የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጳውሎስን አገኘሁት /9/

 

ብዙ ስለተጨዋወትን ከቆምን መቀመጥ ፣ ከዋልን ማምሸት ይኖራል ብዬ አስቤ ነበር ። ነገር ግን የቆመ የሚቀመጠው ሲደክመው ነው ፣ የሰማዩ ዓለም ግን ከበረቱ ድካም የለበትም ። ከዋሉም ማምሸት የለበትም ። ለካ ካህናቱ በሙታን ሽኝት ላይ ሲያስተምሩ፡- “ከዚህ የድካም ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ተሸጋገረ” እያሉ የሚናገሩት እውነት ነው አልኩኝ ። እኔም ሐዋርያውን፡- “ስንት ዘመን የኖርህ ይመስልሃል ?” አልኩት ። እርሱም ዘመን የሚቆጥሩ የሚኖሩለት ብዙ ጉዳይ ያላቸው ሰዎች ናቸው ። እኛ ግን የምንኖረው ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ በመሆኑ ከዘመን ቍጥር ወጥተን በዘላለም ውስጥ ተሰውረናል ። ደግሞም በእግዚአብሔር ዘንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ነውና ሁለት ቀን የኖርን አይመስለንም” አለኝ ። እኔም ገና ወደ ምድር ስመለስ የሚጠብቀኝን የኑሮ ትግል በማሰብ ለመጨነቅ ሞከርሁ ። መጨነቅ ግን አልቻልኩም ። ጭንቀት ከማይደርስበት ከፍታ ላይ ነበርሁና ራሴን በደስታ ጥምቀት ውስጥ ተሰውሮ አገኘሁት ። የመጨነቅ መብትን ተጠቅሞ እንኳ መጨነቅ የማይቻልበት ሰማያዊ ዓለም ስላለን ደስ አለኝ ።  ምድርን የመጨረሻ ቤታቸው አድርገው ለሚኖሩና ተስፋ ያደረጉት ነገር ሲሰበርባቸው በእግዚአብሔር መጽናናት ላቃታቸው ወገኖቼ እንዲህ ያለ ተድላ መኖሩን ለመንገር ቸኮልሁ ። 

በአንዱ ልቤ፡- “ሰማይ ደርሶ በመምጣቱ ተአምር ሆነለት” ብለው እንደሚቀበሉኝ እንጂ ከልባቸው የሰማይን ምሥጢር ለማወቅ እንደማይሹ አወቅሁና አዘንሁ ። መለኮታዊ የሆነ መገለጥን ትተው ስለ ሽሮና በርበሬ እንዲነገራቸው የሚፈልጉ ፣ ስለ ሰማይ ሰርግ ትምህርት ይሰጣል ሲባል ቀርተው ጓደኛ መያዝ እንዴት ይቻላል ? የሚል ትምህርትን ከቤተ ክርስቲያን የሚናፍቁ ሰዎችን በማሰብ ልቤ ስርቅ አለብኝ ። ጳውሎስ ሊገድል ወጥቶ ሐዋርያ ሆኖ ተመለሰ ። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ያለው ብዙ ወገን ግን ሊድን መጥቶ ገዳይ ሆነ ። የእስራኤል የመጀመሪያው ንጉሥ ሳኦል አህያ ፍለጋ ወጥቶ ንጉሥ ሆኖ ተመለሰ ። አሁን የያዝነው ምእመን ግን ክርስቶስን ብሎ መጥቶ ሥጋዊ ነገር ይዞ ይመለሳል ። በሰማያዊና በመንፈሳዊ በረከት ተባርከሃል ሲባል አይሞቀውም ፣ በትዳር ተባረክሁ ብሎ ግን የምስጋና መርሐ ግብር ይዘረጋል ። ክርስቶስ ሞተልህ ሲባል ጆሮውን ጥጥ ደፍኖ ልጅ አልወለድሁም እያለ የእግዚአብሔርን ስጦታ ነቢይ ነን ከሚሉ ሰዎች ይፈልጋል ።

ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አሥራ አራቱ መልእክታቱ ከመተንተኑ በፊት ስለ መጨረሻው የሕይወት ታሪኩ እንዲነግረኝ ፈለግሁ ። ሐዋርያውም፡- “ኔሮ ቄሣርን እወደዋለሁ” አለኝ ። እኔም ድንግጥ አልኩኝ ። ሐዋርያውም፡- “የምወደው እርሱ ባይገድለኝ ሰማዕት ፣ እርሱ ሞትን ባይፈርድብኝ ሰማይን ቶሎ አላይም ነበር ። ደግሞም ለፊልጵስዩስ ሰዎች የምመኘውን ትልቅ ነገር ነግሬአቸው ነበር ። እርሱም ክርስቶስን በሞቱ ልመስለው ነበር ። ይህን ሕልሜን ያሟላልኝ ይህ ንጉሥ ነው ። እጅግ ክፉ በሆነ ሰው እጅግ ደግ ነገር ሆነልኝ ። እንደ ሻማ ብርሃን የሆነችውን ሕይወቴን ለመንጠቅ ሞክሮ ምሽት ከሌለበት ቀን ፣ ከማይጠልቅ ፀሐይ ውስጥ ነፍሴን ጨመራት ። ሰዎች ያጎደሉብህ ሲመስላቸው ብዙ እየጨመሩልህ ነው ። ፣ ያመሰገኑህ ሲመስላቸው ግን ብዙ እያጎደሉብህ ነው ። ኔሮ ቄሣር በ54 ዓ.ም ሥልጣን ይዞ እስከ 64 ዓ.ም. በክርስቲያኖች ላይ ጥላቻ አልነበረውም ። በድንገት ግን ይህ ጠባዩ ተለወጠ ። ሰዋዊ የሆነ ቅንነት በድንገት ይለወጣል ። ምክንያቱም የመቅረዝ ብርሃን ዘይት ካልተሞላ እንደሚጨልም ፣ የሰው መልካምነትም ከእግዚአብሔር ጸጋ ካልተጠጋ እየጎደለ ይመጣል ። እጅግ ክፉ ነገሥታት የሚባሉ ደግ የነበሩ ናቸው ። ሰው ለደግነታቸው የሰጣቸውን ክፉ ምላሽ ይቆጥሩና በአቅማቸው ልክ ክፉ ይሆናሉ ። ሰው የሚያጠፋው የአቅሙን ያህል ነውና ጥፋታቸውም ምድር የማትችለው ይሆናል ። ኔሮን ቄሣር ለሥልጣንና ለምቾት የነበረው ስስት ወደ እብደት እየወሰደው መጣ ። ሥልጣንን ማፍቀር እብድ ያደርጋል ። በዚህ ምክንያት እናታቸውን የገደሉ ፣ ወንድሞቻቸውን የሰየፉ አያሌ ናቸው ። ሥልጣን ዕለታዊ እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የለውም ። ሥልጣንን ከሥልጣን ውጭ ሲያዩትና ሲቀመጡበት እይታው ለየራስ ነው ። የምቾት ፍቅር ያሳብዳል ። ምክንያቱም ብዙዎች እየተራቡ ስለ ትርፍ ነገር ማሰብ በራሱ መንፈሰ እግዚአብሔርን ስለሚያርቅ ነው ። ራስ ወዳድነት ከእግዚአብሔር መጽናናት ይለያል ። 

ሐዋርያው ክርስቶስን በሞቱ ለመምሰል ሲመኘው የነበረ ሐቅ ነው ። ዛሬ ክርስቶስን በትንሣኤ ኃይሉ ፣ ድሆችን ባጠገበበት በረከቱ ፣ ባሕር ላይ በተራመደበት ብርታቱ ሊመስሉት የሚፈልጉ ፣ ተአምርን እንደ ትርኢት እያሳዩ ሀብትን ለማከማቸት የሚከጅሉ ብዙ ክርስቲያኖች አሉ ። ወይም አለን ። ሐዋርያው ግን ክርስቶስ በሞተበት መንገድ በአልጋ ፣ በአስታማሚ መሐል ፣ በሐኪም እርዳታ ውስጥ ሆኖ ሳይሆን በሰማዕትነትና በዓለም በመገፋት ለማለፍ ይሻ ነበር ። በርግጥ ክርስቶስ ሲሞት ቤዛ ፣ ሐዋርያው ሲሞት ሰማዕት ነው ። ሐዋርያው ስለ ክርስቶስ ሞተ ፣ ክርስቶስ ግን ስለ እኛ ሞተ ። ሐዋርያው አሁንም ሳይታክት የልቤን መሻት የአንደበቴን ጥያቄ ለመሙላት ተነሣ ። 

