ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ትክ ብሎ ወደ እኔ ተመለከተ ። መምህራን ትክ ብለው ሲመለከቱና አንድን አሳብ ደጋግመው ሲናገሩ ለነገሩ አጽንኦት እየሰጡ ነው ። እኔም በጆሮዬ ብቻ ሳይሆን በልቤ ለመስማት ተዘጋጀሁ ። የሰው ልጅ አፈር ነው ስንል ከአፈር ጋር ተመሳሳይነት ስላለው ነው ። አፈር ድንጋይ አለው ፣ ሰውም አጥንት አለው ። አፈር ሣር አለው ሰውም ፀጉር አለው ። አፈር ውኃ አለው ፣ ሰውም ደም አለው ። አፈር ሥራሥር አለው ፣ ሰውም የደም ሥሮች አሉት ። አፈር እህልን ያስገኛል ፣ ሰውም ፍሬ ይሰጣል ። አፈር ኃይሉን ይጨርሳል ፣ ሰውም አቅሙን ይጨርሳል ። አፈር በማዳበሪያ የድካም ዘመኑን ያሳልፋል ፣ ሰውም በቅባትና በምርኩዝ ሽምግልናውን ያሳልፋል ። አፈር ደም ከነካው ያርራል ፣ ሰውም ግፍ ከፈጸመ ሰላም ያጣል ። አፈር ዋጋው ርካሽ ነው ፣ ሰውም ከንቱ ነው ። አፈር ድንበር የለውም ፣ ሰውም በተፈጥሮው አንድ ነው ። አፈር የእህል እናት ነውና ውድ ነው ፣ ሰውም የእውቀት ማጉያ ነውና ድንቅ ነው ። አፈር ዛሬ እንበላዋለን ፣ ነገ ይበላናል ። ሰውም ዛሬ ይሰጣል ፣ ነገ ይቀበላል ። አፈር ትሕትናን ያስተምራል ፣ ሰውም ሞቱን እያሰበ ትሑት መሆን ይገባዋል ። አፈር አራት ዓይነት ቀለም አለው ። ጥቁር ፣ ነጭ ፣ ቢጫና ቀይ ። የሰውም መልክ አራት ዓይነት ነው ። አፈር አራት ዓይነት መልክ ቢኖረውም ስሙ አንድ አፈር ነው ፣ ሰውም የተለያየ መልክ ቢኖረውም አንድ የሰው ልጅ ነው ።
የሰው ልጅ አምስት ውጫዊና አምስት ውስጣዊ ሕዋሳት አሉት ። ሰውን እያየነው አናየውምና እናልፈዋለን ፣ በዚህ ጊዜ “ምነው አይተህ አለፍከኝ ?” ሲለን “ልብ ካላየ ዓይን መች ያያል” እንላለን ። በዚህም ውስጣዊ ዓይን እንዳለ እየመሰከርን ነው ። የውጭ ጆሮ እንዳለ ዕዝነ ልቡና ደግሞ አለ ። ሐዋርያው ትክ ብሎ ያየኝ በልብ ማስተዋል ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያትን ፣ በዕዝነ ልቡና ደግሞ ምክሩን እንድሰማ ነው ። እኔም እኔን እያየ የሚያስተምር መምህር በዓለመ ነፍስ ስላገኘሁ ደስ አለኝ ። መምህራን ሲወድዱ ወደ ደቀ መዛሙርቶቻቸው እያዩ ያስተምራሉ ። ወዳጅ የሚገኘው ከወዳጅ ከእግዚአብሔር ነውና እኔም ሐዋርያውን አከበርኩት ። እርሱ የእኔን ምድር የመጣበት መንገድ ነውና ሊነግረኝ ይችላል ። የሚሄዱበትን መንገድ ከሚመለሱት መጠየቅ መልካም ነው ። የእርሱን ዓለም ግን ገና አላየሁትምና ምንም መናገር አልችልም ። ሐዋርያውም መንግሥተ ሥላሴን የቃላት አስረጂነት ሊገልጣት እንደማይችል በሕይወተ ሥጋ ሳለ ተናግሮ ነበር ።