የጠርሴሱ ጳውሎስን በአካለ ነፍስ በማግኘቴ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ። ነፍስ አካል አላት ። ነፍስ በዚህ ዓለም ላይ በሥጋ ገዝፋ ትታያለች ። በባሕርይዋ ረሀብ የሌለባት ብትሆንም ከሥጋ ጋር ተዋሕዳለችና የሥጋን ረሀብ የራስዋ አድርጋ ራበኝ ትላለች ። ሥጋ በነፍስ የማትሞት ፣ ነፍስም በሥጋ የምትሞት ናት ። ተዋሕዶ የሚሞተውን የማይሞት ፣ የማይሞተውን የሚሞት ያደርገዋል ። ሁሉም በአገሩ ያስተናግዳል ። ሥጋ አገሩ ምድር ላይ ነው ። የመጀመሪያው ሰው አዳምም የስሙ ትርጓሜ አፈር ወይም መሬት ማለት ነው ። ሥጋ ነፍስን በዚህች ዓለም ታስተናግዳለች ። የሥጋ ታቦት ወይም ማደሪያ ትሆናለች ። ቤቱ ሲፈርስ ሰውዬው እንዲወጣ ሥጋ ሲፈርስም አዳሪዋ ነፍስ ትወጣለች ። ነፍስም በአካልዋ ፍጹምነት ዛሬ በገነት ፣ ነገ በመንግሥተ ሰማያት ትኖራለች ። ረቂቃን አካላት ብለን የምንጠራቸው ራሱ እግዚአብሔር ፣ ቅዱሳን መላእክትና ነፍስ ናቸው ። የእግዚአብሔር መንፈስነት በቦታና በጊዜ የማይወሰን ነው ። የመላእክት መንፈስነት ተፈጥሮአቸውን የሚገልጥ ፣ ረቂቃን ወይም መናፍስት የሚያሰኛቸው ነው ። የነፍስ መንፈስነት በሚታይ ሥጋ ውስጥ የማይታይ ህልውና መሆንዋን ነው ። ነፍስ አካል ያላት ስትሆን በራስዋ ለመኖር ትችላለች ። በዚህ ዓለም ግን ያለ ሥጋ ደግ አልሠራችምና ፣ ነፍስ ብትራራ የሰጠችው በሥጋ እጅ ነውና ሥጋም አብሮ ሊከብር ትንሣኤ ሙታንን ይጠብቃል ።
በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ብርሃን የለበሱ ናቸው ። የነፍስን ውበት መግለጥ አይቻልም ። እንኳን የነፍስን ውበት ለነፍስ የተዘጋጀውን የመንግሥተ ሰማያትን ውበት መግለጥ አይቻልም ። በገነት የአንዱ ክብር ካንዱ ክብር ይበልጣል ። የዛሬው ሞኝና ላይ ላዩን የሚሄድ ክርስቲያን ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እኩል ክብር የሚያገኝ ይመስለዋል ። የድንግል ማርያም ክብርም ከፍጥረታት ሁሉ የከበረ ነው ። በአንድ ገነት ውስጥ የተለያዩ ክብሮች አሉ ። ይህ ክብር እንደ ሥራ መጠን የሚሰጥ ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “የፀሐይ ክብር አንድ ነው የጨረቃም ክብር ሌላ ነው የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው፤ በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና” ይላል /1ቆሮ. 15፡41 /።