/ክፍል 1/
ሰው መሞቻው ሲቃረብ መቀበሪያ አገሩን መራቅ አይፈልግም ። የኢየሩሳሌም ሐዋርያ ሁኖ ኑሮ አሁን ደግሞ የሮም ሰማዕት ለመሆን ፈልጓል ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ወደ ሮም እንደ መጣ ሰማሁ ። ወደ ሮም የሚመጡ የዓለምን ትልቅ ከተማና ንጉሠ ነገሥቱ ያለበትን ውብ መንደር ለማየት ነው ። ለኑሮው የተጠየፋትን ሮምን ለሞቱ ሲመርጣት ፣ ተሸሽጎ ኑሮ ፣ በኢየሩሳሌም ገጠር ተጥሎ በደማቅ ከተማ ሊሠዋ መከጀሉ እጅግ ገረመኝ ። ጌታ ሲጠራው 58 ዓመቱ ገደማ እንደነበር ባለፈው ያገኘሁት ጳውሎስ ነገረኝ ። አሁን ደግሞ ከጥሪው እስከ አገልግሎቱ 37 ዓመት ይሆነዋል ። እንደምገምተው ጴጥሮስ የ95 ዓመት አረጋዊ ነው ። አሟሟቴን አሳምርልኝ በሚባልበት ዕድሜ ቁልቁል ሊሰቀል መምጣቱ ገረመኝ ። ላገኘው ማሰስ ጀመርሁ ። ሀገረ ስብከቱን ለቆ እንዴት መጣ ስል ኢየሩሳሌምም በአርበኞች ግንባር እንቅስቃሴ ከሮማውያን ጋር ብርቱ ጦርነት ውስጥ ናት ። ደግሞም ለንጉሠ ነገሥቱ ሳይመሰክር ሞት እንዳይቀድመው ሰግቷል ። ኔሮን ቄሣር ጠባዩ ተለውጦ ለስህተቱ ክርስቲያኖችን ተጠያቂ ማድረግ የጀመረው በ64 ዓ.ም. ጀምሮ ነው ። በዚህ የቍጣና የስደት ጊዜ መምጣቱ ገረመኝ ። በኢየሩሳሌምም ሁከት ፣ በሮምም ጭንቀት ነበረ ። ሮም ተጨማሪ ቤተ መንግሥት ለመሥራት ከተማ አቃጥላ ክርስቲያኖች ላይ በማሳበብ ጭፍጨፋ ታካሂዳለች ። ኢየሩሳሌም ደግሞ ነጻነት ወይስ ሞት ብላ ትፋለማለች ። በሁሉም ቤትና አገር እሳት አለ ።
ባሻገር ሳይ ሐዋርያው ጴጥሮስን አየሁት ፤ በዚያ ዕድሜው እየተጣደፈ ሲሄድ ጎበዝ አይቀድመውም ። እኔም አጠገቡ ያለውን ሰው እየመከረው ነውና ላደናቅፈው አልፈለግሁም ። እርሱ ግን እንዲህ እያለ ሲናገር ጆሮዬን ጥዬ እየሰማሁ ከኋላቸው ክው ክው እል ነበር ።
“ልቤ እንደ ባሕሩ ይዋልላል ። ቢጸና ብዬ ብመኝም በሚበልጥ ማዕበል ይናጣል ። የቆምሁበት መሠረት ሲናወጥ ፣ የማየው ሰማይ በደመና ፣ ዙሪያዬ በጉም ይጋረዳል ። ታንኳዬን ሠውቼ ራሴን ለማዳን ብዙ ጥረት አድርጌአለሁ ። ንብረት ስለ ሰው እንጂ ሰው ስለ ንብረት አልተፈጠረም ብዬ ያለኝን ሁሉ ለሰላሜ ስል ከፍያለሁ ። ለማግኘት ማግኘት ብቻ ሳይሆን ሰላምን ለማግኘት ገንዘብን መጣል አስፈላጊ እንደሆነ ተረድቻለሁ ። ከጠፋው ጥሪት ጋር ከጠፋሁ ፣ ከተወረሰው ርስት ጋር ካልተቀበርሁ ካልሁ እኔ እኔ መሆኔ ይቀራል ። ያምናው ማዕበል