የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጳውሎስን አገኘሁት /6/

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ  ሕይወት ምርጫው እንዲነግረኝ በልቤ ሳስብ የማስበውን አውቆ መልስ ሊሰጠኝ ተዘጋጀ ። እኔም መልሴ እንደ ደረሰ ተሰማኝና ለመስማት ተዘጋጀሁ ። አንደኛው ልቤ ሲደነቅ ሌላኛው ልቤ ደግሞ የእግዚአብሔር ሰዎች ሳይነጋገሩ ይግባባሉ የሚለውን ማሰብ ጀመረ ። እግዚአብሔር በመካከላችን ከሌለ በተነጋገርን ቍጥር እንደበላለቃለን ። እግዚአብሔር በመካከላችን ካለ ግን ሳንነጋገር እንግባባለን ። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ድንግላዊ ሕይወቱ ሊነግረኝ ፈለገ ። “ከዘመዶቼና ከቤተሰቦቼ አሳብ የተለየሁት በመረጥሁት በድንግልና ሕይወትም ነው ። ዘመዶቼ በሥጋ እንዳሉ መጠን የሚያስቡት ሥጋዊ የሆነ አሳብ ነው ። የሚያዩልኝ ትንሽ ጎጆ ፣ የሚቆጥሩልኝም ጥቂት ልጆችን ነበር ። እኔ ግን ሰፊው ዓለም ቤቴ ፣ የሰው ዘር ልጆቼ እንዲሆኑ እናፍቅ ነበር ። በፈሪሳዊ ቀናዒነቴና በብሉይ ኪዳን መምህርነቴ ዘመን ይህን የድንግልና ሕይወት ብወስንም በክርስቶስ ካመንሁ በኋላ ግን የበለጠ ለትልቅ ዓላማ ላውለው እንደምችል ተሰማኝ ። ስለ ክርስቶስ የሚጎዳኝን በመተዉ የምመካ ሞኝ አይደለሁም ፣ የሚጠቅመኝን ነገር ለመተውም ዝግጁ ነበርሁ ። በእናንተ አገር፡- “ኧረ ልጅ ማሰሪያው ፣ ኧረ ልጅ ገመዱ ፤ ቤትማ ምን ይላል ዘግተውት ቢሄዱ” ትላላችሁ ። እኔም የሚሊየኖች አባት ለመሆን ከኢየሩሳሌም እስከ ምድር ጥግ እስከ ስፔን ወንጌልን ለመስበክ ተጨማሪ ነጻነት አገኝ ዘንድ ድንግልናዊ ሕይወትን መረጥሁ ። እኔ ባለመውለዴ የዓለም ሕዝብ አይቀንስም ። የተወለደውን ለትልቅ ዓላማ ብወልድ ግን የዚህችን ዓለም ስቃይ እቀንሳለሁ ፣ ብዙዎችንም ለክርስቶስ ሙሽርነት አዘጋጃለሁ ። ሐዋርያው ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ እስከ አሥራ ሁለተኛው ምዕራፍ ነበረ ። ከዚያ በኋላ ቤቱን እንዲያስተዳድርም የኢየሩሳሌም ሐዋርያ አደረግነው ። በመጨረሻ ላይ በሮም አደባባይ በሰማዕትነት እስክንገናኝ ድረስ እኔ በዓለም ሁሉ እዞራለሁ ፣ እርሱ ግን ቤቱንም ቤተ ክርስቲያንንም እያገለገለ ነበር ። ይህ ቅዱስ ሐዋርያ በድንግልናዊ ሕይወት ያለ መያዣ የሚሮጥ ልጅ አፍርቷል ። እኔም የእርሱን በረከት ተቀብዬ እሮጥ ነበር ።” 

“የድንግልናዊ ሕይወት ታላቁ ነቢይ ኤልያስ ፣ በእርሱ መንፈስና ኃይል ይራመድ የነበረው ዮሐንስ መጥምቅ የተጓዙበት መንገድ ነው ። መጥምቁ ዮሐንስ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ በእርጅና ዘመናቸው የወለዱት ቢሆንም እኔ ካልወለድሁ ዘራቸው ተቋረጠ የሚል ሥጋዊ አሳብ ውስጥ አልገባም ። ድንግላዊ ብቻ ሳይሆን ባሕታዊም ሆኖ በምድረ በዳ የእግዚአብሔር ድምፅ ነበረ ። በመንግሥተ ሰማያትም ከሁሉ የበለጠ ትልቅ ሆነ ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወደ ዓለም የመጣው ለትምህርት ፣ ለአርአያነትና ለቤዛነት ነው ። በትምህርቱ ለእግዚአብሔር መንግሥት ራሳቸውን ጃንደረባ ስለሚያደርጉ ደናግላን ተናገረ ። /ማቴ. 19፡10-12/ በአርአያነቱ ደግሞ ድንግልናዊ ኑሮን በመኖር አሳየ ። ድንግልናዊ ኑሮ ጌታችን የባረከው ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የኖረችው ሕይወት ነው ። እርስዋ ድንግልና እናት ብትሆንም ዘላለማዊት ድንግል ናት ። ድንግልናዊ ሕይወት ታላላቅ ነቢያቶች ፣ ከሁሉ በላይ የሚሆን ክርስቶስ ፣ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም አርአያ የሆኑበት ነው ።” 

