የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 13

 

የሮማ ጎዳናዎች የቀደመውን መልካቸውን ባያጡም ኔሮን በ64 ዓ.ም. ሮም እንድትቃጠል በማድረጉ ብዙ ፍርስራሽ ቤቶች ይታያሉ ። ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ኔሮን ቄሣር ሮምን ያቃጠለው ቤተ መንግሥቱን ለማስፋፋት አስቦ ነው ። ያቃጠሉትም ክርስቲያኖች ናቸው በማለቱ ሕዝቡ ሁሉ ባገኘበት ቦታ እንዲገድላቸው መንገዱን አመቻቸ ። በ54 ዓ.ም የነገሠው ኔሮን እስከ 64 ዓ.ም. በክርስቲያኖች ላይ ጥላቻ አላሳየም ነበር ። ግማሽ እብድ ተብሎ የሚጠራው ኔሮን የከተማይቱን መቃጠል ቁልቁል እያየ ይደሰት ነበር ። ከተማይቱም ሁለት ሦስተኛዋ በእሳት ነደደ ። እርሱም ሕዝቡም በሐሰተኛ ክስ ወንጀለኛ በተደረጉት ክርስቲያኖች ላይ የመዓት ጅራፋቸውን አነሡ ። እነዚህ ዓመታት ከባድ ናቸው ። ከሮማ ነገሥታትም የመከራው ጀማሪ እርሱ ሆነ ። ሮም ግን በፍርስራሽና በቃጠሎ ውስጥም ሁና ታምራለች ። ጎዳናውን ሳየው ሁሉም መንገዶች በእቅድ የተሠሩ ከሮም እንዲያወጡና ወደ ሮም እንዲያደርሱ ሁነው የተሠሩ ነበሩ ። ሕዝቡ ግን ንብረቱ ስለወደመበት አንዴ ንጉሡ ነው ሌላ ጊዜም ክርስቲያኖች ናቸው አንዳንዴም አማልክትን ክርስቲያኖች ስለ አስቆጡአቸው መዓት አምጥተውብን ነው ይል ነበር ። እኔም ከአውግስጦስ ቄሣር ጎዳና ተነሥቼ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ቤት የምጓዘው የሕዝቡን የጥላቻ አስተያየት እያየሁ ነበር ። የዓለምን እንኳን ጥላቻውን ፍቅሩንም ንቄው ነበርና አልተገረምኩም ። ላመነበት ነገር ጠንካራ የሆነው የሮም ሕዝብ ክርስትናን ቢያውቅ ከእኔ የተሻለ በሕይወቱ ይኖረው ነበረ ። በጥላቻና በፍቅር ፣ በኀዘንና በደስታ ውስጥ ጎዳናውን አቋርጥ ነበር ። እግሬ ሠረገላ ባይሳፈርም ልቤ ግን በአሳብ ሠረገላ ላይ ነበረ ። 