ዘንድሮ ፣ ያለፈው ወጀብ ዛሬ ይመጣል ። ማዕበል ያው ማዕበል ነው ። ሁከት ነውና ሰላም መሆን አይችልም ። ባሕርዩና ሥሪቱ አይፈቅድለትም ። በለውጥ ሕግ የምመራ እኔ ግን ያው ሆኜ መጠበቅ አይገባኝም ። ካለፈው ዓመት ይልቅ የዘንድሮ ፈተና ለተማሪው ይከብደዋል ። ያው ፈተና ከመጣ ተማሪው ክፍሉን አልለወጠም ። ሌላ ፈተና ከመጣ ግን ደረጃው አድጓል ማለት ነው ። ማዕበል ከባሕሩ ዳርቻ ላለ ሰው መዝናኛው ነው ። መጣሁ ሄድሁ ሲል እንደ ባሕል ጭፈራ እንደ ሕብረት ውዝዋዜ የሚያስገርም ነው ። ባሕሩ መሐል ላለ ግን ማዕበሉ አስጨናቂ ነው ። ዳር ሆነው የሚታዘቡ ፣ በሰው ቍስል እንጨት የሚሰድዱ አመስግን ፣ ለመከራ እጅ አትስጥ ፣ ደግሞም ስምህ ካልጠፋ የእግዚአብሔርን ስም ማክበር አትችልም ይላሉ ። በዳርቻው ላይ ያለ ስለ ማዕበል ያመሰግናል ። ሳይሰለች የሚያጫውት ፣ ከፍ ዝቅ የሚል ፍልቅልቅ ሕፃን ነውና ። በባሕር መካከል ያለ ግን ከማዕበሉ አውጣኝ እያለ ይጸልያል ። ያስጨነቀኝ ማዕበል የምስጋና ርእስ ይሆንልኛል ። መሐል ላይ ያስለቀሰኝ ከሰማዩ ዳርቻ ላይ የዝማሬ ቅኔ ያስገኝልኛል ።
በትዳር ዓለም ከገባሁ ቢያንስ አርባ ዓመት ይሆነኛል ። ክርስቶስን አላገኘሁትም ያለሁበት ድረስ መጥቶ ያገኘኝ እርሱ ነው ። እርሱ ሲያገኘኝ የአርባ ዓመት የትዳር እውቀቴ እርሱን ለማወቅ ተጨማሪ ጥበብ አልሆነልኝም ። ብርሃኑን ጌታ በብርሃን ቃሉ ማየት ግድ ይላል ። በፀሐይ ብርሃን ፣ በመቅረዝ ወጋገን እርሱ አይታይም ። እርሱ የሚታየው በቃሉ ብርሃን ነው ። ከብርሃን ጌታ የተገኘው ብርሃን ቃሉ ራሴን ያሳየኛል ። ልክ የሆነውን ማሳየት ብቻ ሳይሆን ውሳኔዬን እየተከተለ ልክ ያደርገኛል ። ልክ ስለሆኑ ነገሮች ብዙ እውቀት ያላቸው ልክ ያልሆኑ ሰዎች አሉ ። እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያለው ዓላማ ልክ የሆኑ ነገሮችን የምናውቅ ሳይሆን ልክ የሆኑ ሰዎች ማድረግ ነው ።”
የሚናገረው ሁሉ ብርቱ ቃል ነው ። ከሽምግልና እውቀት ይልቅ የሰማይ ጥበብ ያለበት ነው ። የጁልየስ ቄሣር ጎዳና ላይ እንደደረስን የጳውሎስ ተማሪ የነበረችው ድንግላዊት ፌበንን አገኘናት ። እኔ ከኋላቸው እየተከተልሁ መሆኔን አላወቁም ። ጴጥሮስም በጉባዔ እንደ ተሰየመ ፣ አትሮኖንስ እንደ ጨበጠ ሁኖ ይናገር ነበር ። መንገደኛው ሁሉ ምን እያለ ነው እያለ ዞር ብሎ አይቶ አይሁዳዊ መሆኑን ከአለባበሱ ተረድቶ ገላምጦት