የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጳውሎስን አገኘሁት /7/

 

እንኳን ለ2013 ዓ.ም. ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ !

ቅዱሳን በምድር ትዕግሥትን ያፈራሉ ፣ በሰማይ ደግሞ የትዕግሥትን ዋጋ ያገኛሉ  ። ትዕግሥት የሚያስፈልገው በምድር ነው ። ከአሁኑ የተሻለ ነገር ይጠብቀኛል ብሎ ተስፋ ማድረግ እርሱ ትዕግሥት ነው ። ትዕግሥት በፍቅር ላይ ተመሥርቶ በተስፋ ላይ ድምድማቱን ይሠራል ። መምህር ተማሪውን እስኪገባው ድረስ መታገሥ አለበት ። ለዓለም ታላላቅ ነገር ያበረከቱ ሁሉ ትምህርት አልገባ ብሎአቸው የተሰደዱ ሰዎች ናቸው ። እነዚህ ሰዎች ትምህርቱን አልቻሉትም ሳይሆን ትምህርት ቤቱ እነርሱን አልቻላቸውም ማለት ይቀላል ። ብዙ ቅዱሳንም ትምህርት እንቢ ብሎአቸው ኋላ ግን የሰማይ መስኮት ተከፍቶላቸው ረክተው ምድርን አርክተዋል ። ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ ሰማያዊ ዜማ የተገለጠለት ፣ ብሉይና ሐዲስን ያመሰጠረ ፣ ቅኔን ያበረከተ ትልቅ መምህር ነው ። ቅዱስ ያሬድ ግን ትምህርት እንቢ ብሎት አዝኖ የተሰደደ ፣ እንደገና ተስፋ አድርጎ የተቀመጠና የእግዚአብሔርን ጸጋ ያገኘ ኢትዮጵያዊው ነቢዩ ዳዊት ነው ። መምህራን ተማሪዎቻቸውን በትዕግሥት ማስተማር ይገባቸዋል ። የትዕግሥት ቅጠሉ መራራ ፣ ፍሬው ግን ጣፋጭ ነው ። በሥጋ የሚወልዱ ያምጣሉ ፣ በነፍስ የሚወልዱ በአእምሮ የሚያሳድጉ የበለጠ ሊያምጡ ይገባቸዋል ። ተማሪዎችም ዛሬ አልገባ ያላቸው እውቀት ነገ ላይ በቀላሉ እንደሚይዙት ፣ እውቀት ከዕድሜም ጋር ተናባቢ መሆኑን ማወቅ አለባቸው ። በሰባት ዓመታችን የተማርነውን በሃያ ዓመታችን ብንማረው የዓመቱን በወር እንፈጽመው ነበር ። የልጆች የጨዋታ ዘመናቸው ተከብሮ ቀለል ያለ ትምህርት ቢሰጥ ፣ ጠንካራውን ከፍ ባለ ዕድሜ ቢሰጥ መልካም ነበር ። ለትምህርትም የሚያልፍ ጊዜ የለም ። 

ምድር ዱላ ያለባት ትምህርት ቤት ናት ። በልጅነት በሰበዝ ሀሁ እንላለን ፣ ስናድግ ደግሞ በብረት በትር እየተመታን የሕይወትን ሆሄ እንቆጥራለን ። በልጅነት ሰበዙ የሚነካው ፊደሉን ነበር ፣ በጎልማሳነት ግን ብረቱ የሚነካው እኛን ነው ። ፊደል እየነካን ተምረን ኋላ ደግሞ መከራው እየነካን  እንማራለን ። ሐዋርያው ጳውሎስ በትዕግሥት ጠበቀኝ ። በጆሮ የሰማሁትን በልቤ እስክሰማው ድረስ ታገሠኝ ። በመታገሡ መጠበቅ ነበረበት ። መታገሥ መጠበቅ ነው ። ሰውን በቃል ብቻ ማስተማር ከባድ ነው  ። የመምህራን አቅም በቃል ማስተማር ነው ። እግዚአብሔር ግን በሕይወት ውስጥ እያሳለፈ ያስተምራል ። መምህራን በሕይወት ውስጥ ፣ በጉዳትም በስብራትም እንደሚማሩ በማወቅ ደቀ መዛሙርቶቻቸውን መጠበቅ ወይም መታገሥ አለባቸው ። መታገሥ ተስፋ ማድረግ ነው ፣ እኔም ለዚህ የእውቀት ብርሃን እንደበቃሁ እርሱም ይበቃል ብሎ በሌላው ላይ ተስፋ አለመቁረጥ የመምህርነት መገለጫ ነው ። ልጅ ያልነበረ አባት ፣ ደቀ መዝሙር ያልነበረ መምህር የለምና ያሳለፍነውን እያሰብን የሚያልፉትን ተማሪዎች መታገሥ ይገባል ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በትዕግሥት ጠበቀኝ ። እስኪገባኝ ብቻ ሳይሆን እውነቱ ውስጤን እስኪቆጣጠረው ድረስ ታገሠኝ ።

