ዘመኑ የሚደርሰው ለሰሚው ሰው ነው ። ፈጥኖ ንስሐ ካልገባ ዘመን ኪሣራና ዕዳ ይሆንበታል” አለኝ ። እኔም ሐዋርያውን፡- “ያመኑ እየካዱ ፣ የሰበኩ እየፈሩ ፣ ጠንካሮች የነበሩ በገዛ ደቀ መዛሙርቶቻቸው እየተሰናከሉ ምድረ በዳ እየቀሩ ነው” አልኩት ። እርሱም ባለመደነቅ፡- “ሙሴ ምድረ በዳ የቀረው ከነዓን ሊያስገባው ባስወጣው ሕዝብ ነውና አትደነቅ” አለኝ ። ደግሞም፡- “ዴማስን ጥዬ ጢሞቴዎስን አንጠልጥዬ ገነት እንደ ገባሁ አትዘንጋ ፣ እግዚአብሔር የጻፈልህ ላይ ደርበህ መጻፍ ያንተ ድርሻ ነው ፤ እግዚአብሔር በማጽደቁ ብቻ ሳይሆን ነጻ ፈቃድ በመስጠቱም ፍቅር መሆኑን ይገልጣል” አለኝ ። በመቀጠልም፡- “ሳይህ ፖለቲካው ፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደሩ ፣ የወንድሞች ፍቅር ማጣት ፣ የአብያተ ክርስቲያናት ሁከት እየረበሸህ ነው ፣ ከተረበሽህ ሥራ መሥራት አትችልምና በመረጋጋት ቁም ። ለምን እንዲህ ሆነ ? ከማለት የሚሆነው መሆን ስላለበት መሆኑን ተረዳ” አለኝ ። እግዚአብሔር ትልቅ አምላክ በመሆኑ ለሁሉም ግራ መጋባቶች ዝርዝር መልስ አይሰጥም ። ሰማይ ስትደርስ ያልተመለሱልህን ጥያቄዎች አትጠይቅም ። የበጉን ፊት ስታየው ጥያቄህ እንደ ጢስ ይበናል” አለኝ ። 

ሐዋርያው ጳውሎስ ዕድገቱንና ትምህርቱን እንዲነግረኝ ፈለግሁ ። እርሱም፡- “ሰው ይታነጽበት ዘንድ አገልጋዮች ልምዳቸውንና ታሪካቸውን መናገራቸው መልካም ነው ። አሁን በምድር ላይ እያዳበራችሁት ያለው ግንኙነት ከምእመናን ጋር ድብብቆሽ የምትጫወቱ ይመስላል ። ያለ አቅማችሁ መልአክ የሚያደርጉአችሁና ያለ ግብራቸው ደግሞ ሰይጣን የሚያደርጉአችሁ ምእመናን እንደ ተፈጠሩ እናውቃለን ፤ የዚህ ትልቅ ችግር የእውቀት ማነስ ነው ። ምእመናን አገልጋይ ሰው መሆኑን ማወቅና መማር አለባቸው ። ነቢዩ ዳዊት ወደቀ ተብሎ የተጻፈው ለሐሜት ሳይሆን እኔም ብወድቅ እነሣለሁ ለሚል እምነት ነው” አለኝ ። ሐዋርያው የልጅነት ዘመኑን ሊተርክልኝ ተሰናዳ ። ያለ ማስታወሻ የሚናገረውን ሁሉ እይዝ ነበር ። ዝንጋዔ ያለው በምድር ላይ ነውና ። 

ይቀጥላል 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ታሕሣሥ 21 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