ከቀልቤ ጋር ባልሆንም ጎዳናውን በትክክል እያቋረጥሁ መንገዱንም ሳልስት በጳውሎስ ደጃፍ ደረስሁ ። ወዴት እንደምሄድ አውቅ ነበርና ሰዓቱን አልባከነብኝም ። እንዴት በአሳብ ዓለም ጠፍቼ ሳለሁ በደመ ነፍስ መንገዱን አወቅሁት ብዬ ራሴን ስጠይቅ አንደኛ ማንነቴ እግዚአብሔር መንገዱን እየመራህ ነበር አለኝ ። ከሚወጣና ከሚገባ ሰው የተነሣ ክርስቲያኖች በዚህ ቤት መሰባሰባቸው ብዙም እንዳይታወቅ የጳውሎስ ቤት በሩ ገርበብ ያለ ነበር ። ደግሞም የአገልጋይ ደጃፍ የእግዚአብሔር ደጃፍ ነውና በሩ ዝግ መሆን የለበትም ። እኔም ሰላምታ ሰጥቼ ወደ ውስጥ ስገባ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከመሬት መኝታው ለመነሣትና እኔን ለመቀበል መቧጠጥ ጀመረ ። ሐዋርያው ሥልጣኑ አገልጋይ እንጂ ጌታ አላደረገውም ። እኔም አይገባም ብዬ መኝታው ላይ ሳለ ያዝሁት ፣ ጉልበቱንም ስሜ ዝቅ አልኩ ። እርሱም ወትሮ እንደሚያደርገው እጆቹን በግንባሬ ላይ አድርጎ ባረከኝ ። ታላቅ ሸክምም ሲናድልኝ እየተሰማኝ የነፍስ አርነት ወደ ውስጤ መግባት ጀመረ ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከላይ ሲያዩት ቍጠኛ ፣ ንግግሩም ኃይለኛ ቢመስልም ውስጡ ግን በፍቅር የረጠበ ፣ በእንባም ቋንቋ የሚናገር ነበረ ። ሐዋርያው ጳውሎስም ከጴጥሮስ ተቀብሎኝ እቅፉ ውስጥ አስገብቶ ሰላምታ ሰጠኝ ። በአባታዊ ፍቅርም ጀርባዬን እየጠበጠበ አቀረበኝ ። እኔም የሁለቱን ቅዱሳን ሐዋርያት በረከት ሳገኝ ሁለት ክንፍ እንዳበቀለ ተሰማኝና በአየራቱ ላይ ለመብረር ለልቤ መልእክት ላኩበት ። ለካ የእግዚአብሔርን አገልጋይ ማግኘት ትልቅ በረከት አለው ! 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ በራ ወይም የሚያበራ ነበር ። አሁን በጋ እየመጣ ስለነበር ገለጥ አድርጎታል ። ቁመቱ አጭር ሲሆን ከእቅፉ ውስጥ ለመግባት ዝቅ ማለት ነበረብኝ ። ሐዋርያው አቅሙ ደካማ በበሽታ የተጎዳ ነበር ። የሥጋ ብርታት የእግዚአብሔርን መንግሥት አያገለግልም ። የመንፈስ ሙላት ግን ለብዙዎች መዳን ምክንያት ይሆናል ። ሐዋርያው በልብሱ ቅዳጅ ፣ በአካሉ ጥላ ድዉይ እየፈወሰ እርሱ ግን ታማሚ ነበረ ። በተሰጠው ጸጋ እንዳይታበይ በሽታው መጠበቂያ ሆኖለት ነበር ። ከበሽታ በላይ ትዕቢት ትልቅ በሽታ ነው ። እኛ ራስ ምታትን እንፈራለን ፣ እግዚአብሔር ግን ትዕቢትን ይፈራልናል ። ዲያብሎስ የወደቀው በዝሙት ሳይሆን በትእቢት ነው ። ትዕቢት የኃጢአት መነሻ ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስ የማያቋርጥ ራስ ምታት ደግሞም የዓይን ሕመም ያሰቃየው ነበር ። መልእክቱንም ዓይኑን ጨፍኖ እየተናገረ ፀሐፍያኑ ይጽፉለት ነበር ። በመጨረሻ መልእክቱን ሲዘጋ ለፊርማው እርሱ ይቀበላቸው ነበር ። 