ያልፋል ። እኔም ከኋላቸው እንደ ጥላ እየተከተልሁ ፣ ስውር ደቀ መዝሙር ሆኜ እየተማርሁ ነበር ። ያቺ ፌበን በጎዳናቸው ትክክል መጣች ። የምትሄድበትን መንገድ ጥላ ከእነ ጴጥሮስ ጋር ተመለሰች ። ከእግዚአብሔር ሰው ጋር የማሳልፈው የማይደገም ዕድል ሊሆን ይችላል ። ሌላው ነገር ይደረስበታል ። ጽድቅ ቀዳሚ ሲሆን ጉዳይ ተከታይ ይሆናል ። ጉዳይ ሲቀድም ጽድቅ ይከተላል የሚል ስሜት ተቆጣጠረኝ ። ያች እማሆይ ፌበን ጴጥሮስን አንድ ጥያቄ ነበረኝ አለችው ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ሊሰማት ጆሮውን ቀሰረ፡- “ጌታችን አንዳንድ ሰዎችን የገሠጸበት ቃል ስድብ አይመስልም ወይ” ብላ ጠየቀች ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በሰፊው ሊመልስላት ጉሮሮውን ሞረደ፡-
“ጌታችን ፈሪሳውያንንና መሪዎችን ይዘልፍ ነበረ ። እርሱ መደበኛ ትምህርትን ለደቀ መዛሙርት ሲሰጥ መደበኛ ያልሆኑ ትምህርቶችን አንድ ጊዜ ለሚያገኛቸውና ተግሣጽ ለሚያስፈልጋቸው ያስተላልፍ ነበር ። ብዙ ጊዜ ትምህርትን የማይማር የትምህርት ተቃዋሚ ነው ። እውቀት ብልጭ እንዳትል ዘብ የቆሙ ሰዎች አሉ ። አደንቁረው የሚገዙ ሕዝብ ሲማር አልገዛም ብሎ ያምጻል ስለሚሉ ትምህርትን አይወዱም ። ያልተማረ ሰው ቢጭኑበት አህያ ፣ ቢጋልቡት ፈረስ ነው ። በቅሎ አትወልድም የሚወልድም አትወድም ይባላል ። ፈሪሳውያንም አይማሩም ፣ የሚማርም አይወዱም ። ጌታም እንደዚህ ያሉትን ሰዎች ይገሥጽ ነበር ። ተግሣጽ በስህተቱ ለሚኮራና ለሚቀጥል የሚሰጥ የትምህርት ዓይነት ነው ። ተግሣጽና ዘለፋ አንዱ የማስተማሪያ ዘዴ ነው ። ተግሣጽ ረቂቅ ዱላ ፣ ሕሊናን የሚገርፍ ጅራፍ ነው ። በትምህርት ቤት ከተማርነው ትምህርት ይልቅ የተሳሳትነውና የተቀጣነውን አንረሳውም ። የአምናው ትምህርት ዘንድሮ ይረሳል ። በመከራ የተማርነው ግን በዓለት ላይ የተቀረጸ በመሆኑ አይጠፋም ። እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ የሚያስተምረን ትምህርቱ እንዳይጠፋን ነው ። ተግሣጽም የቅጽበት መከራ ነው ። ትምህርቱም አይረሳም ።
