የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጴጥሮስን አገኘሁት /ክፍል 16/

 

የሐምሌ ወር እየባተ ነው ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሥራዎቹን ቶሎ ቶሎ እየፈጸመ ነው ። እያንዳንዱን ቀን እንደ መጨረሻ ቀኑ እየኖረ በመሆኑ ሥራው ይፈጥንለት ነበር ። ዘላለም የሚያርፍ ክርስቲያን ሰባና ሰማንያ ዓመት ለአምላኩ ቢሮጥ ከቍጥርም የሚገባ አይደለም ። ማልደን ቃለ እግዚአብሔር ለመስማት ተገናኘን ። በምድረ በዳ የነበሩት እስራኤል በማለዳ መና ይለቅሙ ነበር ። ይህም የመናው የመጀመሪያ ሕግ ነው ። ፀሐይ ከወጣ መናው ይቀልጣል ፣ እነርሱም ይደክማሉ ። እንዲሁም ማልዶ መጸለይና ቃለ እግዚአብሔር መስማት አስፈላጊ ነው ። በጠዋት የተነሡ ቀኑ ይረዝምላቸዋል ፣ ጉልበትም ይኖራቸዋል ። የእግዚአብሔርን ቃል በማለዳ መስማት ቀኑን በጠዋቱ መግዛት ነው ። የሚውልብን ሳይሆን የምንውልበት ቀን የሚፈጠረው በጸሎት ነው ። ቀኑን በወሬ የሚጀምሩ በትካዜ ወደ ጸሎት ይሄዳሉ ። ቀኑን በጸሎትና በቃለ እግዚአብሔር የጀመሩ ብርታት ተሞልተው ይሰማራሉ ። ማለዳ ሰው ሳያናግሩ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር የቀኑን መና መልቀም ነው ። ሳይዘናጋ ላነጋልን አምላክ ምስጋናን መርሳት በቁም መሞት ነው ። 

ገባዔያችንን ከፈትን ። እማሆይ ፌበን ወደ ኋላ ብትዘገይም ጉባዔው በሰዓቱ ተከፈተ ። እግዚአብሔር ተገኝቶ ፍጡር አይጠበቅምና ። ደግሞም እየሄድን እንጂ ቆምን የምንጠበቅ አይደለንምና ። ሎጥ የከበረው ጥሪውን ብቻ እያሰበ በመውጣቱ ነው ። እንደ አዳም ሚስቴን ፣ እንደ ካህኑ ዔሊ ልጆቼን ቢል ኖሮ የሰዶም ጥፋት ያገኘው ነበር ። ሎጥ አካሉ ብትሆንም ሚስቱን እየሄደ ጠበቃት እንጂ ቆሞ አልጠበቃትም ። እርሷ ግን የሰዶምን ውበት ፣ የጎረቤቶቿን ጨዋታ አስታውሳ ዞር ብትል የጨው ሐውልት ሁና ቀረች ። የጨው ሐውልት ዝናብ ሲመጣ የሚሟሟ ነው ። እግዚአብሔር ወደ ኋላ በሚያዩ አይደሰትም ። ንስሐ የገቡበትን የኋላውን ታሪክ እያሰቡ በሚጨነቁም ደስ አይለውም ። ወደ ኋላ ከታሰበ ጴጥሮስም ከሀዲ ጳውሎስም ነፍሰ ገዳይ ናቸው ። የእግዚአብሔር ጉባዔ አንድ ሰው ቢገኝም መጀመር አለበት ። ጉባዔውን ታላቅ የሚያደርገው ታላቁ እግዚአብሔር መገኘቱ ነው ። ታላቅ ጉባዔ እያሉ የሚናገሩ ሰዎች አሉ ። የጉባዔ ታናሽ የለውም ። እግዚአብሔርን የሚጠራው ኅብረታችን እንጂ ቍጥራችን አይደለም ።

የዕለቱን መርሐ ግብር ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዕድሜው አንጋፋነት ፣ በማዕረጉም ትልቅነት ፣ በማመኑ ቀዳሚነት በጸሎት ከፈተ ። የጸሎቱ ማሰሪያም ልብ የሚነካ ነበር ። 

“እኔን ከከሀዲነት ጳውሎስን ከአሳዳጅነት መልሰህ የራስህ ያደረከን ፣ ጠላትን መወዳጀት ፣ አውሬን ማልመድ ትችልበታለህ ። በደም ጠብታ የወደድከንን እኛም በሰማዕትነት ልናከብርህ ቀኑ ርቆብን ናፍቆት ላይ ነን ። የሰው ዓለም የሚደነቀው ፍቅር እስከ መቃብር እያለ ነው ። አንተ ግን የትንሣኤ አምላክ ነህና ከሞት የሚዘልቅ ፍቅር አለህ ። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይገባሃል ። የመንፈስህ ኅብረት ከሁላችን ጋር ይሁን ። አሜን ።”

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እኛ ስንቀመጥ እርሱ በቆመበት ጸና ። በጉባዔ ላይ በሚታየው አገልጋይ ላይ ድሮ የሚያስተምረን የማይታየው መምህር ክርስቶስ ነው ። ሐዋርያው ትምህርቱን ቀጠለ፡-

“ዛሬ የምተርክላችሁ ንስሐን ስለሚወድ አምላክ ነው ። የበደለ ሁሉ ይክሳል ። እኛ ስንናዘዝ ግን በቀራንዮ ራሱ ጌታ ክሷልና ነጻ እንወጣለን ። በዳይን ክሶ የሚታረቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። እግዚአብሔር ሰውንና ንስሐን የሚወድ አምላክ ነው ። በመጽናት ካላከበራችሁት ንስሐ በመግባት አክብሩት ። ንስሐ ስትገቡ እግዚአብሔር መሐሪ ነው እያላችሁ ነው ። ንስሐ ምስክርነት ነው ። የሰማይን መንገድ ፣ የአምልኮ በርን ክፍት የምናደርገው በንስሐ ነው ። ንስሐ መንፈሳዊ ሕክምና ነው ። እኛ እንናዘዛለን ፣ እርሱ እኛን ይፈውሳል ። የሰው ልጅ ኃጢአቱን ከማመን በላይ አልተጠየቀም ። ቢጠየቅም ማቅረብ አይችልም ። ኃጢአት የበግ ለምድ ያለብሳል ፣ ንስሐ ግን ለእግዚአብሔር መራቆት ነው ። ኃጢአት አንገት ያስደፋል ፣ ንስሐ ግን ከእስር መፈታት ነው ። ኃጢአት ራስንና እግዚአብሔር መክዳት ነው ፣ ንስሐ ግን ማትረፍ ነው ። ኃጢአት ከገነት ያስወጣል ፣ ንስሐ ግን ወደ ገነት መመለስ ነው ። ኃጢአት ግንብ ነው ፣ ንስሐ ግን ድልድይ ነው ። ኃጢአት በሰይጣን መዝገብ መታወቅ ነው ፣ ንስሐ ግን በልበ ሥላሴ መመዝገብ ነው ። ንስሐ እኔን ሐዋርያ ያደረገ ነው ። እኛ ይቅርታ ብንፈልግም እርሱ ይቅር አልልም ቢል ይችላል ፣ አሁን ግን የሰው ልጅ የበዳይ አኩራፊ ሆኗል ። በንስሐ አዲስ መንገድ ፣ አዲስ አስተሳሰብ ይገኛል ። ፈላስፎች ሰውን ሰው ያደረገ ሥራ ነው ይላሉ ። ሰውን ሰው ያደረገ ግን ንስሐ ነው ። 

እኔ ለራስዋ የምትፈራዋን ገረድ ፈርቼ ጌታዬን ካድሁ ። በእንጀራ አምኜው በፈተና ካድሁት ። በገበታ አብሬ ሁኜ በመስቀል ሸሸሁት ። ይቅር የማይባል በደል ቢሆንም እግዚአብሔር ግን ይቅር የማይለው በደል የለም ። ንስሐ የሌለው ነገር ንስሐ አለመግባት ብቻ ነው ። እኔም ባሕር ላይ ስራመድ በደስታ ፣ ስሰጥም በጩኸት አድነኝ እላለሁ ። ስፎክር በደስታ ቢሆንም ስበድል የሚያቃጥል እንባ አፈስሳለሁ ። ካፈርኩ አይመልሰኝ የምል አይደለሁም ። ሰይጣን የሚጠላው ሀብታም መሆናችሁን ሳይሆን ንስሐ መግባታችሁን ነው ። ንስሐ ስትገቡ የሲኦልን ዜግነት መልሳችሁ የገነትን ዜግነት ትወስዳላችሁ ። ከሰይጣን ጋር በቍርጥ የምትለያዩት በመገሠጽ ሳይሆን ንስሐ በመግባት ነው ። 

ጌታ ከሞት ሲነሣ ትንሣኤውን ለጴጥሮስም በተለይ ንገሩት አለ ። በፍርሀት የካድሁት እኔ ፣ በሐፍረት ዳግም እንዳልጠፋ ተጠነቀቀልኝ ። አፍሬ ቀረሁ የሚል ሰው እውነተኛ ፍቅር የለውም ። እውነተኛ ፍቅር ያለው መጥቻለሁ ብትፈልግ ግደለኝ የሚል ነው ። ሳገኘውም አላፈርሁም ፍቅር እንደ ሆነ አውቃለሁ ። ከእርሱ ወዴት እሸሻለሁ ? ከእግዚአብሔር የምደበቀው በእግዚአብሔር ውስጥ ብቻ ነው ። ። ከካድሁ ጥቂት ቀናት ቢያልፉም እርሱ ግን የምእመናንን አደራ ሰጠኝ ። የካዳችሁን ሰው ከቀናት በኋላ ኃላፊት ትሰጡታላችሁ ወይ ? ጌታዬ ስክደው አመነኝ ። ሕፃናትን እንድንከባከብ ግልገሎች አድርጎ ሰጠኝ ። ከወጣቶች ጋር ትግል አለብኝና ጠቦቶች አድርጎ ጠብቅ አለኝ ። ሽማግሌዎችን እንዳሰማራ በጎች አድርጎ ሰጠኝ ። ንስሐ ስርየትን ብቻ ሳይሆን ክብረትን ታመጣለች ። ይሁዳ ቢመለስ ታላቅ አደራ ይሰጠው ነበረ ። ልዩነታችን አለመደበል ሳይሆን መመለስ ነው ። ለመካድም ንስሐን እንቢ ለማለትም ሰው ነጻ ፈቃድ አለው ። በመጀመሪያ ይጎመዣል ፣ በመጨረሻ ልቡን ያደነድናል ። አንዴ ታምሜአለሁ ብሎ መድኃኒትን የሚርቅ የለምና ንስሐ መግባት ይገባናል ። 

ከንስሐ አትዘግዩ ። ፀሐይ ሳትጠልቅ የበደላችሁትን ሰው ይቅርታ ጠይቁ ። በእናንተ ምክንያት እንቅልፉ አይታወክበት ፣ ቀኑ አይበላሽበት ። ሰው በዚህ ዓለም በድሎ እንዴት ዘላለም ይቀጣል ? አትበሉ ፣ በዚህ ዓለም ንስሐ ገብቶ እንዴት ዘላለም ይከብራል ? በሉ ። በሰላም ለመተኛትም በሰላም ለመሞትም ንስሐ አስፈላጊ ነው ። የገነት ጠባቂም የትላንትን ሽፍታነት አያይም ፣ የዛሬን ንስሐና ደመ ማኅተሙን ብቻ ያያል ። በንስሐ ገነት ይከፈታል ፣ ሲኦል ይዘጋል ። 

ልጆቼ መልካሙ አይለፋችሁ ። ከዚህ በላይ እንዳላስተምራችሁ አቅሜም እየተጋፋኝ ነው ። ድካም በሌለበት በትንሣኤ አካል ውስጥ ማደርን እመኛለሁ ። አሜን ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም.

ወድ ወገኖቻችን ለልባችሁ የቀረላችሁን እስቲ ለመጻፍ ሞክሩ ። እግዚአብሔር ከቅዱሳን በረከት ያሳትፋችሁ ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