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ንግግሩን ቀጠለ ። “እኔ የተወለድሁት ከታናሹ ከብንያም ነገድ ነው ። ብንያም ለያዕቆብ የመጨረሻ ልጅ ቢሆንም ታናሽ መባሉ ፍቅርን እንጂ ደረጃን የሚያሳይ አይደለም ። ከዚህ ነገድ ነው የተወለድሁት ማለት ኃጢአት አይደለም ፣ እግዚአብሔር ብቻውን ወስኖ ከዚህ ጎሣ ተወለድ ስላለ ራሳችንን እዚያ አግኝተነዋል ። የእግዚአብሔር ስጦታ ነውና በነገዳችን ማፈር ፣ ደግሞም መመካት አይገባም ። የእግዚአብሔር ስጦታ ነውና እኔ ከዚህ ወገን ነኝ ፣ አንተ ግን ከዚያ ነህ ብሎ መጣላት አይገባም ። ቋንቋም በምድረ ሰናዖር በቅጣት ምክንያት የተደባለቀ ነው ። ርግማንን ሁሉ የቀደሰው ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ሃምሳ መጥቶ ሀብተ ልሳንን በመስጠት ቋንቋን ቀደሰው ። በብሉይ ኪዳን ቋንቋ የርግማን ውጤት ነበረ ፣ በአዲስ ኪዳን ደግሞ በረከት ነው ።”
ሐዋርያው አሁንም ንግግሩን ቀጠለ፡- “ከእስራኤል የመጀመሪያው ንጉሥ ከሳኦል ጋር ተመሳሳይነት አለን ። እርሱ አህያ ፍለጋ ወጥቶ ንግሥና ይዞ ተመለሰ ፣ እኔ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ ወጥቼ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆኜ ተመለስሁ ። ሳኦል ብንያማዊ ነበር ፣ እኔም ብንያማዊ ነኝ ። ሳኦል ስሙ ሳኦል ነው ፣ እኔም የመጀመሪያ ስሜ ሳውል ነበረ ። የሚለያየን ነገር ግን አለ ። ሳኦል በመልካም ጀምሮ በክፉ ፈጸመ ፣ ያከበረውን ጌታ ማክበር አቅቶት በንግሥና ጀምሮ በውርደት ዘመኑን ፈጸመ ። እኔ ደግሞ በግፍና ሐዋርያትን በማሳደድ ጀምሬ በሐዋርያነት ፈጸምሁ ። ለሰው ልጅ ከጠዋቱ ማታው ሲያምርለት መልካም ነው ። በጌታችን መስቀል ላይ ዘመኑን በሙሉ ያገለገለው ሊቀ ካህናት ቀያፋ ወድቆ ዘመኑን በሙሉ ሽፍታ የነበረው ፈያታዊ ዘየማን ዳነ ። ፍጻሜአችን እንዲያምር መጸለይ መልካም ነው ። ሰው ፍጻሜዬን አሳምርልኝ እያለ የሚጸልየው በጥሩ ኑሮ ፣ በከበረ ትዳርና በልጆች ተከብቦ ስለ መሞት ነው ። ከቅዱሳን ግን በእንዲህ ያለ መንገድ የሞተ የለም ። ታዲያ ፍጻሜአቸው ያላማረ ነውን ? በፍጹም አይደለም ። ቅዱሳን ሁሉ እንደ ጎመን ተቀንጥሰው ፣ እንደ ባቄላ ተቀቅለው አልፈዋል ። ፍጻሜው አማረ የሚባለው በክርስቶስ ያረፈ ወይም የሞተ ነው ። ያለ ክርስቶስ ከመኖር በክርስቶስ መሞት የተሻለ ክብር አለው ።”