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስን በክብር ስሙ ጠራሁት ። በሰማይ ውርደት ሳይሆን ክብር ብቻ ነው ያለው ። እግዚአብሔር እንኳ ጥፋት የተቀጠረባትን ከተማ ነነዌን፡- “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ” ብሏል ። ዮና. 1፡2 ። እግዚአብሔር ከተማን እንኳ ታላቂቱ ይላል ። እግዚአብሔር አክባሪ ነው ። የእግዚአብሔር መንፈስ ባለበት ሁሉ ክብር አለ ። በአንድ ስፍራ ላይ መንፈሰ እግዚአብሔር እንዳለ ምልክቱ ክብር ሲኖር ነው ። አባቶች እንደ አባቶች ፣ ወንድሞች እንደ ወንድሞች ፣ እኅቶች እንደ እኅቶች ሲከበሩ በዚያ ቦታ መንፈሰ እግዚአብሔር አለ ማለት ነው ። ሐዋርያው አልኩት ። ሐዋርያ ሖረ ከሚል ግስ የወጣ ሲሆን ሂያጅ ገስጋሽ ፣ የንጉሥ መልእክተኛ ማለት ነው ። ቅዱስ አልኩት ቅዱስ ማለት ልዩ ማለት ሲሆን ዘመኑን ለእግዚአብሔር የለየ ሰው ነውና ደግሞም ከተቀደሱ መርከስ በሌለባት ሰማይ ነውና ቅዱስ አልኩት ። ሐዋርያውም በፍቅር ዓይን እየተመለከተኝ ነበር ። ቅዱሳን ሰውን የሚወዱት ዓላማቸውን ሳይረሱ ነው ። በምድር ላይ ያለን እኛ ግን ለሰው ፍቅር ብለን ዓላማችንን እንረሳለን ። ቤተሰቤ እንዳያዝን ብለን ክርስትናን ፣ ወላጆቼ ተስፋ እንዳይቆርጡብኝ ብለን ምናኔን እንተዋለን ። እግዚአብሔርን ከሁሉ አስተካክለን ሳይሆን አብልጠን መውደድ አልቻልንም ።
ሐዋርያው ንግግሩን ቀጠለ ። ቤተሰቦቼ በጠርሴስ ቢወልዱኝም የሃይማኖትን ትምህርት እንድማር ገና በሰባት ዓመቴ ወደ ኢየሩሳሌም ወስደውኝ እኅቴ ዘንድ አስቀምጠው ፣ ከገማልያል እግር አጠገብ እንድማር አደረጉኝ ። ሰባት ዓመት የዕድሜ አንድ እርከን ነው ። ልጆች የልጅነት የደስታ ጊዜያቸውን በቅጡ አሳልፈው በሰባት ዓመት ወደ ትምህርት ቢመጡ የተሻለ ቁመና ይኖራቸዋል ። አንድ አይሁዳዊ ሕፃን በሰባት ዓመቱ ከመምህር ዘንድ ተሰጥቶ መጀመሪያ የዕብራይስጥ ፊደልንና የብሉይ ኪዳን ንባብን እስከ አሥራ ሁለት ዓመቱ ይማራል ። አሥራ ሁለት ዓመት ለአይሁዳውያን የአካለ መጠን ዘመን ስለሆነ ልጁ ወደ ተግባረ ሥጋ ለመሄድ አሊያም መንፈሳዊውን ትምህርት ለማጠናከር ምርጫ ያደርጋል ። ምርጫው መንፈሳዊውን ትምህርት መማር ከሆነ በንባብ የዘለቀውን ብሉይ ኪዳን በትርጓሜ እስከ ሃያ ዓመቱ ድረስ ይማራል ። እኔም ከሰባት ዓመቴ የጀመርኩትን ትምህርት በሃያ ዓመቴ ፈጸምሁ ። ቋንቋን በቀላሉ ለማወቅ እስከ ሰባት ዓመት ያለው ዕድሜ ወሳኝ ነው ። እስከ ሰባት ዓመት ከአራት ቋንቋ በላይ ማወቅ ይቻላልና ወላጆች ለልጆቻቸው ቋንቋን ቢያስተምሩ መልካም ነው ። እኔም እስከ ሰባት ዓመቴ የዕብራይስጥን ፣ የግሪክንና የሮማይስጥን ቋንቋ አውቅ ነበረ ።