“በ67 ዓ.ም. ሐምሌ 5 ቀን በሮም አደባባይ ለሰማዕትነት ስቆም ሐዋርያውና ትልቁ አባት ጴጥሮስ ተይዞ መጣ ። እኔም ከኢየሩሳሌም ተከስሼ ለቄሣር ይግባኝ ብዬ መጥቼ ነበር ። ያድነኛል ያልሁት ያ ቄሣር ግን የበለጠ ፍርድ አዛባብኝ ። ሁለት ዓመት አሥሮ እንደ ገና የቁም እስረኛ አድርጎ ፈታኝ ። ከዚያም ለመጨረሻ ጊዜ ታስሬ ለሰማዕትነት በአደባባይ ቆምሁ ። ሐዋርያው ጴጥሮስን ሳየው ልቤ ተጽናና ። እግዚአብሔር አንዳችንን ለአንዳችን መጽናናት ብቻ ሳይሆን የጥንካሬ ምንጭ ያደርገናል ። እኔም ሐዋርያውን ሳስብ ትዳሩንና የሽምግልና ክብሩን ሳያስብ ለመሞት በመምጣቱ ልቤ የበለጠ ጨከነ ። ክርስቶስ ከትዳርም ከልጅም በላይ እንደሆነ ተረዳሁ ። ለመፍራት ሽምግልና ጥሩ ምክንያት ነበረ ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ ግን ራሱን ያሳመነውን ምክንያት ክርስቶስን ያሳምነዋል የሚል ፌዝ ውስጥ አልገባም ። ከቃሉ ይልቅ ምክንያታቸውን የሚያምኑ ፣ መለኮትን ማታለል እንደሚችሉ የሚያስቡ ፣ ለእግዚአብሔር የሰጡትን ሕይወትና ዘመን እንዲሁም በረከት መልሰው የሚወስዱ እንደ ሐናንያና ሰጲራ የሞት ፍርድን ይቀበላሉ ። ሐዋርያው ጴጥሮስም እኔን ባየ ጊዜ በረታ ። ልጄ የሚሆን የራሱ የቤት ቍጥርና የራሱ የግል ኑሮ የሌለው ጳውሎስ እንዲህ ሲጨክን ፣ ዓለም ቀረብኝ ብሎ ሳያዝን ፣ በደስታ ሰማዕት ለመሆን ሲመጣ እኔማ የበለጠ መበርታት አለብኝ ብሎ ወደ ገዳዮቹ በፍጥነት ቀረበ ። ገዳዮቹም ሞትን መሸሽ የሰው ተፈጥሮ ሳለ ወደ  ሞት መፍጠን ምን ዓይነት የልብ ቆራጥነት ነው ብለው አሰቡ ። አምላካችን ግን እንደ ሌሎች ነገሥታትና ጣኦታት ሙቱልኝ ሳይለን የሞተልን መሆኑን ማወቅ ነበረባቸውና ይህን ገለጥሁላቸው ። እነርሱም እየተቆጡኝ ያደምጡኝ ነበር ። ያመንሁትን ከመመስከር በላይ ላምንሁበት ዋጋ ስከፍል ዋጋ አስከፋዮቹ የበለጠ የማመልከውን እየወደዱት ይመጣሉ ። እውነት ላልሆነ ነገር በደስታ የሚሞት የለምና ብለው ወደ ክርስቶስ ይጠጋሉ ።” 

