የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 14/

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን ለማየት የነበረኝ ጉጉት ልዩ ነበር ። እግዚአብሔር ከአዋቂ በአስተዋይ ፣ ከብርቱ በገራም ደስ እንደሚለው የቅዱስ ጴጥሮስ ሕይወት ምስክር ነው ። እውቀት ወደ ማስተዋል ካልመራ ፣ ብርታትም ገራም ካላደረገ ጅማሬ እንጂ ፍጻሜ የለውም ። ደስ የሚያሰኝ ጅማሬ ደስታው የሚዘልቀው ፍጻሜ ሲኖረው ነው ። እውቀት ፣ ብርታት ጅማሬ ነው ። ከመጀመሪያው የመጨረሻው ይሻላል ። ሐዋርያው በዚህ ሳምንት ቶሎ ቶሎ እያስተማረን ነው ። እኔም ሁለት ነገሮችን ተገነዘብሁ ። ስፈልገው የነበረውን መንፈሳዊ ገበታ ሳገኘው እንዳልንቀውና እያንዳንዱን ቀን እንደ መጨረሻ ቀናችን አድርገን ከኖርን ብዙ መሥራት እንደምንችል ተረዳሁ ። ሐዋርያው ምስክርነቱን በሰማዕትነት ሊፈጽም ጥቂት ቀን እንደ ቀረው አውቄአለሁ ። ዛሬ ሰኔ 29 ቀን 67 ዓ.ም ነው ። 

ማልጄ ደርሻለሁ ። በቁሙ ያልተጠቀሙበትን ሰው ሲሞት መቆጨት ዋጋ የለውም ። ከዚህ በፊት ስላለፉት ስለ ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስና ስለ ያዕቆብ ሐዋርያ ብዙ ይቆጨኝ ነበር ። ባለፉት ስንቆጭ ያሉትን ማየት ተገቢ ነው ። አሊያ የቁጭት ክምር በላያችን ላይ ያርፋል ። ከትላንት እንደ ተማርን ማስረጃው የዛሬዎቹን ማክበር ነው ። ቅዱስ ጴጥሮስ ዛሬ ብርሃን ለማግኘት ወደ በሩ ተጠግቶ ማስተማር ጀመረ ። እንዲህም አለ፡- 

