የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 11/

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ዙሪያውን ሁሉ አማተረ ። ወደ ቀጣዩ ትረካ ከማለፉ በፊት፡- “ምነው ፌበን አልመጣችም ወይ ?” ብሎ ጠየቀ ። እውነተኛ መምህራን በመጡት ልጆቻቸው ደስ ሲላቸው በቀሩት ደግሞ ልባቸው ይተክዛል ። አባቶች ልጆቻቸውን በደስታ ፣ በኀዘን ፣ በምሽት ጊዜ ማየት ይፈልጋሉ ። እውነተኛ መምህራንም ልጆቻቸውን በጸሎት ፣ በስብከትና በኅብረት ጊዜ ለማየት ይናፍቃሉ ። ተማሪዎች ከሌሉ መምህርነት የባከነ ጸጋ ይሆናል ፤ መምህራንም ከሌሉ ተማሪነት እርካታ የሌለው ጥማት ብቻ ይሆናል ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ከእርጅና የተነሣ ዓይኑ ቢደክም ደግሞም የጳውሎስ ቤት ስርቻ መሳይ ብትሆን አላያት ሁኖ አንድም በአገልግሎቱ ተመሥጦ ልብ ባይላት እንጂ እበሩ ሥር ኩርምት ብላ ትንሽዬ ሕፃን መስላ ቁጭ ብላ ነበር ። ሁሉም ቀጣዩን ትረካ በመናፈቅ “አለች” አሉ ። ወደ ቀጣዩ በቶሎ ሂድ ማለታቸው ነው ። ሐዋርያው ግን እንዲህ አለ፡- “ምግብ ቤት የከፈቱ ሰዎች ሬሳ ጥለው የሚጠብቁ ናቸው ። የበሰለ እህል ሬሳ ነው ። በሰው ሆድ ውስጥ ካተቀበረ የሚጣል ነው ። እንዲሁም አገልጋዮች መንፈሳዊውን ማዕድ አዘጋጅተው ሲጠብቁ ትልቅ ሕመም እንዳለው አውቃለሁ ። ይህን እውቀት ያገኘሁት በአገልግሎት ልምዴ እንጂ በመገለጥ አይደለም ። አገልጋዮች ዐውደ ምሕረቱ ላይ ቁጭ ብለው ፊትና እግር ይጠብቃሉ ። አንድ የእግር ኮቴ ሲሰሙ ማነው ? ብለው ፊቱን ለማየት ይናፍቃሉ ። ሲጠብቁት የነበረው ከመጣ በኋላ አያርፉም ፣ ያልመጣው ጋ ልባቸው ይቀራል ። እናት ዘጠኝ ልጆችዋ ገብተው አንዱን ያመሸ ልጅ እንቅልፍ አጥታ እንደምትጠብቅ ፣ የዘጠኙ ብዛት የአንዱን ልጅ መቅረት እንደማያስረሳት እንዲሁም አገልጋዮች ከሥላሴ ገበታ በሚቀሩ ልጆቻቸው በጣም ያዝናሉ ። የአገልጋይን ምጥ አገልጋይ የሆነ ብቻ ያውቀዋል ። ሐዋርያው ጳውሎስ በገላትያ ሰዎች ምን ያህል ጭንቀት ውስጥ ገብቶ እንደ ነበር አውቃለሁ ። ምእመናን ጭንቀታቸውን ነግረውን ሲሄዱ የማናዝን በድን አይደለንም ። ስለ እነርሱ እናስባለን ፣ በእንባ እንጸልያለን ፣ ስእለት እንሳላለን ። ደስታቸውን ያካፍሉናል ፣ ስእለታችንን እንከፍላለን ብለን ስንጠብቅ ግን ጨርሶ ይረሱናል ። የክፉ ቀን ሚስት ያን ክፉ ቀን መስላ ትታያለች እንዲሉ ይጠሉናል ። እጮኛ ሲከዳቸው ይነግሩናል ፣ ሲያገቡ አይነግሩንም ። ሲወልዱ ዝም ይሉናል ፣ ልጃቸው ሲታመም ይነግሩናል ። እንዲህም ሆኖ ላለማዘን ከራሳችን ጋር እንታገላለን ። የዓለም አማካሪዎች በውድ ገንዘብ ያማክሩአቸዋል ፣ ራሳችሁ ተወጡት ብለው ይለቁአቸዋል ። እኛ ግን በነጻ አማክረናቸው ፣ በጸሎት ስለ እነርሱ እናምጣለን ። ፈላስፎች አስከፍለው ክህደትን ያስተምሩአቸዋል ፣ እኛ ግን በነጻ እምነትን ብናስተምራቸውም ክብር አይሰጡንም ። የከሀዲዎች ክህደት ሳይሆን የአማኞች በልቶ ካጂነት የሚያሳዝነን ሆነናል ። የእግዚአብሔር ሥራ በገንዘብ እጥረት ሲቆም አማኞቻችን ግን ውድ ወርቅ ለመግዛት ፣ ከጎረቤቶቻቸው ጋር የሀብት ውድድር ውስጥ ገብተው በሬ ለመጣል ሲሮጡ እናያለን ። ይህን ሁሉ ካልቻላችሁ አገልጋይ መሆን ያቅታችኋል ። የአገልጋዮች ኀዘን ግን ምእመናንን ያስራል ። በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል የተባለው እውነተኛ ኀዘን ዋጋ እንዳለው የሚያሳይ ነው ። ይህማ መናፍቃንን ለማውገዝ ነው ትሉ ይሆናል ። አሥራት በኵራቱን የማያወጣና የእግዚአብሔርን አገልጋይ የማይረዳ እርሱ መናፍቅ አይደለም ወይ ?”

ሐዋርያው ጴጥሮስ እግረ መንገዱን የአገልጋዮችን ጥማት ፣ ኀዘንና የምእመናንን ንፍገት ከተናገረ በኋላ የተገሠጸበትን ቀን አስታወሰ ። ተግሣጽ የማይረሳ ትምህርት መገኛ ነው ። የሚገሥጽ ግን ወዳጅ የሆነ መምህር ነው ። መድኃኒት መራራ ሁኖ እንዲፈውስ ተግሣጽም እንዲሁ ነው ። 

“ጌታዬ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከመሰከርሁ በኋላ ለማንም ይህን እንዳንናገር አዘዘን ። የዚህም ምክንያቱ ብዙ ነው ። ምስክርነት በጊዜው ካልሆነ መከራ ያመጣል ። እውቀቱ ሳይበስል ብንመሰክር ተከራካሪ የመጣ እንደሆነ መመለስ ያቅተናል ። ምስክርነት የሚያስከፍለው ዋጋ አለና ሳንጸና መከራው ቢመጣ መካድ ይከተላል ። በዚህ ምክንያት ጌታ ለማንም እንዳንናገር እስከ ጊዜው ያዝዘን ነበር ። ታዲያ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ መሆኑን በመሰከርሁበት ቀን ምስጋና ተቀብዬ ሳለሁ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሊሆን መምጣቱን ዘነጋሁ ። ጌታችንም ስለ መከራውና ሞቱ ሲናገር መስማትም አልፈለግሁም ። በልጅነቴ እናቴ እኔ ብሞትስ ? እያለች ስታወራ ልቤ ይጨነቅ ነበር ። ሳላስበውም አለቅስ ነበር ። አሁንም ገና ያልጠገብሁት አዲሱ ኑሮ ላይ ጌታ እሞታለሁ ሲለኝ ያ የሕፃንነት ስቃዬ ተመልሶ መጣብኝ ። ክርስቶስ ለመኖርና ለመንገሥ የመጣ መስሎኝ ተረጋግቼ ተቀምጫለሁ ። እርሱ ግን ለዓለሙ ሁሉ ሊሞት መምጣቱን ሲናገር ተቆጣሁት ። ዳግም እሞታለሁ የሚል አሳብ እንዳያነሣ ተማጸንሁት ። የእኔ ስስት አብ ለልጁ ካለው ፍቅር አይበልጥም ። ውረድ ተወለድ ፣ ሙት አድን ተብሎ በአባቱ ስምረት ፣ በፈቃደ መንፈስ ቅዱስ በራሱም ውዴታ መምጣቱን አላወቅሁም ። እኔም እንደ ልጅ እየተከታተልሁ ፣ ወደ ራሴም እየወሰድሁ ፣ በወዳጅነት መንፈስ የመስቀል ጉዞውን ላቋርጠው ፈለግሁ ፣ ባንተ ይህ አይደርስብህም እያልሁ ደግነቱን እያዘከርሁ ላባባው ፣ መላ እንዲፈልግ ላግባባው ሞከርሁ ። ጌታም ስከታተለው ፣ ወደ ራሴም ወስጄ ሳማክረው ፣ ላባባው በእንባ ስማጸነው ታገሠኝ ። እኔም ከዚያ አልፌ መገሠጽ ጀመርሁ ። እርሱ ባይሞት ዓለም እንደማይድን እኔ አልገባኝም ። ንጉሣዊነቱን እንጂ ሟችነቱን መቀበል አልፈለግሁም ። ከተአምራት ወደ ተአምራት መሸጋገር ብቻ እፈልግ ነበር ። አበርክቶ ማብላቱን ብቻ እወደዋለሁ ፣ ነፍሱን አበርክቶ ለዓለም ሊሰጥ ሲል በግልጽ መቃወም ጀመርሁ ። ሳላስበው የዓለምን መዳንና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ተቃወምሁ ። ክርስቶስ ባይሞትና ባይነሣ ኖሮ ዛሬ ሐዋርያ ነገ ሰማዕት ለመሆን አልዘጋጅም ነበር ። ለካ ከእኔ ይልቅ የክርስቶስ የመስቀል ሞት ሰይጣንን ያሳስበዋል ። ሞትን በሞቱ ፣ እሾህን በእሾህ ሊነቅል መምጣቱን አውቆታል ። በለቢሰ ሥጋ ውስጥ ያለው የክርስቶስ ነገር ግራ አጋብቶታል ። አንዴ ይሙት ብሎ ሄሮድስን በሕፃንነቱ አስነሣበት ። በገዳመ ቆሮንቶስ ፈተናውም ራስን ወርውር አለው ። አይሁድንም አነሣሥቶ ብዙ ጊዜ ከገደል ሊጥለው ፣ በድንጋይ ሊያስወግረው ፈለገ ። አሁን ግን የክርስቶስ ሞት የጠላት ሞት መሆኑን ሰይጣን ያወቀ ይመስላል ። በዚህ ምክንያት አለማወቄ የሰይጣን መጠቀሚያ አደረገኝ ። አለማወቅ የሰይጣን መሥሪያ ቤት ነው ።

ታላቅ ራእይና ተጋድሎ ያላቸውን ሰዎች ጠላት በወዳጅ በኩል ይታገላቸዋል ። ጠላት ሆኖ ቢመጣ እነዚህ ሰዎች የበለጠ ይጠነክራሉ ። ክርስቲያንና ምስማር በመቱት ቍጥር ይጠብቃልና ። ሰይጣን ግን በወዳጅነት በኩል ይመጣባቸዋል ። ዝናህ ለምን ይቀበራል ? ሁሉ ይስማውና እኛም ባንተ ስማችን ይጠራል ። በአገልግሎትህም የጋራ ተጠቃሚነትን እናገኛለን ይላቸዋል ። በእግዚአብሔር ጊዜ መገለጥ አለብኝ ብለው ይህን ፈተና ድል ሲነሡ ቀጣዩ ግላዊ ምክሮችን በማቅረብ ፣ በለሆሳስና ወደ ደረት ቀረብ በማድረግ ሁሉም ራሱን እየለወጠ ነው ፣ ለምን ደህና ደረጃ ላይ አትደርስም ። ተቸግሮ ከማዘን አግኝቶ ማመስገን ይሻላል ፣ ሁሉም በዚህ መንገድ ሂዶ ነው ከፍ ያለ ማማ ላይ የወጣው ይላል ። እነዚህ ባለራእዮች ይህንንም ፈተና ሲያሸንፉና ለመከራ መስቀሉ ራሳቸውን ሲያስጨክኑ የሚያባባ ድምፅ ይሰማል ። ላንተ ይህ አይገባህም የሚል ውዳሴ ከንቱ ይመጣል ። እናትን ፣ ሚስትን ፣ ልጆችንና የቅርብ ወዳጆችን በማስተባበር ለእኛም እዘንልን ። ያንተ መከራ መከራችን ነው በማለት ማባባት ይፈልጋል ። ይህንንም ሲያልፍ መገሠጽና መቃወም ይጀምራሉ ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ዋና ተዋናዩ ሰይጣን ነው ። ጠቡ ያለው ከፈረሱ ሳይሆን ከጋላቢው ነው ። ጠላትን ማወቅ ጉልበት ከመጨረስ ያድናል ። 