“በምድረ እስራኤል ላይ የተለያዩ የሃይማኖት ቡድኖች ነበሩ ። የታወቁት ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ናቸው ። ሌሎቹም ቀናተኞች ወይም ቀነናውያን ዳግመኛም ገዳማውያን ወይም ኤሤይ ይባላሉ ። ፈሪሳውያን ከባቢሎን ምርኮ በኋላ የተመሠረቱ የሃይማኖት ቀናተኞች ሕብረት ነው ። መላውን ብሉይ ኪዳን ሲቀበሉ መሢሑ መጥቶ በጦር ኃይል ከሮማውያን እጅ ነጻ ያወጣናል ብለው ያምናሉ ። ፈሪሳዊ ማለት የተለየ ማለት ነው ። ቀናተኞችና በመቅደሱ ዙሪያ በጸሎት የተጠመዱ ሲሆኑ ሰፊውን ሕዝብ ይዘውት ነበር ። ሰዱቃውያን ደግሞ በካህኑ በሳዶቅ ሰዱቃውያን የሚል ስያሜ አግኝተዋል ። እነዚህ ሰዱቃውያን አምስቱን ብሔረ ኦሪት ወይም የሙሴን መጻሕፍት ብቻ ሲቀበሉ በመላእክትና በነፍስ ህልውና እንዲሁም በትንሣኤ ሙታን አያምኑም ነበር ። ቀናተኞች የሚባሉት ደግሞ እስራኤልን በአርበኝነት ነጻ ለማውጣት የሚታገሉ ፣ በየጊዜውም አደጋ የሚጥሉ ናቸው ። በ66 ዓ.ም. በሮማውያን ላይ በጣሉት አደጋና ባስነሡት የእምቢታ ተቃውሞ እስራኤል ለሁለት ዓመት ከበባ ውስጥ ገብታ በ70 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ተደምስሳለች ። ገዳማውያኑ ወይም ኤሤዮች ደግሞ በኢየሩሳሌም ምሥራቅ ደቡብ ላይ በሙት ባሕር አጠገብ ባለው በኩምራን ገዳም ይኖሩ የነበሩ ቍጥራቸውም ከአራት ሺህ በላይ የሆኑ መናንያን ናቸው ። እነዚህ ገዳማውያን የላመ የጣመ ከመብላት እንዲሁም ጋብቻ ከመመሥረት ተነጥለው እስራኤል በተአምራት ነጻ ትወጣለች በማለት በጸሎት ይተጉ ነበረ ። ዕድሜአቸውንም የሚፈጽሙት ቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጻፍ ነው ። እነዚህ ገዳማውያን ከፈሪሳውያን የተገነጠሉ ቡድኖች ሲሆኑ በመሢሑ መምጣት ያምናሉ ፣ ልዩነታቸው ፈሪሳውያን በጦር ኃይል መሢሑ ነጻ ያወጣናል ብለው ሲያምኑ ገዳማውያኑ ግን በተአምራት ነጻ እንወጣለን ብለው ያምኑ ነበር። እኔ ሐዋርያው ጳውሎስ ከእነዚህ ቡድኖች የፈሪሳውያን ቡድን አባል ነበርሁ ። በዚህ ምክንያት ቅንዓት ነበረኝና ክርስትና ሲሰበክ የብሉይ ኪዳን የተስፋው ፍጻሜ መሆኑን ዘንግቼ ለመቃወም ሰይፍ አነሣሁ ። ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አፈረስሁ ፣ እስጢፋኖስ ሲገደልም መመሪያ ሰጪና አለቃው እኔ ነበርሁ ።”
ሐዋርያው የሚነግረኝ እውቀት ሁሉ በጆሮዬ እየገባ በልቤ ይፈስስ ነበር ። ምነው ባላቆመ እያልሁ እመኝ ነበር ። ከእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉም እውቀት ይገኛል ። የሳይንስ ፣ የፍልስፍና ፣ የታሪክ ፣ የሥነ ልቡና ፣ የሕክምና ፣ የማኅበራዊ ኑሮ ፣ የሥርዓተ መንግሥት ፣ የሕግ… እውቀት አለ አልኩኝ ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 1 ቀን 2013 ዓ.ም.