“ባለፉት ቀናት እንደ ነገርኳችሁ ታሪኬ ከክርስቶስ ጋር የተሳሰረ ነው ። ታሪኬ ያለ ክርስቶስ መቆም አይችልም ፣ ይወድቃል ። ጠባዬን ዞር ብዬ ሳየው የተለያየ ነው ። አንዳንዱ የማይጨበጥ ነው ። ክርስቶስ ከዚህ ማንነቴ ጋር እንደ ወደደኝ ሳስብ ኩራት ይሰማኛል ። መከፋቴና መደሰቴ በፊቴ ላይ ቶሎ ይታወቃል ። ሰውን መውደድ እንጂ መደለል አልወድም ። ላመንኩበት ነገር ሕይወቴን እሰጣለሁ ። ብዙ ዘመን ዋጋ ብከፍልበትም ውሸት መሆኑን ሳውቅ ቶሎ እጥላለሁ እንጂ እንዴት ይህን ሁሉ ዋጋ የከፈልኩበትን በቀላል እጥላለሁ ብዬ እልህ አልጋባም ። የዛሬ እውነት የብዙ ዘመንን ውሸት ትክሳለች ። ያልገባኝን ነገር ለመጠየቅ አላፍርም ። ዕድሜዬን ፣ ሽበቴን በማሰብ ወይም በሰብአዊ ኩራት ውስጥ ሆኜ ያልገባኝን ነገር እንደ ገባኝ ለማስመሰል አልጥርም ። ይሉኝታን አልፈራም ። የሰው ልጅ ትልቅ ወጥመድ ይሉኝታ ነው ። እኔ ከዚያ ተፈትቻለሁ ። ዙሪያዬን አይቼ ያመንኩበትን ነገር አልክድም ። ብቻዬን ብቆምም ያመንኩትን አከብረዋለሁ ። ከብዙኃን መጣላትን አልፈራም ። እኔ መጣላት አልፈልግም ፣ ሰዎች ግን እኔን ባሳረፈኝ እውነት መጣላት ከፈለጉ አልጨነቅም ። እንባ ያጠቃኛል ። ስሜቴ ስስ ነው ። ከሰዎች ብዙ እጠብቃለሁ ። ለነገሮች ሁሉ ፈጣን ነኝ ። ፈጥኜ ብሠራም ውጤቱ ግን ያንስብኛል ። የተረዳሁትን እውቀት ቶሎ ለማስተላለፍ እፈልጋለሁ ። የምሥራቹን ይዞ ማደር ያስጨንቀኛል ። ሰው ሁሉ እንደ እኔ ቢሆን እፈልጋለሁ ። ጸሎትን ትቼ ፉከራ አበዛለሁ ። የወደድኩትን ሰው እስከ ዘላለም የምወደው እየመሰለኝ እፎክራለሁ ። መፎከር ጸሎትን ያስረሳል ። ሰው የሚወድቀው እንደሚያሸንፈው እርግጠኛ በሆነበት ነገር ነው ። ምክንያቱም በዚያ ጉዳይ መጸለይ አቁሟና ይዘናጋል ። መንፈሳዊውን ውጊያ በሥጋ መሣሪያ ለማሸነፍ ሰይፍ መምዘዝ እወድ ነበረ ። ሰዎች ፊታቸውን ቅጭም ሲያደርጉብኝ ፀሐይ የጠለቀች ያህል እፈራ ነበር ። ሁሉም ሰው ምን ያውቃል ደግ ነው ሲለኝ ክፉ ነው እንዳይለኝ እባክን ነበር ። የምወደውን ሰው ሞቱን ሳስብ ቁጭ ብዬ አለቅሳለሁ ። መዋደድ እንዳለ ጠብ ፣ መኖር እንዳለ ሞት ተረስቶኝ ነበር ። ኑሮዬ የዕለት ነው ። በትዳር ብኖርም የሌጣ ያህል ገንዘብን እበትን ነበረ ። ምን እሆናለሁ ? የሚል ሙግት በውስጤ ይወዘውዘኝ ነበር ። በይቅርታ ባምንም ሰባት ጊዜ እንጂ ከዚያ በላይ ይቅር ማለት አለብኝ ብዬ አላምንም ነበር ። ይህን ሁሉ ጠባዬን የክርስቶስ ፍቅር ፣ የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት አስተካከለልኝ ። 

እናንተም ቋሚ ማንነት ይኑራችሁ ። እንደ ቀኑ የአየር ሁኔታ ተለዋዋጭ አትሁኑ ። የአየር ንብረት ቋሚ ነው ፣ የአየር ሁኔታ ግን ተለዋዋጭ ነው ። አሁን ሳቂታ ቀጥሎ አኩራፊ ፣ አሁን አመስጋኝ ቀጥሎ ተራጋሚ ፣ አሁን ቸር ቀጥሎ ቢስ አትሁኑ ። እንዲህ ዓይነት ጠባይ ከቀላልነት ፣ ከስሜታዊነትና ከሱሰኛነት የሚመጣ ነው ። መንገደኛና ዛሬ ያወቃችሁ በቀላሉ የሚያነባችሁ ሰው አትሁኑ ። ችግራችሁን በልባችሁ መቻል አቅቷችሁ በፊታችሁ አደባባይ አታስነብቡ ። ሊረዱአችሁ የማይችሉት ልጆቻችሁ ይሳቀቃሉ ። ወዳጆቻችሁ ምን ሆነው ነው በማለት ይጠራጠራሉ ። ጠላቶቻችሁ ይስቃሉ ። ይህን ስላችሁ እውነተኛ ስሜታችሁን አትግለጡ ማለቴ አይደለም ። ቦታውን ግን ምረጡ ። ሰውን በተግባር ውደዱት ። ከእናንተ ጋር ግን መኖር ያለበት በፍቅር እንጂ በማባበላችሁ መሆን የለበትም ። ማባበል ሆድ ማስባስ ነው ። በፍቅር ዓለም ብከዳስ ብላችሁ አታስቡ ። እናንተ ከፍቅራችሁ ጋር ከቀራችሁ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና ከእግዚአብሔር ጋር ቀርታችኋል ። ላመናችሁበት ነገር ስትኖሩ የሚያስከትለውን ውጤት ተምኑ እንጂ አትፍሩ ። ዋጋ ለመክፈል የፈራችሁበት ነገር በደንብ ያልተረዳችሁት ነገር ነው ። ጥላቻም ዋጋ ያስከፍላል ፣ ለፍቅር ዋጋ መክፈል ግን ያኮራል ። የኖርኩበትን ዘመን ውሸት ነበር አልልም ብላችሁ ሐሰትን ለመጣል አትግደርደሩ ። የእናንተን እውነት ከእግዚአብሔር እውነት ለዩ ። አልገባውም እንዳትባሉ ፈርታችሁ ያልገባችሁን ነገር ገብቶኛል አትበሉ ። መጠየቅ የእውቀት እናት ናት ። ሁሉን ለማወቅ እንኳን ምድር ሰማይም ብትሄዱ አይበቃም ። በዓለም ካሳለፋችሁት አእላፍ ቀናት በእግዚአብሔር ቤት የምታሳልፉት አንድ ቀን ይበልጣል ። የሰማንያ ዓመት ኃጢአት በአንድ ሰዓት ንስሐ ይካሳልና ንስሐ ለመግባት አትፍሩ ። ዘመን ያመጣው ዘፈን እንቅርት ያፈርጣል እንዲሉ በወቅታዊ ርእስ ተንታኝ አትሁኑ ። 

ትላንትን ባስብ እኔ ከሀዲ ነበርሁ ። ጌታዬ እኔን የተማመነኝን ያህል እኔ በእርሱ አላመንኩም ነበር ። ዓለቱን ጌታ ተጠራጥሬ ሸምበቆ የምሆን እኔን ግን አምኖ አደራ ሰጠኝ ። ይሉኝታን አትፍሩ ። ሰው የሚለው አያጣም ። ትሑት ብትሆኑ ልምጥምጥ ፣ ትዕቢተኛ ብትሆኑ ጨካኝ ፤ ብትሰጡ በታኝ ፣ ብትሰስቱ ዱሽ ይላችኋል ። እንደ ሰው ማን ጸድቆ ፣ እንደ ክርስቶስ ማን ተኰንኖ ! 

ልጆቼ ሆይ ስሙኝ ። የተማራችሁት ብዙኃኑ ለተስማማበት ሐሰት አሜን እንድትሉ አይደለም ። መማር ልዩነት ካላመጣ አለመማር ነው ። ከብዙኃኑ ይነጥለኛል ብላችሁ መለኮታዊን ነገር አትጣሉ ። ማማት እንጂ መታማትን አትፍሩ ፣ አትጣሉ እንጂ ቢጣሉአችሁ አትስጉ ።  ሰው ከዳኝ ፣ ንብረት ተወሰደብኝ ብላችሁ እንባን አታፍስሱ ። የማይከዳው ጌታ ከእናንተ ጋር ነው ። ርስተ መንግሥተ ሰማያትም ይጠብቃችኋል ። አንድ ቀን ሁሉን ትታችሁ በጨርቅ ተጠቅልላችሁ ወደ መቃብር ስትወርዱ ሁሉም ትቷችሁ ይመለሳል ። ንብረታችሁም ለጠላችሁት ሰው ይሆናል ። ከሰዎች ብዙ እንድትጠብቁ ሰይጣን ሲፈትናችሁ ሰዎቹ ደግሞ በጥቂቱ እንዳይገኙ ይዋጋቸዋል ። እግዚአብሔርን የጠበቀ ፍሬውን ይበላል ። ሰውን የጠበቀ ያፍራል ። ፍጥነት ሁሉ ትጋት ፣ ማዝገም ሁሉ ትዕግሥት አይደለም ። ዛሬ ልትሠሩት ስትችሉ ነገ ብላችሁ ሥራን አታሳድሩ ። የሰማችሁትን ቃለ እግዚአብሔር ለሌሎች ማሰማት ተገቢ ነው ። አዋጅ ያልሰማህ ስማ ፣ የሰማህ ላልሰማ አሰማ ነውና ። ሰው እንደ ራሱ እንጂ እንደ እናንተ አይሆንምና ትግል ውስጥ አትግቡ ። ጸሎትን የሚያስተው ሥጋዊ መተማመን ነውና ተጠንቀቁ ። ካልደፈረሰ አይጠራም ብላችሁም ነገሮችን አታደበላልቁ ፣ ሰው ያደፈረሰው አይጠራምና ። መንፈሳዊ ውጊያን በሥጋ መሣሪያ በስድብ ፣ በትችት አትመክቱ ። ጸጋ እግዚአብሔር እየራቃችሁ ይመጣል ። የነቀፋ ትምህርት ማስተማር የለመደ ጤነኛ ትምህርት ማስተማር ይቸገራል ። ነቀፋ ያልቃል ፣ ቃለ እግዚአብሔር ግን አያልቅምና ኩሬውን ትታችሁ ከምንጩ ቅዱ ። 