ቅዱስ ጴጥሮስም ለማታ የእግር ፣ ለጠዋት የፊት ውኃ የሚያቀርብለትን ማርቆስን ጠራው ። ሲላስና ጢሞቴዎስ ቢኖሩም እንዲህ ያሉ ትእዛዛትን ለማዘዝ ማርቆስ ይቀለው ነበር ። ከጣትም ጣት ይበልጣል እንዲሉ ማርቆስ ያረካው ነበር ። የማርቆስ ወንጌልም የጴጥሮስ ወንጌል ነው ። ጴጥሮስ ታሪኩን እየነገረው ጻፈው ። ነገር ግን ትሑት ነውና በአንተ ስም ይሁን በማለት የማርቆስ ወንጌል ተብሎ ተሰየመ ። ማርቆስ ስሜቱ ቶሎ የሚረበሽ ልጅነት የሚያጠቃው ቢሆንም ጴጥሮስ ግን ያንን የድሮውን ሕፃንነቱን እያሰበ ይራራለት ነበር ። ማርቆስም እንደ ተቀባበለ መሣሪያ ፈጥኖ የታዘዘውን አደረገ ። አባት ለመሆን ልጅ ፣ መምህር ለመባልም ተማሪ መሆን ግድ ይላል ። የረድዕ ጆሮ ንቁ ፣ ክንፉም ለመብረር የተዘረጋ ነው ። ጴጥሮስም የፊት ውኃ እንደ ቀረበለት ማርቆስን፡- “የግብጽን ቤተ ክርስቲያን ትመራለህ ፣ አባት ተብለህም ትጠራለህ ። ሰብአ ኢትዮጵያም ማርቆስ አባቴ  ብለው ይጠሩሃል ። በመንበርህም የሚሾም አይታጣም” በማለት የጅምሩን ፍጻሜ ነገረው ። ማርቆስም ደስ አለው ። አንድ የፊት ውኃ አቅርቦ ይህን ሁሉ በረከት መቀበል እግዚአብሔር ባለጠጋ ነው እንድል አደረገኝ ። ማርቆስም ጴጥሮስን ፣ እነ ሲላስም ጳውሎስን ሊሰናበቱ የመጡ መሰለኝ ። የመጨረሻው ሰዓት ሁሉን ይሰበስባል ። 

ሐዋርያው ጴጥሮስም የእግዚአብሔርን ሥራ ሊናገር ሲል የደከመው አቅሙ በረታ ። ቃለ እግዚአብሔር አጥንትን የሚያጸና ፣ ሥጋን የሚያለመልም ነውና ። ጉባዔውን በጸሎት ከፈተ ። ሐዋርያውም መናገር ጀመረ ፡- 

ከደብረ ታቦር ከወረድን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም መጣን ። በዚያም ግብር የሚያስከፍሉ ሰዎች ግብር እንድንከፍል አዘዙን ። በቀጥታ ክርስቶስን አልጠየቁም ፣ እኛን ጠየቁን ። የዓለሙ መምህር ሳለም መምህራችሁ ግብር አይከፍልም ወይ ? የሚል ጥያቄ አቀረቡልን ። ጥያቄውንም ያቀረቡት በይበልጥ ለእኔ ነበርና ግራ ገብቶኝ ነበር ። እንዲህ በአሳብ እየተጉላላው ወደ ቤት ገባሁ ። ይህ በብዙ መንገድ ከባድ ነበረ ። ግብር የሚሰበስቡት ለሮማ መንግሥት ነበረ ። ጌታን ከሚከተሉ አብዛኞቹ ከሮማውያን ነጻ ያወጣናል ፣ አንድ ቀንም እንቢ ለሮማውያን ብሎ ያዘምተናል ብለው በእምነት ሳይሆን በአርበኝነት መንፈስ የሚከተሉት ነበሩ ። ቀነናዊ ስምዖንም ከአርበኝነት የተጠራ ነውና ስሜቱ ስስ ነው ። ግብርን ሲከፍል ሲያዩት የሮማ መንግሥት ወዳጅ ነውና መሢሕ አይደለም ለማለት ቅርብ የነበሩ ሰዎች አሉ ። ግብርን አልከፍልም ቢል ደግሞ የሮማ መንግሥትን ይቃወማል ይባላል ። ከሁሉ በላይ እርሱ ንጉሠ ነገሥት ሳለ ግብር ይገባለታል እንጂ አይገብርም ። ጌታ ግን የሰዎቹንም ጥያቄ የእኔንም ግራ መጋባት ያውቃል ። ወደ ቤት እንደ ገባን አንድ ጥያቄ ጠየቀኝ፡- ስምዖን ሆይ ፥ ምን ይመስልሃል ? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ ? ከልጆቻቸውን ወይስ ከእንግዶች ? ሲለኝ ከእንግዶች አልኩት ፤ ጌታም እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው ። ነገር ግን እንዳናሰናክላቸው ፥ ወደ ባሕር ሂድና መቃጥን ጣል ፥ መጀመሪያም የሚወጣውን ዓሣ ውሰድና አፉን ስትከፍት እስታቴር ታገኛለህ ፤ ያን ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ስጣቸው አለኝ ። እኔም ያዘዘኝን አደረግሁ ። 