“ድንግልናዊ ሕይወትን በየዘመናቱ የተነሡ ሊቃውንት ፣ ደናግልና መነኮሳት ኖረውታል ። አስቀድሞ ፈላስፎች ሁሉን መርምረው ዓለም ከንቱ ነው እያሉ ይህን ሕይወት ይመርጡ ነበር ። እነርሱ ዓለም ከንቱ ነው የሚሉት ሁሉም ነገር ባዶ ሆኖባቸው ነው ፣ እኛ ግን ዓለም ከንቱ ነው የምንለው የክርስቶስ ውበት በልጦብን ነው ። ድንግልናዊ ሕይወትም ተስፋ መቍረጥ የወለደው ሳይሆን ትልቅ ተስፋ የሚወልደው ነው ። የክርስቶስ እጮኛ ከመሆን የበለጠ ክብር የለምና ። ድንግልናዊ ሕይወት ኃላፊነትን ለመሸሽ የምንገባበት ሳይሆን የበለጠ ኃላፊነትን የምንቀበልበት ነው ። ለጥቂቶች ከመኖር ለሚሊየኖች መኖር እንዲቻል ነው ። እኔ በመላው ዓለም ዞሬ ወንጌል ማስተማሬ ከጴጥሮስ ይልቅ ድንግልናዊ ሕይወቴ ተጨማሪ ነጻነት ስለሰጠኝ ነው ። እኔ አሥራ አራት መልእክት ስጽፍ ጴጥሮስ ግን ሁለት መልእክት መጻፉ የኑሮ ጫናም ስለነበረበት ነው ። ነገር ግን ድንግልናዊ ሕይወት ስጦታ ፣ ምርጫና ፍላጎት ነው ። ሰው እጾማለሁ ብሎ ሲነሣ አይርበኝም ማለቱ አይደለም ። ቢርበኝም ለዓላማዬ እተጋለሁ ማለቱ ነው ። እንዲሁም ድንግልናዊ ሕይወት የመረጡ ሰዎች ሥጋዊ ስሜት የላቸውም ማለት ሳይሆን ለዓላማቸውና ለሚበልጠው ተግባር ይቋቋሙታል ማለት ነው ። በጦርነት ብዙ ዘመን በጫካ የሚያሳልፉ ነጻ አውጪዎች በንጽሕና እንዲኖሩ መመሪያ ይሰጣሉ ። ሥጋዊ ስሜትን ማገልገል ከጀመሩ ከትግል ይደናቀፋሉ ። አሥርና ሃያ ዓመታት ራሳቸውን ዐቅበው እንደኖሩ ታሪክ ይናገራል ። ሰዎች ለጦርነት ዓላማና ለምድራዊ ድል ይህን ዋጋ መክፈል ከቻሉ እኛማ ለማያልፈው መንግሥት ዋጋ መክፈል ይኖርብናል ።” 

“ብዙዎች እንደሚያስቡት ድንግልናዊ ሕይወት የሚኖሩ ሰዎች ስለ ጋብቻ ማማከር የሚችሉ አይመስላቸውም ። የጋብቻ ምክር ግን ከመንፈስ ቅዱስ እንጂ ከማግባት የሚገኝ አይደለም ። ያ ቢሆን ኖሮ እኔ ስለ ጋብቻ የጻፍኩትን ያህል የጻፈ የለም ። ያ ቢሆን ኖሮ ያገቡ ሁሉ የጋብቻ አማካሪ ቢሮ ያቋቁሙ ነበር ። የጋብቻ መሥራች እግዚአብሔር ነውና መመሪያውም የሚገኘው ከእርሱ ነው ። ስለ ዕቃው አጠቃቀም የሠራው ፋብሪካ ቢናገር የተሻለ እንደሆነ ስለ ጋብቻም እግዚአብሔር ሲናገር ያማረ የሠመረ ነው ።” 

“በድንግልና መኖር ለብዙ ዘመናት ነበረ ። በኋለኛው ዘመን የተነሡ የእኛን ዐሠረ ፍኖት የተከተሉ አባቶች ምንኵስናንም አዘጋጁ ። ድንግልናዊ ሕይወት ምርጫ ሲሆን ምንኵስና ደግሞ ቃል ኪዳኑ ነው ። አማራጭ የጽድቅ መንገድ ሆኖ የክርስቶስን መሥዋዕትነት የሚተካ ሳይሆን ወንጌልን ለማሮጥ የቃልኪዳን ሠራዊት የሚያደርግ ነው ። ምንኵስና ብቻ ሳይሆን ገዳማዊ ኑሮም እንዲመሠረት አድርገዋል ። ድንግልናዊ ሕይወት ከሰው ሽሽት ሳይሆን ሕብረት መሆኑን ገዳማዊው ኑሮ ያሳያል ። አብሮ መኖር ፣ አብሮ መብላትና መጠጣት ፣ አብሮ መጸለይና ለወንጌል ተልእኮ መዝመት ያለበት ነው ። ለቤተ ክርስቲያንና ለብዙ ትዳሮችም የጸሎት ደጀን የሚሆኑት እነዚህ ደናግል መነኮሳት ናቸው ። ድንግልናዊ ሕይወት ጋብቻን በመጥላት የመጣ ሳይሆን ጋብቻ በሥጋ የሚወልዳቸውን ልጆች በመንፈስ ለመውለድ የተዘጋጀ ቅዱስ ተግባር ነው ። በዚህ ምክንያት የሙት ልጆችን የሚንከባከቡና የሚያሳድጉ መነኮሳት ናቸው ። ዛሬ በእናንተ ዘመን የሚታዩት ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ገዳማት ነበሩ ። ገዳማውያኑ ትምህርቱን ሲሰጡ ቆይተው በመጨረሻ የትውልድ መቅረጫ እንዲሆን ለትምህርት ተዉት ። የሚመረቁ ተማሪዎች የሚለብሱት ቆብና ቀሚስ የመነኮሳት ልብስ ነው ። መነኮሳቱ አስተማሩና በምን ልብስ እንመርቃቸው ሲሉ የራሳቸውን ልብስ አልብሰው መረቁአቸው ። በዚህ ምክንያት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ እናንተ ዘመን ድረስ ተማሪዎች በክብር የሚመረቁት በመነኮሳት ልብስ ነው ። ይህን ግን የሚያስተውሉ አይመስለኝም ።” 

እስከ ስድስተኛው ክፍለ ዘመንም ያገቡ ወገኖች ጳጳሳት ይሆኑ ነበር ። ጳጳሱና ፓትርያርኩ ሲሞት ሚስትና ልጆች የአባታችንን አስኬማ ለማስታወሻ ፣ የወርቅ ወንበሩ ለመተዳደሪያ ያስፈልገናል እያሉ በዓለም ፍርድ ቤት ክስ መመሥረት ጀመሩ ። ቤተ ክርስቲያንም በሚጠላት ዓለም ፊት ከገዛ ልጆችዋ ጋር መካሰስ ምስክርነትዋንና ተልእኮዋን እንዲሁም ህልውናዋን የሚጋፋ ሲሆን ጳጳሳትና ፓትርያርክ የሚሆኑ ደናግል መነኮሳት መሆን እንዳለባቸው ወስናለች ። ቤተ ክርስቲያን ሁለቱንም መንገድ በቃል ኪዳን ታስራለች ፣ ታከብራለች ። ለሚያገቡት ሥርዓተ ተክሊልን ፣ የክርስቶስ እጮኞች ነን ለሚሉ ምንኵስናን ትፈጽማለች ። ቃል ኪዳን ከሌለበት ያልታሰረ ነዶ ሁኖ ይበተናልና ድንግልናዊ ሕይወት ቃል ኪዳን ይፈልጋል ። 

ሐዋርያው ሲናገር ልቤ ተነነ ። በአንድ አሚኑ አልረጋ ያለው ትውልድ ስለ ድንግልናዊ ሕይወት ቢነገረው ሰልፍ ይወጣል ብዬ አሰብሁ ። ነገር ግን ሙሉ ዘመናቸውን ሰጥተው ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ ደናግል መነኮሳት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አሁን እንደሚያስፈልጉን ማሰብ ጀመርሁ ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ሊቀጥልልኝ ሲል ለማሰላሰል ትንሽ ጊዜ ለመንሁት ። 

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