 

እኔም ሐዋርያው ጳውሎስን ቀናተኛ ፈሪሳዊ ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን ስለማሳደዱ ጠየቅሁት ። ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ አለ፡- “ለእግዚአብሔር ብቀና እግዚአብሔር የሚወደውን ሰው አልጠላም ነበር ፣ የእኔ ቡድን ለምለው መቅናቴ ግን እግዚአብሔር የሚወደውን ሰው እንድጠላ አደረገኝ ። የቅንዓቱ እሳት ውስጤ ሲትጎለጎል ከእኔ አስተሳሰብ ውጭ ያሉት መጥፋት አለባቸው ብዬ እንዳምን አደረገኝ ።  ዓለም የጋራ ቤት መሆንዋን ረስቼ ፣ ሁሉ እንደ እኔ ካላሰበ የሚል አዙሪት ውስጥ ገባሁ ። አዙሪት የያዘው ሰው ሁሉም ነገር ይዞርብኛል ይላል ፣ ነገሮች ግን ባሉበት አሉ ፣ የእርሱ አእምሮ ግን ስፍራውን ለቋል ። ስለዚህ ከቆመ ነገር ጋር ይጋጫል ። ክርስትናው እኛን በመንቀፍ አልጀመረም ፣ ፈሪሳዊ ቅንዓቴ ግን ክርስትናውን በመጥላት ጀመረ ። ተነጋግሮ ለመግባባት እውቀት ቢኖረኝም አቅም ግን አልነበረኝም ። ከማይነጋገር ምሁር የሚነጋገር መሃይም በደህና ይኖራል ። ለዚህ ነው በገጠሩ በሽማግሌ ሲታረቁ በከተማው ግን በመጽሐፍ ቅዱስም አይታረቁም ። ጠብ በምሁራን ከገነነ መማር አለመማር ሆነ ። በቃል የማይነጋገር በድንጋይ መነጋገር ይጀምራል ። የሚናገር አምላክ የሚነጋገሩ የሰው ልጆችን ፈጠረ ። የሰው ልጆች የሚናገር አንደበት ይዘው ካልተነጋገሩ ተፈጥሮ ይባክናል ። ባለመነጋገር አእምሮ ሥራ ይፈታል ። አእምሮ ሥራ ሲፈታ እየዛገ ይመጣል ። የመርሳት በሽታ ይመጣል ። ባለመነጋገር የአፍ ጠረን እየተበላሸ ይመጣል ። ባለመነጋገር በግምት መጥፋት ይጀመራል ። “ይህን ጊዜ እንዲህ እያሰበ ነው የቀረው” በማለት አደጋ ደርሶበት የቀረውን ሰው “የአልኮል መጠጥ ሲጠጣ ነው የቀረው” ለሚል ግምት አሳልፎ ይሰጣል ። ባለመነጋገር ሰው ሁሉ የመሰለውን እያዳመጠ እውነትን ገሸሽ ብሎ ከወንድሙ ጋር ይጣላል ። ባለመነጋገር እየተፋቀሩ ሰዎች ይጣላሉ ። ባለመነጋገር ትንሹ ችግር አድጎ ቤት ያፈርሳል ። ባለመነጋገር የአገር መሠረቱ ይናዳል ። ባለመነጋገር ሰው ሁሉ የተፈበረከ ውሸትን ያምናል ። ባለመነጋገር በቆዳው ቀለም እገሌ እንዲህ ነው ብሎ ብይን መስጠት ይጀምራል ። 

የሰው ልጆች መነጋገርን የሚጠሉት ትንሽ ጉዳይ ትልቅ ጠብ ትወልዳለችና ከተነጋገሩ የምክንያቱ ትንሽነት ስለሚያስገምታቸው ነው ። የሰው ልጆች መነጋገርን የሚጠሉት ተሳስቻለሁ ለማለት ባለመፈለግና ካፈርሁ አይመልሰኝ ለሚል ድርቅና ታማኝ ለመሆን ነው ። መነጋገርን መጥላት በቂ እውቀት የለኝም ብሎ መረታትን መፍራት ነው ። መነጋገርን መጥላት ለፍቅር ያለን ዋጋ አናሳ መሆን ነው ። መነጋገርን መጥላት ለትውልድ አለማሰብ ነው ። መነጋገርን መጥላት ሐሜትንና ለዚያ ሰው ያለንን ሐሰተኛ ግምት ማመን ነው ። እባካችሁ ተነጋገሩ ። ካልተነጋገራችሁ እንደ እኔ ነፍሰ ገዳይ ትሆናላችሁ ። ያውም ቅዱሱን እስጢፋኖስን ታስወግራላችሁ” አለኝ ። 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ታላቅ ግለት ውስጥ ሲገባ የእኔም መንፈስ ማተኮስ ጀመረ ። የነቃ ያነቃል ፣ የጋለ ያግላል ። እውቀቴ ፣ ስሜቴ ሳይሆን እምነቴ ተቀጣጠለ ። እውቀቴ ሲግል የትምህርት ምስክር ወረቀት ለመሰብሰብ ይፈልጋል ። ስሜቴ ሲግል አሁን ዓለምን ካልያዝሁ ይላል ። እምነቴ ሲግል እግዚአብሔር ይታየኛል ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የአሳዳጅነት ዘመኑን መተረክ ቀጠለ፡-

“ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነኝ ያንን ወጣት እስጢፋኖስን ማስገደሌ ነው ። እስጢፋኖስ ለትንሽ ተግባር ተሹሞ ለትልቅ ክብር የበቃ ነው ። ለማዕድ ማስተላለፍ ተሹሞ ለወንጌል ምስክርነት የደረሰ ፣ ሐዋርያትን እንዲራዳ ተጠርቶ ከሐዋርያት ቀድሞ ሰማዕት የሆነ ነው ። እስጢፋኖስ ማለት አክሊል ማለት ነው ። ስምን መልአክ ያወጣዋል ትሉ የለ ። እስጢፋኖስ እንደ ስሙ የሰማዕትነትን አክሊል አገኘ ። ቀዳሜ ሰማዕት ሆነ ። እርሱ ሰማዕት በሆነባት ቀን እኔ ግን ነፍሰ ገዳይ ሆንኩኝ ። አንዷን ቀን አንዱ ሰማዕት አንዱ ገዳይ ፣ አንዱ ጻድቅ አንዱ ርኵስ ሲሆኑባት ይውላሉ ። እኔን የለወጠኝ ጸጸቱ አልነበረም ፣ ልቤ እየደነደነ ስለነበር ሌላም መግደል ያምረኝ ነበር ። የለወጠኝ የእስጢፋኖስ የይቅርታ ጸሎት ነበር ። እስጢፋኖስ ክርስቶስን መሰለ ። የእስጢፋኖስ የይቅርታ ጸሎትም የልቤን ደጃፍ አንኳኳ ። ተቃዋሚዎችን የክፋት ምላሽ የበለጠ ሲያደነድናቸው የፍቅር ምላሽ ግን ይሰብራቸዋል ። በዓለም ላይ መጥላት ቀላል ሲሆን ጠላትን መውደድ ግን ከባድ ነው ። ለጠላቶች መማለድ የሚጠቅመው የተበዳይን ልብ ከቂምና ከመሰበር ስለሚጠብቅ ፣ ተቃዋሚዎችም የሚመለሱበትን ጸጋ ስለሚልክላቸው ነው ። በእስጢፋኖስ ላይ ካወረድሁት ድንጋይ እርሱ የወረወረው የፍቅር ቃል የበለጠ አሸነፈኝ ። እስጢፋኖስ በሥጋ ሞተ ፣ እኔን ግን ልበ ሙሉ እንዳልሆን አደረገኝ ። ከዚያ በኋላ ፈቃድ ተቀብዬ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ብወጣም ልበ ሙሉ ግን አልሆንሁም ። ከዚያ ሁሉ በላይ እስጢፋኖስ ቤተሰቡን ያሳመነ ስለነበር የልጃቸው ገዳይ ብሆንም በእኔ እጅ መጠመቅ ፈለጉ ። እኔም ካጠመቅሁት ሁሉ የእስጢፋኖስን ቤተሰብ በማጥመቄ ትልቅ ዕረፍት ይሰማኛል ። ክርስቶስ ደም ለተቃቡትም ፍቅር ይሰጣል ። ብዙ የይቅርታ ታሪኮች አሉ ። እስጢፋኖስ የድንጋዩ ናዳ ከአናቱ ላይ ሳይበርድ የሰጠው ይቅርታ ፣ የእስጢፋኖስ ቤተሰብም የልጃቸው ገዳይ ሳለሁ በጳውሎስ እጅ ነው የምንጠመቀው ብለው ግድ ማለታቸው ከሁሉ የሚልቅ የይቅርታ ታሪክ ነው  ። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ማጥፋት ሲችል መሞቱ ከሁሉ በላይ ያሳዝነኛል ። 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጌታውን ፍቅር አስቦ ልቡ ሲነካ እኔም ኀዘኑ እንዳይቀጥል ላረጋጋው ፈለግሁ ። እኔ እንኳን ለወገሩኝ ክፉ አስበውብኛል ብዬ ስንቱን መቀየሜን አስታወስኩና ልቡና ስጠኝ አልኩኝ ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥር 11 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