የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 12/ 

 

 በታቦር ተራራ ላይ ቆሞ ወደ ታች ቁልቁል ሲታይ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ በተዘረጋው ረጅም መሬት ብዙ ክስተቶች እንደተፈጸሙና ወደ ፊትም እንደሚፈጸሙ ማሰብ ይቻላል ። ደብረ ታቦር የአርማጌዶን ዘመቻ ሲናገር በኢየሩሳሌም ያለው ደብረ ዘይት ደግሞ ክርስቶስ የሚመጣበት ተራራ ሁኖ ይታያል ። ጌታችን በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ፣ ክብረ መንግሥቱን እንደ ገለጠ ሊናገር ሲል ይህን እያስታወስሁ ነበር ። ቅዱስ ጴጥሮስ አሁን ዐረፍ ብሎ ለመናገር ጉባዔውን አስፈቀደ ። ሁሉም ከመቀመጫው ተነሥቶ ዐረፍ ይል ዘንድ ለመነው ። የበረታ መንፈስ የደከመ ሥጋን ስለሚሸከም እንጂ በዘጠና ዓመት ዕድሜ ውስጥ ያለውን ጴጥሮስን እንዲህ ባለ ብርታት አናገኘውም ነበር ። ክርስቶስ ባይጠራው ኖሮ “አሟሟቴን አሳምርልኝ” ብሎ የሚጸልይ አረጋዊ ነበር ። አሁን ግን በሕይወቱ ብቻ ሳይሆን በሞቱም ጌታን ሊያከብረው ወደ ሮም መጣ ። ጳውሎስም በሞቱ ሊመስለው ተስሎ ነበር ። ምቾትን የሚለምን ክርስቲያን ባለበት ዓለም በሞትህ እንድመስልህ እርዳኝ ብሎ መለመን መታደል ነው ። የክርስቶስ ሞት በዋናነት ቤዛነት ቢሆንም ለእውነት መስክሮ በእውነት ተከስሶ በእውነት የሞተም ነው ። ስለ ክርስቶስ በመሞት ከሞቱ ጋር መተባበር ይቻላል ። ኃጢአትን እንቢ ብሎ ሥጋዊ መሻትን መግደልም መሞት ነውና ሰማዕትነት ይባላል ። ሐዋርያው ጴጥሮስ በሕይወቱ ከማይረሳቸው ቀኖች አንዱ የደብረ ታቦር ክስተት እንደሆነ በመልእክቱ ጽፏል ። “ከገናናው ክብር፡- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና ፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን” ብሏል ። 2ጴጥ. 1፡16-18 ። 