ሐዋርያው አሁን ቀጠለ፡- የተማርኩት በታወቀው በገማልያል እግር ሥር ቁጭ ብዬ ነው ። ገማልያል በትክክል ያወቀ ፣ በታሪክና በዛሬው ሁነት መካከል ያለው ትስስር የለየ ፣ የሚሆነው ሲሆን የነበረ ነው ብሎ የሚያምን ፣ ከእግዚአብሔር የሆነውን ማንም እንደማያጠፋው ፣ ከእግዚአብሔር ያልሆነው ደግሞ ሰው ሁሉ እየወደደው በራሱ እንደሚጠፋ የሚያምን መምህር ነበር ። ከመምህር የሚወሰድ እውቀት እርግጠኝነት አለው ። ከመምህር መማር የማይፈልጉ የተለያዩ ችግሮች ይገጥሟዋል ። የመጀመሪያው ሐረገ ትውልዱን ይስታሉ ። አበው ለነቢያት ፣ ነቢያት ለሐዋርያት ፣ ሐዋርያት ለሊቃውንት ፣ ሊቃውንት ለመነኮሳትና ለጳጳሳት እያቀበሉ መንፈሳዊ ውርስ ተላልፏል ። ከመምህር የማይማር ይህን ሐረገ ትውልድ ስለማያገኝ የተገነጠለ ቅርንጫፍ ይሆናል ። ለጊዜው ቢለመልምም ቆይቶ ግን ይደርቃል ። ሁለተኛው ችግር ራስን መውለድ ብርቱ ድካም አለው ። አባት ያለው የሚያምጥለት አለው ። አባት የሌለው ግን ራሱ አምጦ ራሱን የሚወልድ ነውና በከንቱ ጉልበቱን ይጨርሳል ። ሦስተኛ የኑሮ ልምድ አይኖረውም ። መምህራን በቃላቸው ብቻ ሳይሆን በኑሮአቸውም ያስተምራሉ ። ደቀ መዝሙሩም መምህሩ ለተጠየቁት ጥያቄ ፣ ለደረሰባቸው ፈተና የሰጡትን መልስ እያየ ይማራል ። የሕይወት እውቀት ዕድሜና እውነት ካስተማራቸው የሚገኝ ነው ። በቤተሰብ ሕግ ታናሹ የአንድ ዓመት ታላቁን ያከብራል ። በመንፈሳዊ ዓለምም እኛን በማመን የቀደሙንን ማክበር ይገባል ። መምህራን በማመን የቀደሙን ፣ እኛ በንባብ የምንጮኸውን እነርሱ በትርጓሜና በሕይወት የሚያውቁት ናቸው ። አራተኛ ከመምህራን አለመማር ያልተጣራ እውቀት ለመያዝ ይዳርጋል ። አምስተኛ እርግጠኛነት ኖሮት ለማስተማር ይቸገራል ። ያልተማረ ያለው ሀብት ድፍረት ቢሆንም እምነት ግን የሚገኘው በቅጡ በትሕትና ከመማር ነው ። ከመምህር እግር ሥር ቁጭ ብሎ መማርን ሰማይ ያከብረዋል ።
ከመምህር እግር ሥር ቁጭ ብሎ መማር ማለት በትሕትና በታዛዥነት ዘመንን በመስጠት መማር ነው ። ደቀ መዝሙር ማለት ተመላላሽ ተማሪ ሳይሆን አዳሪ ተማሪ ነው ። ማቄን ጨርቄን የማይሉ ደቀ መዛሙርት ካልተገኙ ፣ ዘመናቸውን በሙሉነት ለክርስቶስ የሰጡ ካልመጡ ወንጌል ጉዞ አይሮጥም ። በዱላ ቅብብሎሽ የመጨረሻ ሯ ፈጣን መሆን አለበት ። እናንተም የመጨረሻ ዘመን ሯጮች ናችሁና መፍጠን አለባችሁ” አለኝ ። በሐዋርያው ንግግር ወደ ታላቅ ተመስጦ ገባሁ ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 27 ቀን 2013 ዓ.ም.