ጌታችን እግረ መንገዱን ያስተማረው ቋሚ የሆነውን ትምህርት ነው ። በዚህ ዓለም ላይ አንግዶች ነን ። እንግዳ ከቤቱ ርቆ የሚኖር ነው ። እኛም ከመኖሪያችን ርቀን ያለን እንግዶች ነን ። እንግዳ በትሩን በእጁ ይዞ ፣ ወገቡን ታጥቆ ፣ የጫማውን ማዘቢያ ቋጥሮ የሚበላ ነው ። እኛም ሰማይን እያሰብን የምንማርና የምንሠራ ነን ። እንግዳ ቢዘገይም መሄዱ አይቀርም ፣ እኛም ማለፋችን አይቀርም ። አንድ ቀን የሚውለውም ሳምንትና ወራት የሚከርመውም ሁሉም እንግዳ ይባላሉ ። በዕለት የሞተውም በሰማንያ ዓመት የሚሞተውም እንግዳ ናቸው ። እንግዳ ፊት አይነሡትም ፣ ነገ ይሄዳልና ፤ እኛም ወንድማችንን ከደቂቃ በኋላ ልናጣው እንችላለንና ክፉ ፊት ልናሳየው ፣ ክፉ ቃል ልንናገረው አይገባም ። እንግዳ መሄዱን እያሰበ አመሉን አያስቆጥርም ። ክርስቲያንም ሞቱን እያሰበ በቅዱስ ፍርሃት ይኖራል ። ጌታ የነገሥታት ንጉሥ ሳለ ግብር ከፈለ ። እኛም የእርሱን ትሕትና እያሰብን ግብር መክፈል ይገባናል ። የመንግሥት ሥርዓት የእግዚአብሔር ሥርዓት ነውና ማክበር ያስፈልገናል ። ጌታችን በተአምራት ከዓሣ ሆድ የተገኘውን እስታቴር እንድገብር አደረገ ። በዚህም መገበር የማይችል በኪሱ ገንዘብ የሌለው ፍጹም ድሀ መሆኑን ፣ መስጠት የሚችል የተአምራት አምላክ መሆኑን ገለጠ ። 

ሐዋርያው ጳውሎስም በዚህ አለ ፣ ጢሞቴዎስም በዚህ አለ ። ባለፈው በላከው በጢሞቴዎስ መልእክት በምዕራፍ ሁለት ላይ፡- “እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ።” ብሏል ። ነገሥታትን ማክበር ማለት ግብርን በታማኝነት መክፈል  ነው ። ደግሞም ክርስቶስ ለእነርሱም ሙቷልና የመዳንን ወንጌል ማድረስ ፣ ከሁሉ በፊት ስለ መሪዎች መጸለይ ይገባል ። የመርከቡ ካፒቴን ሲታወክ ተሳፋሪውም አብሮ ይታወካል ። የመርከቡ አደጋ መርከቡ ላይ ሁሉ የተሳፈሩትን ይነካል እንጂ እኔን አይመለከተኝም የሚባል አይደለምና ለአገራችሁም ጸልዩ ። ርቃችሁ በሮም ብትኖሩም ለምትኖሩበት አገርም ጸልዩ ። እግዚአብሔር በጸጋ በበረከት ይጠብቃችሁ።”

ሁላችንም ተነሣን “አሜን” አልን ። አገራችን ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም እንደምትደመሰስ ትንቢት ሰምተናልና ለመጸለይ ልባችን መደንዘዙን የሐዋርያው ምክር አነቃን ። ለመፋቀርም ፣ ወድቆ ለመነሣትም አገር ያስፈልጋል ። በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የኢየሩሳሌም ብሔራዊ መዝሙር መስፈሩ አገር ክቡር መሆኑን ፣ ደግሞም አገራችን ለእኛ ኢየሩሳሌም መሆንዋን እንድናስብ ነው ። ሰማያዊት አገርን የምንወርሰው በምድራዊት አገራችን ላይ ሆነን በምንወስነው የእምነት ውሳኔ ነው ። አቤቱ አገራችንን ጠብቅልን ።

ይቀጥላል 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ማክሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