ወንጌላውያን ረጅም ተራራ ያሉትን ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ ቅዱሱ ተራራ ይለዋል ። የእግዚአብሔር ክብር የተገለጠበት ሰው ብቻ ሳይሆን ተራራም ቅዱስ ይባላል ። ቅዱስ ማለት የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ፣ ለእግዚአብሔር ከተሰየመ በኋላ ለሌላ መሆን የማይችል ማለት ነው ። ደብረ ታቦር ረጅም ብቻ ሳይሆን ሰፊ ተራራ ነው ። ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ቀን የማይረሳውና ልዩ ቀኑ እንደሆነ ያሰበው በምክንያት ነው ። ማንም ቢሆን የተመረቀበትን ቀን አይረሳውም ። ሐዋርያው ጴጥሮስም በፊልጶስ ቂሣርያ ለሰጠው የእምነት ምስክርነት ጌታችን ሽልማት የሰጠው በደብረ ታቦር ላይ ነው ። ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን በመመስከሩ ምስጋና ፣ ሥልጣንና ሽልማት አገኘ ። ጴጥሮስ ለመልካም ነገር ቢፈጥን ይህን ሁሉ አገኘ ። ሳያይ ለመሰከረ ሽልማቱ ያመነውን ማየት ነው ። ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ምስክርነት በሰጠ በስምንተኛው ቀን ወይም በሳምንቱ ሽልማቱን በደብረ ታቦር ሊቀበል ነው ። ጌታ በስምንተኛው ቀን ዋጋ መስጠቱ ያገለገሉትን የማይረሳ አምላክ መሆኑንና በስምንተኛው ሺህም መጥቶ ላገለገሉት ሁሉ ክብር እንደሚሰጥ ማሳያ ነው ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ድምፁን ሞረደና ንግግሩን ቀጠለ፡- “በፊልጶስ ቂሣርያ ክርስቶስ የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ከመሰከርሁ በኋላ በሳምንቱ ወደ ደብረ ታቦር እኔንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞን ወጣ ። እኔን ይዞ መውጣቱ ለምስክርነቴ ሽልማት ሊሰጥ ነው ። ዮሐንስን ይዞ መውጣቱ በዕድሜ የሚቆይና ይህን ክፍለ ዘመን የሚፈጽም ፣ ከሐዋርያትም የመጨረሻው ሁኖ በዕድሜ የሚቆይ ስለሆነ ነው ። ለዘመኑ ሁሉ አቅም እንዲሆነው ይዞት ወጣ ። ያዕቆብን ይዞ መውጣቱ ከሐዋርያት መጀመሪያ የሚሞት ስለሆነ ነው ። የኃይል መገለጥን በትንሣኤው ቢያይም የክብር መገለጥን በደብረ ታቦር እንዲያይ ያዕቆብን ይዞት ወጣ ። እስጢፋኖስ ዘመኑ አጭር ነውና ብዙ ክብር ተገለጠለት ፣ ያዕቆብም አጭር ዘመን አለውና ይህን ክብር አሳየው ። እኛን ይዞ በመውጣቱ ከተራራ ግርጌ የነበሩትን ደቀ መዛሙርት ትጋትን እያስተማራቸው ነው ። ክርስቶስን እስከዚህ ቀን ድረስ በተአምራት ብናውቀውም በመለኮታዊ ክብሩ ግን አናውቀውም ነበር ። ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ ። ፀሐይን ፊት ለፊት ማየት እንደማይቻል ልናየው አልተቻለንም ። በሥጋ ውስጥ የተሰወረው መለኮቱን በደንብ አስተዋልን ። እየቻለ ትሑት ፣ ባለ ግርማ ሳለ እንደ ምስኪን ሆኖ እንደኖረ ተረዳን ። ይህንንም ለናቁት አላሳየም ። ላመኑት ግን አሳየ ። ትንሣኤውንም ለገደሉት ሳይሆን በር ዘግተው ፣ መቃብር ወርደው ለሚናፍቁት እንዳሳየ አሠራሩ አይለወጥም ።

 እርሱ ፀሐይ ነው ፣ አይናወጥም ። እርሱ ፀሐይ ነው ፣ ጨለማን ይገፍፋል ። እርሱ ፀሐይ ነውና የብቸኝነትን ብርድ ያርቃል ፣ ነፍስንም ያሞቃል ። እርሱ ፍጡር ፀሐይ ሳይሆን ፈጣሪ የሆነ ፀሐይ ነው ። ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ ። በስስ ልብስ ላይ ውሳጣዊ ብርሃን ጎልቶ እንደሚወጣ በሥጋው ላይ መለኮቱ አበራ ። ብናምነውም በእንዲህ ያለ ክብር እርሱን መገመት እንቸገር ነበር ። ሥጋ ብቻ ነው እንዳንል መለኮትነቱን ገለጠ ፤ መለኮት ብቻ ነው እንዳንል በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ከፊታችን ቆሞ ይታያል ። አምላክና ሰው ነው ብለን ፈረቃ እንዳንሰጠው አምላክም ሰውም ሁኖ በፊታችን ይታያል ። ይህን ክብር ሳላይ የመሰከርሁት አብ ገልጦልኝ ነው ። አንድ የገሊላን ገበሬ አብ እንዲህ ማክበሩ ድንቅ ነው ። አሁንም ክብረ መንግሥቱን ግርማ መለኮቱን ወልድ ገለጠልኝ ። መንፈስ ቅዱስም ፍርሃት በጥብዓት ለወጠልኝ ። ሙሴና ኤልያስም በዚያ ተራራ ላይ ተገኝተው ነበር ። የማናውቀውን መለኮቱን አሁን ስንረዳው የማናውቃቸውን ሙሴና ኤልያስንም አወቅናቸው ። ሙሴ ሕግን ፣ ኤልያስ ነቢያትን ይወክላሉ ። በሕግና በነቢያት የተነገረለት ክርስቶስ መሆኑን ሊገልጡ መጡ ። ሙሴ የሞቱትን ፣ ኤልያስ ሕያዋንን ይወክላል ። ክርስቶስም የሙታንና የሕያዋን አምላክ መሆኑን ይገልጣሉ ። ሙሴ ባለመጽሐፍ ነው ፣ ኤልያስ የቃል ነቢይ ነው ። በቃልም በመጽሐፍም የተነገረለት እርሱ መሆኑን ሊመሰክሩ መጡ ። ሙሴ መስፍን ነው ፣ ኤልያስ ጭቁን ነው ። ክርስቶስም እንደ ንጉሥ ከሰብአ ሰገል የተገበረለት ፣ እንደ ጭቁን ሄሮድስ ያሳደደው ነው ። ሙሴ ምድረ ከነዓንን አላየም ፣ ኤልያስ ቀርሜሎስን እንጂ ደብረ ታቦርን አያውቅም ። ክርስቶስ ያላየነውን የሚያሳይ ፣ የማናውቀውን የሚያሳውቅ የሕይወት መሪ ፣ የእውቀት ገላጭ መሆኑን ሊመሰክሩ መጡ ። ሙሴ መስክሮለታል ፣ ኤልያስ መንኖለታልና የድካማቸውን ዋጋ ሊቀበሉ መጡ ። ሙሴ የእግዚአብሔርን ፊት ያያል ተብሏል ፣ ኤልያስም የምድር ነገሥታትን ንቋል ። ሙሴም ሰው የሆነውን አምላክ አይቶ የሺህ ዘመን ልመናው እንዲፈጸም ፣ ኤልያስም ነገሥታትን የናቀበትን የነገሥታት ንጉሥ አይቶ እንዲደሰት በደብረ ታቦር ተገኙ ። ሙሴ ያገባ ፣ ኤልያስ ድንግል ነው ። ሰው በተሰጠውና በመረጠው ሕይወት እግዚአብሔርን ቢያከብር ዋጋ እንዳለው ለማሳየት ሙሴና ኤልያስ ተጠሩ ። በዚህም ያገባሁት እኔ ያላገቡት ዮሐንስና ያዕቆብ ትምህርት አገኘን ። ሙሴ ከመቃብር በመነሣቱ ትንሣኤ ሙታን እንዳለ ፣ ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን በመምጣቱ ሀገረ ሕይወት እንዳለ ገለጡ ። በደብረ ታቦር ክብሩ ሲገለጥልኝ ሞቱንም ሙሴና ኤልያስ ሲናገሩ ሰማሁ ። የክብሩ መገለጥ ክብሩን በመመስከሬ ነው ፣ በዚህም ከዳዊት ጋር ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ ብዬ ዘመርሁ ። አትሙት እያልሁ ክርስቶስን ተከላክዬ ነበርና በሕግና በነቢያት የተጻፈው ይፈጸም ዘንድ ክርስቶስ መሞት እንዳለበት ሙሴና ኤልያስ ሲናገሩ ዝም አልሁ ። በክብሩ ውስጥ ትምህርት አለ ። 

 እኔም ደስታና ድንጋጤ ተቀላቀሉብኝ ። እንደ ልቤ እቀርበው የነበረው ክርስቶስ አሁን ከፀሐይ ይልቅ ሲያበራ ሳየው ነፍሴ መቅለጥ ጀመረች ። በደስታ ስካር ፣ በፍርሃት እንቅጥቅጥ ውስጥ ሆኜ ሰከርሁ ። የምናገረውንም አላውቅም ነበር ። ብቻ፡- “ጌታ ሆይ ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው ፤ ብትወድስ ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ” አልኩ ። የሚገርመው አሁንም ክርስቶስ ከተራራው ከወረደ ይሞትብኛል ብዬ ስለ ሳሳሁ በዚህ ክብር ውስጥ እንድንኖር ፈለግሁ ። ዛሬ ለመሞት ሮም ድረስ ተገኘሁ ያኔ ግን እፈራ ነበር ። የነፍሴን አድራሻ ሳውቅ ሞትን ደፈርሁት ። ሦስት ዳስ ለመሥራት ፈለግሁ ። ዳስ እንጂ ቋሚ ቤት አለመፈለጌ ዓለም ከንቱ መሆኗን ስላወቅሁ ነው ። ለስድስት ወገኖች ግን ሦስት ዳስ መመኘቴ እኛ በጌታ ዳስ ውስጥ ለመኖር እንደምንችል አስቤ ነው ። ሙሴ አብሮን ካለ ገዳዮች ቢመጡ እንደ አማሌቃውያን በእግዚአብሔር ስም ያጠፋቸዋል ብዬ ነው ። ኤልያስም አብሮን ካለ እርሱን ሊፈልጉ ወደ ተራራው የመጡትን ሠራዊት እንዳጠፋ ያጠፋልናል ብዬ ነው ። እኛን ይገድሉናል ብዬ አላሰብኩም ፣ ጠላት ለማትረፍ አቅማችን ትንሽ ነበር ። ጠላት የሚያተርፍ የተከበረ ነው ። ይህን ስናገር የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ የነበረው ብሩህ ደመና ጋረደን ። ደመና ጨለማ ነው ። አሁን ግን ብሩህ ደመና መንገዱንና ዙሪያውን የሚያሳይ መሪ መጣልን ። ከክብሩ የተነሣ እንዳንጠፋ የሚጋርደን ደመና ነበር ። ከዚህ በኋላ የምንሰማውን የአብ ቃል መቋቋም እንድንችል ብሩህ ደመና መጣ ። በዮርዳኖስ በርግብ አምሳል የመጣው መንፈስ ቅዱስ አሁን ደግሞ በብሩህ ደመና ተገለጠ ። እስራኤልን የመራ ያ ደመና በበረሃው ዓለም ላይ ሊመራን መጣ ። ቅዱስ እግዚአብሔር አብም ከደመናው በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው ፤ እርሱን ስሙት አለ ። ደብረ ታቦር ምሥጢረ ሥላሴ ለሁለተኛ ጊዜ ተገለጠበት ። የምወደው ልጄ ሲል አንድ ነገር ወደ ውስጤ ገባ ። የሚወደውን ልጁን ለዓለም ቤዛ እንዲሆን የሰጠው ምንኛ ቢወደን ነው ?! እኛ የምንወደውን ልብስ ለታረዘ አንሰጥም ። አብ ግን የሚወደውን ልጁን ለዓለም ሰጠ ። የአብ ድምፅ ገናና ነበር ። በዚህ ጊዜ ወድቀን ሰገድን ። ፍርሃትም ያንቀጠቅጠን ነበር ። በዚህ ጊዜ ክርስቶስ ቀርቦ ዳሰሰንና አትፍሩ ብሎ አረጋጋን ። ለእርሱ ወድቀናልና በእርሱ ተነሣን ። ዓይናችንን ገልጠን ብናይ ከእርሱ በቀር ማንንም አላየንም ። ደብረ ታቦር ሦስቱ መለኮታዊ አካላት የተገለጡበት ፣ የብሉይ ምሰሶዎች ሙሴና ኤልያስ የተገኙበት ፣ የአዲስ ኪዳን አገልጋዮች ሦስታችን የነበርንበት ቅዱስ ስፍራ ነው ። በደብረ ታቦር ብዙ ምሥጢር አለ ። በደብረ ታቦር የተገለጠው ክብር በእናንተም ላይ ሲያበራ ይኑር ።” 

 ሁላችንም ቆምን ። ቡራኬውንም ለመቀበል በግንባራችን መሬት ላይ ተደፋን ። ቡራኬ የበረከት ሸክም ነውና ዝቅ ማለት ይጠይቃል ። መቀበል ብቻ ሳይሆን ማቀበልም ያለበት ነው ። እግዚአብሔር ሆይ ስጠኝ ማለት በውስጡ የምሰጠው ስጠኝ የሚል ልመና አለበት ። እግዚአብሔር አብርሃምን ባረከና ለበረከት ሁን አለው ። መባረክ ብቻውን በቂ አይደለም ፣ ለሌላው በረከት መሆን ያስፈልጋል ። አዎ የደብረ ታቦር ብርሃን በቤታችን እንዳበራ ይኑር። 

 ይቀጥላል 

 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን 

ሐሙስ ሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