እኔ በገባሁበት ጦርነት ሁሉ ሲባባስ እንጂ ሲበርድ አይቼ አላውቅም ። የጦርነት መጨረሻ ጦርነት አይሆንም ። ሥጋዊ ውጊያ ግን ሁልጊዜ በጦርነት ያኖራል ። እግዚአብሔር ይዋጋላችሁ ዘንድ እመኑት ። ወዶኛልና አዳነኝ ይላል ። ሰው ወድዶ ሊያድን አይችልም ። የማያድነውን የሰው ፍቅር አታሳድዱ ። ደግ ነው የሚል ዜማ ለመስማት ገንዘባችሁን አትበትኑ ። ያለ ምርቃትም መስጠትን ተለማመዱ ። ገንዘብ ዘር ነውና የት ነው የምዘራው ? በሉ ። ለባለጠጋ ድሀ ብትሰጡ እሾህ ላይ የተዘራ ነውና ይታነቃል ። ይገባኛል የሚሉ ደንዳኖች ላይ ብትዘሩ ድንጋይ ላይ የወደቀ ነው ። ሱሰኞች ላይ ብታባክኑ መንገድ ዳር የተዘራ ነው ። ጥሩ ልብ ላላቸው ፣ አትርፈው ለሚጸልዩላችሁ ገንዘባችሁን ዝሩ ። ሰው በፍቅር ጀምሮ በጠብ መጨረሱ የተለመደ ነው ። ያልወደደውን አይጣላምና በሰው ተለዋዋጭነት አትገረሙ ። የምትወዱት ሰው የሞተው የከዳችሁ ቀን ነው ። የተፈጥሮ ሞትን ቢሞት የሰው ሁሉ መንገድ ነው ። ምን እሆናለሁ ? ማለት የአሕዛብ ጥያቄ ነው ። የሰው ዕድሉ በእግዚአብሔር እጅ ነው ። እግዚአብሔር የጻፈላችሁን ሰው አይሰርዘውም ። ያለ ገደብ ይቅር ተብላችኋልና ለይቅርታ ገደብ አይኑራችሁ ። ያዘናችሁበትን ሰው ተቀይሜሃለሁ በሉ እንጂ የውሸት እወድድሃለሁ አትበሉ ። ያም ሰው ስህተቱን ማወቅ እናንተም ከቂም መዳን አለባችሁ ።

በሉ ለዛሬው ይበቃናል ። እግዚአብሔር በሰማያዊና በምድራዊ በረከት ይባርካችሁ !

ሁላችንም ከተቀመጥንበት ተነሥተን አሜን አልን ። ሐዋርያውም በአሚነ ሥላሴ ያጽናችሁ ብሎ ባረከን ! 

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