የጌታችን ትምህርት ተግሣጽም ማስጠንቀቂያም ያዘለ ነው ። እርሱ ያልተማሩትን ሲያስረዳቸው ተምረው የደነቆሩትን ግን ይገሥጻቸዋል ። ማስተማር በሰው ሕሊና ላይ ሥዕል መሳል ነው ፤ ሰሌዳውም ፣ ቡሩሹም ፣ ቀለሙም አይታይም ። ትምህርቶች ሥዕል ይበዛባቸዋል ። ከተራ ሰው ይልቅ ሠዓሊዎች ትምህርት ሲማሩ ይገባቸዋል ። በሕሊናቸው ማጠራቀሚያ የሚያቁሩት በምስል ነው ። ጌታችን የሰማይ ወፎችን እዩ እያለ ስለ ኑሮ ዋስትና ፣ አበቦችን እየዳሰሰ እንዴት እኖራለሁ የሚል ፍርሃትን ይጥል ነበር ። ቀና ካሉ የሰማይ ወፎች ፣ ካማተሩ የመስክ አበቦች አሉና ትምህርቱ አይረሳም ። ፍጥረታት ደስታዎቻችን ብቻ ሳይሆን መማሪያዎቻችንም ናቸው ። መጽሐፍ ቅዱስ በሥዕል የተሞላ መጽሐፍ ነው ።
በተግሣጾች ውስጥ ስድብ የሚመስሉ ነገሮች ተስተውለው ከሆነ ትርጉማቸውን ማየት ያስፈልጋል ። ጌታችን የገሠጸው በአብዛኛው በኃላፊነት ላይ የነበሩትን ነው ። ሄሮድስን ቀበሮ ብሎታል ። ቀበሮ ሲታይ ውሻ ይመስላል ። ነገር ግን አውሬ ነው ። ሄሮድስም ሲታይ የአይሁድን ሃይማኖት የተቀበለ ይመስላል ፣ ልቡ ግን አረማዊ ነው ። ሄሮድሳውያን የኤዶም ወይም የዔሣው ዘሮች ናቸው ። ዔሣው አደነተኛ የበረሃ ሰው ነበር ። ሄሮድሳውያን ወዲህ ቤተ መቅደስን አስፋፍተው ያድሳሉ ፣ ወዲህ ሕፃናትን ያርዳሉ ። ፍቅርን ያልመረጠ ፣ ታማኝነት የሌለው ነውና ቀበሮ መባሉ ገላጭ ነው ። እንደ ሰው ለመሆን የፈለጉ አራዊት ባይኖሩም እንደ አራዊት የሆኑ ሰዎች ግን ነበሩ ። ውሻ ሰውን መርጦ የቀረ የቀበሮ ዘመድ ነው ። ድመትም ሰውን መርጣ የቀረች የነብር ዘር ናት ። ሄሮድስ ግን ፍቅርን ያልመረጠ ቀበሮ ነው ።
ጌታችን ፈሪሳውያንንም ገሥጾአል ። ታላቅ የሃይማኖት ቡድን አቋቁመው ፣ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ተውኔታቸው ልቡን ሰልበው ፣ በላያቸው ቅዱሳን በውስጣቸው ቀማኞች የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎችን መገሠጹ እውነት ነው ። ጌታችን ዕውር ፣ ደንቆሮ መሪዎች ብሏቸዋል ። አያስተውሉም ፣ ውስጣዊ እይታቸው የተንሸዋረረ ነውና ዕውር ያለው የውጭ ዓይናቸውን ሳይሆን አስተሳሰባቸውን ነው ። በርግጥም የሚበልጠውን የማያውቅ ፣ ከመቅደሱ ወርቁን ፣ ከሰጪው ስጦታውን የሚያስበልጥ ዕውር ነው ። እናውቃለን ፣ እንመራለን የሚሉት ዕውራን ናቸውና ዕውር መሪ የሚያደርሰው ወደ ገደል ነው ። ተግሣጹ ከጥፋታቸው አይበልጥም ። ደንቆሮ ማለቱም የማይሰሙና የመጨረሻ አዋቂዎች ነን ብለው ራሳቸውን በማስቀመጣቸው ነው ። የማወቅ ዕድሉን የማይጠቀምበት ደንቆሮ ነው ። ስለ እጅ ንጽሕና እየተጨነቁ ስለ ልብ ክፋት ግዴለሽ የሆኑትን ትንኝን የምታጠሩ ግመልን የምትውጡ ብሎ መገሠጹ እውነት ነው ።
