ማለዳው ብሩህ መስሎ ታየኝ ። ማለዳው ብርሃን ሆኖ የሚታየው በሁለት ነገሮች ነው ። አንደኛው የምንሄድበት ሲኖረን ሁለተኛ የምንሄደው በረከተ እግዚአብሔር ያለበት ስፍራ ሲሆን ነው ። ትላንት ወደ ቤቴ ስሄድ ደስታ ኃይል ሰጥቶኝ ነበር ። ያለ ሰረገላ በምንጣፍ ላይ እንደሚጓዝ ያህል መንገዱ ምቹ ሆኖልኝ ነበር ። በግራ በቀኜም ብዙ ጠባቂዎች እንዳሉኝ እየተሰማኝ ልቤ ሙሉ ነበር ። የሮም አደጋ ጣዮችና ቀማኞችን እንደ ዛሬ ደፍሬ አላውቅም ። ክፉዎችን እኔ የማያቸው እነርሱ ግን የማያዩኝ መስሎ ይሰማኝ ነበር ። የእግዚአብሔርን ቃል ስንሰማ ከዋልን ቅዱሳን መላእክት በታላቅ ጥበቃ ወደ ማደሪያችን ያደርሱናል ። የሚታየውንና የማይታየውን ጠላት በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ተከልለን ማለፍ እንችላለን ። ደስታ የሚያስተኛ ይመስለኝ ነበር ። ደስታ ግን እንቅልፍ የሚሰጠውን አቅም ስለሚሰጥ ያነቃል ። ሰው በአምስት ነገሮች እንቅልፍ እንቢ ሊለው ይችላል ። የመጀመሪያው ሕመም ሲሰማው ፣ ሁለተኛው ሲርበው ፣ ሦስተኛ ነገር ሲገባው ፣ አራተኛ በጣም ሲደክመው ፣ አምስተኛ በጣም ደስ ሲለው ነው ። ደስታ እንቅልፌን አራቀው ። ልቤ እንደ እንቦሳ ይዘላል ። አፌ በዚያ ውድቅት ሌሊት እልል ሊል መዝጊያውን ይታገላል ። ክርስቲያን የጎረቤቱን ሰላምና ምቾት የሚጠብቅ በመሆኑ ስሜቴን ታገሥ እለዋለሁ ። ከእግዚአብሔር ሰዎች ጋር መዋል ብቻውን ያጽናናል ። እንደ እኔ የሚያምን ሰው መኖሩን ማየት በራሱ አቅም ይሰጣል ። የእግዚአብሔር ሰዎች ጋር የምንለዋወጠው ምስክርነት ለእምነታችን ጽናትን ይሰጣል ። እግዚአብሔር ያደረገልንን እንናገር ። የደከመው መንፈሳችን ይበረታታል ። የደከሙ ሰዎችንም ያነቃቃል ። ምስክርነቶች እምነትን ይጨምራሉ ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ተከራይቶት የነበረው ቤት ስደርስ በሩ እንደ ትላንቱ ክፍት ነበረ ። በውስጤም የአገልጋይ ቤት የእግዚአብሔር ደጅ ነውና አይዘጋም አልኩኝ ። ሐዋርያው ጳውሎስ ከሰው ገንዘብ መቀበል እየተሰቀቀ ድንኳን ሲሰፋ ፣ ከሰው ቤት መጠጋትን እንቢ እያለ ቤት ሲከራይ መኖሩ ገረመኝ ። እሰው ቤት የሄደና መሬት ላይ የወደቀ ሥጋ ጉድፍ ሳይዝ አይነሣም ይባላል ። ሁሉም ሰው የራሱ አመልና ገመና አለው ። የሚችለውም ቤቱ ነው ። ደጃፉን ለወጉ ጸፋሁና “ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን” ብዬ ስገባ “የክርስቶስ ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ መለሰልኝ ። እውነተኛ ምርቃት ነውና ሲያረሰርሰኝ ይሰማኝ ነበር ። ቅዱስ ጴጥሮስ ትላንት በተነጠፈለት ምንጣፍ መሬት ላይ ተኝቶ ነበር ። በልጅ ልጅ ተከብቦ ፣ በቤቱ ተከብሮ ፣ በሰፈሩ አረጋዊ ተብሎ ሰዋዊ ክብር ከሚያገኝበት ከገሊላ ኑሮው ተላቅቆ ለክርስቶስ በሰማዕትነት ጽዋ ለመመስከር ወደ ሮም መምጣቱ አስገረመኝ ። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ስለ ጴጥሮስና ስለ ጳውሎስ አገልግሎት ብቻ የተጻፈ ይመስላል ። ብዙ ከተጻፈላቸው ብዙ መከራ ይጠብቃቸዋል ። ወንጌላዊ ሉቃስ አስተባብሮ ከጻፈላቸው እነርሱም ተባብረው ለክርስቶስ ሰማዕት ለመሆን ተሰባሰቡ ። ያገናኛቸው ቀጠሮ “ሰማዕትነት አያምልጥህ” የሚለው መንፈሳዊ ጥሪ ነው ።
ሐዋርያው ጴጥሮስም ከመኝታው ብድግ ብሎ ተነሣ ። የመጨረሻው ሰዓት እየተቃረበ ነውና መልእክቱን በተተኪዎቹ ውስጥ ለመጻፍ እየተጋ ነው ። ጸሎት ከደረሰ በኋላ ሁላችንም ስፍራችንን ይዘን ተቀመጥን ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- “ዛሬ የምነግራችሁ በፊልጶስ ቂሣርያ ስለተፈጸመው ቅዱስ ማቴዎስ በምዕራፍ 16 ላይ ስለመዘገበው ክስተት ነው ። ፊልጶስ ቂሣርያ የተባለችው በታላቁ ሄሮድስ ልጅ በፊልጶስ ተሠርታ ስለ ነበርና በባሕሩ ዳርቻ ካለችው ቂሣርያ ለመለየት ነው ። በሰሜን እስራኤል ከአርሞንየም ተራራ በስተደቡብ የምትገኝ የዮርዳኖስ ወንዝ መፍለቂያ ናት ። በዚህች ከተማ ታላቅ በረከትንና ጸጋን አገኘሁ ። ይህች ከተማ የዮርዳኖስ ወንዝ መፍለቂያ ስትሆን ጌታን ያገኘሁበትን የመጀመሪያውን ቀን ታስታውሰኛለች ። ከጌታዬ ጋር የተገናኘነው ዮሐንስ በሚያጠምቅበት በጌልጌላ አቅራቢያ ባለው በዮርዳኖስ ፍጻሜ አካባቢ ነው ። ዛሬ ደግሞ ወደ መነሻው መጣሁ ። በመጀመሪያው ቀንና በዮርዳኖስ ወንዝ ፍጻሜ ስሜ ተለወጠ ። ስምዖን ሳለሁ ኬፋ ተባልሁ ፤ በዮርዳኖስ መነሻም በፊልጶስ ቂሣርያ ጴጥሮስ ተብዬ እንደገና ስሜ ተለወጠልኝ ። ኬፋም በአራማይክ ፣ ጴጥሮስም በግሪክ ዓለት ማለት ነው ። ያ ዓለትም የማይፈረፈርና ጽኑ የሆነ ዓለት ነው ። ልቤን ፣ አቋሜን ፣ ኑሮዬን ሳስበው ይህ ስም አይገባኝም ። እኔ የሆንኩትን ሳይ ጌታዬ ግን የምሆነውን ያሳየኝ ነበር ። በዮርዳኖስ ፍጻሜ ጌታዬ መሰከረልኝ ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ መነሻ ደግሞ እኔ መሰከርሁለት ። ከፍጻሜው ወደ ጅማሬ የሚሄደው የአምላክ አሠራር ይገርመኛል ። እርሱ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ ። ሰማይ ጉልላት ድምድማት በመሆኑ ፍጻሜ ነው ። ሥራውን የጀመረው ከፍጻሜው ነው ። እስራኤልን ከግብጽ ምድር ሲያወጣ ይነግራቸው የነበረው ማርና ወተት ስለምታፈስሰው አገር ነው ። በግብጽ ጭንቅ ውስጥ ሳሉ እርሱ ግን ከነዓን ቆሞ ጠራቸው ። ፍጻሜው ላይ ቆሞ ይጠራናልና ማንም ሊያስቆመን አይችልም ። የእግዚአብሔርን ጥሪ በሚመለከት መፍራት ያለብን ጠላትን ሳይሆን እልኸኛውን ልባችንን ነው ። እግዚአብሔር አሰበ ማለት ፈጸመ ማለት ነው ። በእግዚአብሔር ጅማሬና ፍጻሜ መካከል ምንም ልዩነት የለም ። ሲሻ ከመጀመሪያው ሲሻም ከመጨረሻው ይጀምራል ። በጥሪዬ ቀን ወንድሜ እንድርያስ ወደ ጌታ አቀረበኝ ፣ ዛሬ ግን ከሁሉም ቀድሜ አምላክም ሰውም መሆኑን መሰከርሁ ። ሰው እንደ ትላንቱ አይሆንም ። ሕይወት ጉዞ ናትና ለውጥ ይኖረዋል ። ከእኛም የተሻለ ይሆናል ። መኖር ያልጨረሰ ሰው መለወጡ አይቀርም ።
ጌታችን በፊልጶስ ቂሣርያ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል ብሎ ጠየቀን ። ሰዎች የሚሉትን ቢያውቀውም መስማት ግን ፈለገ ። ይሉኛልን ፈርተን ወደ ኋላ እንዳንል ፣ ሰዎች ግምታቸውን እንደ እውነት ሲናገሩ ፈገግ ብለን እንድናልፍ ይህን ጥያቄ አነሣ ። ሰዎች እርሱን የሚሉት ብዙ ነበር ። ሎቱ ስብሐት አብዷል ፣ በብዔል ዜቡል ይመራል ፣ ሕግ ያፈርሳል ፣ አገር ያስወርራል ይሉት ነበር ። እኛ ግን ይህን አላልነውም ። ክፉ ነገር ለወዳጅ አይነገርም ። እዚያው መልስ ሰጥተን መምጣት እንጂ ክፉ ወሬ ይዘን ወደ ወዳጃችን መምጣት እንቅልፍ መንሣት ነው ። ለጌታችን ጥያቄ የሰጠነው መልስ መልካም መልካሙን ነበረ ። እርሱ ግን ከመልካም በላይ ነበር ። “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ፥ ሌሎችም ኤልያስ ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” አልነው ። መጥምቁ ዮሐንስ ነው የሚሉት መናኔ ንብረት ፣ የከተማ ባሕታዊ መሆኑን አይተው ነው ። እርሱ ድንግልናዊ ሕይወትን አርአያ የሆነበት ፣ በተጠመቀ ቀንም ወደ ገዳም ወደ ደናግል መኖሪያ የሄደ ነው ። የደናግል መኖሪያ በከተማ ከሆነ ፣ የዚያም ምክንያት እነርሱን እያዩ ሰዎች ዓለምን እንዲንቁ ነው ። እንደ ዮሐንስ መጥምቅም በምድረ በዳ መኖር ይቻላል ። የድንግልናዊ ኑሮ ዓላማም ሕዝብን ወደ ክርስቶስ ለመመለስ ነው ። ጌታችን ዓለምን የናቀ ፣ ኑሮው ለደናግል አብነት የሆነ ነውና ዮሐንስ መጥምቅ ነው ይሉት ነበር ። ኤልያስም ኤርምያስም ደናግላን ናቸውና ነቢያትም ዓለምን የናቁ ናቸውና ግምታቸው ኑሮውን በማየት ነበር ። ነገር ግን እርሱ የነቢያት አምላክ እንጂ ከነቢያት አንዱ አልነበረም ።
ጌታችን ሰዎች የሚሉትን መስማት የመጨረሻ ግቡ አልነበረም ። እርሱ መስማት የፈለገው እኛ የምናምነውን ነው ። አምኖ መመስከርና መስክሮ ማመን ይለያያል ። እኔም ለበጎ ነገር መዘግየት ብሎም ግራና ቀኝ መተያየት አይገባምና ፈጥኜ መልስ ሰጠሁ ። የአእምሮ ውጤቴ አልነበረም ። ጌታ እንደመሰከረልኝ ተገልጦልኝ ነው ። አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ አልኩት ። ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን በአጭር ቃል ገልጥሁ ። ይህን ምስክርነት ባለማጽናት በኋለኛው ዘመን ቤተ ክርስቲያን ትከፈላለች ። አርዮስ አምላክነቱን ዘንግቶ ፍጡር በመለኮቱ ይለዋል ። በዚህም በኒቅያ ታላቅ ጉባዔ ይደረጋል ። አውጣኪም ፍጹም ሰውነቱን ረስቶ አምላክ ብቻ ነው ይለዋል ። ከሥጋዌ በኋላ ያለውን በአንድ አካል መለኮትና ሰውነት ተዋሕደው መኖራቸውን ይክዳል ። ንስጥሮስም ሁለት አካልና ሁለት ባሕርይን ሲያስተምር የእርሱ ተከታዮች ደግሞ አንድ አካል ሁለት ባሕርይ ብለው ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት ይከፍሏታል ።
ይህን ምስክርነት እንደሰጠሁ ጌታችን አመሰገነኝ ። “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።” አለኝ ። ምስክርነት እርሱን ደስ ያሰኘዋል ። ብፁዕ የተባልሁት አብ አምኖ ስለገለጠልኝ እንጂ ተመራምሬ ስለደረስሁበት አይደለም ። የተገለጠልኝን መግለጤም ብፅዕናን አስገኘልኝ ። ቤተ ክርስቲያኔን እመሠርታለሁ በማለትም ቤተ ክርስቲያን የእኔ ሳይሆን የራሱ መሆኗን መሰከረ ። በቃለ አሚንም ቤተ ክርስቲያን መመሥረቷን አወጀ ። እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን አንድ አካል አንድ ባሕርይ ብላ በክርስቶስ የምታምን ናት ። ሥልጣንንም ዛሬ ለእኔ ነገ ለተተኪዎች ሰጠ ። የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎችን ማለትም የጸጋ ስጦታዎችን ሲሰጠኝ ፣ የገሀነም ደጆችን ኃጢአትና ዓመፃ ቤተ ክርስቲያንን እንደማይችሏት አበሰረ ። የማሰርና የመፍታት ሥልጣንን ለእኔና ለቀጣይ የወንጌል አገልጋዮች ሰጠ ። ምድራዊውን ወንጌላዊ መግፋት ሰማያዊውን ክርስቶስ መግፋት ነው ። በረከተ ሐዋርያት በላያችሁ ላይ ይደር” ብሎ ዐረፍ አለ ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
እሑድ ግንቦት 22 ቀን 2013 ዓ.ም.