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም በጠላት ፈተና ውስጥ እንደ ወደቅሁ አወቀ ። ለትንሣኤው ምስክርነት ተጠርቼ ሞቱን እየተቃወምሁ መሆኔን አየና ለእኔ አዝኖ ጠላትን ግን ገሠጸው ። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል ሲል የሆነ ነገር ከላዬ ላይ ብድግ ብሎ ሲሄድ ተሰማኝ ። ወደ ደቀ መዛሙርቱም ዘወር ብሎ፡- እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ ። ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል ፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል ። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል ? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል ? አለ ። 

ክርስቶስን መቅደም ውስጥ ገብቼ ነበርና ተከተለኝ አለኝ ። ከእግዚአብሔር በላይ አዋቂና አዛኝ መሆን አሳፋሪ ነገር ነው ። ለማመን መካድ ግድ ነውና ክርስቶስን ለማመን ራስን መካድ አስፈላጊ ነው ። ክርስቶስ ጋ መከራው ከደረሰ እኔንም አያጣኝም ብዬ ሰግቼ ነበርና መስቀሉን ተሸከም አለኝ ። መስቀል የመጣ ቀን መስቀል መሸከም ለመጣል ይዳርጋል ። መስቀሉን ተሸክሞ መኖር ፣ በመስቀል የታነጸ ሕሊና መያዝ ግን ያስፈልጋል ። ተአምራት ሊሆንም ላይሆንም ይችላል ። መከራ ግን አይቀርም ። የማይቀረውን ማሰብ ያሻል ። ነፍሱን ከሥጋ መከራ ሊያድን የሚወድ ከዘላለም መከራ ውስጥ ይጥላታል ፣ ነፍሱን በመከራ ውስጥ የሚያጠፋ ግን በሰማይ ያገኛታል ። ሰው ዓለሙ ሁሉ ያንተ ነው ተብሎ ቀጥሎ ግን ትሞታለህ ቢባል ምንም አይጠቅመውም ። በሬሳ አጠገብ እንደ ተቀመጠ መልካም መዓዛ እንዳለው ምግብ ነው ። እኔም ከዚያ ቀን ጀምሮ መስቀሉን በሕሊናዬ ተሸከምሁ ። ከጥቂት ቀናት በኋላም ምስክርነቴን በሰማዕትነት ለመፈጸም ሮም ተገኝቻለሁ ። 

ልጆቼ!! ባለ ራእዮችን አታደናቅፉ ። በጠላትነት ስድብ ብቻ ሳይሆን በወዳጅነት ማባባትም ከእግዚአብሔር ዓላማ አታስቀሩአቸው ። ለእግዚአብሔር ካልሆኑ ለእናንተም አይሆኑም ። ሚስቶችም ባለ ራእይ ባሎቻችሁን እቤት ውስጥ በቅናት አስራችሁ አታስቀምጡ ። እግዚአብሔር ይቀጣችኋል ። ወላጆችም ባለ ራእይ ልጆቻችሁን እንደ ልጅ ሳትዘል ፣ ሳትጨፍር ፣ እንደ ሰው ልብላ ልዝረፍ ሳትል እያላችሁ ከትልቅ ዓላማ ለማውረድ ጥረት አታድርጉ ። አማሌቅ ዝክሩ ከምድር ላይ የተደመሰሰው ባለ ዓላማ ሠራዊትን አላሳልፍም በማለቱ ነው ። ባለ ራእዮችን የሚያደናቅፉ ለዘላለም ይደመሰሳሉ ። የእናንተ የልማድ ነዋሪ መሆን ሳይበቃችሁ የተጋውን ባለ ራእይ አታስንፉ ። እግዚአብሔር ከዚህ ይጠብቀን !” 

ሁላችንም በቅዱስ ፍርሃት ውስጥ ሆነን “አሜን” አልን ። 

ይቀጥላል 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሐሙስ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