“ወታደሮቹና የሞት አስፈጻሚዎቹም ጳውሎስ ውርደት ባለበት የመስቀል ሞት እንዳይሞት ብለው አዘዙ ። ሮማዊ ዜግነት ያለው በመስቀል ሞት አይቀጣምና ። ጴጥሮስ ግን በመስቀል ሞት ይቀጣል ሲሉ ወዲያው ከአፋቸው ነጥቆ እኔ የምሞተው የቁልቁሊት ተሰቅዬ ነው ብሎ ወታደሮቹ እግር ሥር ወድቆ ለመነ ። እኔም ግራ ገባኝ ። ወታደሮቹም እጅግ በከፋ ሁናቴ ለመሞት መወሰኑን ማመን አቃታቸው ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ግን፡- “እንደ ጌታዬ ተሰቅዬ ለመሞት ሕሊናዬ አይፈቅድልኝም ፣ የቁልቁሊት ስቀሉኝ” አለ ። አንደኛው ወታደርም ልቡ በክርስቶስ ፍቅር መወጋት ጀመረ ። ግዳጁ ነውና የሞት ፍርዱን ለማስፈጸም ተነሣ ። እኔም ከሥጋዬ ማደሪያ ተለይቼ ወደ ሰማይ መጓዝ ጀመርሁ ።”

በሰማይ ወደብ ላይ የመሰከርሁለት ክርስቶስ ከአእላፋት መላእክት ጋር ሁኖ ሊቀበለኝ መጣ ። የድል ነሺ የመለከት ድምፅ እጅግ ያስተጋባ ነበር ። እልልታው ሲሰማ ውስጤን እንደ መብረቅ ይሰነጣጥቀው ነበር ። በምድር ላይ የኖርሁበትን ዘመን ሁሉ የሚክስ ያ ሰዓት ነበረ ። የብሉይ ኪዳን ደጋግ አባቶች ፣ የአዲስ ኪዳን አማንያን የተባረኩት ቅዱሳን በታላቅ ሽብሸባ ፣ መቆሚያ በሌለው ቅኔ ይዘምሩ ነበር ። ከዝማሬው የተነሣ ራሴ ሊያመልጠኝ ይታገለኝ ነበር ። የሚገርመው ያንን ቅኔና ቋንቋ ሰምቼው አላውቅም ፤ ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ ግን አብሬ መዘመር ጀመርሁ ። የበገናው አንዱ አውታር ሲመታ ዳርቻ እስከ ዳርቻ ይሰማ ነበር ። አሥሩ አውታር ሲነካ ታላቅ መናወጥ ይከሰት ነበር ። ከአጀቡ የተነሣ ክርስቶስ ጋ እንዴት ልድረስ ። ሁሉም የደስታ አበባ ያስታቅፉኛል ። ከአቤል ጀምሮ ያረፉትን ሰማዕታት እያገኘሁ ከሺህ ዓመታት ጋር በአንድ ቅጽበት ውስጥ እየተነጋገርሁ ነበር ። ያለፈውና የሚመጣው ዘመን ሁሉ አሁን ሆኖልኝ ነበር ። በምድር የሰዓት አቆጣጠር ስንት ዘመን እንደ ፈጀብኝ አላውቅም ። የደስታውና የዝማሬ ጅረት ግን ልክ አልነበረውም ። በመጨረሻ የሰበክሁትን ክርስቶስን ለማግኘት ወደ ክብሩ ፀዳል ቀረብሁ ። በምድር ላይ እንደ ነበረው በትሕትና አልነበረም ። በአይሁድ ሸንጎ ተከስሶ ሲቆም አይቼው ነበር ። አሁን ግን ዓይን ሊያየው አይደፍርም ። ሳገኘው ዘልዬ የምጠመጠምበት ይመስለኝ ነበር ። እንዳልቀርበው ግርማው ፣ እንዳልርቀው ሞገሱ ይታገሉኝ ነበር ። እርሱም ወደ ራሱ አቅርቦ ሳመኝ ። ታጅቤም ርስቴን ተቀበልሁ ።” 

ሐዋርያው እነዚህን ነገሮች ምነው ባልጨረሰ እያልሁ ጭንቀት ያዘኝ ። “አንተ ገና በሥጋ ማደሪያ ውስጥ ነህና መስማት በምትችለው መጠን እንጂ በእውነቱ ልክ አይነገርህም” አለኝ ። እኔም “እውነት ነው” ብዬ እጅ ነሣሁ ።

ይቀጥላል

የካቲት 2 ቀን 2013 ዓ.ም

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