እናንተ ግብዞች እያለም ገሥጾአል ። ሌቦች እንዳይታወቁ ጭንብል ያጠልቃሉ ። ሁሉም ሌቦች ሳይሆኑ የሰለጠኑ ሌቦች ባለ ጭንብል ናቸው ። ሌብነቱን ይፈልጋሉ ፣ ሌባ መባልን ግን አይፈልጉም ። ፈሪሳውያን የነፍስ ሌቦች ነበሩ ። የገንዘብ ሌባን እየገሠጽን የነፍስ ሌባን ዝም ማለት አይገባም ። ፈሪሳውያን ላዩ ያማረውን የተለሰነ የመቃብር ድንጋይ እንደሚመስሉ ተናገረ ። የመቃብር ድንጋይ ውብ ነው ። የፍቅር መግለጫ አበባ አለበት ። የሃይማኖት ምልክት የሆነው መስቀልም ፣ የዳዊት ኮከብም ይቀመጥበታል ። የሕይወት ታሪክን ይዟል ። የቅዱስ መጽሐፍ ጥቅስም አለበት ። የሚወዱት ሰዎች ስም ዝርዝርም ተጽፎአል ። እርሱ ግን አበባውንም ፍቅሩንም ሊቀበል የማይችል ፍርስራሽ ሆኖ በውስጥ አለ ። ላዩን ያዩ ቢከፈት ግን አጽምን ማየት አይችሉም ። ግብዞችም እንዲሁ ናቸው ። አበባ ይሰጣቸዋል የሚወዳቸው ግን የለም ፤ የሕይወት ታሪካቸው ይነገርላቸዋል ፣ ሕይወት ግን የላቸውም ። ጥቅስ ተሸክመዋል ፣ እነርሱ ግን አያነቡትም ። እነዚህን መገሠጽ ለጌታችን ሥልጣኑ ነው ። የሰው ልጅ ያልጣመውን እውነት ስድብ ይለዋል ።
አንድ ሐኪም ሲያክም በሰው ሰውኛ ክብርን ሽሮ ነው ። ዓይኑን ወደታች ከፍቶ ፣ አፍህን ክፈት ብሎ ፣ ምላስህን አውጣ ብሎ ፣ ልብስ አስወልቆ ፣ ባለቤቱ ብቻ የሚያገኘውን የአካል ክፍል ነክቶ ፣ ቆዳን በስለት ቆርጦ ያክማል ። ከእነዚህ ነገሮች አንዱም ከሐኪም ውጭ በሌላ ሰው ቢደረግ የመጋደል ርእስ ይሆናል ። ሐኪም ግን የሚያክመው ውርደት በሚመስል ነገር ነው ። ተግሣጽ ውርደት ቢመስልም ድኅነት ያለበት ነው ።
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠውን ምላሽ ትክ ብላ የሰማችው የክንክራኦስዋ ፌበን በፊትዋ ታላቅ ደስታ ይነበብ ነበር ። ሰላምታ ሊሰጣት ቡራኬም ሊያክልበት ጀመረ ። ከሰላምታ በፊት እርስዋም ጥያቄዋን አስቀደመች ፣ ሐዋርያውም መልሱን አስቀደመ ። ፌበን ሆይ በ56 ዓ.ም . ገደማ የሮሜን መልእክት ይዘሽ እንደመጣሽ እዚሁ ቀረሽ ወይ ? ሲላት እኔም አብሬ ለመጠየቅ ተነሣሣሁ ። እንደምከተላቸው ግን ገና አላወቁምና ዝም አልሁ ። ትምህርት በመደበኛ ሰዓትና ቦታ ይሰጣል ። መደበኛ ባልሆነ ቦታና ሰዓትም ትምህርት ይኖራል ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም.