የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 15/

 

የዛሬውን መርሐ ግብር የጀመርነው ትንሽ ዘግየት ብለን ነው ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ራስ ምታቱ ሌሊቱን በሙሉ ሲያሰቃየው አድሯል አሉ ። ከአይሁድ ክፍል ቀነናውያን ተብለው የሚጠሩ አርበኞች በሮማውያን ላይ በማመፅ የነጻነት እንቅስቃሴ በገሀድ ጀምረዋል ። ይህንንም ዓመፅ በ60 ዓ.ም ጀምረው በ66 ዓ.ም ኢየሩሳሌምንና መቅደሱን ከሮማውያን ነጻ አደረጉ ። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ኔሮን ቄሣር ቬስፓስያን የተባለውን ጀነራል ስድሳ ሺህ ጦር አስይዞ ኢየሩሳሌም ላይ አዘመተው ። ሐዋርያው ጳውሎስ ጦሩ በቅርቡ በዚሁ በ67 ዓ.ም. መንቀሳቀሱን ሲሰማ ስለ ወገኖቹ አዘነ ። ደግሞም ከ64 ዓ.ም ጀምሮ በሮማና በሮም ግዛቶች በክርስቲያኖች ላይ ስደትና መከራ ጸንቶ ነበር ። ሐዋርያው ስለ ክርስቲያኖች መከራም ትላንት ማታ ሰምቶ ነበርና ቍጡ ጠባዩ የበለጠ ሕመሙን ቀሰቀሰበት ። እንዲሁም ሐሰተኛ ነቢያትና መምህራን በስንዴው ላይ እንክርዳድ ዘርተውበት ፣ በእህሉ ላይ አፈር በትነውበት ነበርና ስለ ወንጌል  አገልግሎት አዘነ ። የዕብራውያን ክርስቲያኖችም ወደ ኋላ መመለሳቸውን አላቆሙምና በቆሮንቶስም አገልጋዮችን መዳፈር በርክቷልና ይህን ሁሉ ሲሰማ ውስጡ ተጎዳ ። ስሜት ሲጎዳ አካልን ይሰብራልና በማለዳ ሳየው ተጎሳቁሎ ነበር ። ፊትን ከሚያፈኩ ነገሮች አንዱ መልካም ወሬ ነው ። 

ጢሞቴዎስና ሲላስም አብረውት ሌሊቱን በሙሉ ሲጨነቁ አድረዋል ። ማለዳ እንደ ምንም ከመኝታው ቢነሣም ዓይኖቹ ግን ሊገለጡ ከብዷቸው ነበር ። ራስ ምታቱም ተነሥቶበታልና ብርሃን ማየት ተቸገረ ፣ የማቅለሽለሽ ስሜትም ስላለው ምግብ ለመቅመስ እንቢ አለ ። እኔ ተኝቼ ነው ያደርሁት ። መምህሩ ጳውሎስና ደቀ መዛሙርቱ ግን ሲጨነቁ አድረዋል ። ያስታማሚ በሽታው ከታማሚው በላይ ነው ። አስታማሚ እግዚአብሔር ይማርህ የማይባል በሽተኛ ነው ። ሰውን ማስታመም በበረሃ በተጋድሎ ከመኖር በላይ ዋጋ አለው ። ማርቆስ ግን ከጴጥሮስ እግር ሥር ተኝቶ ነበርና ጴጥሮስ እንዳይረበሽ ብለው የጳውሎስን ሕመም አልነገሩትም ነበር ። ቅዱስ ጴጥሮስ እርጅናም እየተጫጫነው ነው ። ጤናው ግን የተሻለ ነው ። “በዘጠና የለም ጤና” ቢባልም ጴጥሮስ ግን ጎበዝ ነበር ። ሲበላው የኖረው የገሊላ ዓሣ ይሁን አይታወቅም ፣ አእምሮው ብሩህና ምንም ነገር የማይረሳ ነው ። ቶሎ ይቅር ስለሚልና የነገሮችን በጎ ትርጉም ስለሚፈልግ እንዲሁም በገራምነቱ ይመስላል ጤነኛ ነበር ። 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ድውያንን እየፈወሰ በሽተኛ ነበር ። ደዌው ግን የጸጋ ነበር ። እግዚአብሔር የሚበልጥ ችግርን በሚያንስ ችግር ያስወግዳል ። ሁሉም በሽታ ከአጋንንት ፣ ሁሉም በሽታ የኃጢአት ውጤት አይደለም ። ይህን የሚያስቡ ክርስቲያን ፈሪሳውያን ናቸው ። የጸጋ ደዌም አለ ። የጸጋ ደዌ ቅዱሳን በተሰጣቸው ስጦታ እንዳይታበዩ የሚጠብቃቸው መንፈሳዊ አጥር ነው ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በደከመ ስሜት ሆኖ “ስነሣ ይቀለኛል ፣ ቃለ እግዚአብሔር ስሰማ ደግሞ ይርቅልኛል” ብሎ ጉባዔውን ተቀላቀለ ። ክርስቲያንም እንደ ዓለማውያን ይፈተናል ። የሚለያዩት በፈተናው ሳይሆን በውጤቱ ነው ። 

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጉባዔውን በጸሎት ሊከፍት ሲነሣ ሁላችንም ቆምን ። ጸሎቱ እንደ ተፈጸመም ትላንት ካቆመበት ከለሰና የዛሬውን ትምህርት ቀጠለ፡-

“ዛሬ የምነግራችሁ የምሴተ ሐሙስ ነገርን ነው ። ከጌታችን ጋር የመጨረሻ እራት የበላንባት ቀን ፣ የብሉይ ፋሲካ የተፈጸመባት ፣ ሐዲሱ ፋሲካ ክርስቶስ የተበሰረባት ዕለት ናት ። በዚህች ምሽት ጌታችን ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ለእኛ የሚሰጥበትን የቅዱስ ቍርባንን ሥርዓት ሠራልን ። ሥጋዬን ብሉ ፣ ደሜንም ጠጡ በማለት ታላቅ ፍቅርን ገለጠልን ። በዚህች ምሽትም ታላቅ ክህደት ተፈጽሟል ። ‘ባለጌ የተመከረ ዕለት ፣ ቁንጫ የተጠረገ ዕለት ይብስበታል’ እንዲሉ ይሁዳ የባሰበት ምሽት ፣ እኔም እንደ ገበቴ ውኃ የዋለልኩበት ሰዓት ነው ። የታሰረ ወዳጃችሁን አውቀዋለሁ ማለት ምንም ችግር የለውም ። ጊዜ ከድቶት የታሰረውን ወዳጃችሁን እስር ቤት ሄዳችሁ ለመጠየቅ ትቸገራላችሁ ። ምክንያቱም መከራው ወደ እኔ ቢመጣስ ብላችሁ ትፈራላችሁ ። አንድን ሰው ማወቅ ግን ወንጀል አይደለም ። ይህ ግን ከንቱ ፍርሃት ነው ። ወዳጅነት ለክፉ ቀን ካልተገኘ ወዳጅነቱ ምንም አይጠቅምም ። በሰላም ቀን ሁሉም አለሁ ይላል ። የመከራን ጽዋ የተሸከመውን ግን አይዞህ በማለት ማገዝ ይገባል ። ክርስቶስ ጌታዬ እንጀራ ሲያበረክት አምስት ሺህ ሰው ተከተለው ፣ ሲታሰር ግን ከዮሐንስና ከድንግል ማርያም ውጭ ማንም አጠገቡ አልነበረውም ። ብዙ ጠላት ከቦታል ወዳጅ ግን አንሶበታል ። ሆሳዕና ያለውም ሕዝብ ይሰቀል ሲለው አላፈረም ። በሆሳዕናና በስቀለው መካከል የነበረው አምስት ቀን ነው ። ንጉሥ ያሉትን ሽፍታ ሲሉት አልተሰቀቁም ። ሕዝብ አንዳንዴ ለመውረድ ደረጃ አይፈልግም ፣ ከሺህ ደረጃ ሲዘልም ሕዝብ አይሰበርም ። ፖለቲከኞች የሚሰጡትን የወሬ ጡጦ እየጠባ አብዛኛው ሕዝብ ልጅ ይሆናል ። እኔም በሥጋዊነትና ባልጸና ፍቅር ጌታዬ ሲታሰር ካድሁት ። ትላንት ስትዘምሩላቸው የነበሩ ዛሬ ደግሞ ሙሾ የምታወርዱባቸው ወዳጆቻችሁ አሉ ። ሆሳዕና ስትሉም ባለማወቅ ፣ ይሰቀል ስትሉም በስሜት መሆኑ ያሳዝናል ። በአንድ ሰውነታችሁ ለአንድ አሳብ ብቻ እደሩ ። ሁሉን ፈትኑ መልካሙን ያዙ ። የሚሞትላችሁ እውነት የለም ፣ የምትሞቱለት እውነት ግን አለ ። የሞተላችሁ እውነትም ክርስቶስ ነው ! 

ከመካከላችን አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል ፣ ሁላችሁም በእስራቴ ጊዜ ትበተናላችሁ ሲለን እኔ ግን በኵራት ሆኜ ሁሉ ቢክዱህ እኔ አልክድህም አልኩት ። ውጤቱ ግን ሁሉም አልካዱም እኔ ብቻ ካድሁ ። ትምክሕት ሌላውን ከሀዲ ራሴን አማኝ አድርጌ እንድመለከት አደረገኝ ። ሰው በተናገረው ይፈተናልና ተፈተንሁ ። ሙት ሲያሥነሣ ከፊት ለፊት ነበርሁ ፤ ሞት ሲፈረድበት ግን ወደ ኋላ ሸሸሁ  ። የኋላ ሰዎችም እንዲህ ብለው ገጠሙብኝ ሲባል ሰምቻለሁ፡-

ወዳጅ ለክፉ ቀን ይሆናል አትበለው ፣

ስትያዝ ይከዳል ሰው የጴጥሮስ ልጅ ነው ፤

የመፎከር ትልቁ ችግር መጸለይን ያስረሳል ። መፎከር በክንዴ አሸንፋለሁ ማለት ሲሆን መጸለይ ግን በኃይለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ብሎ መሰማራት ነው ። መፎከርም የፍርሃት ምንጭ ሊሆን ይችላል ። ጠላት በዚህ ጊዜ ይቀርበናል ። የሚፎክር ሰው አይጸልይምና ድል አያደርግም ። መፎከር ተግባርን በሙሉ ያስረሳና ተግባር ልሁን ይላል ። ‘ጡሩንባ ነፊ ቀብር አይወጣም’ እንዲሉ ፎካሪም ዋናው ሰዓት ላይ አይገኝም ። እኔም ከጌታዬ ጋር በጭንቁ ሰዓት ለአንድ ሰዓት እንኳ መትጋት አቅቶኝ በእንቅልፍ ወደቅሁ ። ለጸሎት የደከመኝ ሰይፍ ለመምዘዝ ግን ነቃሁኝ ። በጸሎት የማከብረውን ጌታ በመሳደብ አላከብረውም ። ሰማንያ ሺህ ሠራዊትን በአንድ ቅጽበት የገደለ ፣ ሰናክሬምን ያዋረደ ቅዱስ ሚካኤል የሚባል መልአክ ያለውን ጌታ እኔ የጆሮ ቀንበጥን በሰይፍ በመበጠስ ፣ ያውም ባሪያና ችግረኛ የሆነው ማልኮስ ላይ በመበርታት ጌታዬን አላስከብረውም ። ንጉሡ መናፍቅ ሲሆን ተራማጅ እንለዋለን ፣ ድሀ መናፍቅ ሲሆን የተገረመ እንለዋለን ። ባለ ጸጋ ቢያደናቅፈው ‘በሞትኩት ለእኔ ይሁን’ እንለዋለን ፣ ድሀ ቢወድቅ ‘ሞቶ ባረፈው’ እንላለን ። ድሀ በንግግር ቢሳሳት ‘ምነው ዝም ቢል’ እንላለን ፣ ሹም የአፍ ወለምታ ሲገጥመው ‘እንዲህ ያሉት እንዲህ ለማለት ፈልገው ነው’ በማለት የንግግር ወጌሻ እንሆናለን ። እኔም የሮማን ወታደር ትቼ ባሪያ የነበረውን ማልኮስን ጆሮውን ቀነጠብኩት ። በጀግንነት ሳይሆን ፎክሬ እንዴት እቀራለሁ ብዬ ለመግደርደር ነው ። ውጤቱ ግን በፈተና ወድቄአለሁ ። 

መጸለይን ትቼ ነፍሰ ገዳይ ልሆን ነበር ። በመጨረሻ አላውቀውም ብዬ ጌታዬን ካድሁት ። ልብ አድርጉ፡- መፎከር አለመጸለይን ወለደ ፣ አለመጸለይ በሥጋ መዋጋትን አመጣ ፣ በሥጋ መዋጋትም አላውቀውም የሚል ክህደትን አመነጨ ። ጸልዩ ፈተናውን የምታልፉት በመጸለይ ነው ። አሁንም አገራችን ኢየሩሳሌም ፣ በመላው ዓለም በሮም ግዛት ያሉ ወገኖቻችን አደጋ ውስጥ ናቸው ። ከዚህ የምንወጣው በመጸለይ ነው።”

ሐዋርያው ትምህርቱን እየቋጨ ነበርና ሁላችንም ለጸሎት ብድግ አልን ። እርሱም በሐዋርያዊ ቡራኬ ባረከን፡- “እግዚአብሔር አምላካችን ኃይላችሁን እንደ ንሥር ያድስላችሁ ። ቢሰፈር ከማይጎድለው ከፍጹም መዝገቡ ይሙላላችሁ ። በጸናው እጁ ይህን ዘመን ያሻግራችሁ ።”

ሁላችን “አሜን” አልን ። አሜን ካለማለት በረከት ይቀራልና ። 

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም.

ወድ ወገኖቻችን ለልባችሁ የቀረላችሁን እስቲ ለመጻፍ ሞክሩ ። እግዚአብሔር ከሚሻገሩት ወገኖች ይደምራችሁ ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